የምዕራባውያኑና የአገር ውስጥ የጥፋት ኃይሎች ሴራ ተፅዕኖ ዓይኑን አፍጥጦ ኢትዮጵያችን ላይ ተጋርጧል። አገራችን የውጭም የውስጥም ጫና በርትቶባታል። የውጭዎቹ ኃይሎች ለውስጦቹ ፤ የውስጦቹ ለውጭዎቹ ኃይሎች ደጀን የመሆናቸው የትብብር ሴራ እውነታም ገሀድ እየወጣ ይገኛል።
እነዚህ ኃይሎች በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በዓለምና በአፍሪካ ባላት ተደማጭነት፣ የነፃነትና የሉዓላዊነት መገለጫ ተደርጋ በምትታየውን አገራችን ላይ እያሳደሩ ያለው ከፍ ያላ ጫና የሕዝባችን የነገ ተስፋዎች የማጨለም ተልእኮ እንዳላቸውም የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ውሎ አድሯል ።
ከሁሉም በላይ ገለልተኛ ነው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ መርህ ለዓለም ሰላምና ደህንነት ይሠራል በሚል ብዙዎች ተስፋ የሚጥሉበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሳይቀር የዚሁ ጣልቃ ገብነት ማስፈጸሚያ የመሆኑ እውነታ በብዙ አነጋጋሪ ሆኗል።
ድርጅቱ በማያገባው ከሁሉም በላይ የአገሪቱ ውስጥ ጉዳይ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ የተመሰረተበት ዓላማና የሚገዛበትን ሕግና ሥርዓት በሚፈታተን መልኩ ለ10 ጊዜ ስብሰባዎችን ጠርቷል ። የአውሮፓ ህብረትም በተመሳሳይ መንገድ በተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ጫናዎች ለመፍጠር በስፋት እየሰራ ይገኛል።
ከዚህ በላይ የጆ ባይደን አስተዳደር ግልጽ በሆነ መንገድና ዓለም አቀፍ አደባባዮችን እየሞላ ባለ አካሄድ ከዓለም አቀፍ ሕግና መርህ ባፈነገጠ መንገድ በአገራችን ላይ ግልጽ የሆነ ጣልቃ ገብነት ውስጥ ይገኛል።
እነዚህ ኃይሎች የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃኖችንና ዘመናዊውን የመረጃ ማሰራጫ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተሳሳቱ መረጃዎችን በስፋት በማሰራጨት ከፍተኛ ጫናዎችን በአገራችን ላይ እያሳደሩ ይገኛሉ። በማህበራዊ ሚዲያዎች መረጃዎችን በማዛባት፣ ባልተገባ መንገድ በመተርጎም ፣ ጥቁር ፕሮፓጋንዳዎችን በመፈብረክና በማሰራጨት ተግባራት በስፋት ተሰማርተዋል።
ይሄ ድርጊታቸው አገሪቱ የጀመረችውን ለውጥ ለመቀልበስ፤ በአገሪቱ የተፈጠረውን በራስ የመተማመን መንፈስ ለመግደልና ስለ ብልጽግና በተፈጠረው መነቃቃት ላይ ውሃ የመከለስ ዓላማ ያነገበ ነው። ከዛም አልፎ ሕዝባችንን በመከፋፈል ወደ ግጭት ለመንዳት እና አገርን እንደ አገር የማፍረስ ሴራም የተሸከመ ነው።
እነዚህ ኃይሎች አሸባሪውን ሕወሓትና ሸኔ እንዲሁም ሌሎች ተላላኪዎቻቸው በሀገራችን ላይ እየፈጸሙት ያለውን እኩይ ተግባር አንድም እያበረታቱ፤ ሁለትም ድርጊታቸውን ወድደውና ፈቅደው እየደገፉ ያሉበት ሁኔታ በግልጽ እየታየ ከመጣም ከራርሟል።
በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜያቶች ቀውስን እየፈጠሩ አገራዊ አለመረጋጋት እና ቀውስ እየፈጠሩ ያሉ የሽብር ኃይሎች የመደገፉ እውነታ ዛሬ ላይ የተጀመረ ባይሆንም አሁን የደረሰበት ደረጃ ግን አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ የአደባባ ሚስጥር ነው ። እነዚህ ሃይሎች አገርን ለማዳከም፣ እርሙንም አደራውንም የሚበላ ደካማ፣ ተላላኪና ድርጎኛ መንግሥት ለመፍጠር እየሰሩ ነው።
“ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ “እንደሚባለው እነዚህ ኃይሎች በአገራችን እያሳደሩ ያለው ጫናና ጫናው ሊፈጥር ከሚችለው አደጋ አንጻር ድርጊታቸው በአግባቡ ማየት ተገቢ ነው ። እውነታውን ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል እንዲገነዘበው ማድረግ ይገባል።
በእርግጥ ሕዝባችን ስለችግሩ አሳሳቢነት እስከ አሁን ሳይገነዘበው ቀርቷል የሚል እምነት የለኝም። ነገር ግን የነዚህ ኃይሎች ሴራ የቱን ያህል አገርና ህዝብን የከፋ አደጋ ውስጥ ሊጥል እንደሚችል በተገቢው መንገድ ለህዝባችን ማሳወቅ ትልቅ ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን መልካም ስምና ተደማጭነት የማሳጣት፣ የሰራቻቸውንና እየሰራቻቸው ያሉትን በጎ ሥራዎች የማጠልሸት፣ በኢኮኖሚ የማዳከም ቀውስን የመፍጠር እኩይ ሴራ ለሕዝባችን በየእለቱ ማሳወቅ ፤ሴራውን ለመቀልበስ ዝግጁነቱን ማሳደር ያስፈልጋል ።
ወቅቱ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በተለየ መልኩ ቆም ብለን እንድናስብ የምንገደድበት ነው። የስንዴ ድርጎም ሆነ በዚህ ሲሰጡ በዚያ እንደ ሰላቢ መልሰው የሚወስዱት ልግስና ከሉዓላዊነታችን አይበልጥብንም። ነፃነታችንን ያገኘነውና እስከ ዛሬ ያስጠበቅነው በስንዴ ድርጎ ወይም በተላላኪዎች ወይም በማንም ስጦታ አይደለም። አባቶቻችን ደምና አጥንታቸውን ገብረው ያወረሱን ነው ።
ነጻነታችንን ! በደም፣ በአጥንት፣ በስንት በመስዋትነት ያገኘነው ነው። በብዙ መስዋእትነት ያገኘነውንና አስጠብቀን ያቆየነውን ነጻነታችን ለማስቀጠል የሚጠበቅብንን ሁሉ እንደ ትውልድ ለመወጣት እራሳችንን ማዘጋጀት ይኖርብናል። ይሄን ከአልማዝም ሆነ ከእንቁ የከበረና መተኪያ የሌለውን ነፃነታችንን በርካሽ ነገሮች አሳልፈን እንደማንሰጥ ጫና ፈጣሪዎቹም ሆኑ የነሱ ተላላኪዎች እንዲያውቁልን ማድረግ ይገባል።
እንደ ቀደሙት አባቶቻችን በአንድነት ቆመን ጫናው ከነፃነታችንና ከሉዓላዊነታችን አይበልጥብንም ልንላቸው ይገባል ። በአንድ ድምፅ በየትኛውም ዓይነት ጫናና ተፅዕኖ ህልውናችንን አንሸጥም ሉዓላዊነታችንን አሳልፈን አንሰጥም ልንል ፤ ድምጻችንን ከፍ አድርገን ልናሰማ ይገባል!
በአገር ጉዳይ በምንም ነገር የማንደራደር እና አገራችንን አሳልፈን የማንሰጥ መሆናችንንም ከቃላት ባለፈ በተጨባጭ በተግባር ማሳየት፤ በውስጥ ተላላኪዎች አማካኝነት በህልውናችን በሉዓላዊነታችን የሚፈጠር ጫናዎችን በተባበረ ክንድ ለመቀልበስ ተቀናጅተን ልንቀሳቀስ ይገባል ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18 ቀን 2014 ዓ.ም