በሰዎችና በድርጅቶች መካከል የሚደረጉ ውሎችንና መሰል ህጋዊ ግንኙነቶችን የሚወስኑ ሰነዶችን የፌዴራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጂንሲ በህግ አግባብ ያጣራል። በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በመታገዝ ያረጋግጣል እንዲሁም ይመዘግባል። በተጨማሪ ሲፈልጉ በቀላሉ ማግኘት እንዲቻሉ ያደርጋል። እነዚህ ለኤጀንሲው ከተሰጡት ሥልጣንና ኃላፊነቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
ኤጀንሲው አገራዊ ወጥነት ያለው የመረጃ አያያዝ ስርዓት በመዘርጋት፣ በማደራጀትና በማስተዳደር ተገማችና ተደራሽ አገልግሎት ለመስጠት ምን እያደረገ ነው ? እንዲሁም ከሦስት ወራት በፊት አቋርጦት የነበረውንና ብዙዎች እየተቸገሩበት ያለውን የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ሽያጭና በስጦታ የማስተላለፍ ውል አገልግሎት መቼ ይጀምራል? ስንል ለኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ለአቶ ሙሉቀን አማረ ጥያቄዎችን አቅርበናል።
አዲስ ዘመን ፦ ኤጀንሲው የተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት ምን ይመስላል ከሚለው እንጀምር?
አቶ ሙሉቀን ፦ የፌዴራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ በአሁኑ የአዲስ ምዕራፍ አደረጃጀት የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ አገልግሎት በህግ ከተሰጡት ሥልጣንና ኃላፊነቶች መካከል ሰነድ የማረጋገጥና የመመዝገብ ሥራ ዋናው ነው። እዚህ ላይ ማረጋገጥ ሲባል ከኢትዮጵያ ህግና ሞራል ጋር የማይቃረኑ መሆናቸውን በማረጋገጥ ሰነዶቹን የመመዝገብ ሥራ አንደኛው ነው። ከዚህ አንጻር ወደ ተቋሙ የተለያዩ በርካታ ሰነዶች ይመጣሉ። እስከ አሁን ባለው የተቋሙ ልምድና የሥራ ዘመን ቆይታ በብዛት የሚሠራው ውክልና፣ የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል እንዲሁም የአክሲዮን ማህበራት መመሥረቻና መተዳደሪያ ደንቦች እና ቃለ ጉባኤዎች ተረጋግጠው ይመዘገባሉ።
በዚህም ማንኛውም አይነት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ የሽርክን ማህበር እንዲሁም ሌሎች የንግድ እንቅስቃሴን ለመመሥረት ሲያስቡ የመመሥረቻ ውሎችና ቃለ ጉባኤዎች ወደ አገልግሎት የሚገቡት በተቋም ተረጋግጠው ከተመዘገቡ በኋላ ነው ።
እዚህ ተቋም ላይ እንደ ዲክላራሲዮን፣ ቃለ መሃላ፣ ኑዛዜና ሌሎችም እየተረጋገጡ የሚመዘገቡ ናቸው። እነዚህ ነገሮች ደግሞ ወደ ተቋሙ ሲመጡ መጀመሪያ የሚታየው በሰነዶቹ ላይ የሰፈሩት ነገሮች ከአገሪቱ ህግ ጋር ይቃረናሉ? ከማሕበረሰባችን ሞራል እና እሴቶች ጋር ምን ያህል ይቆራኛሉ? የሚለው በጥንቃቄ ከታየ በኋላ ሰነዶቹ ተረጋግጠውና ተመዝግበው ወደ ሥራ ይገባሉ ። ተቋሙ ምንም እንኳን ገቢ ሰብሳቢ ባይሆንም በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ቀላል የማይባል ገቢን እያስገኘ ነው።
አዲስ ዘመን ፦እንደ አገር ሰነድ የማረጋገጥና የምዝገባ ሂደቱ ወጥነት ያለው እንዲሆን ኤጀንሲ ምን እየሰራ ነው?
አቶ ሙሉቀን፦ አዎ ኤጀንሲው መረጃዎች እንደ አገር ወጥነት ያላቸው እንዲሆኑ ብሎም በአንድ ማዕከል ተሰባስበው እንዲተዳደሩ ለማድረግ ክልሎችን የማስተባበር የመደገፍ ስልጠና የመስጠት ሥራን ይሰራል።
አዲስ ዘመን ፦ ኤጀንሲው የተሰጠው ተልዕኮ በጣም ትልቅና ሰፊ ከመሆኑ አንጻር በሥራው ላይ እያጋጠሙት ያሉት ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? ችግሮቹን ለማለፍ የሚያደርገው ጥረት የቱን ያህል ውጤት አስገኝቶለታል?
አቶ ሙሉቀን፦ ተቋሙ አገልግሎት ሰጪ በመሆኑ ትልቁ ሥራው የተገልጋይ ፍላጎትን ማርካት ነው። የተገልጋይ ፍላጎት ደግሞ ከቀን ወደቀን በጣም እየጨመረ የሚሄድ ነው። ይህንን ፍላጎት ሊያረካ የሚችል ሥራ አደረጃጀት እንዲሁም የሰው ኃይል የመመጠንና በዛው ልክ የመገንባት ሥራ ይሠራል። ከዚህ በፊት ተቋሙ አገልግሎት የሚሰጠው በተወሰኑ ቅርንጫፎች ብቻ ነበር። በዚህ ምክንያት ከፍተኛ የተደራሽነት ችግር ነበረበት። ይህንን ለማቅረፍ ጥረት አድርጓል። የሰው ኃይልን ከመገንባት አንጻር ትልቅ ሥራ ሠርቷል። በሌላ በኩልም የሚገለገልባቸው የሥራ መሣሪያዎች ከዘመኑ ጋር የተዋጁ እንዲሆኑ ልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተግባራዊ አድርጓል።
እነዚህ ሁሉ ነገሮች ሲሠሩ ትልቁ ማነቆ የሆነው የሐሰተኛ መታወቂያ ጉዳይ ነው። ሐሰተኛ መታወቂያ ለተቋሙ ትልቅ ፈተና እየሆነበት ነው። በተለይም ሰነድ ሲረጋገጥና ሲመዘገብ የአንድን ሰው ሕጋዊነት ለማረጋገጥ ማንነቱን በግልጽ የሚያሳይ መታወቂያ ይዞ መምጣት አለበት፤ ነገር ግን ሐሰተኛ መታወቂያ ሥራውን እያወከው ነው። ተቋሙ አንድ ሰው የንብረት ሽያጭ ውል ሲፈጽም ያገባ ወይም ያላገባ መሆኑን ማረጋገጥ ጀምሯል። በተለይም ያገቡ ሰዎች የሚወስኑት ውሳኔ የጋብቻ አጋሮቻቸው ሙሉ ፍቃደኝነት ያለበት መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ነገር ግን በጣም በርካታ ሐሰተኛ ያላገባ መሆኑን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች እየቀረቡ ህገወጥ ሥራዎች እየተሠሩና ለተቋሙም ትልቅ ፈተና እየሆኑ ነው።
ከዚህም ውጪ ከተቋሙ የሚወጡ ሰነዶች ሳይቀሩ በሐሰተኝነት ይሠራሉ። ይህ ዓይነቱ ሰነድ ወደኛ ተመልሶ በሚመጣበት ወቅት የራሳችን የማረጋገጫ መንገዶች ያሉን በመሆኑ እንደርስበታለን በተቻለ መጠንም እኛን አያታልሉንም። ነገር ግን ሌሎች ተቋማት ላይ እንዳይገለገሉበት መጠንቀቅ ይገባል።
አዲስ ዘመን ፦ አዎ የሐሰተኛ ማስረጃ ማቅረብ ጉዳይ በጣም ፈታኝ ነው። ከላይ የገለጹልኝ በተለይም ከተቋሙ የሚወጡና በሐሰተኛ መንገድ የተዘጋጁ ሰነዶች ሌሎች ቦታዎች ላይ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የምታደርጉበት መንገድ ካለ ?
አቶ ሙሉቀን፦ ለምሳሌ ባለፈው በጀት ዓመት ወደ 261 የሐሰተኛ ሰነዶች ተይዘዋል ፤ ከዚህ ውስጥ 57 በመቶ የሚሆነው መታወቂያ ነው። እነዚህ እኛ የያዝናቸው ብቻ ናቸው። ሳንይዛቸውም የሾለኩ ሊኖር ይችላል። እዚህ ላይ እንደ አገር ብዙ አይነት መታወቂያዎችን ጥቅም ላይ የምናውልና የምንገለገል ነን። በመሆኑም ይህ መሰሉ ህገ ወጥ ተግባር እንዳይበራከት ልናደርግ የምንችለው መታወቂያ ከሚሰጡ ተቋማት ጋር ተቀራርቦ በመሥራትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን በመስጠት ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ በተለይም መታወቂያዎች የሚመጡት ከአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ነው፤ ከኤጀንሲው ጋርም የመግባቢያ ስምምነቶችን ተፈራርመን እንደ አንድ ተቋም ተቀራርበን እየሠራን ነው። አንድ አጠራጣሪ መታወቂያ እጃችን ላይ ሲገባ ቀጥታ ከወጣበት ወረዳ ጋር ስልክ ደውለን ስለ ሁኔታው የምናጣራበትን መንገድ ፈጥረናል። ነገር ግን ዘለቄታዊ መፍትሔ የሚሰጠው ብሔራዊ መታወቂያ የሚባለው ጥቅም ላይ ሲውል ብቻ ነው ። እስከዛው ድረስ የጥንቃቄ መንገድ ይሆናል በሚል በቅርበት እየሠራን ነው።
በቀጣይ ከተማ አስተዳደሩ ዲጅታል መታወቂያ እየሰጠ በመሆኑ ምን ያህል ሰዎች እጅ ይህ መታወቂያ ገብቷል? የሚለውን በደንብ እናውቃለን። እስከ አሁን ድረስ ከግማሽ ሚሊየን ህዝብ በላይ መታወቂያውን አልወሰደም። ይህ እንዳለ ሆኖ መታወቂያው በብዛት ታትሞ ወደ ተቋማችን ከመጣ ልክ ነው አይደለም የሚለውን በደንብ ለማጣራት ያግዘናል። ባለፈው በጀት ዓመትም በርካታ ሐሰተኛ መታወቂያዎችን ለመያዝ የቻልነው በዚህ መንገድ በመሄዳችን ነው። እዚህ ላይ የምናጣራው መታወቂያ ብቻ ሳይሆን ያገባ ያላገባ ማስረጃንም ይጨምራል ። በጠቅላላው ግን ጅማሬው ጥሩ ነው።
ይህ እንግዲህ ጥሩ ውጤት ቢታይበትም የሚፈለገውን ያህል ችግሮችን ወይንም ደግሞ ህገ ወጥ ተግባራትን ይይዛል ማለት አይደለም። መፍትሔው በአገረ አቀፍ ደረጃ አንድ ወጥነት ያለው ብሔራዊ መታወቂያን ወደሥራ ማስገባት ነው። ይህ ከእኛ ተቋም ውጪ ነው። በተቋማችን የሚመጡ የሐሰት ማስረጃዎችን እንዴት እንከላከላለን? ብለን ስናስብ ቀደም ሲል በሐሰተኛ ውክልና የሰዎች ገንዘብ ከባንክ ይወጣል ። ይህ ለመሆኑ ደግሞ በርካታ መረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። ይህንን መሠረት በማድረግ ባንኮች በሐሰተኛ ውክልና ገንዘብ ላልተገባ አካል እንዳይሰጡ የሚያደርግ አሠራር (ሲስተም) ዘርግተናል።
በዚህም በ2013 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር መጀመሪያ ተፈራርመናል። ቀጥለን ከቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር በመቀጠል ከሁሉም የግል ባንኮች ጋር ተፈራርመናል። በአሁኑ ወቅትም የእኛ አሠራር (ሲስተም) በየትኛውም ክልልና ወረዳ ውስጥ ቢገኙ ውክልና ሲመጣላቸው ወደ እኛ የመረጃ ቋት በመግባት የቀረበው ውክልና ትክክለኛ ስለመሆኑ ያረጋግጣሉ።
ይህ ስርዓት ሳይዘረጋ በፊት ግን አንድ አጠራጣሪ ውክልና ሲመጣላቸው የሚጠይቁት ግልባጩን ( ኮፒውን) ይዘው የራሳቸውን ባለሙያ ደብዳቤ አስይዘው በመላክ ነበር። ይህ ሂደት ከክልሎችና ከወረዳዎች ሲሆን የሚፈጀው ጊዜና የሕብረተሰቡም መጉላላት ብዙ ነበር። በዚህ መካከል ወንጀለኛን እንከላከላለን ብለን ሃቀኛውንና ትክክለኛ ሰነድ ይዞ የቀረበውን ሰው እያጉላላን ረጅም ጊዜን እንፈጅ ነበር ። አሁን ግን የደቂቃዎች ጉዳይ ለማድረግ ችለናል።
በአዲሱ አሠራራችን መሠረት ውክልና ሲሰጥ የወካዩም ይሁን የተወካዩ ፎቶግራፎች በወረቀቶቹ ላይ አይታይም፤ ይህ የሆነውም ወንጀለኞች ውጪ ወጥተው እንዳይቀይሩት በማሰብ ነው። እኛ በውስጣችን ኪው አር ኮድ የምንላት አለች ይህንን ኮድ አስገብቶ በመፈለግ ብቻ ማን መጥቶ እንደፈረመ እናያለን ። ባንኮችም ከእኛ ጋር ያገናኙትን አሠራር (ሲስተም) ሲከፍቱ በቀጥታ የግለሰቡን ስምና ፎቶግራፍ ያገኛሉ። በዚህም ቀደም ሲል የነበረ ደንበኛቸው ፎቶግራፍ ስላላቸው ከዛ ጋር ያስተያዩታል ምናልባት ለማጭበርበር የፈለገው ሰው መታወቂያውን ፎቶግራፍ ቀይሮ ቢያዘጋጅ እጅ ከፈንጅ ይያዛል ማለትነው።
አዲስ ዘመን ፦ ከውክልና ጋር ተያይዞ የሚሰሩ የሙስናና የሌብነት ችግሮች እንዳሉ ይነገራል። ለምሳሌ ሰዎች በውክልና ስም ንብረት በህገ ወጥ መንገድ የሚሻሻጡበት አይነት ፤ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ምን እየሠራችሁ ነው?
አቶ ሙሉቀን፦ የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ውልን በተመለከተ እኛው ጋር የሚያልቅ በመሆኑ ችግሮችም ካሉ እዛው እንይዛለን ። ነገር ግን ለምሳሌ መኪናን በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የሚባል ተቋም አለ። ይህ ተቋም ከእኛ የሚሄዱለትን የሽያጭ ውሎች በሙሉ ልክ እንደ ባንኮቹ ሁሉ በሲስተም ተጠቅሞ ትክክለኝነታቸውን ያረጋግጣል። በተንቀሳቃሽ ስልኮች ላይ በሚጫኑ አፕልኬሽኖችም ታግዞ ማጣራት ይቻላል። ይህንን በመሰለ ሁኔታ ህገወጥነትና ሌብነትን ለመከላከል እየሠራን ቢሆንም አሁንም የተደራጀ የመረጃ ቋት አለመኖሩ በሥራው ላይ እንቅፋት መፍጠሩ አልቀረም።
በመሆኑም አሁን ላይ ከ2011 ዓ.ም ሐምሌ ወር ጀምሮ በዚህ ተቋም ላይ የሚረጋገጡ ውክልና ሽያጭ እንዲሁም ሌሎች ሰነዶች በሙሉ በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ (ዲጂታላይዝድ ) እንዲሆኑ ተደርጓል። ወደኋላም እየሄድን ተመሳሳይ ሥራዎችን እየሠራን እንገኛለን። ችግሩንም ቀስ በቀስ እንፈታዋለን ብለን እናስባለን።
አዲስ ዘመን ፦ እንደው እዚህ ላይ በተለይም ማሕበረሰባችን ውክልናን እንደ ቀላል ነገር በመቁጠር ለቤተሰቡ ብሎም በቅጡ ለማያውቃቸው አካላት ሁሉ ንብረቱን ሃብቱን በውክልና የሚሰጥበት ሁኔታ አለ። ከዚህ አንጻር የሕብረተሰባችን ግንዛቤ ዳብሯል ማለት እንችላለን? የእናንተ ተቋም ውክልና መሰጣጣትን የሚያየው እንዴት ነው?
አቶ ሙሉቀን ፦ ውክልና መስጠት ማለት እከሌ እንደ እኔ ሆኖ ይሥራልኝ ፤ይሽጥ ይለውጥ ያስተዳድር ማለት ነው። እውነት ለመናገር ውክልና መስጠት በጣም ከባድ ነው። እኛ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 14 ቅርንጫፎች አሉን። በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ውልን በተመለከተ የጽህፈት አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች፤ የተቋሙ ሠራተኞች የሚመስሏቸው ብዙ ተገልጋዮች አሉ። በዚህ ምክንያትም ሕብረተሰቡ የሚፈልገውን ነገር ይነግራቸዋል። ራሳቸው በአዘጋጁት ፎርማት መሰረት ጽፈው ይሰጧቸዋል። እኛ ጋር መጥተው ህጋዊ አድርገው ይሄዳሉ ። ነገር ግን በዚህ ጽሁፍ ውስጥ አንዳንድ ጊዜ ውክልና ሰጪው ያልፈለገውን መሸጥ መለወጥ ይችላል የሚሉ እና ሌሎች ነገሮችንም እየጻፉ ወካዩም ልብ ብሎ ባለማየት ወይም ባለማወቅ ይፈርምና ለብዙ ችግር ሲጋለጥ ኖሯል።
ኤጀንሲው ይህንን ክፍተት ተረድቶ ሥራውን ወደ ሲስተም በማስገባት አሁን ላይ ምንም ነገር ውጪ አይጻፍም ባለበት ሆኖ ራሱ ውክልና ሰጪው ፎርም ሞልቶ ማመልከቻውን ያስገባል። ወደ ቅርንጫፎች ሲመጣም የሞላው ፎርም ደብዳቤ ሆኖ ይወጣና አይቶ አረጋግጦ ይፈርማል። ይህ አሠራራችን ከዚህ ቀደም የነበረውን ክፍተት ደፍኖታል።
ኤጀንሲው ይህንን አሠራር ሲዘረጋ በጽህፈት አገልግሎቱ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩና ለራሳቸውም የሚኖሩ ሰዎች ከሥራው እንዳይወጡ ለማድረግ በየቅርንጫፉ ያሉ ውል ጸሃፊዎችን አሰልጥኗል። ሲስተሙንም አውቀውና ተረድተው አገልግሎቱን እንዲሰጡ ለማድረግ ተሞክሯል። በይነ መረብ (ኢንተርኔት ) አግኝተው በቤታቸው መሙላት ላልቻሉ አገልግሎት ፈላጊዎች አገልግሎቱን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሰጡም አድርጓል። ምናልባት ውሉን በለመዱት ወይም በሚፈልጉት መልኩ እንዳይሞሉ ወይም ስህተት እንዳይፈጽሙ ከማሠልጠን ባሻገር የትኛውም ውል ጸሃፊ በየትኛው ቅርንጫፍ ላይ እንደሞላ የምንከታተልበት በዚህም ስህተቶች ሲገኙ እንዲታረሙ የምናደርግበት አሠራርን ፈጥረናል።
በሌላ በኩል ግን የተጻፈውን ውል ይዘው ወደ ኤጀንሲው ለሚመጡ ሰዎች አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት ቢያጽፉ የእኛ ባለሙያዎች ከማስፈረማቸው በፊት እያንዳንዷን ቃል በትኩረት እንዲረዷቸው በማድረግ እንዲዋዋሉ ያግዛሉ። አሁንም ግን ችግሮቹ ሙሉ በሙሉ ተፈተዋል የሚባልበት ደረጃ ላይ አልደረስንም። ከቀደመው ጊዜ የውክልና አሠጣጥ በተሻለ ሁኔታ ግንዛቤ ዳብሯል ማለት ግን ይቻላል። ከዚህ አንጻር አሁን ላይ የውክልና ግንዛቤ እያደገ መጥቷል።
አዲስ ዘመን ፦ ቴክኖሎጂ እንጠቀማለን ብለው ከላይ ነካ አድርገውታልና ዘመኑ ለልማት ብቻ ሳይሆን ለጥፋትም የረቀቁ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ይኖራል። ኤጀንሲው በቴክኖሎጂ አጭበርባሪዎችን ቀድሞ ለመሄድ እያደረገ ያለው ጥረት ምን ይመስላል?
አቶ ሙሉቀን፦ ከቴክኖሎጂ ትግበራዎቻችን አንጻር ስናየው አንዳንድ ቴክኖሎጂዎቻችን በዚህ አገር ላይ ባሉ ተቋማት ውስጥ የማይታወቁ ሁሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አሉን። ለምሳሌ ለአንድ አገልግሎት ፎቶግራፍ ብትነሺ ፎቶው የሚወጣው በተጠየቀው ሰነድ ላይ ታትሞ ነው ። ኤጀንሲያችን ግን ያደረገው በሰዎች መረጃ ላይ ፎቶግራፍ ከመለጠፍ ከፍ ብለን አንድ ደረጃ እንሂድ በማለት ኮድ አድርገን ኮዱ በቀጥታ ከዳታ ቤዝ እንዲነበብ ሆኗል ። ይህ በራሱ ከአጭበርባሪዎች አንድ እርምጃ ቀድመንበታል ብለን የምናስበው የቴክኖሎጂ ውጤት ነው።
ነገር ግን በየትኛውም ዓለም ላይ ወንጀልን በመከላከል ዙሪያ የተሰማሩ አካላት አጭበርባሪዎችን ያን ያህል መቅደም ስለማይችሉ ይከተላሉ። እኛም በተቻለን መጠን ወንጀለኞችን አንድ እርምጃ ለመቅደም እየጣርን በአንዳንድ ጉዳዮች ላይም እየተከተልንና ከስር ከስር እያረምን እየሄድን ነው ።
ይህ በእኛ ተቋም ነው ።በጣም ከባድ የሆኑና ከተቋሙ ውጪ ያሉ የማጭበርበር ሁኔታዎች ደግሞ አሉ። ለምሳሌ እንደ መታወቂያ፣ ያገባ ያላገባ መረጃና የመሳሰሉት በዚህም ላይ ተቀናጅተን ለመሥራት እየሞከርን ነው። ከላይ እንደገለጽኩት ባንኮች ወደኛ ስለመጡ አይደለም አብረን መሥራት የጀመርነው እኛ ሄደን አጭበርባሪዎችን በዚህ መልኩ በቴክኖሎጂ ታግዘን እንከላከላቸው በማለታችን ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ወንጀልን መከላከል የጋራ ሥራ መሆኑ እሙን ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ተቋም ወጪ የምትገናኟቸው አካላት ምን ያህል እያገዟችሁ ነው?
አቶ ሙሉቀን፦ እውነት ለመናገር መጀመሪያ አካባቢ በጣም አስቸጋሪ ነበር። አሁን ባለው ሁኔታ ግን አረዳዱ ጥሩ ነው ። ሁሉም ባንኮች በጣም ቀና ናቸው። ይህ ምን ማለት መሰለሽ መጀመሪያ አካባቢ ይህንን ሲስተም ሞክሩት? ብለን የሰጠነው ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነበር። እነሱም ካዩት በኋላ ይህማ በጣም ስንፈልገው የነበረ ነው በቶሎ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመን ወደ ሥራ እንግባ አሉ። ወደ ሥራ ገባን። በመቀጠል ከግል ባንኮች መካከል ቡና ኢንተርናሽናል ባንክን አማከርናቸው፤ ተስማሙና ጀመሩት ፤ እነርሱን ሲያዩ 15ቱም የግል ባንኮች በራችንን ማንኳኳት ጀመሩ። ከዚህ አንጻር በጣም ጥሩ አረዳድ አለ ብሎ መውሰድ ይቻላል። በመሆኑም እኛ ቴክኖሎጂውን አመንጭተን ተግብሩት ብለን ከሠጠናቸው የግልም የመንግሥትም ተቋማት ላይ ተቀባይነት ያጣንበት ወይም ያልተሳካልን የለም።
አዲስ ዘመን ፦ በቅንጅታዊ አሠራሩ እንደአገር ከምን አይነት ኪሳራ መዳን ተቻለ?
አቶ ሙሉቀን፦ እኛ የፌዴራል ተቋም ነን። የምንሠራው አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ላይ ነው ። ለምሳሌ ከባንኮች ጋር በቅንጅት መሥራታችን ምን ያህል ገንዘብ በተሳሳተ ማስረጃ ይወጣ እንደነበርና አሁን እንደዳነ የሚያውቁት እነርሱ ናቸው። ብዙ ሪከርዶችም ይኖሯቸዋል ብዬ አስባለሁ ። ከምንም በላይ ግን አንድ ሰው ገንዘብ ለማውጣት ወደ ባንክ ሲሄድ በተለይም ክልሎች ላይ ሰነዱ ተጣርቶ እስኪመጣ ድረስ ሰባት ቀናት ይፈጅ ስለነበር ምናልባት ሰውዬው ገንዘቡን የሚያወጣው ለህከምና ቢሆን ህይወት ማዳን ሁሉ ላይችል ይችላል። በእኛ ሲስተም ግን ይህ አሠራር ወደ ደቂቃዎች መጥቷል። ይህ እንግዲህ ከገንዘብም በላይ በአገልግሎት አሠጣጥ የሚማረር የኅብረተሰብ ክፍል እንዳይኖር በከፍተኛ ሁኔታ እገዛን አድርጓል። መጭበርበሮችንም ቀንሷል። እንደ አገርም እኛ የማቀናጀት አገራዊ ተልዕኮ ያለን በመሆኑ ከቤንሻንጉል በቀር በሁሉም ክልሎች ላይ ጥናቶችን አጥንተናል ክፍተታቸው ምንድ ነው? ብለን ለይተን አሁን አገራዊ የመረጃ ቋት ለመፍጠር እየሠራን ነው። ይህ እውን እንዲሆን እንግዲህ የክልሎች ተነሳሽነትና ፍቃደኝነት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ ኤጀንሲው በሲስተም ማሻሻያ ሥራዎች ምክንያት የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች በሽያጭና በስጦታ የማስተላለፍ ውል ማቋረጡ ይታወሳል። ይህ ሥራ ከሦስት ወራት ያላነሰ ጊዜን ፈጅቷል። አሁን ምን ደረጃ ላይ ነው?
አቶ ሙሉቀን፦ የሲስተም ማሻሻያ ሥራችንን መሠረት አድርገን አገልግሎቱን ያቋረጥነው ሐምሌ 5 ቀን 2013 ዓ.ም ነው። ይህም ሲሆን በተለይም ኅብረተሰቡ ላይ ምሬት እንዳይፈጠር ጊዜውን የመረጥነው በጥናት ላይ ተመስርተን ነው። ሥራውን ለማቋረጣችን ዋናው ምክንያትም ሲስተሞች ሲሻሻሉ ዳታዎች ከቀድሞው ወደ አዲሱ መተላለፍ ስላለባቸው ነው። ካልተቋረጠ በቀር የፍርድ ቤት ክርከር ኖሮባቸው የታገዱ በርካታ ንብረቶች ሊያልፉብን ስለሚችሉ የተወሰነ ጊዜ ለማቋረጥ ተገደናል።
በውስጣችን ለ15 ቀን ብለን አቅደን ገብተናል። ባቀድነው ጊዜ ሥራችንን አጠናቅቀናል። ነገር ግን ልክ ሐምሌ 20 ኤጀንሲው የማጠናቀቂያ ሥራውን አከናውኖ ሐምሌ 21 ቀን 2013 ዓ.ም አገልግሎቱን ሊጀምር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት ማኔጅመንት ‹‹የምሠራው የአደረጃጀትና የአሠራር ማሻሻያ አለ። ከመሬትና ቤት ጋር በተያያዘ ብዙ ህገወጥ ተግባራት ስላሉ እነሱን ለይቼ እስካሳውቃችሁ ድረስ ንብረትን በሽያጭም በስጦታም የማስተላለፍ ሂደትን አዘግዩልን›› በማለታቸው ኤጀንሲው የሲስተም ማሻሻያ ሥራውን ቢያጠናቅቅም ወደ መደበኛ ተግባሩ መግባት ሳይችል ቀርቷል።
አሁንም ሥራቸውን አጠናቀው ‹‹እነዚህ ህገ ወጥ ናቸው›› ብለው ከለዩልን እነሱን በአንድ ቋት ይዘን ወደመደበኛ አገልግሎታችን የማንገባበት ምንም ምክንያት የለም። አሁንም ቢሆን የኅብረተሰቡን ቅሬታ ለከተማ አስተዳደሩ በቃልም በጽሁፍም እያሳወቅን ነው። ጊዜ እየፈጀ መሆኑንም እየተናገርን ነው። ነገር ግን እነሱም አስቸጋሪ ሁኔታ ስለገጠማቸው እስከ አሁን አላጠናቀቁም። ነገር ግን እነሱ ዛሬ 4 ሰዓት ላይ ጨርሰናል የሚል ደብዳቤ ቢያደርሱን ኤጀንሲው 4 ሰዓት ከ 5 ደቂቃ ላይ አገልግሎቱን የማይጀምርበት ምንም ምክንይት የለም።
አዲስ ዘመን ፦ አገልግሎቱ ከተቋረጠ ሶስት ወራት አለፉ። በእነዚህ ጊዜያት ደግሞ ከፍተኛ የአገልግሎት ፈላጊ ቁጥር ይኖራል።ይህንንስ ኤጀንሲው በምን መልኩ እወጣዋለሁ ብሎ ያስባል?
አቶ ሙሉቀን፦ ትልቁ ነገር እርሱ ነው። ኤጀንሲው ሁኔታውን ከግንዛቤ በማስገባት በበይነ መረብ አማካይነት ሰዎች በቀጥታ ድረ ገጻችን ላይ እየገቡ ወረፋ የሚይዙበትን መንገድ አመቻችተናል። ነገር ግን ይህ ዘዴ አሁን ላይ ጊዜውም ከመርዘሙ የተነሳ ብዙ አዋጭ ሆኖ አላገኘነውም ። ስለዚህ ሌላ መንገድ መጠቀም ስላላብን አገልግሎቱ ሲጀመር የሚመጣው አገልግሎት ፈላጊ ለማስተናገድ ብቁ የሆነ አቅም ያለው የሰው ሃይልም በማደራጀት ላይ እንገኛለን ።
በመሆኑም እስከ አሁን የተከማቸው አገልግሎት ፈላጊ ቢያንስ በአንድ ሳምንት ውስጥ ተስተናግዶ ማለቅ አለበት የሚል ግብ አስቀምጠናል። ይህንን የምናደርገው ደግሞ ለምሳሌ በያዝነው ወር አገልግሎቱን የምንጀምር ከሆነ የኪራይ ውል የሚያዋውሉ ባለሙያዎቻችን በዚህ ወር ብዙ ስራ ስለማይበዛባቸው እነሱን ወደ እዚህኛው አገልግሎት እንዲዞሩ እናደርጋለን። በተመሳሳይ የአክሲዮን ማህበራት ቃለ ጉባኤ ማሻሻልና መሰል ስራዎች አሁን ስለማይበዙ እዛም ላይ ያለው ሠራተኛ ወደ እዚህ መጥቶ አገልግሎቱን በተቀላጠፈ፤ ሰልፍን በሚያስወግድ ሁኔታ እንዲሰጥ እናደርጋለን ። ለእዚህ ደግሞ አቅሙም ልምዱም ስላለን ምንም የሚቸግረን ነገር አይኖርም። እዚህ ላይ ግን ትልቁ ነገር አገልግሎት ፈላጊዎች ወደ ቅርንጫፎቻችን ሲመጡ ሊያሟሏቸው የሚገቡ ነገሮችን አሟልተው መገኘታቸው ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ኤጀንሲው አገልግሎት ሰጪ ተቋም እንደመሆኑ በየቅርንጫፎቹ በቀን ውስጥ በርካታ ደንበኞች ይመጣሉ። በዚህ መካከል ደግሞ በአንዳንድ ሠራተኞቻችሁ ላይ የሚነሱ የሥነ ምግባር ችግሮችም አሉ። እነዚህን ችግሮች የምትቆጣጠሩት እንዴት ባለው መልኩ ነው?
አቶ ሙሉቀን፦ ልክ ነው አገልግሎት ሰጪ ከመሆናችን ጋር በተገናኘ በርካታ የስነ ምግባር ችግሮች ያጋጥሙናል። የሥነ ምግባር ጉዳይም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ከሥነ ምግባርም ያፈነገጡ ሠራተኞችም ሲኖሩ ችግሩን እያጣራን እርምጃ እንወስዳለን።
በነገራችን ላይ በየቅርንጫፎቻችን የምንከተለው ሲስተም እያንዳንዱ ሰው ምን ሠራ የሚለውን በየጊዜው መረጃ እንድናገኝ ያግዘናል። በዚህ ምክንያትም አንዳንድ ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ ሥራን ሰርተው የተገኙ ባለሙያዎች ጉዳዩን ለመካድ እንኳን አይችሉም። በኤጀንሲው ደንብ መሠረት የተቀጡ ለፍትህ አካላትም ተላልፈው የተሰጡም አሉ።
ኤጀንሲው ለሥነ ምግባር ችግሮች ትልቅ ትኩረት በመስጠት የሥነ ምግባር ክፍልን እንደ ዋና የሥራ ሂደትም የሚጠቀም ሲሆን ቅርንጫፍ ያሉ የሃሳብ መስጫ መዝገቦች ላይም ኅብረተሰቡ ሃሳቡን የሚገልጸው ጥሩ የሠራለትንም ሆነ ያልተገባ ጥቅም የጠየቀውን ሠራተኛ ስም ጽፎ በመሆኑ እዛው ሃሳቡ ስር መልሳችንን ወይንም ደግሞ የተወሰደውን ርምጃም በማሳወቅ ጥሩ ተግባቦት እያደረግን ነው። በሌላ በኩልም በየወሩ ከሳጥንም ከመዝገቡም ላይ ያሉ አስተያየቶች ሰብስቦ በመተንተን የባለሙያዎች ስም በመጥቀስና ያሉ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት እርምጃ የመውሰድ ሥራ ይሠራል ።
አዲስ ዘመን ፦ እንደ አገር በተለይም በአንድ ቋት የመረጃ አያያዝ ደረጃ የት ላይ ነው?
አቶ ሙሉቀን ፦ የተለያዩ አገራት የሰነድ ማርጋገጥና ምዝገባን የሚሠሩት እንደ አገራቸው ህግ ስለሆነ ሁሉም አንድ ይሆናል ማለት አይደለም። ለምሳሌ አንዳንድ አገራት ላይ ሰነድ የሚረጋገጠው በግለሰቦች ነው ። የእኛ አገር ሁኔታ ደግሞ ፍጹም የተለየ ሲሆን የሰነዱ ይዘት ሁሉ ከአገሪቱ ህግ ጋር አለመጣረሱን በሚገባ ይለያል። አሁን በፌዴራል ደረጃ የመረጃ አያያዝ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ጥሩ መሻሻሎች ያሉት ተስፋ ሰጪ ጅምሮች የሚታዩበት ነው ።
እዚህ ተቋም ላይ ምንም እንኳን ከ1938 ዓ.ም ጀምሮ ሰነዶች ያሉ ቢሆንም እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ብዙ አልነበሩም ። አሁን ደግሞ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ያሉትን በአንድ ቋት እያስገባን በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ እያደረግን ነው። በቀጣይም ወደኋላ ሄደን እስከ 2000 ዓ.ም ያሉትን በዚህ መልኩ ማደራጀት ከቻልን እጅግ በጣም ጥሩ የሰነድ አያያዝ ይኖረናል ። እዚህ ላይ ግን ይህ ሰነዶችን በአንድ ቋት የማደራጀት ሥራ እየተሠራ ያለው በፌዴራል መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማና በድሬዳዋ ላይ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ሥራው ሙሉ እንዲሆን ስላላስቻለው በቀጣይ ሁሉም ክልሎች ወደዚህ መግባት አለባቸው በማለት እየሠራን ነው። ክልሎችም የራሳቸውን ጥረት ካደረጉ በአጭር ዓመት ውስጥ ወጥነት ያለው የአንድ ቋት የመረጃ አያያዝ ስርዓት ይኖረናል።
አዲስ ዘመን፦ ኤጀንሲው ያሰበበት ደረጃ ይደረስ ዘንድ ከማን ምን ይጠበቃል?
አቶ ሙሉቀን፦ ምንም ያህል ቴክኖሎጂ ቢመጣ የሰው ሃይል ልማት ወሳኝ ነው። የአገልጋይነት መንፈስ የተላበሰ ሠራተኛ ሊፈጠር ይገባል። ከዚህ አንጻር የሚመለከታቸው አካላት ለአገልግሎት ሰጪው በርካታ ሥልጠናዎችን ማዘጋጀትና ራሱን እንዲገነባ አውቆም እንዲያገለግል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በመሆኑም የሰው ኃይል ልማታችን ላይ የሚያግዘን የግልም የመንግሥትም ተቋም እንፈልጋለን።
ዋናውና የኤጀንሲው ሥራ ላይ ትልቅ ጥላ እያጠላ ያለው የሐሰተኛ መታወቂያ ጉዳይ በመሆኑ በእርሱ በኩል ያሉ ሥራዎች በቶሎ ተጠናቀው ሁሉም ዜጋ ብሔራዊ መታወቂያን በቶሎ እንዲያገኝ የሚመለከታቸው አካላት በፍጥነት ቢሄዱበት እላለሁ። ይህ በፍጥነት የሚሆን ከሆነ ደግሞ የኤጀንሲውን ፈተና ከማቅለሉም ባለይ ኅብረተሰቡንም ከመጭበርበር ለማዳን ያስችላል ።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ሙሉቀን ፦ እኔም አመሰግናለሁ
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2014