አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥና በግጭት ምክንያት የተረጂዎች ቁጥር ስምንት ሚሊዮን መድረሱን ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
ምክትል ኮሚሽነር ዳመነ ዳሮታ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት በ2011 ዓ.ም ታህሳስ ወር መጨረሻ ድረስ በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የተረጂዎች ቁጥር በአገሪቱ ሰባት ነጥብ 95 ነበር። ከጥር ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የተረጂዎች ቁጥር ስምንት ሚሊዮን ደርሷል።
ከነዚህ መካከል ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑት በሀገሪቱ በተፈጠሩ ግጭቶች የተፈናቀሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ዳመነ ገለጻ፣ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ከኦሮሚያና ከሶማሌ ግጭቶች ጋር ተያይዞ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በቅንጂታዊ ሥራ መሰራቱን የጠቆሙት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ በዚሁ መሰረት አንድ ሚሊዮን 20 ሺህ 234 ሰዎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን አንድ ሚሊዮን 787 ሺህ 931 ሰዎች ደግሞ በመጠለያ ካምፖች ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የመኸር ምርትና የበልግ ምርትን መሰረት በማድረግ በየሥድስት ወሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሚመሩት ግብረ ኃይል መደበኛ ግምገማ እንደሚካሄድ የጠቆሙት ኮሚሽነሩ ተረጅዎቹ 60 በመቶ በመንግስት፣ 22 በመቶ በዓለም ምግብ ፕሮግራም እና 18 በመቶ ደግሞ መንግስታዊ ባልሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጥምረት ድጋፉ እየተደረገላቸው መሆኑን አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2011
በመሀመድ ሁሴን