የዛሬው የዘመን እንግዳችን ኢትዮጵያን በመወከል በተለያዩ የአፍሪካ አገራት እየተዘዋወሩ የእግር ኳስ ጨዋታን በዳኝነት የመሩ አንጋፋና ዓለምአቀፍ ዳኛ ናቸው። ውልደታቸውም ሆነ እድገታቸው እዚሁ አዲስ አበባ አማኑኤል እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ጳውሎስ፣ ተፈሪ መኮንን፣ ባልቻ አባ ነፍሶ በተባሉ ትምህርት ቤቶች የተማሩ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በልዑል መኮንን ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። ከዚያው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስር ይገኝ በነበረው ንግድ ሥራ ትምህርት ቤት ገብተው በአካውንቲንግ ዲፕሎማቸውን ይዘዋል። ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በኢትዮጵያ ባህር ትራንዚት ድርጅት ውስጥ በተማሩበት ሙያ ለስምንት ዓመታት አገልግለዋል።
በተወለዱበት መንደር በምትገኝ ሜዳ ላይ እግር ኳስ መጫወት ያዘወትሩ የነበሩት እኚሁ ሰው በተለይም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ ፈጣን ማሞ ካቻ በተባለ የህፃናት ቡድን ውስጥ ገብተው ድንቅ ብቃታቸውን አሳይተዋል። በመቀጠልም ለኢትዮጵያ ወጣት ቡድን፣ ለባህር ትራንዚት እንዲሁም ለአሰብ ምርጥ ቡድን ተጫውተዋል። ከዚሁ ጎን ለጎንም የአሰልጣኝነትና የእግር ኳስ ዳኝነት ስልጠና እድል አገኙና ሰልጥነው የተለያዩ ቡድኖችን በማሰልጠንና በዳኝነት መርተዋል።
ከመንግሥት ለውጥ ጋር ተያይዞ ወደ አዲስ አበባ ተቀይረው ለገሀር ባህር ትራንዚት ውስጥ ማገልገል ጀመሩ። ብዙም ሳይቆዩ የእቃ ማጓጓዝ ክፍል ምክትል ኃላፊ ሆነው ቦሌ አየር መንገድ ተመድበው መስራት ጀመሩ። ዓለም አቀፉ የስፖርት ፌዴሬሽን (ፊፋ) ያወጣውን ማስታወቂያ ተወዳድረው በማለፍ ዳኛ ሆነው ሙሉ ለሙሉ ሥራቸውን ቀጠሉ። ደቡብ አፍሪካ፤ ግብፅና ኬኒያ እየተዘዋወሩ በዳኝነት አገለገሉ።
ይሁንና ህወሓት መራሹ መንግሥት አጠቃላይ ስርዓቱ አላምር ያላቸው እንግዳችን በያዙት ሙያና ደመወዝ በሀገር ውስጥ እየሰሩ መቀጠል እንደማያዋጣ ተገነዘቡ። ስለሆነም ያላቸውን ዓለምአቀፍ ግንኙነት በመጠቀም በሙያቸው በነፃነት ሊሰሩበት በሚችሉባት አሜሪካ ጓዛቸውን ጠቅልለው ገቡ። ከ35 ዓመታት በላይ በዳኝነትና በአሰልጣኝነት የቆዩት እንግዳችን በሄዱበት ሀገርም የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ስፖርት ማህበርን በመቀላቀል ከሙያቸው ባሻገር ለዲያስፖራ ማህበረሰብ የእርስበርስ ግንኙነት መጠናከር ጉልህ ሚና መጫወታቸው ይጠቀሳል።
ከዚህም በተጨማሪ ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ የዲሲ ግብረኃይልን ከመሰረቱት ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ናቸው። በተለይም በዚህ ግብረኃይል አማካኝነት ህወሓት በኢትዮጵያውያን ላይ ይፈፅም የነበረውን ግፍ በመቃወም፤ ለዓለም ህዝብ በማሳወቅና በማጋለጥ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ ቆይተዋል። ውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያውያን አንድነት ለመበተን ሲሰራ የቆየውን ይህንኑ አሸባሪ ቡድን ሴራ በማክሸፍ ረገድም ለህዝባቸውና ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር በተግባር ማረጋገጥ የቻሉ ሰው ስለመሆናቸውን ይነገራል።
በኢትዮጵያ የመጣውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎም የለውጡን ኃይል በመደገፍ የተለያዩ የድጋፍ ሥራዎችን ሲያከናውኑ የቆዩት እንግዳችን በተለይም በታላቁ ህዳሴ ግድብና የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በውጭ ኃይሎች የሚደረጉትን ጫናዎች የሚቃወሙ ሰልፎችን በማስተባበር የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ። በቅርቡ ደግሞ ዓለምአቀፍ ጫናውን በመቃምና ታላቁን የህዳሴ ግድብን በተግባር ለመደገፍ ሲባል ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ 500 በላይ ዲያስፖራዎች መካከል እሳቸው አንዱ ሆነዋል። ኢንተርናሽናል የእግር ኳስ ዳኛ እና በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስፖርት ማህበር የውድድርና ሥነሥርዓት ደንብ ማስከበር ኮሚቴ አመራር የሆኑት አቶ ግርማ ታፈሰ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- የአፄ ኃይለስላሴን መንግሥት ገና ታዳጊ ሳሉ መቃወም እንደጀመሩ ሰምቻለሁ። እስቲ ስለዚህ ጉዳይ ያጫውቱንና ውይይታችንን ብንጀምር?
ኢንተርናሽናል ዳኛ ግርማ፡- ልክ ነሽ፤ የንጉሱን ስርዓት በዚያ በጨቅላ እድሜያችን ‹‹መሬት ላራሹ›› እያልን ቤተመንግሥት ድረስ በመሄድ እንቃወም ነበር። ይህንን የምናደርገው ግን ገብቶን ሳይሆን ታላላቆቻችን የነበሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲያደርጉ ስላየንና ትክክል ነው ብለን ስላመንን ነበር። በተለይ አንድ ቀን እማርበት ከነበረው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት በቀጥታ ወጥተን ቤተመንግስት በር ላይ ስንጮህ ፖሊሶች አስለቃሽ ጭስ ረጭተውን በዚያ የልጅነት አዕምሯችን የተሰማን ድንጋጤ አልረሳውም። እነዚያ ፖሊሶች የረጩንን አስለቃሽ ጭስ ለመታጠብ ጊዮን ሆቴል ስር ካለው ድልድይ ታጥበን ልንወጣ ስንል በፖሊሶቹ ተያዝን። ጭነውን ሊወስዱን ሲሉ በአጋጣሚ ደግሞ ንጉሱ ይመጡና ጉዳዩን ይጠይቁና ስለሁኔታው ይረዳሉ። እሳቸው ግን ‹‹ ለእነዚህ ህፃናት ያለፈቃድ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄድ እንደማይቻል አስቀድማችሁ ሳትነግሯቸው ለምን ታስሯቸዋላችሁ ፤ በሉ አውርዷቸው›› ብለው ተቆጡ። የሚገርምሽ ግን ልክ እንደለቀቁን ተቃውሟችንን ረስተን ከቤተመንግሥቱ ጀምረን መርካቶ እስከምንደርስ ድረስ ‹‹ አባባ ጃንሆይ የእኛ እናት አባት፤ አስተምረውናል በማር በወተት›› የሚለውን መዝሙር እየዘመርን ነው የሄድነው። በሶስተኛው ቀን ትምህርት ቤት በር ላይ እንቅስቃሴ ስናደርግ ታሰርኩኝ። ለሳምንት ታስሬ ከተፈታሁኝ በኋላ ታላቅ ወንድሜ ሁለተኛ እዚህ ትምህርት ቤት አትሄድም ብሎ አስወጥቶኝ ባልቻ አባነፍሶ ትምህርት ቤት አስገባኝ። እናም ያኔ ነው እንግዲህ የትግል ህይወት የተጀመረው።
አዲስ ዘመን፡-የደርግ መንግሥት እንዳበቃ ሌላ አስገራሚ ነገር እንደሰሩ ሰምቻለሁ። ስለዚህ ጉዳይ ምንነት ይንገሩኝ?
ኢንተርናሽናል ዳኛ ግርማ፡- የደርግ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ እዚህ የነበሩ የራሺያ ወታደሮች ወደ ሀገራቸው የኢትዮጵያን ሃብት ይዘው ሊወጡ ሲሉ የተፈጠረ ነገር ነው። እኔ በዚያ ወቅት አየር መንገድ እስራ ስለነበር 28 የሄሊኮፍተር ኢንጅን ጭነው ሊበሩ ሲል በአጋጣሚ አየሁና ለሚመለከተው አካል ጠቆምኩኝ። በወቅቱ ታዲያ የእኔን ጥቆማ ተንተርሶ ፍተሻ ሲደረግ በጣም ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ ከአዶላ ዘርፈው ሊወጡ ሲሉ ተያዙ። በወቅቱ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ፈርሶ ስለነበር የማምለጥ እድል ነበራቸው። ግን እኔ በአጋጣሚ ትራንዚት ላይ መስራቴ ጠቀመኝና በማየቴ ኢንጅኑን ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የወርቅ ክምችትን ማዳን ችያለሁ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሌላው ያጋጠመኝ ነገር ላጫውትሽ፤ በዚሁ ወቅት አራተኛ ክፍለጦር ጥይት ቤት ይቃጠላል። ግን በወቅቱ የእሳት አደጋ ሰራተኞች በሙሉ ተበትነው ስለነበር እኔና ጓደኞቼ ሆነን ያንን እሳት ለማጥፋት ግማሽ ቀን ፈጅተን ራሳችን ለአደጋ ሰጥተን እሳቱ እንዳይዛመት አድርገናል። እነዚህ ሁለት ገጠመኞች አይዘነጋኝም።
አዲስ ዘመን፡- የሚወዷትን አገር ጥለው ለመሰደድ የተገደዱበት ሁኔታ ምን ነበር?
ኢንተርናሽናል ዳኛ ግርማ፡- በአጋጣሚ ከአገር ልወጣ የቻልኩት አባቴ ከፕሮፌሰር አስራት ጋር ነበር የሚሰራው። እሱ ታሞ ሆስፒታል ከገባ በኋላ እሱን ማስታመም ሆነ የነበሩኝ ሁለት ልጆች በዳኝነት በማገኘው ደመወዝ መቀጠል ከባድ ሆነብኝ። በሌላ በኩል የወያኔ መንግሥት ሁኔታ በተለይ ብሄር ተኮር ሥርዓቱ አዕምሮዬ ሊቀበለው አልቻለም። እዚህ ብቆይም አያሰሩኝም የሚል ስጋት አደረብኝ። ከደቡብ አፍሪካ እንደተመለስኩኝ የአሜሪካ ቪዛ ስጠይቅ ያለምንም ችግር ተፈቀደልኝና ወደ አሜሪካ ሄድኩኝ። እኔ ቅዳሜ ልሄድ ገነነው ሊብሮ የተባለ የስፖርት ጋዜጠኛ ቶሮንቶ ልበር እንደሆነ ዘገበ። ያንን መረጃ ይዘው የደህንነት ሰዎች እኔ ቅዳሜ አሜሪካ ገብቼ እነሱ ሰኞ እለት አየር መንገድ ይጠብቁኝ ነበር።
ከሀገር ከወጣሁ በኋላ ከጫካ የመጣውን ወያኔ ከመጀመሪያውኑ ጀምሮ እታገለው ነበር። በስደት በኖርኩባቸው ዓመታት ሙሉ የዲሲ ግብረኃይል አባላት ጋር በመሆን ኤምባሲ ውስጥ የነበረውን የወያኔን ባንዲራ አውርደን ትክክለኛውን የኢትዮጵያን ባንዲራ ሰቅለናል። በዚህ ወቅት የነበረው አምባሳደር ግርማ ብሩ ሽጉጥ አውጥቶ ተኩሶብናል። እኛ ግን በዚያም አልተወሰንም፤ ለነበረው መንግሥት ተቃውሟችንን ስናንፀባርቅ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ህወሓት የዘረጋው ብሄር ተኮር የፌዴራሊዝም ሥርዓት ላይ ያለዎት ምልከታ ምንድን ነው?
ኢንተርናሽናል ዳኛ ግርማ፡- ይህ ሁኔታ ዛሬም ድረስ ያመኛል። ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስና ለማበላሸት ገና ከጥንስሱ ነው የሴራ ፖለቲካውን የጀመረው። አለቆቻቸውን ሳይቀር ገድለው የመጡት ይህንኑ ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ነው። እኔና ባልደረቦቼ አየር መንገድ ላይ በራሺያ ንብረታችን እንዳይዘረፍ የሞከርነው አገራችንን ለመታደግ እንጂ የሆነ ብሔር አባላትን ለማዳን ብቻ አይደለም። እኔ ከልጅነት እስከ እውቀቴ ብሄር የሚባል ነገር አላውቅም። ወያኔ ስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት ግን ትውልዱ ላይ የተዘራው የልዩነት ክፉ መንፈስ አገሪቱ አሁን ለገባችበት ስቃይ ዋነኛ ምክንያት ነው ባይ ነኝ። ምንአልባት አሁን ላይ ወደቀደመው ህብረታችን የሚመልሱን ጭላንጭሎች መኖራቸው ለእኔ ትልቅ ተስፋ ነው። የለውጡ መንግሥት ውስጥ ያሉ ጥቂት የመንግሥት ባስልጣናት የሚያደርጉት ጥረት የሚመሰገን ነው።
ሆኖም ቁስሉ ሰር የሰደደ በመሆኑ ዛሬም እዚያም እየፈነዳ ኢትዮጵያ ይበልጥ እያሳመማት ነው ያለው። በግሌ እኔ ቤተሰቤን ከመምራትና ልጆቼን ከማሳደግ በላይ ወያኔ ስልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታት ሙሉ ይህንን የዘር ፖለቲካ ስቃወም ነው የቆየሁት። ብዙ መከራ አይቼበታለሁ። ህይወቴን ለማጥፋትም ብዙ ሙከራ ተደርጎብኛል። ፈጣሪ ይመስገንና አሁን ላይ የመጣው መሪ ከፈጣሪ የተላከ እንደሆነ ነው የማምነው። ሀገራችንም ከዚህ ሁሉ መዓት ያወጣናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
ዶክተር አብይ አሜሪካ በመጣበት ጊዜም ኢትዮጵያን በማስቀደሙ ከእሱ በፊት እኔ ልሞትለት ቃል ገብቼለታለሁ። ምክንያቱም ከዚህ በፊት ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚል መሪ ሰምተንም አናውቅም። ዋናውና ትልቁ ነገር አሁን ላይ ያንን አስተሳሰብ የሚያራምደው አካል መወገዱ ነው። አሁንም እርስበርስ ከተሳሰብን የነበረውን ህብረታችንን መመለስ እንችላለን። ከዚህ ባሻገር እኛ አንድ ከሆንን ማንም የውጭ ወራሪ ሊደፍረን አይችልም። በመሰረቱ እኛ የጥንታዊ ስልጣኔ አገር ባለቤት እንደመሆናችን እኛ ሳንሆን ልንሰደድ ይገባን የነበረው እኛ ነበርን ስደተኞችን ልንቀበል የሚገባን።
በነገራችን ላይ አሜሪካም እንደኛ በፌዴራሊዝም የምትመራ ሀገር ነች። በውስጧ 84 በላይ ቋንቋዎች ይነገሩባታል። ከዚህ በተጨማሪ አማርኛ ሳይቀር የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ተደርጓል። ይህ የሚያሳየው እኛ ከተግባባን በቋንቋ መለያየታችን ለጸብ ምክንያት እንደማይሆን ነው። አሁንም ለነጭ ሳይገዙ ህይወታቸውን ገብረው ይህችን አገር ያቆዩልንን የአባቶቻችንን አደራ መወጣት የምንችለው የተዘራብንን ልዩነት አጥፍተን አንድነታችንን ማጠናከር ስንችል ነው። ይህንን ስናደርግም ነው ከስንዴ ልመና የምንወጣው። ወያኔ በታሪካችን ታይቶ በማይታቅ ሁኔታ በዘር ከፋፍሎናል፤ በሃይማኖት እና በቋንቋ ለያይቶናል። ለዘመናት አብረን እንዳንኖር የሚያደርግ መርዝ ተክሏል። አሁን ላይ ያ ክፉ መንፈስ ተሰብሯል። ለአዲሱ መንግሥት ጊዜ ከሰጠነው ርዝራዦቹን ማጥፋት እንችላለን። ሌብነትም ማስወገድ እንችላለን።
በነገራችን ላይ እኔ ወደአገሬ ተመልሼ የመጣሁት ይህ የዘር አስተሳሰብ ለማስወገድ የሚያስችል ስርዓት እየተፈጠረ መሆኑ በፈጠረብኝ ታላቅ ደስታ የተነሳና በዚህም ሙሉ እምነት ስላለኝ ነው። በተጨማሪም ወያኔ በቀሰቀሰው ጦርነት ስለባ ለሆኑ ወገኖቻችን አለኝታነታችን ለመግለፅ ከዚሁ ጎን ለጎን እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሉ የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ ዓላማ ይዘን ነው የመጣነው። ለዓባይ ግድብ 1ሺ700 ዶላር አስገብተን ነው የመጣነው። አሁንም ለግድቡ ዋንጫና ‹‹የአባይ ንጉስ›› በሚል የታተመ ቲሸርት በመሸጥ ድጋፍ የምናደርግ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ይሄ በብሄር የመለያትና እርስ በርስ የመባላቱ ሁኔታ ዲያስፖራው ድረስ መስረፁ በሀገሪቱ ገፅታ ላይ ምን አይነት አሉታዊ ሚና ነበረው ብለው ያምናሉ?
ኢንተርናሽናል ዳኛ ግርማ ፡- በጣም ጥሩ ሃሳብ ነው ያነሳሽው። አንቺም እንዳልሽ በወያኔ ስርዓት ምክንያት እዚህ ያለው ህዝብ ብቻ ሳይሆን ዲያስፖራውን በዘር ሲያባሉን ነው የኖሩት። አስቀድሜ የጠቀስኩልሽ የዲሲ ግብረኃይል ስር ሆነን ስንታገል የነበርነው ይህንን ለመስበር ነው። እኛ ይህንን እናደርግ የነበረውም የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል ሆነን ወይም የሆነ ብሄርን ወክለን አይደለም፤ ነገር ግን ለኢትዮጵያዊነታችን ስንል ነው ስንታገል የነበረው። ኢትዮጵያ በሚደርስባት ችግር ምክንያት የሆነው ነገር ለማጥፋት ዓለምን ሁሉ ቀስቅሰናል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመጨረሻውን ሰብሰባ ሲያደርግ ሌሊት በአውሮፕላን ሳይቀር ተሰባስበን አዳራሽ እንዳይገቡ በር ዘግተን ተቃውሟችንን ስንገልፅ ነው የነበረው። ኢትዮጵያ ላይ መጥፎ ውሳኔ እንዳይወስኑ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥረናል። 11 ጊዜ ሲሰበሰቡ መወሰን ያልቻሉት በእኛ ብርቱ ትግል ነው።
አሁን ላይ በዚህ መጠን ያለው ዲያስፖራ ይዘን መምጣት የቻልነው ከምንም በላይ ለኢትዮጵያዊነታችን ቅድሚያ ስለሰጠን ነው። በዚህ ግብረኃይል መካከል ከተለያየ ብሔር የመጣን ብንሆንም በብሔራችን ምክንያት ግን ተለያይተን አናውቅም። ያ ቢሆን ኖሮ አሁን በአንድነት እንዲህ ተሰባስበን በዚህ ደረጃ ሀገራችንን ለመደገፍ ባልመጣን ነበር። በእርግጥ በአንድ ጊዜ ማጥፋት ከባድ ነው። ከልጅነት እስከ እውቀት የተነገራቸው አንዱ ብሔር በሌላ ጠላት እንደሆነ ነው። ያንን ለመቀየር ብዙ መስራት ይጠበቅብናል። መቼም ፈጣሪ ቸር በመሆኑ ነው ባላሰቡት ሁኔታ ስልጣናቸውን አስረክበው መቀሌ መክተማቸው፤ ያም በመሆኑ ነው ማንነታቸውን ይበልጥ ህዝቡ ሊያውቀው የቻለው። አሁን ላይ ትናንት እነሱን ሲደግፉ የነበሩ እውነታውን ሲገነዘቡ እኛን ይቅርታ ጠይቀው ገንዘብ የሚያዋጡበት ሰዓት ላይ ነው የተደረሰው። ያኔ ንጉሱን የቃወምነው ስርዓቱን ተጠይፈን የብሄር ጉዳይ አሳስቦን አልነበረም። በመሰረቱ በወቅቱ የነበሩ ባለስልጣናት ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የመጡ እንጂ በዘር ተጠራርተው የተሾሙ አልነበሩም። አሁን ላይ ፕሮፌሰር ተብሎ ሰዎችን በጎሳ የሚለያይ ትምህርት ሲሰጥና ሀገር ሲጠፋ ነው የሚስተዋለው። ስለዚህ አሁን ላይ እነዚህ ሰዎች አደብ የማስገዛቱና ህብረታችንን ዳግም ማጠናከሩ የሁላችንም ኃላፊነት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አኳያ የነበረው ቁልፍ ችግር ምን ነበር ይላሉ?
ኢንተርናሽናል ዳኛ ግርማ፡- ወያኔ ህገመንግሥት ቀርፆ የስም ዴሞክራሲ እገነባለሁ ቢልም በተጨባጭ የታየው ግን ያንን የሚያሳይ አልነበረም። በ1997 ዓ.ም ላይ ምርጫ ሲካሄድ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጭላንጭል ይመጣል የሚል ትልቅ ተስፋ ነበረን። ሆኖም የቅንጅትን መሪዎች የአሜሪካ ኤምባሲ ስብሰባ ብሎ ጠርቶ ለወያኔ አሳልፈው ከሰጧቸውና ከታሰሩ በኋላ የጓጓንለት ተስፋ ብን ብሎ ጠፋ። ለውጡ እስከሚመጣ ጊዜ ድረስ በእኔ እምነት አገሪቱ በዴሞክራሲ መብት እጦት አዘቅት ውስጥ የገባችበት ሁኔታ ነበር የነበረው። የሕዝቡም ኑሮ ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚባለው ሆኖ ነው የቆየው።
በነገራችን ላይ እነዚያ ከጫካ የመጡት ሰዎች እኛ እንድንጫረስ ቢያደርጉንም የቅርብ የምንላቸው ሰዎች ሳይቀሩ የእነሱ ተላላኪ ሆነው አገር ሲያጠፉ ህዝብ ሲያጨርሱ እንደነበር መዘንጋት የለብንም። አሁንም ቢሆን ምንም እንኳን የቱን ያህል ቢሰራበት ወጣቱን ካስተማርነው ለውጥ ይመጣል ብዬ አስባለሁ። በለውጡ ስር ተሸሽገው ግን ደግሞ የወያኔን አጀንዳ የሚያራግቡ አካላትን መንጥሮ ማውጣት ይገባል። በተለይም ዛሬም የዘር ፖለቲካን ለማስቀጠል ጥረት የሚያደርጉትን መለየትና ማጋለጥ የሁሉም ኃላፊነት መሆን አለበት። ምክንያቱም አሁንም ከመሰላሉ ላይ ወርደው ያላለቁ ኃይሎች በመኖራቸው ነው። እነዚህን ለቅሞ ለማውጣት ግን ኢትዮጵያን ማዳን የሚፈልግ ሁሉ ሰው ትብብር ያስፈልጋል። አገርን ማስቀደም ያስፈልጋል። ይህንን ብናደርግ የትኛውም የውጭ ኃይል ሊደፍረን አይችልም። ከዚሁ ጎን ለጎን ይህንን አስተሳሰብ ከታች ጀምሮ ባለው አመራር ዘንድ ማስረፅ ይጠይቃል። አጭበርባሪውን ለመለየት ደግሞ በህግ የሚደገፍ ስርዓት መደገፍ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ከ27 ዓመታት በኋላ ወደኢትዮጵያ ሲመለሱ በልማት ረገድ የጠበቁትን ነገር ነው ያገኙት?
ኢንተርናሽናል ዳኛ ግርማ፡– እኔ በቆይታዬ በአጭር ጊዜ ብዙ የተሰሩ ነገሮች እንዳሉ ለማየት ችያለሁ። ግን በተጨባጭ ሲታይ ሰው ላይ በመስራት ረገድ ብዙ ይቀረናል። እርግጥ ነው በዚህ በአጭር ጊዜ ብዙ ይሰራል ተብሎ አይጠበቅም። ሆኖም ግን ባለፉት 27 ዓመታት በተለይ አዲስ አበባ ላይ ፎቆችን ከመደርደር በላይ ነዋሪውን የሚጠቅሙ የልማት ሥራዎች ቢሰሩ ተመራጭ ነበር። ለወጣቱ የሥራ እድል የሚፈጥሩ ኢንዱስትሪዎች መገንባት ላይ እዚህ ግባ የሚባል ሥራ አልተሰራም። ስለዚህ ለእኔ አሁንም ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ዜጎች ከድህነት የሚላቀቁበትን ሥራ መፍጠር ላይ ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ ብዙ ያልተነካ ሃብት አላት ። መልክዓ-ምድሯም ምቹ ነው። ይህንን የተፈጥሮ ሃብት ጥቅም ላይ ማዋል ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ነገር ልንገርሽ። አሰብ ላይ ነዳጅ አለ፤ ግን እንድናወጣው ስለማይፈለግ እርስበርስ እንድንባላ አገሪቱም እንድትከፋፈል ተደረገ። አሁን አሰብ ላይ ያለው የነዳጅ ማጣሪያ ተደፍኖ ነው ያለው።
አፋር ውስጥ ያለው የጨው ክምር መሬቱ ቢቀፈር እንኳን በዓለም ላይ የሌሉ በርካታ ማዕድናት አሉ። ግን እንድናወጣውና እንድንጠቀምበት አይፈለግም። አሁንም ወያኔዎቹ አፋር ላይ ትኩረት የሚያደርጉት። ይህ ሀብት እንዳለ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነው። ከዚያ ባሻገር የተፈጥሮ ዘይት፤ ጋዝና ፤ አልሙኒየም አለን። ይህንን ሀብት አውጥተን ብንጠቀም መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ እንደልቡ የሚያኖር ነው። ግብፆች ውሃችንን ወስደው ኤሌክትሪክ ኃይል ሽጠው ህዝባቸውን ያኖራሉ። እኛ ግን አሁንም አብዛኛው ህዝባችን በውሃና በመብራት እጦት ችግር ውስጥ ነው ያለው። እርግጥ ነው በመንገድ መሰረተ ልማት ላይ የተሰራው ሥራ የሚመሰገን ነው። ግን ሌብነት በመንግሥት ደረጃ እውቅና አግኝቶ የተንሰራፋበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተሰራ የተባለው ልማት እንኳን በአግባቡ ህዝብን ተጠቃሚ አላደረገም። በመሆኑም ከምንም በላይ ከልጅ እስከአዋቂው ላይ የሌብነት አስተሳሰብን አስቀድሞ ማፅዳት የዚህ መንግሥት ትልቁ የቤት ሥራ ነው ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ሰዎች ከውጭ ዲፕሎ ማሲው አኳያ አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት የቱንም ያህል ጥረት ቢያደርግ የህወሓት ሰዎች የሰሩትን በተንኮል የተሞላ ዲፕሎማሲ ማሸነፍ ከባድ እንደሆነበት ያነሳሉ። እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
ኢንተርናሽናል ዳኛ ግርማ፡- እንዳልሽው ወያኔ ስልጣን ላይ እያለም ሆነ አሁን ባሉት ተላላኪዎቹ አማካኝነት የአገርን ጥቅም እየሸጠም ቢሆን ምዕራባውያንን ማሳመን ችሏል። በተደጋጋሚ እኛ እንደምንጮኸው አሁንም ድረስ ከላይ ከሚቀመጠው አምባሳደር ባለፈ ተራ ጉዳይ አስፈፃሚ ሳይቀር የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው። እነዚህ ሰዎች እየሰሩ ያሉትም የወያኔን ፕሮፓጋንዳ ነው። አሁን ላይ በየአደባባዩ እየተንከባለሉ የሚጮሁት ሁሉ ከወያኔ ይከፈላቸው የነበረው ጥቅም ስለቀረባቸው ነው። እዚህም ቢሆን ያሉት የውጭ ዲፕሎማቶች ከነበረው መንግሥት ደመወዝ ተከፋዮች ናቸው። ያንን ኃይል ካልደገፈ እዚህ መቆየት አይችሉም። እኛ በተደጋጋሚ ሰልፍ ስናደርግና ስንቃወም የነበረው የአገራችን በዚህ ሁኔታ ለውጭ ኃይል አሳልፋ መስጠቷ ስለሚያንገበግበን ነው። የውጭ ኃይሎች እንደሚፈልጉትማ ቢሆን ኖሮ በግልፅ ወታደር ልከው ያጨፋጭፉን ነበር። ግን አልቻሉም። አሁንም በከፍተኛ ንቃት መከታተል ይጠበቅብናል። ያሉን ዲፕሎማቶች በንቃት ሊከታተሉና ጫና መፍጠር ይገባቸዋል።
እርግጥ ነው፤ አሁን ላይ የተሾሙት ዲፕሎማቶች ከቀደሙት የተሻሉ ናቸው። የየራሳቸውን ጥረት እያደረጉ ነው ያሉት። እነሱን መርዳት ከሁላችንም ይጠበቃል። በተለይም ምሁራኑ ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ያላቸውን አለኝታነት በተግባር ማረጋገጥ ይገባቸዋል። የማይካድራው ነገር ከመንግሥት በላይ ጥቂት የሚባሉ ምሁራን ብርቱ ትግል እያደረጉ ነው ያሉት። ይህም በመሆኑ ነው ይህ ሁሉ የውጭ ጫና እያለ ኢትዮጵያን መታደግና ማቆየት እየተቻለ ያለው።
እኔ እርግጠኛ ሆኜ የምነግርሽ ግን አሁን በተጀመረው አግባብ መንግሥትና ዲያስፖራው ተናቦ ከሰራ አሜሪካም ሆነች ሌላ የውጭ ኃይል አላማ ሊሳካ እንደማይችል ነው። እኛ ህብረት ካለን የውጭ ተፅዕኖ ይጎዳናል ብዬ አላስብም። በመሰረቱ አሜሪካ ድሮም ቢሆን ከኢትዮጵያ ተቃራኒ የሆኑ ኃይሎችን ሁሉ የምትደግፍ አገር ነች። ይሁንና አሜሪካ አሁን ላይ በዓለም ያላት ተቀባይነትና ተሰሚነት እየቀነሰ የመጣበት ወቅትም በመሆኑ ደፍራ ከዚህ በላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ትንቀሳቀሳለች የሚል እምነት የለኝም።
አዲስ ዘመን፡- ግን በዚህ ደረጃ ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያ መንግሥትን እየተቃወሙ ያሉት ምን ስለቀረባቸው ነው ብለው ያስባሉ? ከዚህስ አኳያ ምን መስራት ይጠበቃል?
ኢንተርናሽናል ዳኛ ግርማ፡– ኢትዮጵያ ለነጮች ያልተንበረከከች የጥቁሮች አገር መሆንዋ በራሱ እነሱን የሚያስቆጫቸውና የሚያንገበግባቸው ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ። ከዚህም አልፎ አሁንም ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት ከተጠቀመችና ህዝቧ ተባብሮ ከሰራ ከድህነት ትወጣና ሌሎች የአፍሪካ አገራትን ታስተባብርብናለች የሚል ስጋት አላቸው። በነገራችን ላይ አሁንም ቢሆን ምዕራባውያኑ አፍሪካን መቆጣጠርና መያዝ ይፈልጋሉ። እንደእነሱ ምኞት ያለንን ሀብት ለእነሱ እየሰጠን የሚያመርቱትን እየገዛን እኛ ግን ለዘላለም በድህነት አዙሪት ውስጥ እንድንኖር ነው የሚፈለገው። በጥቅሉ እነሱ ወደባርነት ሊመልሱን ስለሚፈልጉ ነው ያንን ያህል ኢትዮጵያን በተፅዕኖ ውስጥ መክተት የሚፈልጉት። ይህንን እውነታ ሁላችን ጠንቅቀን ልንገነዘብ ያስፈልጋል። ደግሞም እኛ እስከዛሬ ያጠፋነውን ካረምና በህብረት አሁንም ከቆምን የፈለጉትን ቢያደርጉም ተፅዕኗቸው ሊነካን አይችል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- በጦርነቱ መራዘም እየደረሰ ያለውን ጉዳት ከመቀነስ ረገድ ከማን ምን ይጠበቃል?
ኢንተርናሽናል ዳኛ ግርማ፡- እንዳልሽው የጦርነት መራዘም አገርንም ሆነ ህዝብን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጎዳ ግልፅ ነው። በተለይም ደግሞ ይህን ሰበብ በማድረግ ሀገሪቱ ላይ ጫና መፍጠር ለሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች ትልቅ እድል ይሰጣቸዋል የሚል ስጋት አለኝ። ይህንን የምልሽ ደግሞ እንዲሁ አይደለም። ባለፈው እንደታየው የአሜሪካው የልማት ድርጅት በእርዳታ ሰበብ አሸባሪውን ኃይል በግልፅ እንደሚደግፉ ታውቋል። እርግጥ ጦርነት አይደለም ምንም ነገር በአንድ ጀምበር ግብ ሊመታ አይችልም። ደግሞም የውጭ ድጋፍ በመኖሩ ምክንያት ነው ጦርነቱ መቋጫ ያላገኘው። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ጦርነቱን ብታቆም ባታቆመውም እነሱ እኛ ላይ ጫና ከመፍር አይቦዝኑም። በመሰረቱ የኢትዮጵያ መንግሥት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም አድርጎ ነበር ሆኖ እውቅና ለመስጠት ፍቃደኛ አልነበሩም። አሸባሪውንም ኃይል በግልፅ ለመተቸት አልደፈሩም። እንዳውም ድጋፍ ሲያደርጉ ነው የተገኙት።
በሌላ በኩልም ጦርነቱ መቋጫ ያላገኘው በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አቅም ስላነሰ ነው ብዬ አላምንም። እንዳውም በሙሉ ኃይሉ ከተሰለፈ ከአንድ ሳምንት ባላነሰ ጊዜ መቋጫ ሊያገኝለት ይችላል። ግን የህዝብን ህይወት ለመታደግ የሚደረግ ጥንቃቄ በመኖሩ ነው። አሁንም የሚያሳዝነኝ ነገር በዚያኛው ወገን በኩል ምንም የማያውቅ ህዝብ በገፍ በጦርነት እንዲማገድ መደረጉ ነው። ገንዝብ ተከፍሎት ወደዚህ የሚገባው ወዶ ነው ብለን ልንተወው እንችላለን ፤ እነዚህ ግን ንፁህና አርሶ የሚበላው ገበሬና ህፃናት ማለቃቸው ልብ የሚሰብር ጉዳይ ነው። በአጠቃላይ ግን ጦርነቱ በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ ዲያስፖራው በተለይ በዲጂታል ዲፕሎማሲ ረገድ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው የሚገኘው፡ ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በምን መደገፍ አለበት ብለው ያምናሉ?
ኢንተርናሽናል ዳኛ ግርማ፡- አስቀድሜ እንደገለ ጽኩልሽ በርካታ ኢትዮጵያውያን ምሁራን በዲጂታል ዲፕሎማሲው ረገድ የመንግሥትን ሥራ በሚያስንቅ መልኩ እየሰሩ ነው። ሆኖም አሁን ጥቂት የማይባሉት ምሁራን በምን አገባኝነት አፋቸውን ዘግተው ተቀምጠዋል። የዓለምን ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅሱ ፤ ሳይንስና ምርምር የሚያከናውኑ ታዋቂ ምሁራን በየአገሩ አሉን። እነዚያ ሰዎች በኩርፊም ሆነ በራሳቸው ምክንያት ዝምታ መምረጣቸው ተገቢ አይደለም የሚል አቋም አለኝ። ምንም ቢሆን ያፈራቻቸው አገርና ህዝብ ሲጠፋ ዝም ብሎ መቀመጥ በራሱ ከጤነኛ አስተሳሰብ የሚመነጭ አይደለም። እነዚህ ሰዎች ሊነቁ ይገባል ባይ ነኝ። ግን ደግሞ እንደእነ ነዓምን ዘለቀ ያሉ ታላቅ ኢትዮጵያውያን ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ሌት ተቀን እያደረጉ ያሉት ጥረት ሊደነቅ ይገባል። እየዞሩ ድጋፍ እያሰባሰቡ ነው ያሉት። እነዚህ ምሁራን ከዚህ ቀደም ከዚህ ተሰደው ጥገኝነት ጠይቀው የገቡ ናቸው። ዛሬ ግን ለአገራቸው ህልውና ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ጀግኖች ናቸው። በዚህ ረገድ እነሱ እየሰሩ ያሉት ሥራ ሁላችንንም ከእንቅልፋችን እንድንነቃ አድርጎናል። እኔም ብሆን ዛሬ በዚህ እድሜዬ ከአገሬ በላይ ቅድሚያ የምሰጠው ነገር የለም። በመሆኑም ከጠየቅሽኝ ጥያቄ አንፃር መንግሥት እነዚህን ጀግና ኢትዮጵውያንን መደገፍና ከፊት መምራት ይጠበቅበታል ብዬ አምናለሁ። ከእነዚህ ኢትዮጵያውያን ጋር እጅና ጓንት ሆነው ተናበው መስራት ይገባቸዋል።
አዲስ ዘመን፡– በጦርነቱ ምክንያት በርካታ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለው በችግር ውስጥ ነው ያሉት። እነዚህን ዜጎች ሕይወት ከመታደግ አኳያ ከማን ምን ይጠበቃል?
ኢንተርናሽናል ዳኛ ግርማ ፡– ዲያስፖራም ሆነ ሌላው ዜጋ ለኢትዮጵያ አገራቸው ብዙ ሊሰሩት የሚገባ ሥራ አለ ብዬ ነው የማምነው። በተለይ ከኢትዮጵያ ውጭ የሆነ ማንኛውም ሰው ከመቼውም በላይ ኢትዮጵያን ለማዳን እየተረባረበ ነው ያለው። አሁን ይህንን ያህል ቁጥር ያለው ዲያስፖራ አገሩ የመጣው ህይወቱን እየሰጠ ያለው ወታደር እና በዚህ ምክንያት ለተጎዱ ዜጎች የሚችለውን ለማድረግ ነው። ጀምረነዋል፤ እንቀጥለዋለን። ደግሞም ከውጭ መንግሥታት እርዳታ አንጠብቅም ፤ ልክ እንደግድቡ ሁሉ ተረባርበን አገራችንን ማዳን ይገባናል።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ኢንተርናሽናል ዳኛ ግርማ፡- እኔም ዳግም የሀገሬን መሬት ረገጬ ለምወደው ህዝቤ ሃሳቤን እንዳካፍል ስለረዳችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2014