የሰለጠነው ዓለም ዛሬ ላይ በፊልም ኢንዱስትሪ እድገት ልቆ ሄዷል፡፡ ባለሙያዎቹም ዓለምን በአስተሳሰባቸው የማጥለቅለቅ ህልማቸው ሰምሮላቸዋል፡፡ ከዘርፉም እንደ ሀገር ማግኘት የሚገባቸውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከማግኘት ባለፈ ለዘርፉ በተፈጠሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂ ታግዘው ባህልና እምነታቸውን፣ ስልጣኔና ማንነታቸውን፣ የፖለቲካ ፍልስፍናቸውንና ዓለማዊ እይታቸውን በረቀቀ መንገድ ለዓለም አሳይተዋል፡፡ ባሻቸው መልኩ በሰዎች አዕምሮ ውስጥ የእነሱን ምስል አኑረዋል፡፡
ይሄንን የተረዱት ሀገራት ለሙያው ትኩረት በመስጠት ለእድገቱም ልዩ ድጋፍ በማድረግ ዘርፉ ላይ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ፊልም የሚሰራው ሰው ነውና ለፊልም ኢንዱስትሪው ብቁ የሆነ የሰው ኃይል በማፍራት በክህሎትና በእውቀት የታገዘ ተጽዕኖ ፈጣሪ ስራዎችን መስራት በቀላሉ ተቀባይነትን ማግኘት አስችሏቸዋል፡፡ በዚህም በብዙ ሚሊዮን ዶላሮችን ከዘርፉ በማግኘት ኢኮኖሚያቸውን በመደገፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
በሀገራችን ገና በማደግ ላይ ያለው የፊልም ኢንዱስትሪ ሀገራዊ ፋይዳው ለማሳደግና ከዘርፉ የሚገኘውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ለመቋደስ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል፡፡ በተለይም በዘርፉ የሚሰማሩ ሙያተኞችን በማሰልጠን ለሙያው የሚያስፈልገውን ሁሉ የሚያሟሉ ማድረግ ዘመኑን ያገናዘበ ጥራት ያለው ስራ በመስራት ከሌላው ጋር እኩል መሰለፍ ያስችላል፡፡
ፊልም በዝግጅት ወቅት ተገቢ ትኩረት ተሰጥቶት ከተሰራበት ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑ በብዙ ማሳያዎች መግለጽ ይቻላል፡፡ ፊልም ባህልና ስልጣኔን ማሳያ፣ የሰው ልጅ አመለካከትን መቅረጫ፣ የገቢ ምንጭና በጎ አመለካከቶችን በማህበረሰቡ ጥበባዊ በሆነ መንገድ ማሰራጫ ነው፡፡ ይህንን ፋይዳ ከዘርፉ ለማግኘት ደግሞ የፊልም ስራው በሰለጠነና ክህሎቱ ባለው ሙያተኛ መሰራት ይኖርበታል፡፡
በፊልም ስራ ውስጥ የገዘፈ ሚና ያለው ፊልሙን የሚያዘጋጀው ባለሙያ /ዳይሬክተሩ/ ማን ነው? ምን ዓይነት እውቀትና ክህሎት ሊያሟላ ይገባዋል? ተግባርና ኃላፊነቱስ ምንድነው? የሚሉት ጉዳዮች በዛሬ የኪነ ጥበብ አምዳችን ልናሳያችሁ ወደድን፡፡
በፊልም ስራ ውስጥ ተግባሩ የጎላው የፊልሙ አዘጋጅ /ዳይሬክተር/ ለሚያዘጋጀው ፊልም ስኬትና ውድቀት ዋንኛ ተዋናይ ነው፡፡ የሚያዘጋጀው ፊልም ስራ ከጅምሩ አንስቶ ተመልካች ጋር እስኪደርስ በሁሉም ስራዎች የሚሳተፍና ሥራውን በአጠቃላይ በበላይነት የሚመራ ሙያተኛ ነው፡፡
በፊልም ስራ ውስጥ አዘጋጁ ምትክ የሌለው ዘርፈ ብዙ ተግባር ፈጻሚ መሆኑን የፊልም ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ሙሀመድ ኢብራሂም የፊልም አዘጋጅና ደራሲ ነው፡፡ አንድ ፊልም ላይ የሚሳተፍ አዘጋጅ ፊልሙን ፊልም እንዲሆን የሚያደርግ ዋንኛው ሰው መሆኑን ይናገራል፡፡ አዘጋጁ የካሜራ ባለሙያው የሚፈልገው ምስል ከሚፈልገው አቅጣጫ እንዲወስድለት መምራት፣ ተዋናዩ በሚፈልገው መልክ ገጸ ባህሪውን ተላብሶ እየተወነ መሆኑን መከታተል፣ ፊልሙ የሚቀረጽበት ቦታ ለታሪኩ የሚመጥን መሆኑን መለየትና በአጠቃላይ በፊልም ስራ ላይ የመሪነት ሚና የሚጫወተው አዘጋጁ ነው፡፡ ለዚህም ነው የፊልም ስክሪፕት ጻሐፊ /ደራሲ/ እና ፊልሙን ለማሰራት ገንዘብ የሚያወጣ የፊልሙ ባለቤት /ፕሮዲዩሰር/ እያሉ፤ ፊልሙ ሲጠራ የፊልሙ አዘጋጅ /ዳይሬክተሩ/ ስም ተጠቅሶ ‹‹የእገሌ ፊልም›› የሚባለው፡፡
ለፊልም ጥሩ አዘጋጅ ከሌለ ጥሩ ፊልም መስራት ፈጽሞ የማይታለም መሆኑን የፊልም ባለሙያው ሙሀመድ ያስረዳል፡፡ ታሪኩ በምስል አስደግፎ ቃለ ተውኔቱ ከትወናው ጋር አዋህዶ በሰዎች አዕምሮ ውስጥ የሚሳል ሀሳብ ፈጥሮ፤ የሚወደድ የታሪክ ፍሰትን አካቶ፤ ልብ አንጠልጣይ ሁነትን አከታትሎ የሚያሳይ ፊልም ለመስራት በሙያው የበቃ ክህሎትና የፊልም ስራ እውቀት ያለው አዘጋጅ መኖር ግድ የሚለው ለዚህ ነው፡፡ ይህንን ያሟላና ሙያው የሚፈልገው ችሎታ የሌለው የፊልም አዘጋጅ ፊልሙን ይዞት መውረዱ አይቀሬ ነው፡፡ ለዚህም ነው በየሳምንቱ ከሚመረቁ ፊልሞቻችን ውስጥ ተፅዕኖ መፍጠርና መነጋገሪያ መሆን የቻሉት ጥቂት የሆኑት፡፡
ጥሩ ዝግጅት የተደረገበትን ፊልም ለማየት ወደ ሲኒማ ቤት የሚጎርፈው ተመልካች፤ ጥሩ ዝግጅት በማይታይባቸው ፊልሞች ምክንያት ከሲኒማ ቤት ሲርቅ ማየቱ የተለመደ ሆኗል፡፡ ምንም እንኳን ለፊልም ተመልካች ከሲኒማ ቤት መጥፋትና ለፊልም ኢንዱስትሪው መቀዛቀዝ የበዙ ምክንያቶች ቢኖሩም የፊልሙ ባለሙያዎች ስራቸውን በሚፈለገው የጥራት ደረጃ አለመስራት እንደ ዋንኛ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡ ፊልሙን በዋናነት የሚመራው የፊልሙ አዘጋጅ ደግሞ ለፊልም ስራው ጥራትና የተሻለ መሆን ሚናው የጎላ ነው፡፡
አንድ ፊልም አዘጋጅ ሊያሟላቸው ከሚገቡት ነገሮች መካከል በዋናነት ግን ጊዜውን የሚመጥን ሙያዊ እውቀትና ክህሎት ይጠቀሳል፡፡ አንድ የፊልም አዘጋጅ ለፊልም ስራ ምን እንደሚያስፈልግ፣ እንዴትና በምን ሁኔታ እንደሚሰራ፣ ፊልም ዛሬ ላይ የደረሰበት ደረጃ ምን እንደሆነና በስራው ወቅት የሚያስፈልጉ ጉዳዮችን ጠንቅቆ ማወቅና በክህሎት የታገዘ ሙያዊ ብቃት ሊኖረው ግድ ይላል፡፡
በስራው የሚገጥመውን ማንኛውም ከባድ ሁኔታ በብልሀት የሚያልፍበትና ነገሮችን በልዩ ዐይን የሚመለከትበት፣ በጽሑፍ የተመለከተው ታሪክ ነፍስ እንዲዘራ ማድረግ የሚያስችል የፈጠራ ችሎታ ሊኖረው ይገባል፡፡ ታሪኩ የሚያሳይበት ወይም ለመንገር የሚጠቀምበት መንገድም ለፊልሙ ወሳኝነት አለውና የፊልሙ አዘጋጅ ይህንን በብቃት የሚገልጽበት የፈጠራ ችሎታ እንዲኖረው ይጠበቃል፡፡
የፊልም ስራ በባህሪው በቡድን የሚሰራ ነው፡፡ በመሆኑም የፊልም አዘጋጁ የተለያየ ባህሪና ችሎታ ያላቸው ተዋንያን፣ የፊልሙ ቀረጻ ባለሙያዎች፣ አሰሪዎችና ባለቤቶች በአጠቃላይ በፊልም ስራው ውስጥ ያሉ ሙያተኞች ጋር ተግባብቶ መስራቱ ለስራው ስኬታማነት ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ከሁሉም ባለሙያዎች ጋር ተግባብቶ በስምምነት የሚሰራ ስራ ውጤቱ ያማረ ስለሚሆን የፊልም አዘጋጅ ጥሩ የመግባባት ችሎታ ሊኖረው ይገባል፡፡ የፊልም ስራ ሙያተኛን እንደ ባህሪው ማስተናገድ፣ እንደ ፊልሙ ስራ መሪ ትእግስትን መላበስና ነገሮችን በብልሀት መከወን ከአንድ የፊልም አዘጋጅ የሚጠበቅ ልዩ ችሎታ ነው፡፡
ሌላው በፊልም ስራ ውስጥ በመሪነት የሚሳተፈው አዘጋጅ በሙያው ላይ ከሌላ አካል ጣልቃ ገብነትና ከተጽዕኖ ነጻ መሆን እንዳለበትም ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ እንደ አዘጋጅ ውሳኔዎችን በመወሰን ለስራው አስፈላጊ ነው ብሎ ያመነበትን ነገር ማድረግ ይገባዋል፡፡ አሁን ባለው አሰራር የፊልም ባለቤቶችና ሌሎች የፊልም ባለሙያዎች አዘጋጁ ላይ ጫና በመፍጠር የሚፈልገውንና የሚያስበውን በራሱ እንዳይተገብር ያደርጉታል የሚለው ሙሀመድ አዘጋጁ ይሄን በመቋቋም ስራውን በፈለገው መልኩ መምራት ይገባዋል ይላል፡፡
የፊልም አዘጋጅ ሙያው የሚጠይቀውን ብቃት ማሟላት እንዲችል በየጊዜው እራሱን የሚያበቃ ከቴክኖሎጂው ጋር የተዛመደ፣ ስለ ፊልም መስሪያ መሳሪያዎች መሰረታዊ እውቀት ያለው፣ ለፊልም ሙያ ስራ የሚያስፈልግ ክህሎት ያለውና አዳዲስ ፈጠራዎችን ማፍለቅ የሚችል ታታሪ ሙያተኛ ሊሆን ይገባል፡፡
የፊልም ኢንዱስትሪው እድገት እንዲፋጠን ከመንግስትና በፊልም ኢንዱስትሪ ከተሰማሩ ባለ ድርሻ አካላት ብዙ ይጠበቃል፡፡ በተለይም በዘርፉ የሚስተዋለው የሰለጠነ የሰው ሀይል እጥረት በማሟላት በሙያው ላይ የሚያሰለጥኑ ደረጃቸውን የጠበቁ ማሰልጠኛዎች ማቋቋም ወሳኝ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ በፊልም ስራ ውስጥ ዋንኛ ተሳታፊ ሆነው ፊልም አዘጋጅም እራሱን በማብቃት ሁሌም የተሻለ ስራ ይዞ ለህዝብ ማቅረብ አለበት የሚለው መዝጊያ መልዕክታችን ነው፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2011
በተገኝ ብሩ