በዓለም አቀፍ ደረጃ የሳይበር ጥቃት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ በዚህ ጉዳይ ልዕለ ኃያል ናቸው የሚባሉ አገራትም በመረጃ መንታፊዎች በከፋ ሁኔታ በመፈተን ላይ ይገኛሉ፡፡ የአለም የገንዘብ ድርጅት ያወጣው ዘገባ እንደሚያመለክተውም በባንኮች ላይ ብቻ ባነጣጠሩ ጥቃቶች እኤአ 2016 ከነበረበት ከ600 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ኪሳራ፣ በ2020 ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል፡፡ችግሩ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ አሁን በሳይበር ደህንነት ምክንያት ባንኮቹን እያስወጣቸው ካለው 9 በመቶ ጠቅላላ ዓመታዊ ገቢያቸው እስከ 50 በመቶ ድረስ ከፍ ሊል እንደሚችልም በመረጃው ተመልክቷል፡፡
ችግሩ በኢትዮጵያም የሚታይ ሲሆን፣ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትና የጥቃት ሙከራዎች በእጅጉ በመጨመር ላይ ይገኛሉ፡፡ ለማሳያ ያህል በ2012 ዓ.ም ከተሰነዘሩት አደገኛ የሳይበር ጥቃቶች 1 ሺህ 087 ከነበረበት በ2013 ዓ.ም ከ 150 በመቶ በላይ ጨምሮ ከ2 ሺህ 800 በላይ የሳይበር ጥቃቶች መሰንዘራቸውን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ጉዳቱ ከዕለት ወደዕለት እያየለ በመምጣቱ ለችግሩ መፍትሄው ምን ይሆን? እንዴትስ መከላከል ይቻላል? በሚለው ዙሪያና ‹‹የሳይበር ደህንነት የጋራ ኃላፊነት! እንወቅ! እንጠንቀቅ!›› በሚል መሪ ሐሳብ በዚህ ወር ለሁለተኛ ጊዜ እየተከበረ ያለውን የሳይበር ደህንነት ወር በተመለከተ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) የሳይበር አመራርና አስተዳደር ዲቪዥን ኃላፊ አቶ ሃኒባል ለማ ጋር አዲስ ዘመን ያደረገውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሳይበር ጥቃት በማን ይፈጸማል? በዋናነትስ ኢላማ የሚደረገው በምን ላይ ነው?
አቶ ሃኒባል፡- የሳይበር ጥቃት በዋነኝነት እየተፈጸመ ያለው ከውጭ በሚደረግም ጥቃት ጭምር ነው፡፡ ጥቃቱ ሆነ ብለው በሚፈጽሙ አካላትም ሊደርስ ይችላል፡፡ እናም ፈጻሚዎቹ የአገራችንን የመሰረተ ልማት ሰፊ ዳሰሳን በመረጃነት የሚፈልጉ ክትትል አድራጊዎችም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም ባህሪያቸው በጣም የተለያየ ነው፡፡
በአሁን ሰዓት ደግሞ ይህ ሁኔታ ከፍ እያለ መጥቷል ማለት ብቻ ሳይሆን በጣም እየተደጋገመ መምጣቱን መረዳት ይቻላል፡፡ በተለይ በጣም በመደጋገም እየመጣ ያለው የየተቋማቱ የየራሳቸው ድረ ገጾችና የማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው አካውንት ከዚህ ቀደም ከእነርሱ ጋር ይሰሩ በነበሩ ወይም ደግሞ በአሁን ሰዓት አብረዋቸው እየሰሩ ባሉ ሰራተኞች ያለአግባብ የመጠቀም ሁኔታም ይኖራል፡፡
ብዙ ተቋማት ያላቸውን ሀብትና ንብረት ማን እያስተዳደረው ወይም እየመራው እንደሆነ አያውቁም፤ እሱን ተከትሎ የሚመጡ ጥቃቶች የሚዲያ ሽፋንም እያገኙ ስለሆነ እሱ ላይ ትኩረት እየተደረገ ነው ብለን እንወስዳለን እንጂ የጥቃቶቹ አይነት ድሮ ከነበሩት ይበልጥ ተጠናክረው በቁጥርም እየበረከቱ ነው የመጡት፡፡
ሌላው ስም ማጥፋትና በሐሰተኛ ወሬ ማህበረሰቡን ለማጥመድ የሚደረጉ ስራዎች አሁንም በጣም በስፋት ነው የሚስተዋሉት፡፡ በተለይ ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በመንግስትና በህዝብ መካከል ግርታን ብሎም ብዥታን ለመፍጠር እና ያለውን መተማመን ለመቀነስ ኢላማ የተደረጉ ጥቃቶች በስፋትና በግላጭ እየታዩ ናቸው፡፡ እንዲህ አይነቱ ሂደት ደግሞ የተሳሳተ ሆኖ ብቻ የሚቀር ሳይሆን አንዳንዴም ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የሚፈጸመው የሳይበር ጥቃት 90 በመቶ ያህሉ በግንዛቤጉድለት ነው ይባላል፤ ይህን ክፍተት ለመሙላት ከሳይበር ደህንነት ወር ከማክበር በዘለለ ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ሃኒባል፡- ብዙ ጊዜ የሳይበር ጥቃት ሲፈጸምም ባለማወቅ ወይም ቸልተኛ በመሆን ወይም ደግሞ ሆነ ተብሎ በሰዎች በኩል የሚፈጸሙ ክፍተቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ጥቃቶች በቁጥር ከፍ ያሉ ሲሆን፣ አደጋቸውም የዚያን ያህል ላቅ ያለ ነው፡፡ ይህን ለመከላከል የሳይበር ደህንነት ወር፤ ሰዎች ያሉበት የትኛው ነው ብሎ ነው የሚጀምረው፡፡ አንደኛ ሰው፣ የማህበረሰቡ አንድ አካል እንደመሆኑ ወደሰው እንዴት መደረስ አለበት የሚለውን በማንሳት የማህበረሰብ ንቅናቄ እንዲኖር ይደረጋል፡፡
ይህ የማህበረሰብ ንቅናቄ የሳይበር ወርን ጨምሮ በቴሌቪዥን፣ በራዲዮና በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም በማህበራዊ ትስስር ገጾች ተደራሽ ለመሆን ነው እየተሰራ ያለው፡፡ በሳይበር ደህንነት ጉዳዮችም የማሳወቅ በየቀኑም ጥንቃቄ የሚደረጉባቸው ጉዳዮችን ማስታወስ ጭምር ላይ ከመሰራቱም ጎን ለጎን ቀስ በቀስ ማህበረሰቡ ይህን ጉዳዩ ባህሉ እንዲያርግ ነው ጥረት እየተደረገ ያለው፡፡
ሌላው የአንድ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋም ሰራተኛ ወይም የሴኪዩሪቲ ባለሙያ ወይም ደግሞ የአንድ የቴክኖሎጂ ሀብት አስተዳዳሪ ወይም ራሱ ተጠቃሚ ሆኖ ይገኛል፡፡ የተቋሙ ስንል የተቋሞ ደንበኞች ጭምር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ለደንበኞቻቸው የሳይበር ደህንነትን በተመለከተ ተቋሙ የተሰማራበትን ቢዝነስ መሰረት ያደረጉ ስልጠናዎች እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡ ይህ ከኢንሳ ጋርና ከተቋማቱ ጋር በትብብር የሚደረግ ይሆናል፡፡
ከዚህ ከፍ ብለን የምናየው እነዚህ ተቋማት ደግሞ የተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ይሆንና እንደዘርፍ ደግሞ የሚጋሩት የስራ ባህሪ ይኖራል፡፡ እነርሱን ደግሞ እንዴት አድርገን እንድረስባቸው? ምን አይነት የሳይበር ደህንነት ስልጠና ወይም የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና እንስጣቸው? የሚለው ጉዳይ በጋራ ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ ሚዲያው በልዩነት ምን ሊያደርግ ይገባል? የሚለው ነገር ይታያል ማለት ነው፡፡ ሚዲያ ለህዝብ ቅርብ ስለሆነ ጥሩ ነገር ማድረግ እንደሚችል ሁሉ ጉዳትም ሊኖረው ስለሚችል እንዴት አድርገን ነው ቀርበን አብረን የምንሰራው? የሚለውን ለማወቅ የሳይበር ደህንነትን እንደ ባህል ይዞ ማሳደግ የሚለውን መተግበር ይጠይቃል፡፡ የፋይናንሱም ዘርፍ እንዲሁ የራሱ የሆነ አውድ ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ ሁሉንም መሰረት ያደረጉ ስራዎች ይሰራሉ ማለት ነው፡፡
እዚህ ላይ አብሮ መሄድ ያለበት ጉዳይ የዘርፉ ከፍተኛ አመራሮችም ይሁኑ የተቋማት ክፍተኛ አመራሮች የራሳቸው የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና ፕሮግራም ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ለምንድን ነው ለብቻቸው ትኩረት የተሰጣቸው ቢባል የሳይበር ደህንነት ጉዳይ ባለቤትነቱ ከአመራር ሲመጣ የተሻለ ይሆናል በሚል ነው፡፡ ምክንያቱም የመወሰንና ገንዘብ የመመደብ እንዲሁም የማስተባበርና አስፈላጊውን ስርዓት የመዘርጋትና አወቃቀር የመፍጠር ስልጣኑ ስለሚኖራቸውም ጭምር ነው፡፡ ይህ አይነቱ ስራ የተቋማት ከፍተኛ አመራሮችና የዘርፍ ኃላፊዎች ላይ የሚወድቅ ስለሆነ በልዩነት ስልጠና እንዲሰጣቸው ይደረጋል፡፡
ስለዚህ አሁን የምንነሳው ከግለሰብ፣ ግለሰብ ደግሞ እንደ ማህበረሰብ አባል፣ ቀጥሎም ግለሰብ እንደ ተቋም አባል፣ ተቋማትን ደግሞ እንደ ዘርፍ አባል አድርገን ለእያንዳንዱ የሳይበር ንቃተ ህሊና እንዲኖር ለማድረግ ነው ፕሮግራሞች እየተቀረጹ ያሉት፡፡ ከዚህ ባለፈ ከተቋማት ጋር ለመስራት ማናገራችን እንደተጠበቀ ሆኖ በተቋማትም ጥያቄ ስራዎች ይሰራሉ፡፡
በሌላ በኩል የማህበረሰብ ንቅናቄ ሲባል የሳይበር ደህንነት ወር ተጠብቆ ብቻ ሳይሆን በየእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ማስታወስ ስለሚያስፈልግ የተለያዩ
ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለአብነት ከእናንተ ድርጅት ማለትም ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በመተባበር እያሳተምን ያለ አይነት ህትመትም ወደ ማህበረሰቡ ማድረሻ አንድ መንገድ ነው ማለት ይቻላል። በዚህ በዚህ አይነት ስራ ነው ከሳይበር ደህንነት ወር ባለፈ እየሰራን ያለነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- መረጃ ጠላፊዎች እንዳይሳካላቸው በቀጣይ ምንድን ነው መደረግ ያለበት? ምክንያቱም በቅርቡ ከተሰነዘረው የሳይበር ጥቃት መካከል የኢትዮጵያ ብሮድክስቲንግ ኮርፖሬሽን ድረ ገጽ መሆኑ የሚታወስ ነው? መሰል ጥቃቶችን ለማክሸፍ እየተሰራ ያለ ቅንጅታዊ ስራ ምን ይመስላል?
አቶ ሃኒባል፡- ይህን ጉዳይ ሶስት ነገሮች ላይ ትኩረት አድርገን ብናይ መልካም ነው፡፡ የመጀመሪያው ጉዳይ ምን ሀብት አለን የሚለው መታወቅ አለበት። ተቋማት ይህን ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው። እኔ እያስተዳደርኩት ያለውና የምጠቀመው ሀብት እንዲሁም ለሌሎቹ ተደራሽ የምሆንባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው? ለምንስ አይነት ጥቃት ተጋላጭ ናቸው? ማንስ ሊያጠቃን ይችላል? በምንስ አይነት መንገድ ነው ላስጠብቃቸው የምችለው? የሚለው ጉዳይ አንዴ ቁመናው ከታወቀ በኋላ፤ ምን አይነት ጥበቃ ላድርግለት የሚለው ደግሞ በሁለተኛነት የሚመጣ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ያለንን ሀብት በግልጽ ማወቅ፤ ምን አይነት አደጋ ያስከትላል የሚለውን መረዳት፤ ምን አይነት መከላከያ ላብጅለት የሚለውን መገንዘብ ነው፡፡
መከላከያው ዘንድ ስንመጣ ደግሞ በሶስት መንገድ ሊገለጽ የሚችል ደረጃ አለው፡፡ አንደኛ ቴክኖሎጂውን ራሱ በቴክኖሎጂ የመጠበቅ ነገር አለ፡፡ ወይም የምንጠቀማቸውን ሀብቶች ደግሞ ደህንነታቸው በተጠበቀ መንገድ የመጠቀም ጉዳይ ይኖራል፡፡ ቀጥሎ ደግሞ የምንጠቀምባቸውን ቴክኖሎጂዎች በአግባቡ ለማስተዳደር ምን አይነት የአሰራር ስርዓት ሊገነባ ይገባል፤ ምን አይነት አደረጃጀት አለን፤ ከራሳችን ቢዝነስ ጋር የሳይበር ደህንነት በተጣመረ መንገድ መጠቀም እንችላለን የሚለውን የምንረዳበት የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ነው፡፡ አስፈላጊ የሆኑ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት፤ ይህንንም ስርዓት ወደመሬት ማውረድ ይገባቸዋል። ቀጥሎ የሚመጣው ደግሞ ሰው ሲሆን፣ የትኛውን ሀብቴ የትኛው አካል ነው እያስተዳደረው ያለው፤ እየተጠቀመውስ ያለው ማን ነው፤ በምንስ አይነት መንገድ ነው እየተጠቀመ ነው ያለው፤ እንዴትስ ነው በትክክልና ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ እንዲጠቀምበት ማድረግ የሚቻለው፤ ለዚህ ደግሞ አግባብነት ያለው ስልጠና የትኛው ነው፤ የሚለውን አስበን መስራት ይጠበቅብናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ መከላከያ ላይ ስንመጣ ከሰው፣ ከቴክኖሎጂና ከአሰራር ስርዓት ተነስተን ማድረግ የሚገባንን ነገሮች እናደርጋለን ማለት ነው፡፡
እነዚህን ነገሮች ሁሉ ስናደርግ በአንድ ጊዜ አስፈላጊ እውቀት እና ሀብት የሳይበር ደህንነቱን ማስጠበቅ የሚያስችል ላይገኝ ይችላል፡፡ ስለዚህ ማድረግ ያለብን የመጀመሪያው አማራጭ የሳይበር ደህንነትን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስጠበቅ ተብሎ የተቋቋመ ኢንሳ አለ። ስለዚህ ምን እናድርግ ብለው ሊያማክሩን ይችላሉ። ቀድመው ቢጠይቁን አብረውን ሊሰሩ ይችላሉ። ስለዚህ ኢንሳ አሁን ካነሳናቸው የመፍትሄ ሐሳብ በመነሳት በማማከሩም ይሁን በቴክኖሎጂ አቅርቦትና በስልጠናም ጭምር በመሳሰሉት ድጋፎችን ይሰጣል፤ ያግዛልም፡፡
ሌላው ግን አንድ መረሳት የሌለበት ራሳቸው ተቋማት ከተሰማሩበት የቢዝነስ ዘርፍ በመነሳት የሚጋሯቸው ሌሎች አካላት ለምሳሌ ባንኮች ከሆኑ ሌሎች ባንኮች ይኖራሉ፤ ለምሳሌ ሚዲያ ከሆነ ደግሞ ሌላ ሚዲያ ይኖራልና ምን አብረን እንማማር፤
ለምንድን ነው እኛ ለመረጃ መንታፊዎች ኢላማ የሆንነው፤ መከላከልስ ያለብን እንዴት ነው፤ የጋራ ስልትና የጋራ አሰራር ወይም ደግሞ የጋራ የልምድ ልውውጥ በማድረግ መፍታትና በጉዳዩ መተባበር አያስፈልገንም ወይ ብለው በጋራ ለመስራት መነሳሳት ያስፈልጋቸዋል። ስለዚህ ይህን ለማድረግ ከማን ጋር ነው ተባብሬ መስራት ያለብኝ በማለት ይህንኑ ስራ ወደመሬት ማውረድ ይጠበቅባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በመጀመሪያው የሳይበር ወር ላይ ምን ምን ስራዎች ተሰርተዋል? ምን አይነት ንቃተ ህሊና ተገኝቷል? ለየትኞቹ የስራ ዘርፎች እና ሙያዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸዋል?
አቶ ሃኒባል፡- ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ አገር ያከበርነው ባለፈው ዓመት ሳይሆን አቻምና በ2012 ዓ.ም ነበር የሳይበር የተከበረው፡፡ በ2013 ዓ.ም በኮቪድ 19 እና በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ምክንያት ሳይከበር አልፏል፡፡ በዚህም ምክንያት አሁን በዚህ ጥቅምት ወር እያከበርን የምንገኘው የሳይበር ደህንነት ወር ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡
በ2012 ዓ.ም የተከበረው ለአንድ ሳምንት ያህል ብቻ ሲሆን፣ የተከበረውም ለመጀመሪያ ጊዜ ስለነበር የሳይበር ወር ምንድን ነው የሚለው ላይ የማስተዋወቅ ስራ ነው የተሰራው፡፡ በዚህም እግረመንገዳችን ኢመደኤ (ኢንሳ) በሳይበር ደህንነት ዙሪያ የሰራቸው ስራዎች የተዋወቁበት፣ ባለድርሻ አካላት ደግሞ የሳይበር ደህንነት የመጀመሪያ ደረጃ የሚባል የንቃተ ህሊና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል ከተለያዩ ዘርፎችና ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎችና አመራሮችን ግንዛቤ ለመፍጠር ተከታታይ መድረኮች የተዘጋጁበት ነው፡፡
በወቅቱ እንደመክፈቻ ተደርጎ ተይዞ የነበረው መርሃግብር ኮንፈረንስና ኤግዚቢሽን ነበር፡፡ ምን ምን ጉዳይ ተሰርቷል፤ ምን አይነት ምርት ተሰርቷል፤ በቀጣይስ ምን እናደርጋለን በሚል ዙሪያ ነበር ሲካሄድ የቆየው፡፡ በወቅቱ የመጀመሪያው መክፈቻ ስነስርዓቱ የተካሄደውም በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ውስጥ ሲሆን፣ ለተከታታይ አራት ቀናት ደግሞ ተቋሙ በመጀመሪያ በነበረበት ዋና ቅጥር ግቢ ውስጥ ተከታታይ ኤግዚቢሽኖችና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ተከናውነዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዛ ፕሮግራም እንደ አገር የመጣ ለውጥ አለ ማለት ይቻላል? ውጤታማ ነበርን ብላችሁ ታስባላችሁ?
አቶ ሃኒባል፡- ውጤቱን ለመለካት በመጀመሪያ ማድረግ ያለብን የሳይበር ደህንነት ጉዳይ አጀንዳ ሆኖ ተወርቷል ወይ? የሚለው ነው፡፡ ቢያንስ ሳይበር ምንድን ነው? ብሎ ለመጠየቅ፤ የሳይበር ደህንነት ምንድን ነው? ከእኔ ጋርስ ምን ያገናኘዋል? የሚለው ደረጃ የሚታይ ሳይበርን በአጭር ጽሁፍ፣ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃንም ይተላለፍ ስለነበር ስለምንነቱ እንዲጠያየቁበት ምክንያት መሆን በመቻሉ እንደ አንድ ውጤት የሚታይ ነው፡፡
ከዚህ ቀጥሎ መታየት ያለበት ግን ኢንሳ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለሚኖረው ግንኙነት ‹‹እኔ ይህን እየሰራሁ ነው፤ ከእናንተ ደግሞ ይህን አይነት ትብብር እፈልጋለሁ ብሎ ለመጠየቅና ለማውራት እናም የመጀመሪያም ግንኙነት ለመፍጠር አስችሎናል፡፡
ሌላው ከዚህ በፊት ከሳይበር ደህንነት ጋር የማናገናኘው ዘርፎችና ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች በጉዳዩ ላይ ፍላጎት ኖሯቸው እንዲጠይቁና እንዲወያዩ ብሎም ስለጉዳዩ ማሰብ እንዲጀምሩ መነሻ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ እነዚህን እንደስኬት እንወስዳቸዋለን፡፡
ከዛም በኋላ የተደረጉ እንቅስቃሴዎችም የ‹‹አብረን እንስራ›› አይነት ጥያቄዎች መቅረብ የቻሉ ሲሆን፣ ‹‹እኛ በምን አይነት መንገድ ነው የሳይበር ደህንነትን ማስጠበቅ የምንችለው›› በሚል የመጀመሪያ ደረጃ ጥያቄዎች እንዲጠየቁ የቻለ ነበር ማለት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ዓመት በያዝነው ጥቅምት ላይ እየተከበረ ያለው የሳይበር ወር ዓላማው በዋናነት ትኩረት ያደረገው ምን ላይ ነው?
አቶ ሃኒባል፡-ዓላማው ልክ በየዓመቱ ሳይበር የተለያየ መርህ ቃል ይዞ የሚከበር ቢሆንም በዋነኝነት ግን በየዓመቱ ለማህበረሰቡ የሳይበር ደህንነትን ማስታወስና ንቅናቄ በመፍጠር ከፍ ያለ የንቃተ ህሊና ደረጃ እንዲኖር ለማድረግ እንዲሁም ከሳይበር ጋር የተያያዙ አገርኛ ጉዳዮች፣ ወቅታዊ ጉዳዮች ማንሳት እንዲቻል ለማድረግ ነው፡፡ የሌሎች አገሮች ልምድም የሚነግረን ይህንኑ ነው፡፡
ስለዚህም ከባለፈው ከመጀመሪያው ተሞክሮ በመነሳት የአሁኑን ፕሮግራም ሰፋ ልናደርገው ወደድን። ስለዚህም አንድ ሳምንት ከሚሆን የጥቅምትን ወር በአጠቃላይ የሳይበር ወር ንቅናቄ የሚደረግበት አድርገን በማሰብ እንመልከት በሚል ነው፡፡ እንዲህ እንዲሆን የተፈለገበት ጉዳይ ደግሞ ብዙ ተቋማትን እና ብዙ ባለድርሻ አካላትን እንደየጉዳያቸው መድረስ እንድንችል ያደርገናል፡፡ ከዚህ ከነበረው ጥቅል ምልከታ የሳይበር ደህንነት የማሳወቅና የግንዛቤ መስጫ መንገድ አሁን ደግሞ ወደየተቋማቱና ዘርፎች እና ለየራሳችን ጉዳይ አውዱን በዋጀ መንገድ ማቅረብ የምንችልበት የንቃተ ህሊና መፍጠሪያ ፕሮግራም እንዲሆንልን በሚል ተስፋ ተድርጎ ታይቷል፡፡
ሌላው ደግሞ ተቋማቱን በዚህ ልክ የምንደርስ ቢሆንም ከዚህ በፊት በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የምናቀርባቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ በአንድ ሳምንት ውስጥ የተገደበ ነበር፡፡ አሁን ግን ወሩን ሙሉ ይሆንና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትም እኛን ይመለከተናል ብለው ሰዎች ስለጉዳዩ ማውራት እንዲችሉ፣ ተደራሽ የምንሆንባቸውንም መገናኛ ብዙሃኖች ለምሳሌ ከዚህ በፊት ያልሞከርነው የህትመት ውጤቶችን መጠቀም የሚለው አንዱ የምናየው ይሆናል፡፡ በተጨማሪም የማህበራዊ ትስስር ገጾችንና ድረ ገጾችንም እንዲሁ፡፡ ቴሌቪዥንና ሬድዮ ቀድሞ የምንጠቀምበት የነበረ ነው፤ ግን በዛ ተደርጎ ትኩረቱን በሳይበር ወርና የሳይበር ወር ዓላማ ባደረገ ጉዳይ ላይ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ይህን ሁሉ ስናደርግ የዚህ ዓመት የሳይበር ወር ዓላማ ምን ቢሆን ይሻላል በሚል እንደመነሻ የተወሰደው ነገር ደግሞ አለ፤ ለምሳሌ ከዚህ በፊት በነበረው መርሃግብር የሳይበርን ምንነት ለመናገር ሞክረናል፡፡ አሁን ግን እንደ አገር የምንፈልገው የሳይበር ጉዳይ የእያንዳንዳችን ጉዳይ መሆኑ ብቻ ሳይሆን አንድ ግለሰብ ወይም አንድ ተቋም ብቻውን ሊፈጽመውና ሊከውነው የሚችለው ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለዚህ በጋራ መሰራት አለበት ተብሎ የተነሳ ነው፡፡ ምክንያቱም የሳይበር ጉዳይ አንድ ግለሰብ ወይም አንድ ተቋም ብቻውን የሚከውነው ሳይሆን ሁሉን የሚያሳትፍ ነው። ለዚህም ነው መሪ ሐሳቡም ‹‹የሳይበር ደህንነት የጋራ ኃላፊት! እንወቅ! እንጠንቀቅ!›› በሚለው ላይ ትኩረት ተደርጎ ነው የተሰራው፡፡
ወደበጋራ መስራት የተመጣበት ጉዳይ ለምንድን ነው ቢባል በመሰረታዊነት ሁለት ነገሮችን ማንሳት እንችላለን፡፡ አንደኛው ሳይበር በባህሪው አንድ አካልን ብቻ ይዞ የሚንቀሳቀስ አይደለም፡፡ ሁሉን አካላት አሳታፊ ሆኖ የተገኘ ነው፡፡ ስለዚህ ተሳታፊዎች ሁሉ ያልተሳተፉበት ጉዳይ ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ብሎ ለማናገር ከባድ ነው የሚሆነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም የየራሱን ድርሻ እንዲወጣና እንደየተሳትፎውና ሊኖረው እንደሚገባ ሚና ውጤቱን ማምጣት ያፈልጋል፡፡ ይህንን ደግሞ አዲስ የንቅናቄ ወይም ደግሞ የንቃተ ህሊና የምንሰራበት ጉዳይ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
በሌላ በኩል ደግም ሁሌም በሌሎች ጉዳዮች ላይ እንደምናየው የአቅም ጉዳይ ደግሞ አለ፡፡ አቅም ስንል በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በመሰረተ ልማት ወይም ደግሞ በሰው ኃይል እንዲሁም ቀድመን የፈጠርናቸውንም ግንኙነቶች እንደሀብት እንቆጥራቸዋለን፡፡ እነዚህ በሌሉ ጊዜ የምናደርገው ያለውን ሀብት በጋራ ተጠቅሞ በጋራ የሳይበር ደህንነትን የማስጠበቅ ጉዞ ማድረግ ይገባናል በሚል የተፈጠረ ነው፡፡
ስለዚህ የጋራ ኃላፊነት ነው ስንል የጉዳዮቻችንን ችግሮች እንናገራለን ማለት ብቻ ሳይሆን የጋራ መፍትሄዎችንም አብረን እንቀርጻቸዋለን ነው፤ ለተፈጻሚነታቸውም አብረን እንሰራለን ነው፡፡ ያንን ስናደርግ ደግሞ ምናልባትም ስፔሻላይዝድ በሆኑ ዘርፎች ላይ ልናተኩር እንችላለን፡፡ ወይም ደግሞ ተቋማት ባላቸው ልዩ ባህሪያት ላይ በመመስረት ሰብሰብ አድርገን ልናይ እንችላለን፡፡ ‹እንዴት እንሂድ› ብለውም ምክር መጠየቂያ እንዲሁም አብሮ ለመስራት መንገዶችን መክፈቻ አድርጎ የማስቀመጥና ለመግባባት መንገድ የሚፈጥር ይሆናል ብለን እንደመነሻም ያገለግላል ብለን አስበን ነው፡፡ ለዚህም ነው መሪ ሐሳቡ ያንን ቁመና እንድይዝ የተደረገው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ አቻምና ካካሄደው የሳይበር ደህንነት ሳምንት የዘንድሮው የሳይበር ወር ምን የተለየ ነገር ይዞ መጥቷል ማለት ይቻላል?
አቶ ሃኒባል፡- ከአቻምናው በምን ይለያል ለሚለው አንድ መሰረታዊ ጉዳይ ማንሳት መልካም ነው፡፡ በአሁን ወቅት ወደማህበረሰቡ ለማድረስ የምንፈልገው ጉዳይ ‹ሳይበር ምንድን ነው› ከሚለው ያለፈ ይሆናል። የቀደመው መሰረታዊ ነገር ነው የሚሆነው፡፡ አሁን ግን የሳይበር ደህንነትን እንደአገር ለማስጠበቅ ምን ማድረግ አለብን ለሚለው ምላሽ በጋራ መስራት አለብን የሚለውን አመላክቶ ማለፍ የፈለገ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የተከበረው ስለሳይበር ማስተዋወቁ ላይ ነው የነበረው። አሁን ግን በጉዳዩ ላይ በጋራ እንስራ ወደሚለው ለመሄድ የሚያስችል ንቃተ ህሊና ለመፍጠር ነው፡፡
የአገሪቷን በሳይበር ደህንነት ማስጠበቅ የሚቻለው፤ በሳይበር ምህዳሩ የአገርን ፍላጎት መጠበቅ የሚቻለው እንዴት ነው ወደሚል ከፍተኛ ግብ ሊያደርስ የሚችል መነሻዎች ናቸው የሚንጸባረቁት ማለት ነው፡፡
የተሰጠው ጊዜ የአንድ ወር የመሆኑም ጉዳይ በርካታ ተቋማት ዘንድ ለመድረስ እንዲችል ታስቦ ነው፡፡ የነበሩ ህመሞቻችንና ችግሮቻችን በመጀመሪያ ጥቅል ሆነው የቀረቡ ሲሆን፣ አሁን ግን ቀጥታ እኛ ወደተሰማራንበት ዘርፍና ወደሰራነው ስራ አውዱን በጠበቀ ሁኔታ የሚቀርብ ነው የሚሆነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ የሳይበር ደህንነት ንቃተ ህሊና መፍጠር ፕሮግራም በኋላ እንደ ተቋም ብሎም እንደ አገር ምን ይጠበቃል?
አቶ ሃኒባል፡- ይህ ፕሮግራም ስኬታማ የሚሆነው እነዚህ እነዚህ ጉዳዮች ሲሳኩ ነው ብለን ያስቀመጥናቸው መለኪያዎች አሉ፡፡ አንደኛው የምንፈልገው ያህል ሰው አግኝተን፣ እርስ በእርስ ተዋውቀንና ከእነርሱም ጋር ውይይቶች አድርገን የሚፈለገውን መልዕክት ማድረስ ስንችል ብሎም ቀጣይ ሊወሰዱ የሚችሉ እርምጃዎችን ስናመቻች ነው፡፡ በጋራ መስራት የሚያስችሉ መሰረታዊ ጉዳዮችን አንስተን መስማማት ስንችል ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ከየዘርፉ አብረን እንስራ የሚሉ ጥያቄዎች መነሳት ሲችሉ ነው ስኬታማ ነን ብለን መጥቀስ የሚቻለው፡፡ እኛው ወደየዘርፉና ተቋማቱ በምንሄድበት ጊዜ ምን ያህል በሮች ሊከፈቱ ቻሉ የሚለውም ተጠቃሽ ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል እኛ እድለኞች ነን ብለን የምናስበው ዘርፎች፣ ተቋማት በየራሳቸው ፍላጎት ተነሳስተው ‹ይህን ልንሰራ አስበናልና ኑና አማክሩን› ብለው ሲጠየቁን ይሆናል። እየጠበቅነው ያለነው ይህንን ነው፡፡
ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው ትልቁ ነገር ደግሞ ጉዳዩ ተሻሽሎ መሄድ እንዲችል የሚያስችሉ የመነሻ ሐሳብ እና አጀንዳዎችን ወስደናል ወይ የሚለውና ምክረ ሐሳቦችን አግኝተናል ወይ የሚለው ነው፡፡ ሌላው ደግሞ እንደ ዋና ጉዳይ መታየት ያለበት የማህበረሰቡን የንቅናቄ፣ እንቅስቃሴና ሐሳብ የሚገለጽባቸው መድረኮች ላይ አጀንዳ ሆነው ተነስተዋል ወይ የሚለው ጥያቄ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ራሱ የሳይበር ደህንነት ወር ዓላማ ማህበረሰባዊ ንቅናቄን መፍጠር ነው፡፡ የሳይበር ደህንነት ወር ከተጠናቀቀ በኋላ ድህረ ጥናት ተሰርቶ የደረስንበትን አይተን ለቀጣይ ስራዎቻችን ውጤት እንዲሆኑ እናደርጋለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጣም አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ሃኒባል፡– እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11/2014