
አዲስ አበባ፡- በ2017 የስድስተኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና 95 በመቶ ያህል ተፈታኞች የማለፊያ ውጤት በማምጣት ወደ ቀጣይ ክፍል መዛወራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ከተማ አቀፍ የ6ኛ ክፍል ፈተና ውጤትን በትናንትናው እለት ይፋ ባደረገበት ወቅት የቢሮው ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በ2017 ዓ.ም በመዲናዋ 79ሺህ 34 ተማሪዎች የስድስተኛ ክፍል ፈተና ወስደዋል።
የዘንድሮ ዓመት የፈተና ማለፊያ ውጤት 50 በመቶ እንደሆነና ለአካል ጉዳተኛ ተፈታኞች 45 በመቶ እንዲሆን መወሰኑን ተናግረዋል። አጠቃላይ ፈተና ከወሰዱ 75 ሺህ 84 ተማሪዎች 50 በመቶ እና ከዛ በላይ ውጤት ማምጣት እንደቻሉና ይህም የማለፍ ምጣኔው 95 በመቶ እንደሆነ አስረድተዋል።
በመንግሥት ትምህርት ቤት 94 ነጥብ አንድ በመቶ እንዲሁም፤ በግል ትምህርት ቤት 98 ነጥብ ስድስት በመቶ ተማሪዎች ማለፋቸውን ተናግረዋል።
ከፍተኛ ውጤት ካመጡ ተማሪዎች የመጀመሪያዎቹ አራት ተማሪዎች ከመንግሥት ትምህርት ቤቶች እንደሆኑም አመልክተዋል። ይህም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የተሻለ ደረጃ እያስመዘገቡ እንደሆነ እና ማኅበረሰቡ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ ያለውን እይታ እንዲያስተካክል የሚረዳ ነው ብለዋል።
በዘንድሮ ዓመት የስድስተኛ ክፍል ፈተና የሰጡ ትምህርት ቤቶች ቁጥር 734 እንደሆነ የተናገሩት ዘላለም (ዶ/ር)፤ ከእነዚህ ውስጥ 381 ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን መቶ በመቶ ማሳለፍ እንደቻሉ ገልጸዋል።
በማታ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከተማሩ ተማሪዎች 79 ነጥብ ስድስት በመቶ እንዲሁም፤ በግል የማታ ትምህርት ቤቶች ከተማሩ ተማሪዎች 72 በመቶ ማለፋቸውን በመግለጽ፤ የግል ተፈታኞች መቶ በመቶ ማለፋቸውን አስረድተዋል።
አጠቃላይ የተማሪዎች የማለፍ ምጣኔ ፈተናው መሰጠት ከተጀመረ በሦስት ዓመታት ውስጥ እያደገ መምጣቱን ያነሱት ኃላፊው፤ በ2015 ዓ.ም የስድስተኛ ክፍል ፈተና ወስደው ወደ ቀጣይ ክፍል ያለፉ ተማሪዎች 80 ነጥብ ሁለት በመቶ፤ በ2016 ዓ.ም ደግሞ 94 ነጥብ ሦስት በመቶ እንደነበር አስታውሰው፤ በዘንድሮ ዓመት ያለው አፈጻጸም 95 በመቶ እንደሆነና በዚህም እድገት እንደታየ ተናግረዋል።
የትምህርት አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ ትምህርት ቤቶችን መከታተሉ፤ ለትምህርት ቤቶች አስፈላጊው ግብዓት በጊዜ መሟላቱ፤ ምገባ ላይ ኢንቨስት መደረጉ፤ በእንግሊዘኛ እና ሂሳብ ትምህርቶች ላይ የተለየ ትኩረት መሰጠቱ እንዲሁም፤ የቴሌቪዢን የትምህርት ፕሮግራም መጀመሩ ለውጤቱ መሻሻል አስተዋፅዖ እንዳደረጉ አመልክተዋል።
በዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም