የዓባይ ግድብ ሊጠናቀቅ ጫፍ ላይ መድረሱ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ማሳያ ነው

አዲስ አበባ፡- በይቻላል መንፈስ የጀመርነው ዓባይ ግድብ ሊጠናቀቅ ጫፍ ላይ መድረሱ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ማሳያ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫን ለኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ትናንት ሲያስረክቡ እንደገለጹት፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በይቻላል መንፈስ የተጀመረ ነው። ግድቡ መገባደጃ ላይ መድረሱም የኢትዮጵያ የማንሰራራት ማሳያ ነው ብለዋል።

በርካታ ውጣ ውረድ ያለፈው የህዳሴ ግድብ የውጭ እና የውስጥ ጠላቶች ግንባታውን ለማስተጓጎል የሞከሩ ቢሆንም ሳይሳካላቸው የቀረ መሆኑን ኮሚሽነሩ አስታውሰዋል።

እንደ ኮሚሽነር ጌቱ ገለጻ፤ ኢትዮጵያውያንም ግድቡን  ብሔር፣ ሃይማኖት እና ፆታ ሳይለያቸው በመረባረብ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ አድርሰውታል። ግድቡም የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካዊ ኩራት ሆኗል።

በኮሚሽኑም አመራሮች እና በየደረጃው ያሉ የተቋሙ ሠራተኞች በቦንድ ግዥ ለዓባይ ግድብ ከ108 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል። በዋንጫው ቆይታ እና በልዩ ልዩ ፕሮግራም በማዘጋጀት 100 ሚሊዮን ተሰብስቧል። በድምሩም 208 ሚሊዮን ብር በላይ በኮሚሽኑ በመሰብሰብ ገቢ መደረጉን የተናገሩት ኮሚሽነሩ፤ በቀጣይም ተቋሙ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

ኮሚሽነሩ ዋንጫውን የተረከበው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ለግድቡ ታላቅ አስተዋፅዖ ያበረክታል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረው፤ በአዲስ አበባ ለሚገኙ ፖሊስ መምሪያዎች ላበረከቱት አስተዋፅዖ ምስጋና አቅርበዋል።

ዋንጫውን የተረከቡት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ጠቅላይ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ድሪባ መኮንን ባደረጉት ንግግር፤ ኮሚሽኑ ሰላምን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ለህዳሴ ግድብ ቦንድ ግዥ በመፈጸም ከፍተኛ ሚና ሲጫወት ቆይቷል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ግድቡ ድህነትን ለመጠበቅ ከፍተኛ ሚና እንዳለው እንደሚያምን ገልጸው፤ በቀጣይ የሚቻለውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ሌተናል ጄኔራሉም የአዲስ አበባ ፖሊስ ለግድቡ ሲያደርግ የቆየውን ድጋፍ አድንቀው፤ የኦሮሚያ ፖሊስ ዋንጫውን በደስታ በመውሰድ ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የፌዴራል ፖሊስ፣ የመከላከያ ሠራዊትና የክልል የፀጥታ ኃይሎች አመራሮችና አባላት በመላ ሀገሪቱ የሕዝቡን ሠላምና ደኅንነት በማረጋገጥ የመሠረተ ልማት አውታሮችን እና ታላቁ ህዳሴ ግድብ ጨምሮ ከፍተኛ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ከአሸባሪዎችና ከፀረ ሰላም ኃይሎች ጥቃት ከመጠበቅ ባሻገር የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በማድረግ በፋይናንስ እየደገፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ተቋም ሁሉ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ገቢ በማሰባሰብ የራሱን ዐሻራ እያኖረ የሚገኝ የሕዝብ የቁርጥ ቀን ተቋም መሆኑን በተግባር አሳይቷል ያሉት አረጋዊ (ዶ/ር)፤ ላለፉት ዓመታትም ከወር ደመወዛቸው ድጋፍ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ሀገር እንደምታመሰግናቸው ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ መምሪያም ሚያዝያ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የህዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰቢያ የሰላም ዋንጫ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ርክክብ መከናወኑን ተከትሎ የህዳሴ ግድቡን የሚመጥን አቀባበል በማድረግ ገቢ ለማሰባሰብ ለአንድ ዓመት መቆየቱ ይታወቃል።

በመክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You