እሥራኤል ለ60 ቀናት በጋዛ ተኩስ ለማቆም መስማማቷን ትራምፕ አስታወቁ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እሥራኤል በጋዛ የ60 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነትን ለማድረግ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን ለማሟላት እንደተስማማች ተናግረዋል። ፕሬዚዳንቱ በ‹ትሩዝ ሶሻል› (Truth Social) አድራሻቸው፣ ‹‹ጦርነቱን ለማቆም ከሁሉም አካላት ጋር በትብብር እንሠራለን። ሰላም ለማምጣት በጣም ጠንክረው የሠሩት ኳታራውያን እና ግብፃውያን የመጨረሻውን ምክረ ሃሳብ ያቀርባሉ። ሃማስ ይህን ስምምነት ይቀበላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ምክንያቱም የተሻለ አይሆንም፤ እየባሰ ነው የሚሄደው›› ብለዋል። ትራምፕ እሥራኤል ተኩስ ለማቆም የተስማማችባቸው አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች ምን እንደሆኑ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

የትራምፕ መልዕክት የተሰማው እሥራኤል በሰሜናዊ ጋዛ ወታደራዊ ርምጃ መውሰዷን አጠናክራ ከመቀጠሏ በፊት ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ከሰጠች በኋላ ነው። ትራምፕ በሚቀጥለው ሳምንት ከእሥራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በዋሺንግተን ዲሲ ይወያያሉ። የሁለቱ መሪዎች ውይይት ‹‹በጣም ጠንከር ያለ›› እንደሚሆን ትራምፕ ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ ኔታንያሁ በጋዛ ያለውን ጦርነት ማቆም ይፈልጋሉ ብለው ያምናሉ። ኔታንያሁ ጦርነቱን ማቆም ይፈልጋል። እንደሚፈልግ ልነግራችሁ እችላለሁ። በሚቀጥለው ሳምንት ስምምነት ላይ የምንደርስ ይመስለኛል›› ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእሥራኤል አምባሳደር ዳኒ ዳኖን፣ እሥራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ፍላጎት እንዳላት ገልጸው፣ ሐማስ ግን ፈቃደኛ እንዳልሆነ ገልፀዋል። ‹‹በሐማስ ላይ ጫና እየፈጠርን ነው። ወደ ድርድር ጠረጴዛው ካልመጡ ታጋቾቹን ለመመለስ ያለን ብቸኛው አማራጭ ተጨማሪ ወታደራዊ ጫና መፍጠር ነው። ጦርነቱ የሚቆመው ታጋቾቹ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ነው›› ሲሉ ዳኖን ተናግረዋል።

የእሥራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር የተኩስ አቁም እቅዱ ከካቢኔውም ከሕዝቡም ድጋፍ እንዳገኘ ተናግረዋል። የተቃዋሚው መሪ ያኢር ላፒድ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የተኩስ አቁም እቅዱን እንዲቀበሉ የሚያስችላቸውን ድጋፋቸውን ገልፀዋል።

የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትሩ ኢታማር ቤን-ግቪር ከገንዘብ ሚኒስትሩ ቤዛሌል ስሞትሪች ጋር በመሆን የተኩስ አቁም እቅዱን መቃወማቸው ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ ለስሞትሪች ቅርብ የሆኑ ሰዎች ግን ቤን-ግቪር እቅዱን ለመቃወም ከስሞትሪች ጋር አብረዋል መባሉን አስተባብለዋል።

የአልጀዚራው ታሪቅ አቡ አዙም ከጋዛ እንደዘገበው፣ እሥራኤል የ60 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነትን ለማድረግ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን ለማሟላት እንደተስማማች መነገሩን የጋዛ ነዋሪዎች በጥቂት ተስፋና በብዙ ጥርጣሬ ተመልክተውታል። ከዚህ ቀደም የነበሩ የተኩስ አቁም ጥረቶች አለመሳካታቸው የጋዛ ነዋሪዎች የአሁኑንም የተኩስ ማቆም ዜና በጥርጣሬ እንዲመለከቱት አድርጓቸዋል።

‹‹ፍልስጤማውያን ይህን ዓይነቱን የተኩስ ማቆም ጉዳይ ከዚህ ቀደምም ከትራምፕ ሰምተውት ነበር። በእርግጥ ፍልስጤማውያን አሁን ትራምፕ በእስራኤልና በሐማስ ላይ ከበድ ያለ ጫና እየፈጠሩ እንደሆነ ያምናሉ። ፍልስጤማውያን ሙሉና ዘላቂ የሆነ ተኩስ የማቆም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ይፈልጋሉ። ሰላም ሊሰፍንም ሆነ አስከፊ የሆነው ሰብዓዊ ቀውስ ሊፈታ የሚችለው ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ሲኖር ነው›› ብሏል።

ከአንድ ወር በፊት የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ፣ አሜሪካ ያቀረበችውን የጋዛን የተኩስ አቁም እና ታጋቾችን የመልቀቅ ስምምነት እንደማይቀበለው ማስታወቁ ይታወሳል። ቡድኑ ‹‹በአሜሪካ የቀረበው እቅድ በጋዛ ያለው ግድያና ረሃብ እንዲቀጥል ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ የለውም›› ብሎ ውድቅ አድርጎት ነበር። በወቅቱ እሥራኤል ስምምነቱን እንደተቀበለች በአሜሪካ መገለጹ ይታወሳል።

አሜሪካ ያቀረበችው የተኩስ አቁም እና የታጋቾችን የመልቀቅ የስምምነት ሃሳብ ለ60 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም እቅድን የያዘ ሲሆን፣ እሥራኤል በእስር ላይ የሚገኙ ፍልስጤማውያንን እንድትፈታ ሓማስ በሕይወት ያሉ አስር ታጋቾችን እና የ18 ሟቾችን አስከሬን በሁለት ዙር እንዲያስረክብ ይጠይቃል። ሓማስ ስምምነቱን በፈረመ ቅፅበት ርዳታ ወደ ጋዛ እንደሚገባም በስምምነቱ ላይ ስለመካተቱ ተገልጾ እንደነበር ይታወሳል።

ሐማስ ግን ‹‹የስምምነት እቅዱ ጦርነቱን ማቆምን ጨምሮ የፍልስጤማውያንን ዋና ዋና ፍላጎቶች አያሟላም። ይዘቱ በጋዛ እየተካሄደ ያለውን ጭፍጨፋና የተከሰተውን ረሃብ የሚያስቀጥል ብቻ ነው። እቅዱ እሥራኤል ጦርነቱን እንደምታቆም፣ ሠራዊቷንም ከጋዛ እንደምታስወጣና ርዳታ ያለገደብ እንዲገባ እንደምትፈቅድ የሚገልፅና ዋስትና የሚሰጥ ማረጋገጫን አላካተተም›› ብሎ ነበር።

እሥራኤል በአሜሪካ፣ ኳታር እና ግብፅ አደራዳሪነት የተፈረመውና ለስድስት ሳምንታት የዘለቀው የተኩስ አቁም አብቅቶ በመጋቢት ወር አጋማሽ ዳግመኛ የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች ወዲህ እንዳሰበችው የቀሩትን እሥራኤላውያን ታጋቾችን ማስለቀቅ አልቻለችም። ከእገታ የተለቀቀው ኢዳን አሌክሳደር የተባለው እሥራኤላዊ-አሜሪካዊ ወታደር ብቻ ነው። ሓማስ ታጋቹን የለቀቀው ፕሬዚዳንት ትራምፕ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እያደረጉት ላለው ጥረት እውቅና ለመስጠት እንደሆነ ገልጾ ነበር። ወደ 50 የሚጠጉ የእሥራኤል ታጋቾች አሁንም በጋዛ ይገኛሉ፤ ከእነዚህ ውስጥ ቢያንስ 20 ያህሉ በሕይወት እንዳሉ ይታመናል።

እስራኤል እና ሓማስ ተኩስ ለማቆም በየፊናቸው ያስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች የተራራቁ ሆነው ይታያሉ። እሥራኤል ሓማስ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈታ ትፈልጋለች፤ ሓማስ በበኩሉ እሥራኤል ጠቅልላ ከጋዛ እንድትወጣ ይፈልጋል። እሥራኤል ግን የሓማስ መነኻሪያ በሆነችው በጋዛ ሰርጥ የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ ለማድረግ የሚያስችላትን አዲስ እቅድ በደኅንነት ካቢኔዋ አፅድቃ ዘመቻዋን ቀጥላለች።

አዲሱ እቅድ የሀገሪቱ የጦር ሠራዊት በሐማስ ላይ የሚያካሄደውን የጥቃት ዘመቻ የሚያሰፋ ሲሆን፣ በእቅዱ መሠረት የእሥራኤል ወታደሮች በአዲስ አካባቢ ተሰማርተው በምድርና ከምድር በታች የሚገኙ ሁሉንም የሐማስ መሠረተ ልማቶችን ያወድማሉ። በዚህ የእሥራኤል የዘመቻ እቅድ ምክንያት ተባብሶ በቀጠለው የጋዛ ጦርነት በርካታ ንፁሐን በየቀኑ እየሞቱ እንደሆነና አስከፊ ሰብዓዊ ቀውስ እንደተከሰተም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ነው።

በእሥራኤል እና በሃማስ መካከል እ.አ.አ ባለፈው ጥር 19 ተጀምሮ ለስድስት ሳምንታት ከዘለቀ በኋላ በመጋቢት ወር አጋማሽ የፈረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ሦስት እርከኖች እንዲኖሩት ሆኖ የተቀረጸ ቢሆንም የመጀመሪያውን ደረጃ እንኳንን ማለፍ ሳይችል ቀርቷል። የዚህ ስምምነት ሁለተኛው ደረጃ ቋሚ የተኩስ አቁም ላይ መድረስን፣ በእሥራኤል ውስጥ ለታሰሩ ፍልስጤማውያን ምትክ በጋዛ ታግተው የነበሩትን እሥራኤላውያን መልቀቅን እና የእሥራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ መውጣትን ያካተተ መሆኑ ይታወቃል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You