
ዜና ሐተታ
አወንታዊ አስተሳሰብ ለሰው ልጆች ለውጥ ስኬትና ዕድገት አመቺ የሚባሉ ሃሳቦች ይንሸራሸርበታል፡፡ ሁሌም ቢሆን መልካም ቃላትና በጎ ንግግር ለአድማጩ ጥሩ የሚባል ትርጓሜን ይይዛል፡፡ አንድ ሰው በመልካም አንደበቱ ሌሎችን በማውጋት ማሳመን ከቻለ የውስጡ ስሜት የአሸናፊነት ኃይል አለው፡፡
ይህ እውነት ከቤተሰብ ተነስቶ ከፍ ሲል እስከመጪው ትውልድ በጎ ተፅዕኖውን ያሳድራል ሲሉ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
አወንታዊነት ያለው አዕምሮ ደስታን፣ ተስፋንና መልካም ዕቅድን የማይቀበል ጉልበት አለው። ይህ አይነቱ ሐቅ በሰው ልጆች የመኖር ሂደት ውስጥ ሲደጋገም ጥሩ የሚባል የአኗኗር መልክን ይቀርጻል። በመልካም እሳቤ የሚቀባበል ትውልድም መጪውን ጊዜ ያለ ስብራት ለመሻገር አጋጣሚውን ያገኛል።
ዶክተር ጃራ ሰማ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ናቸው። በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የምክር አገልግሎትና ሥልጠና ይሰጣሉ። ‹‹ከሱስ የነፃ ትውልድ›› የሚል መጽሐፍ አዘጋጅተውም ለአንባቢያን አድርሰዋል። ሙያቸው ሕክምና እንደመሆኑ የቀረቧቸውን ሁሉ ከችግራቸው ለመታደግ ወደ ኋላ ብለው እንደማያውቁ ይናገራሉ። በተለይ በሱስ ሕይወት ውስጥ ያሉን ወገኖችን ለመርዳት ውስጣቸው የተጋ መሆኑን የሚገልጹት በተለየ መተማመን ነው። ይህን በማድረጋቸውም ትውልድን ከፈተናዎች አሻግሮ በመልካም ጎዳና ለማራመድ እንዳገዛቸው ይናገራሉ።
እንደ ዶክተር ጃራ አባባል፤ ትውልድ ማለት በዕድሜና ዘመን ተከፋፍሎ የሚታይ ሕያው መነጽር ነው። የአንድ ትውልድ አባላት የተቀራረበ ዕድሜ ባለቤቶች ናቸው። ልጅነታቸው፣ ወጣትነታቸው፣ ጉልምስናና እርጅናቸው በቅርርቦሽ መስመር ይለካል።
እንደሳቸው አገላለጽ፤ የትውልድ ቅብብሎሽ ማለት በጋራ ትርክቶች፣ ድሎችና ጀግንነቶች የሚገለጽ ሐቅ ነው። በዚህም የሀገር ፍቅር፣ አብሮነትና መረዳዳትም ይታከልበታል፡ ዶክተር ጃራ በአወንታዊ አስተሳሰብና አመለካከት የተገነባ ትውልድን ማፍራት ለሀገራዊ አንድነትና ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ይገልጻሉ። ትውልዱን በበጎ ቀርጾ ወደ ተከታዩ ለማሻገር ምን ዓይነት ትውልድ ሊኖር ይገባል ለሚለው ዶክተር ጃራ መልስ አላቸው። እንዲህ አይነቱን ጤናማ ትውልድ ለመገንባት በቅድሚያ ከአሉታዊ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች ማራቅ ግድ እንደሚል ይገልጻሉ። በእነዚህ ክፉ ተሞክሮዎች ሳቢያ በግልጽ የሚስተዋሉ የአደንዛዥ ዕፆች መበራከትና የሱሰኝነት መስፋፋት ለትውልዱ ጠንቅና ፈተናዎች ሆነው ዘልቀዋል ይላሉ።
እንደ ዶክተር ጃራ ገለጻ፤ ዕድሜ ጠገብ አረጋውያን ክህሎትና ተሞክሯቸውን ማካፈላቸው ትውልዱን ከአሉታዊ አመለካከቶች ይታደጋል። በተለይም ባሕልና፣ ታሪክን፣ ሥራ ወዳድነትና፣ የመልካም ቤተሰብ ግንባታን፣ የዓላማ ጽናትንና፣ ሥነ ምግባር ማጋራታቸው በርካቶችን ከአጉል መንገዳቸው ይመልሳል ነው ያሉት።
አወንታዊ አመለካከትና አስተሳሰብን በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ መፍጠር ከአሉታዊ መስመር የመውጣት ውጤት ነው የሚሉት ዶክተር ጃራ፤ በማኅበረሰቡ መሐል የዕውቀት ጥበብን በማስረጽም ለሁለንተናዊ ዕድገት ማትጋት ይቻላል ሲሉ ይገልጻሉ።
ዶክተር ጃራ በመልካም እሳቤና በጤናማ አመለካከት ያልታነጸ ትውልድ ለመጪው ቅብብሎሽ ፋይዳቢስ መሆኑን የሚናገሩት በእርግጠኝነት ነው። በዚህ በጎ መንገድ ያላለፈ ትውልድ ሰላማዊነትን አያውቅም። መከባበር አብሮነትና ፍትሐዊነት አይገባውም። ልቡ ለይቅርታ፣ ለሰብዓዊነትና ለርኅራሄ አይዘጋጅም። የበጎ ተምሳሌት ማሳያ መሆን አይችልም። ሐቀኝነት፣ ኃላፊነትና መተባበር ከእሱ የራቁ ናቸው ሲሉ ያብራራሉ።
ዶክተር ጃራ እንደሚሉትም፤ ይህ ዓይነቱን ገጽታ ከትውልዱ ለማራቅ ወደ መልካም መስመር መጓዝ ያስፈልጋል። ይህ እውነት የሚገኘው ደግሞ አሉታዊ አመለካከቶች ተወግደው በአወንታዊ አስተሳሰቦች ሲተኩ ብቻ ይሆናል።
የ107 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋው አርበኛ ፀጋ መሰለ የዕድሜ ዘመናቸው ብዛት ለአሁኑ ትውልድ ማንነት መሠረት እንደሆነ ይገልጻሉ። እሳቸው ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ የመኖራቸው አንዱ ምስጢር ለሀገራቸው፣ ለሰዎችና ላመኑበት ዓላማ ያላቸው ጽናትና ፍቅር እንደሆነ ይናገራሉ።
አባ ፀጋ በጀግንነት ያለፉበት የአርበኝነት ዘመናቸው የሀገራቸው ፍቅር ማሳያ ምልክት ነው። በካህንነት ያገለገሉበት ጊዜም የሃይማኖታቸውን ጽናት የሚጠቁም ሠንሠለት መሆኑን ይናገራሉ። በሥራ ዓለም ያገለገሉባቸው ዓመታትም የዜግነት ግዴታቸውን የሚያሣይ ጉልህ መነጽር ነው።
ከምንም በላይ ግን አባ ፀጋ እሳቸው ከአባቶቻቸው የወረሱትን መልካምነት የአሁኑ ትውልድ እንዲጋራቸው ይሻሉ። ይህ የሚሆነው ደግሞ በበጎነት የተቀረጸ ማንነት ለመስማት ጆሮውን ሲሰጥ፣ ልቦናውን ሲከፍት ነው ይላሉ። ይህ ከሆነ የጤናማ ትውልድ ቅብብሎሹ እንደሚቀጥል በአባትነት አንደበታቸው ይገልጻሉ።
በመልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም