
አዲስ አበባ፡- አዋሽ ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 2017 ዓ.ም ብቻ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ለማኅበራዊ ኃላፊነት ድጋፍ ማድረጉን ገለጸ።
የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው የባንኩን ዓመታዊ ሥራ አፈፃፀም አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አዋሽ ባንክ በየዓመቱ ለተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ ችግሮች ቀድሞ በመድረስ ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን በማስመስከር ላይ ይገኛል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ለተጋለጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለትምህርት፣ ለጤና እና ለተለያዩ ሰብዓዊ ድርጅቶች ለግሷል።
ለትግራይ ክልል በክልሉ ልማት ማኅበር በኩል በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ ትምህርት ቤቶች መርጃ የሚውል የ10 ሚሊዮን ብር የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፤ በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የስንዴ ዱቄት እና የምግብ ዘይት ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
እንዲሁም በጋሞ ጎፋ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የሰባት ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰው፤ ለመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማኅበር አምስት ሚሊዮን ብር፣ ለሜሪጆይ ኢትዮጵያ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን እና ለተለያዩ ሀገር በቀል ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ባንኩ ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል።
በተመሳሳይ የሥራ ፈጠራ ክህሎት ኖሯቸው በፋይናንስ እጥረት የሥራ ፈጠራ ሃሳባቸውን ወደ ተግባር መቀየር ያልቻሉ ዜጎችን ለማበረታታት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ የሥራ ፈጠራ ውድድር በማከናወን ሁለተኛውን ምዕራፍ ፕሮጀክት በስኬት ማጠናቀቁን አመልክተዋል።
በሌላ በኩልም በጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ለታቀፉ ከ14ሺ በላይ ደንበኞች ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ማበደሩን በመግለፅ፤ በተጨማሪም ከማስተር ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር መስመር (MESMER) በተሰኘ ፕሮግራም ወደ 12ሺህ ለሚጠጉ ማይክሮ ኢንተርፕራይዞች ከአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ማበደሩን ተናግረዋል።
እንዲሁም አዋሽ ለሁሉም በተሰኘ የዲጂታል ብድር አገልግሎት አማካኝነት ከ301ሺህ በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች ያለ ምንም ማስያዣ 493 ሚሊዮን ብር የዲጂታል ብድር መስጠቱን አመልክተዋል።
በሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም