“ይህ ዘመቻ የማይመለከተው ሰው የለም። ኢትዮጵያን ለማፍረስ የመጣን ኃይል ሁሉም በአንድነት ሊመክተው ይገባል። ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ያለን ሁሉን ዜጋ ይመለከተዋል። በየተሰማራበት መስክ የዜግነት ኃላፊነቱን በመወጣት የህልውና ዘመቻው አካል መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል። “ብለዋል የመንግስት የኮምንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ትላንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ። ሚንስቴሩ ከሶስት ዓመታት በኋላ እንደ አዲስ መቋቋሙ መንግስተ ዲዳ አድርጎን የነበረን ተግባቦት አልቦ ጉዞ እልባት ይሰጣል ተብሎ ይታመናል።
ጅምሩ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም በጥብቅ ዲሲፕሊን ሊመራ ይገባል። ስለሚሰጠው መግለጫ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቂ መረጃን ወስዶ በቂ ዝግጅት በማድረግ መላምትን ግምትንና ትንበያን ያስቀረ ሊሆን ይገባል። መግለጫው ቀድሞ በተዘጋጀ ማስታወሻ ላይ የተመሠረት መሆን ይጠበቅበታል። በቀጣይ መግለጫው የሚመለከታቸው አካላትን ስለማካተት ማሰብ አለበት። ስለ ጦርነቱ መግለጫ የሚሰጥ ከሆነ ከመከላከያ ሰራዊት በቀጥታ የሚመለከተው አካል መጋበዝ አለበት። ሁለቱ አካላት ቅድመ መግለጫ ጥልቅ ውይይት በማድረግ መልዕክቱ ከፍሬሙ እንዳይወጣ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ጋዜጣዊ መግለጫዎች ቋሚ የጊዜ ሰሌዳና ለሀገር ውስጥም ለውጭ ሚዲያዎች መዘጋጀት አለበት። በቀጣይ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በጥንቃቄና በስፋት መጠቀም ይጠበቅበታል። ሀሰተኛ መረጃዎችን ከስር ከስር እየተከታተለ በማጣራት (ፋክት ቼክ) በፍጥነት ስለማድረስም አበክሮ ሊያስብበት ይገባል።
ሌላው እንዲህ ያሉ መግለጫዎች በተቻለ መጠን የአሸባሪው ህወሓት ወረራና ጥቃት ሀገር ለማፍረስና እያጣጣምነው ያለን አንጻራዊ እኩልነት ፍትሐዊነት ነጻነትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውጥን ጅምር ለማጨናገፍ እንጂ ለዘረፋ ወይም የደረሰ ሰብል አጭዶ ለመውሰድ አይደለም። ዘረፋው ሀገር የማፍረስ እኩይ አላማ ማሳኪያ ስልት እንጂ በራሱ ግብ አይደለምና። ደሴንና ኮምቦልቻን ቢቆጣጠር ዘርፎ ወደ መቐሌ አይመለስም። ስለ መንግስት የኮምንኬሽን አገልግሎት ይሄን ያህል ካልሁ ወደ ዋናው የመጣጥፌ ነጥብ ልመለስ። እንደ ኤሮፓውያን አቆጣጠር ሴፕቴምበር 17 ቀን፣ 1787 ዓ.ም በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ አለው ይለናል ትንታጉ ጉምቱውና ደማሙ ጋዜጠኛ ጋሽ ሙሉጌታ ሉሌ ነፍሱን ይማርና።
መቼም በዚች ምድር እንደሱ ልቅም ጥንቅቅ ያለ አርበኛ ጋዜጠኛ ገጥሞኝ አያውቅም። ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ስመለስ በጦቢያ፣ ቅጽ 7፣ ቁ.2፣ 1992 ዓ.ም፣ ”እኛም አንናገር እነሱም አይሰሙ፣ የገዥዎቻችን እዳ የለብንም”በሚል ርዕስ ባስነበበን መጣጥፉ። 39 ልዑካን ከ12 ግዛቶች ተወክለው የሕገ መንግስት ጉባዔ መስርተው የውይይታቸውና የእጃቸው ፍሬ የሆነውን ሰነድ ለሕዝቡ ያቀረቡበት ዕለት ነበር። እኔ ደግሞ ወሳኝ መታጠፊያ/critical juncture/እለዋለሁ።
ታሪኩ እንደሚለው በዚህ ዕለት አንዲት ሴት ቤንጃሚን ፍራክሊን ዘንድ ቀርባ፤”እህሳ ዶክተር ምን ተገኘ? ሪፐብሊክ ወይስ ግዛተ ዘውድ!”ብላ ትጠይቃለች። እሱም ወዲያው”ሪፐብሊክ ነው_ልትጠብቂው ከቻልሽ”(A Republic if you can keep it) ሲል መለሰላት። ፍራንክሊን ይህን ያለው ሀገሩን ይዞ የስርዓተ መንግስቱን ቅርጽ ነው ልትጠብቂው ከቻልሽ ሪፐብሊክ ያላት። ባልጠብቀውስ !? ብትለው መቼም መልሱ የእንግሊዝ ግዛተ ዘውድ ፈላጭ ቆራጭ ወይም አምባገነን ቅኝ ገዥ ነበር የሚላት ብየ እምናለሁ። ወገኖቼ የአሸባሪው ህወሓት አፈር ልሶ እንደ ዙምቢ መምጣት ዝም ብሎ የስርዓት ለውጥ ከመሰላችሁ በህይወት ዘመናችሁ ትልቅ ስህተት ፈጽማችኋል።
በመላው አለም ከሚገኙ አመራሮቹና ደጋፊዎቹ ጋር ባደረገው የዙም ውይይትም ሆነ፤ ጂኦፖለቲክስ ፕሬስ ይፋ ባደረገው “ከባዝማ እስከ ኢትዮጵያ”ሰነድም ሆነ በአሸባሪው ቃል አቀባይ በእብሪት”ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንወርዳለን፤” ከማለቱ በአሜሪካ የሚገኙ ጭፍራዎቹ”በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ታላቋ ትግራይ እውን”እንደምትሆኑ ሲፎክሩ በአማራና በአፋር ክልሎች ሰርጎ የገባው አሸባሪ አባቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ያቆዩን ባንዲራ አውርደው የራሳቸውን መናኛ አርማ ሲሰቅሉ፤ ሟቹ መለስ ባንዲራውን ጨርቅ ነው ይል ስለነበር ብጤዎቹ የዱቄት መቋጠሪያ አድርገውት እንደነበር ስታስታውስ ህወሓት በመዝረፍና መንግስት በመለወጥ ብቻ የሚቆም አለመሆኑን መገንዘብ ይገባል።
አዎ አሸባሪው ህወሓት የሚመጣው ሀገር የማፍረስ ጅምሩን ለማጠናቀቅ ነው። ኢትዮጵያን ወደ ስድስት ሀገራት በመበታተን ታላቋን ትግራይ መመስረት። ይህ እኩይ አላማ በኤርትራም የመንግስት ለውጥ በማድረግ በትግራዋይ የሚመራ አሻንጉሊት መንግስት የማቆም እና ኤርትራን የታላቋ ትግራይ አካል የማድረግ ቅዠትንም ያካትታል።
እኔም ከውስጥና ከውጭ የተናበበና የተቀናጀ ከበባና ጫና የበዛበትን ብዙ ዋጋ ከፍለን ያመጣነውን ለውጥ እንደ አይናችን ብሌን “ልንጠብቀው ከቻልን ሪፐብሊክ”ልንከላከለውና ልንጠብቀው ካልቻልን አሸባሪው ህወሓት የጀመረውን ኢትዮጵያን የማፍረስ ተልዕኮ እንዲፈጽም፤ ዳግም እንደ ብረት ቀጥቅጦ እንዲገዛን፤ የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለምዕራባውያን አሳልፎ የሚገብር ሲጠሩት አቤት፣ ሲልኩት ወዴት የሚል ተላላኪና ጉዳይ አስፈጻሚ፤ እንዳለፉት 27 ዓመታት በገዛ ሀገራችን ሁለተኛ ዜጋ የምንሆንበት ነጻነት እኩልነት ፍትሐዊነትና ዴሞክራሲያዊነት የሌለበት፤ ዘራፊ አምባገነን ፈላጭ ቆራጭና አፋኝ ኢትዮጵያን አምርሮ የሚጠላ፤ የገዛ ዜጋውን የሚያሰቃይ በግፍ የሚገል የሚገርፍ የሚያግዝ የሚያስር ሕዝብን የሚከፋፍልና ሀገርን የሚያፈርስ አፈር ልሶ የሚነሳው አሸባሪው ህወሓት እጅ ሀገር
ሕዝብ ዳግም ፍዳቸውን ሊያዩ ይወድቃሉ ማለት ነው። በግሌ ወደዛ የግፍ የመከራና የጨለማ ዘመን ከምመለስ አንድ ጊዜ አይደለም አስር ጊዜ ደጋግሜ መሞትን እመርጣለሁ።
የመንግስቴን ጥሪ ያለምንም ማቅማማት የተቀበልሁት ለዚህ ነው። አሜሪካዊው ፓትሪክ ሔነሪ “ነጻነትን ስጡኝ ወይም ሞትን አትንፈጉኝ!”/Give liberty or give me death/ እንዳለው። ሔነሪ ነጻነቴን ያለው ሀገሩ ላይ ቆሞ ስለሆነ እኔ ግን ቆሜ ነጻነቴን የምጠይቅባት ምትክ የሌላት ሀገሬ ላይ የህልውና አደጋ ስለተደቀነባት፤ እናት ሀገሬ ወይም ሞት ! ለማለት ተገድጃለሁ።
የኮምንኬሽን አገልግሎት ሚንስትሩ እንዳሉት፤ ከአሸባሪው ህወሓት ጭፍራዎች በስተቀር የሁሉም ኢትዮጵያዊ ምርጫ ይኸው ነው። ኢትዮጵያውያን የህወሓት ቂመኛ ከሀዲና ዘራፊ ቡድን ዳግም የጭቆና ቀንበር እንዲጭንባቸው አይፈቅዱም። አንቅረው ወደተፉት ግፈኛ አገዛዝ ጥፋት አይመለሱም። ወደጥፋቱ የሚመለስ እሪያ ነውና። ይህ እንዳይሆን ግን መላ ኢትዮጵያውያን በአንድ ልብ ይህን ለውጥ መጠበቅና መከላከል ይጠበቅባቸዋል። ጠላቶቻቸውን ሳይቀር ያስገረመ ሰላማዊ ምርጫ በማካሄድ፤ ለጀግናው መከላከያ ሰራዊት ደጀን በመሆን፤ የሕዳሴውን ግድብ ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በመደገፍ አለኝታነታቸውን አረጋግጠዋል።
ለሰብዓዊነት ሲል መንግስት ያወጀውን የተናጠል የተኩስ አቁም አሸባሪው ህወሓት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ትንኮሳ ከማድረግ አልፎ ወረራ ፈጽሟል። በአራት ግንባር በሕዝባዊ መዓበል የታገዘ ጦርነት ከፍቷል።”ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እወርዳለሁ። “በሚል የእብደት መሀላ ተማምሎ ሀገርን ለማፍረስ ከየጎሬው ሲወጣ፤ ኢትዮጵያውያን እንደ ጀግኖች አባቶቻቸው በአንድነት ቀፎው እንደተነካ ንብ ወደ ሰሜን ተመዋል። ይተማሉ።
በተደጋጋሚ በዚህ ጋዜጣ ለመግለጽ እንደሞከርሁት ክቡር ጠቅላይ ሚንስትርን ወደ ኃላፊነት ያመጣው ለውጥ ከቀደመው አብዮትም ለውጥም ፍጹም ይለያል። ደርግ ንጉሳዊውን አገዛዝ በመፈንቅለ መንግስት ገርስሶ በምትኩ የባሰ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን ተከለ። ትህነግ/ኢህአዴግ ሶሻሊስታዊ አምባገነን ገዥ የነበረውን ደርግ ለ17 ዓመት ነፍጥን ከሴራና ደባ አጃምሎ ለስልጣን ቢበቃም ታገልሁለት ያለው እኩልነትና ነጻነት ክዶ የአንድን አውራጃ የበላይነት ብቻ ሳይሆን ለ30 ዓመታት አንድም ቀን የመንግስትነት ባህሪ ሳያሳይ በአሳፋሪ ሁኔታ ራሱን በራሱ አጥፍቷል።
ለነገሩ መንግስት የመሆን ቅን ፍላጎትም አልነበረውም። ሕገ መንግስት ያለው ብቸኛ ማፊያ ቡድን እንጂ። በመጨረሻዎቹ የክህደትና የአረመኔነት ቀናት ያረጋገጠልን ይህን ማፊያነቱን ነበር። ሆኖም በፖለቲካው መልክዓ የነዛው የጥላቻ፣ የልዩነትና የመጠራጠር መርዝ በቀላሉ አይረክስም። እንኳን
ለ47 ዓመታት የተለፈፈ የጥላቻና የፈጠራ ትርክት፤ በጣሊያን የአምስት ዓመታት ቆይታ ለዛውም በጀግኖች አርበኞች ተጋድሎ ለአንድ ቀን እንኳ ያለስጋት ውሎ ባላደረበት ለከፋፍሎ መግዛት እንዲያመቸው የዘራው የማንነትና ጨቋኝ ተጨቋኝ የፈጠራ ትርክት በቀላሉ ሰኮናው ሳይነቀል ኖሮ በ60ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ከሶሻሊዝም ጋር ተላቁጦ የሀገራችንን ፖለቲካ እስከመበየን ደርሷልና ከዚህ አባዜ ሰብሮ ለመውጣት ብርቱ ጥረትና ቁርጠኝነት ይጠይቃል፤ ለደቂቃም ቢሆን አይንን ከትልቁ ስዕል ሳያነሱ።
የአፄ ሀይለስላሴ፣ የደርግና የትህነግ አገዛዞች ያባከኗቸውን ወሳኝ መታጠፊያዎች ሀገራችንን ምን ያህል ውድ ዋጋ እንዳስከፈሏት በውል ተገንዝቦ ከሶስት ዓመት ወዲህ በእጁ የገባውን ወሳኝ መታጠፊያ በብልህነትና በአስተዋይነት መጠቀምን የሞት ሽረት ጉዳይ ማድረግን ይጠይቃል።
እዚህ ላይ በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ለሚመራው የለውጥ ኃይል ከእነ ውስንነቶቹ ያለንፍገት እውቅና ሊቸረው ይገባል። ይሁንና ይቺ ሀገር እንደ ቀደሙት ሶስት የቅርብ ዓመታት መታጠፊያዎች የምታባክነው እድልም ሆነ አጋጣሚ እንደማይኖርና እንደ ከዚህ በፊቱ ብታባክነው አምባገነናዊ አገዛዝ በመተካት ብቻ የሚቆም ሳይሆን በሀገር ቀጣይ ህልውና ላይ አደጋ የሚደቅን መሆኑን በውል ተገንዝበው የአምባገነንነት ቀለበቱን ሰብሮ ለመውጣት የሚያግዝ ስልት ተልመዋል።
አሳታፊ ፖለቲካዊ ስርዓትና አካታች የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለማስፈን ቆርጠዋል። እንገጭ እገው እንዳለ ሆኖ። ቁርጠኝነታቸውንም የዴሞክራሲ ተቋማትን በመገንባትና ኢኮኖሚውም ፍትሐዊ እንዲሆን ማሻሻያ ቀርጸው ወደ ትግበራ ገብተዋል። ሆኖም ለውጡ ከቀደሙ አብዮቶቹም ሆነ ለውጦች በፍጹም ሊባል በሚችል ሁኔታ የተለየ በመሆኑ፤ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ የተዘራው ልዩነትና ጥላቻ፤ ትህነግ ጥርሱን በነቀለበት ሴራና ደባ መቐሌ ላይ መሽጎ እንዲቀጥል ጊዜ ማግኘቱ፤ ለውጡ ቢያንስ ሆን ተብሎ የባረቁ ሶስት ለውጦችና አብዮት ዘርፈ ብዙ ቀውስን እንደ ትኩስ ድንች ተቀባብለው ተቀባብለው የጣሉበት ባለዕዳ በመሆኑ የቀውሶች ቋጥኝ በአንድ ላይ ስለ ወደቁበት እና በለውጡ ተዋንያን ወጥ ቁርጠኝነት ባለመያዙ ምልዑ – በኩሌ ሳይሆን ቀርቷል። ምንም እንኳ የእውነተኛ ለውጥ መንገድ አሚካላና ኩርንችት የበዛበት ቢሆንም የተገኘው አበረታች ውጤት በዚህ ሁሉ እሾህ ታንቆ ያለፈ እንዳይመስል አድርጎታል።
ከእሾሁ ህወሓት ጋር የሚደረገው ጦርነት መራር ያደረገው የሀገር ሉዓላዊነትና ህልውና ከማስቀጠል በላይ ወደ ጨለማው የጭቆና አገዛዝ ቀንበር ያለመመለስ የሞት ሽረት ትግል መሆንን ተገንዝቦ በጽናት ከመንግስት ጎን መቆም ግድ ይላል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11/2014