የዘንድሮው አዲስ ዓመት በርካታ አዲስ ነገሮችን ጀባ ብሎን ያለፈ ነው።እንደ እስከዛሬው በአደይ አበባና በመስቀል ወፍ ብቻ የታጀበ አልነበረም።ለኢትዮጵያ የሚሆን በርካታ የተስፋና የንጋት ብርሀን የፈነጠቀ ነበር፤ መስከረም አዲስ ዓመት።
የሰኔን ገመገም፣ የሐምሌን ጨለማ፣ የነሐሴን ጭጋግ በብርሃን ኩሎ ጸደይን ያመጣ ከሁሉ ልዩ ማለዳ ነበር፤ መስከረም አዲስ ዓመት።ጊዜ ሚዛን ነውና በተፈጥሮ ለበቅ ሸኮናውን ተብሎ የአዲስ ዓመት አብራክ መስከረም ብኩርናውን እንደያዘ ኢትዮጵያውያንን በተስፋና በአዲስነት ሞሽሮ ወደ ፊት እያዘገመ ነው..።እንቁጣጣሽ በየዓመቱ ያምጣሽ ብለን ሳንጨርስ፣ የዳቦው ሽታ፣ የአበባው መአዛ ርቆ ሳይርቀን በማለዳ አዲስ መንግሥት መሰረትን፤ አዲስ ተስፋ ሰነቅን።እነሆ የመስከረም በረከት።
የዘንድሮው መስከረም አዲስ ዓመት ብቻ አይደለም።አገራችን ኢትዮጵያ ለአምስት አመት የሚያስተዳድራትን አዲሱን መንግስት ወደ ስልጣን ያመጣችበት የተስፋ ዋዜማም ነው።የአዲስ ዓመትን መንፈስ አጣጥመን ሳናበቃ፣ የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ ከቀየው ላይ ሳይሰወሩ ሌላ ደማቅ ታሪክ ጻፍን።የአዲስ አገር፣ የአዲስ መንግሥት፣ የአዲስ አስተሳሰብ ታሪክ..
አዲስ አገር ስል ብዕሬን ያሰላሁት በምክንያት ነው።በህወሓት የሥልጣን ዘመን ያጣናቸውን በጎ ኢትዮጵያዊ ቀለሞች የመለስንበት በመሆኑና ሁላችንም ወደምንናፍቀው የከፍታ ጉዞ በመሄድ ላይ ስለሆንን በዚህ ሁሉ አዲስ አገር ስል ተነሳሁ።ይሄ ብቻ አይደለም በለውጡ መንግሥት የተሳሉ የኢትዮጵያን ወቅታዊ አዲስነት የሚመሰክሩ በርካታ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል።
የተራመድናቸው የከፍታ ርምጃዎች ሁሉ በአዲስነት የተበጁ ናቸው።በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው በተለያዩ ዘርፎች ላይ እየመጡ ያሉ አገራዊ ለውጦች ሁሉ በአዲስ አገር ምስረታ ላይ የመሆናችን ሌሎች ማሳያዎች ናቸው እላለሁ።ይህ የእኔ እውነት ብቻ አይደለም የሁላችንም የጋራ እውነት ነው።ይህ የለውጥ እርምጃ አገርና ሕዝብን መሰረት ባደረገ መልኩ ተጀምሮ ዛሬ ላይ የደረሰ በመሆኑ የአዲስ አገር ግንባታ ጅማሮ ብዬዋለሁ።
ልክ እንደ አዲስ አገር ሁሉ አዲስ መንግሥትም ስል የተነሳሁት በምክንያት ነው።የሰሞኑን የመንግሥት ምስረታ መነሻ በማድረግ ሀሳቤን ላካፍላችሁ መጥቻለሁ።መስከረም ሃያ አራት ሁለቱን ታላላቅ በዓላት ማለትም የመስቀልንና የኢሬቻን በዓል ታኮ የተመሰረተው አዲሱ መንግሥት ኢትዮጵያን አዲስነት ካላበሳት የመስከረም ገጸ በረከት ውስጥ አንዱ ነው።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ አዲስነት የጀመረው የለውጡ መንግሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ ነበር።ይሄ አዲስነት ደግሞ ሶስት አመት ጠብቆ በወርሐ ሰኔ በአስራ አራተኛው ቀን የምርጫ ወቅትን ጠብቆ በይበልጥ አዲስ ሆኖ ኢትዮጵያዊነትን አገነነ።ሕዝብ በሚያስደንቅ ተሳትፎ መረጠ፤ በውጤቱም ኢትዮጵያ አሸነፈች።
በሕዝብ ነጻ ፍቃድ ይሁንታ ያገኘው ፓርቲም ቀጣዮቹን አምስት ዓመታት አገርና ሕዝብን በታማኝነት እንዲያገለግል ራሱን በመንግሥትነት እንደ አዲስ አዋቀረ፤ በዚህም ኢትዮጵያውያን ተስፋ የጣሉበት አዲስ መንግስት ተመሰረተ።ይሄ ብቻ አይደለም አዲሱ መንግሥት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ወደ ሥልጣን በማምጣት መንግስት መመስረቱ ደግሞ ሁኔታውን በይበልጥ ልዩ ያደርገዋል።
ከዚህ በላይ አዲስነት ምን አለ? ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ እንደሚባለው ከዚህ በፊት ምን እንደነበርን ሁላችንም የምናውቀው ሀቅ ነው።ዛሬ ከትላንት ሌላ ነን፤ ይሄ ሌላነት ደግሞ በተለየ አስተሳሰብ፣ በተለየ አመራር፣ በተለየ ጥረት የመጣ እንጂ ዝም ብሎ የሆነ አይደለም።ብታምኑም ባታምኑም አያሌ ጸጋዎቻችን በለውጡ መንግሥት የፖለቲካ ፍልስፍና የተፈጠሩ ናቸው።አሁን ላይ እያኖሩን ያሉ በረከቶቻችን በለውጡ መንግሥት የታደሉን እድሎች ናቸው ስል መናገር እችላለሁ።
ወደ ቀጣዩ መነሻ ሀሳቤ ሳዘግም አዲስ አስተሳሰብ የሚል ጽንሰ ሀሳብ እናገኛለን።በዚህ እውነት ታጅቤ ስመጣ እናንተን ምስክር አድርጌ ነው።ከላይ የገለጽኩላችሁ አገርና መንግሥት፣ ከላይ የገለጽኩላችሁ ለውጥና ስኬት ይሄን ሶስተኛውን ጽንሰ ሀሳብ ተንተርሰው ነፍስ የዘሩ ናቸው።ይሄ ሀሳብ የትም ቦታ ላይ ህልውና ያለው ሀሳብ ነው።ተጀምሮ የሚያበቃበት የሕይወት ስፍራ የለውም።ሁሉም ቦታ ላይ መሪና ቀዳሚ ሆኖ የሚቆም እውነት ነው።
በለውጡ መንግሥት ያየናቸው የተስፋ ብርሃኖች ሀሳብን መሰረት አድርገው የመጡ ናቸው።የአዲሱ መንግሥት አደረጃጀትም የሀሳብ የበላይነትን መሰረት ያደረገ ነበር።ነገ የሚፈጠረው አዲሱ ትውልድም በዚህ የሀሳብ አዲስነት ውስጥ የተቀመጠ ነው እላለሁ።
ቀደም ባለው የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ኃይል እንጂ ሀሳብ ቦታ አልነበረውም።ክርክር እንጂ ውይይት ስፍራ አልነበረውም።ያለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ከመቼውም ጊዜ በላይ አገርና ሕዝብ፣ ባህልና ታሪክ ዋጋ ያጡበት የምንምነት ዘመን ነበሩ ማለት ይቻላል።በነዚህ ዘመናት ውስጥ ለእርቅና ለሰላም የሚሆኑ አስታራቂ ሀሳቦች አልነበሩም።በውሸት ትርክት የተፈጠሩ በአገርና ትውልድ ላይ መርዝ የሚረጩ የጥላቻ ሀሳቦች የበዙበት ዘመን ነበር።ያ ዘመን ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ የአንድ ቡድን የበላይነት የሚቀነቀንበት እጅግ አስነዋሪ ጊዜ ነበር።በዚያ ጊዜ አገርና ሕዝብ የሚገባቸውን ክብር አላገኙም።
ይሄ ሁሉ አልፎ በለውጡ መንግሥት የመደመር ፍልስፍና በኢትዮጵያ ምድር የአንድነት ጸሐይ ወጣ።የኢትዮጵያዊነት ብርሃን ፈነጠቀ።የሀሳብ መድረክ ተፈጠረ።ይሄንን እንግዳ እውነት አዲስ አስተሳሰብ ስል ጠራሁት።
አሁን ጊዜው የኢትዮጵያ ነው።በህወሓት የሥልጣን ዘመን የባከኑብንን ወርቃማ ጊዜያት በአሸናፊ ሀሳብ የምንመልስበት የማሸነፍ ጊዜ ላይ እንገኛለን።በአዲስ አገር፣ በአዲስ መንግሥት፣ በአዲስ አስተሳሰብ ርዕዮተ ዓለም ውስጥ ነን።እንደ ህወሓት ካሉ ከመግደልና ከማስጨነቅ ሌላ ትርፍ ከሌላቸው ጠላቶቻችን ጋር እየታገልን ኢትዮጵያን በሀሳብ የበላይነት እንደምናሻግራት ስነግራችሁ ከልቤ ነው።
በጀመርነው የለውጥና የብልጽግና ጎዳና ላይ ተዋናይ በመሆን ለአዲሱ ትውልድ ታሪክ ልንጽፍ ብዕራችንን የሰደርን ብዙዎች ነን።ከፊታችን ፊተኞች አሉ.፤ አዲስ አገር፣ አዲስ መንግሥት እየጠበቁን ነው፤ በአዲስ አስተሳሰብ አዲስ ታሪክ መጻፍ የእኛ ፋንታ ነው።በአዲስ አስተሳሰብ አዲስ ታሪክ እንድንጽፍ አደራ እያልኩ ላብቃ ቸር ሰንብቱ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ.ም