ጥንታዊ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የሚጽፏቸው መጻሕፍት ለሕዝብ የሚቀርቡት ብራና ተፍቆ፣ ቀለም ተቀምሞ በእጅ ተፅፎ እንደነበረ የታሪክ ሰነዶች ያስረዳሉ። በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ-መንግሥት የተጀመረው ይኸው የዘመናዊ ሕትመት ሥራ በሀገሪቱ ቁጥራቸውና መጠናቸው በርከት ያሉ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ መጻሕፍት፣ እንዲሁም ሌሎች የሕትመት ውጤቶች መታተም በመጀመራቸው የትምህርትና የሥልጣኔ መስፋፋት ላይ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል። አሁን በኢትዮጵያ የሚገኘው ትልቁ መንግሥታዊ ማተሚያ ድርጅት ግን ሥራውን የጀመረው ከመቶ ዓመታት በፊት ‹‹ብርሃንና ሰላም›› በተሰኘች አነስተኛ ጋዜጣ ነው፤ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት።
ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መጻሕፍት፣ ጋዜጦች፣ መጽሔቶችና የምስጢራዊ ሕትመት ሥራዎች በተለያዩ ቋንቋዎች እያተመ ይገኛል። ከመንግሥት እና ከግል ጋዜጦችና ህትመቶች ባሻገርም በርካታ የፈተና ሥራዎችን በማተም ይታወቃል። ከሰሞኑ ደግሞ የተመሰረተበትን መቶኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ለአራት ወራት የሚዘልቁ መርሃግብሮችን እያካሄደ ይገኛል።
በመርሃግብሩ በተለይም የተለያዩ ማህበራዊ ኃላፊነቶችን በመወጣት ላይ ያተኮሩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ። የፓናል ውይይቶች ፤ ኤግዚቪሽኖች መሰል ሕዝብ አሳታፊ ክዋኔዎች የሚኖሩት ይኸው መርሃግበር የተለያዩ የመንግሥት አካላትም በተገኙበት የበዓሉ መዝጊያ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣም ስለአጠቃላይ የድርጅቱ ታሪካዊ ሂደት እና በዓሉን በተመለከተ ከዋና ሥራአስፈፃሚው አቶ ሽታሁን ዋለ ጋር ቆይታ አድርጓል። ከዋና ሥራአስፈፃሚው ጋር ያደረግነውን ቃለምልልስ ከማቅረባችን በፊት ግን ጥቂት ስለ እንግዳችን እንበላችሁ።
አቶ ሽታሁን ዋለ ውልደታቸውም ሆነ እድገታቸው ደብረ ማርቆስ ከተማ ሲሆን የመጀመሪያና መለስተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንደማጣኢየሱስና ንጉስ ተክለሃይማኖት በተባሉ ትምህርት ቤቶች ተምረዋል። በደብረማርቆስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ከአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዲሁም በቢዝነስ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
በአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ለአራት ዓመታት በአስተዳደርነት ሰርተዋል። የአርባ ምንጭ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካንም ለሁለት ዓመት አስተዳደር ሆነው መርተዋል። በመቀጠልም የካቲት የወረቀት ሥራዎች ድርጅት በዋና ክፍል ኃላፊነትና በአስተዳደር መምሪያ ሥራአስኪያጅነት በድምሩ ለአስር ዓመታት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅትንም ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ የተቋሙ አስተዳደር መምሪያ ሥራአስኪያጅ፣ ምክትል ዋና ሥራአስፈፃሚ፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ዋና ሥራአስፈፃሚ ሆነው እየመሩ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፡- ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በቅርቡ መቶኛ ዓመቱን አክብሯል፤ በእነዚህ ዓመታት ለኢንዱስትሪው እድገት ያበረከተውን አስተዋፅኦ ይንገሩንና ውይይታችንን ብንጀምር?
አቶ ሽታሁን፡– እንደሚታወቀው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በሀገራችን የሕትመት ኢንዱስትሪ ፈር ቀዳጅ ማተሚያ ተቋም ነው። መስከረም 14 ቀን 1914 ዓ.ም በዳግማዊ ምኒልክ ሲቋቋም በተለይም ቤተክህነት አካባቢ ያሉ ጽሑፎችን ለማተም ታስቦ ቢሆንም ከዚያ በኋላ በሂደት የተለያዩ መጽሔቶችንና ጋዜጣዎችን ወደማተም ገብቷል። ሥራውን የጀመረው በጣም አነስተኛ በሆኑና በሰው ጉልበት በሚንቀሳቀሱ ማሽኖች ነው። ፊደሎችን በመልቀምና በማገጣጠም ነበር ሲታተም የነበረው። ይህ ፊደሎችን በመልቀም የሚሰራው ሥራ በጣም አድካሚና ጊዜ የሚወስድ ነበር። ከዚያም ቀስ በቀስ ድርጅቱ በዓለም ላይ ያለው የህትመት ቴክኖሎጂ በማስመጣት በየጊዜው የህትመት አቅሙንና ጥራቱን እያሳደገ መጣ።
በአሁኑ ወቅትም በየጊዜው ወቅቱን የሚዋጁ የተለያዩ ዘመናዊ ማሽኖችን እና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሚሰጠውን የህትመት አገልግሎት በማሻሻል ተደራሽነቱን ማስፋት ችሏል። በተለይም ቴክኖሎጂው በየጊዜው የሚለዋወጥና የደንበኞችም ፍላጎት የህትመት ጥራትና ዓይነት በየጊዜው የሚቀያየር በመሆኑ የደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት ድርጅቱ አቅሙ በፈቀደ መልኩ ራሱን ለማሳደግ ጥረት አድርጓል። አሁን በፊደል ለቀማ የተጀመረው የሕትመት ሂደት ከኮምፒዩተር ወደ ፕሌት የሚደረግ የህትመት ደረጃ ላይ ደርሷል። እርግጥ ነው አሁን ላይ በዓለም ላይ ያለው የመጨረሻ ደረጃ ከኮምፒዩተር በቀጥታ ወደ ማተሚያ ማሽኑ የሚላክበት ሂደት የተሻሻለ ቴክኖሎጂ ነው። አሁን እኛ የምንጠቀምበት ቴክኖሎጂ በዘመናዊነቱ በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀስ ነው።
ድርጅታችን በቀጥታ ከኮምፒዩተር ወደ ማተሚያ ማሽኑ እንዲገባ ለማድረግ ወደሚያስችል የህትመት ቴክኖሎጂ ለመግባት በቀደሙት ዓመታት ጥናት አጥንተን ቴክኖሎጂውን የመረጥን ሲሆን የሚያስፈልገውን በጀት ለይተን ለመንግሥት አቅርበን ተፈቅዶልንም ነበር። ይሁንና ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገሪቱ ካጋጠመው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር በተያያዘ
እቅዳችንን ተፈፃሚ ማድረግ አልቻልንም። ስለዚህ አሁን ድርጅታችን የሚጠቀምባቸው አብዛኞቹ መሣሪያዎች ረጅም ጊዜ ያገለገሉ ከመሆናቸው አንፃር በምንፈልገው መጠን የህትመት ጥራታችንን ማሳደግ አዳጋች ሆኖብናል። ስለዚህ ይህንን ብቻ መተግበር ሲቀር ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ግን እየተጠቀምን የህትመት አገልግሎትን ለሚፈልጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሚፈልጉት አግባብ የህትመት አገልግሎቱን እየሰጠን እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ባለው ቴክኖሎጂ ድርጅቱ የማተም አቅሙና ተደራሽነቱ ምን ደረጃ ደርሷል ማለት ይቻላል?
አቶ ሽታሁን፡- እንደአጠቃላይ ድርጅታችን የሚሰጣቸው የህትመት አገልግሎት መደበኛ እና ምስጢራዊ የህትመት አገልግሎት በሚል ሲሆን መደበኛው ህትመት በመንግሥት የሚታተሙት ከአዲስ ዘመንና ሄራልድ ጀምሮ የግል ጋዜጦች በአጠቃላይ እዚህ ነው የሚታተሙት። በእኛ ድርጅት የተማሪዎች መማሪያ መጽሐፍቶችንም ሆነ ደራሲያን የሚያዘጋጇቸው መጻሕፍት፣ መጽሔቶች የገቢ መሰብሰቢያ ደረሰኞች፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚዘጋጁ ልዩ ልዩ አዋጆች እና ደንቦች ነጋሪት ጋዜጦች ይታተማሉ። ከምስጢራዊ ህትመት አንፃር ሎተሪ እና ባንኮች የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ ቼኮች እኛ ጋር ነው የሚታተሙት። ከዚህም ባሻገር የቦንድ ህትመት የተለያዩ ሰርተፍኬቶችንም ጭምር የማተም ኃላፊነት አለበት።
በተለይም በምስጢራዊ ህትመት ከጀመርን 50 ዓመታት በላይ ቢሆንም በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የህትመቱን ምስጢራዊ ደህንነቱን ከማስጠበቅ አኳያ እስካሁን የጎላ ክፍተት አጋጥሞን አያውቅም። ይህም ሊሆን የቻለው ሠራተኛው በረጅም ጊዜ ልምድ ያዳበረ፤ ሥራውን ደህንነቱን ጠብቆ ከመስራት ጋር በተያያዘ የተሻለ ተሞክሮ ያለው በመሆኑ ነው። ሁለተኛ ደግሞ በደህንነት መስሪያ ቤትም ሥራውን የሚከታተሉ ደህንነቱን የሚጠብቁ አካላት ተመድበው በአጠቃላይ በፌዴራል ፖሊስ፣ በደህንነት መስሪያ ቤቱና በድርጅታችን ሠራተኞችም የተለያዩ ጥበቃዎች ስለሚደረጉ አስመስሎ በመስራት ወይም ደግሞ የታተመው ህትመት በመውጣት የተለየ ችግር እስካሁን ያጋጠመበት ሁኔታ የለም። በዚህ ረገድ
በደንበኞቻችን ዘንድ ታማኝነትን በማትረፍ መልካም ስም ያለው ድርጅት ነው። ከምስጢራዊ ህትመት ጋር በተያያዘ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚዘጋጁ ብሔራዊ ፈተናዎች በድርጅታችን ይታተማሉ። እነዚህንም በተቻለ መጠን አገራዊ ጉዳዮች ስለሆኑ ድርጅቱም ሆነ ሠራተኛው በልዩ ትኩረት በጥንቃቄ ሥራዎችን የሚሰራበት ሁኔታ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡-ድርጅቱ ከተሰጠው ተልዕኮ አንፃር ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪቱና ብቃቱ እንዴት ይመዘናል?
አቶ ሽታሁን፡– ብቃት ሲባል ድርጅቱ የሚሰጠውን አገልግሎት ደንበኞችን ከማርካት ጋር የሚያያዝ ነው። ይህም ከሠራተኛው አቅምና ችሎታ፣ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲሁም አጠቃላይ ከድርጅቱ አደረጃጀት ጋር የሚያያዝ ነው። በሠራተኛው በኩል አጠቃላይ የረጅም ጊዜ ልምድ ያዳበረ ስለሆነ ሥራውን በጥንቃቄና ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ በኃላፊነት በመስራት አንፃር ምንም ችግር የለበትም። እንደክፍተትና አቅሙን ማጠናከር ይገባዋል ተብሎ የሚጠበቀው ድርጅቱ በዋናነት የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ ላይ ነው።
ስለዚህ አስቀድሜ እንደገለፅኩት ቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ አብዛኞቹ ማሽኖች የቆዩ እና ረጅም ጊዜ ያገለገሉ ናቸው። እነዚህን ማሽኖች በአዲስና በተሻለ ቴክኖሎጂ መተካት ይኖርባቸዋል። በተወሰነ ደረጃ አዳዲስ ማሽኖችን ለማስገባት ቢሞከረም ከዕድሜው አንፃር ተቋሙ ሊጠቀም ከሚገባው ቴክኖሎጂና አጠቃላይ አቅሙ ሲታይ ክፍተቶች አሉ። በዚህ ምክንያት በርካታ የመማሪያ መጽሐፍትና ምስጢራዊ ህትመቶች ውጭ ሀገር ይታተማሉ። እነዚያን በእኛ ነው መታተም የነበረባቸው። እንዲያውም በምሥራቅ አፍሪካ ከሚታሰበው ቀጣናዊ ትስስር አኳያ ድርጅቱ ሀገር ውስጥ ያለውን ፍላጎት ማርካት ብቻ ሳይሆን ከውጭም ህትመቶችን እየተቀበለ ማተምና የውጭ ምንዛሬ ማግኘት የሚችልበት አቅም ላይ መድረስ ነበረበት። በመሆኑም በቀጣይ አቅሙን በማሻሻል የሚተገብረው ነው የሚሆነው።
በሌላ በኩል የሠራተኛው አቅም በልምድ የዳበረ ቢሆንም ይህንን ልምዱን ደግሞ በእውቀት እንዲጠናክር ታስቦ ድርጅታችን የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ከፍቶ የሠራተኞችን አቅም የማጎልበት ሥራ እየተሰራ ነው ያለው። እናም በዚህ ረገድ የማተም አቅምን የማሳደግ የቴክሎጂ አጠቃቀምን የማሻሻል ሥራዎች በእቅድ ተይዘው እየተሰሩ ነው ያሉት።
አዲስ ዘመን፡-ድርጅቱ ተቋማዊ ቅርፁን ከማሻሻል አኳያ ምን እየሰራ ነው የሚገኘው?
አቶ ሽታሁን፡- ተቋማዊ ቅርፅ ሲባል አደረጃጀቱ ማለት ነው። ከዚህ አኳያ ድርጅቱ የሚያስቀምጠው ራዕይና ተልዕኮ እንዲሁም የሚዘጋጀውን ስትራቴጂክ እቅድ ማሳካት በሚችል መልኩ መደራጀት ይገባዋል ተብሎ የተሰሩ ሥራዎች አሉ። በዚህ ረገድ እስከ 2012 በጀት ዓመት ድረስ ሁለት ጊዜ የአምስት ዓመት የልማት እቅዶች ነበሩት። በዚያ አንፃር የተቃኘ አደረጃጀት እንዲኖረው ተደርጓል። ከ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት ጀምሮ የአስር ዓመት መሪ እቅድ አዘጋጅቶ በመንግሥት ፀድቋል። ስለዚህ አሁን ያለውን አደረጃጀት በዚያ በተቀመጠው ስትራቴጂ መሠረት ግቡን በሚያሳካ መልኩ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልጋል። አደረጃጀቱን አይቶ ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል። በተያዘው እቅድ መሠረት መሻሻል የሚገባቸው ነገሮች ተግባራዊ የሚደረጉ ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡-ድርጅቱ በእስከዛሬ ሂደቱ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ያለውን አበርክቶ ቢጠቅሱልን?
አቶ ሽታሁን፡- ባለፉት መቶ ዓመታት አስቀድሜ የገፅኳቸውን የህትመት አገልግሎቶች በመስጠት በሀገር ደረጃ የተቀመጡ የኢኮኖሚም ሆነ ማህበራዊ እቅዶችን እንዲሳኩ የበኩሉን አስተዋፅኦ ሲያበርክት ቆይቷል። ከኢኮኖሚ አኳያ ሲታይ ያስቀመጠውን እቅድ በማሳካት ረገድ ትርፋማ በመሆን እየቀጠለ ያለ ድርጅት ነው። ትርፋማ በመሆኑ ደግሞ የሚገኘውን ትርፍ ለመንግሥት ፈሰስ በማድረግ ለኢኮኖሚው እድገት አስተዋፅኦ ያደርጋል። በሌላ መልኩ ደግሞ ግብርም በመክፈልና ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ተጠቃሽ ተቋም ነው።
ከማህበራዊ ኃላፊነቱም አንፃር በተለይም የሥራ ዕድል በመፍጠር ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው። እንደሚታወቀው ብርሃንና ሰላም በጣም ውስን የሆነ የሰው ኃይል ይዞ ቢጀምርም አሁን በርካታ ሠራተኞችን አቅፎ እየሰራ ነው ያለው። አሁን ላይ ወደ 941 ቋሚ እና 300 የሚደርሱ ጊዜያዊና ኮንትራት ሠራተኞችን ቀጥሮ ነው እያሰራ ያለው። ስለዚህ በዚህ ረገድ የሥራ ዕድል በመፍጠር ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው። ከፖለቲካውም አንፃር በተለይ መንግሥት የሚያሳትማቸውን ጋዜጦችን በማተም በመንግሥት የሚታሰቡ እቅዶችን ከማስተላለፍ አኳያ ሚናው የጎላ ነው።
በእነዚህ ዓመታት እንደስኬት መግለፅ ከተቻለ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች የአይ.ኤፍ.አር.ኤስ ፕሮግራም ተግባራዊ እንዲደረግ ባለፉት ሦስት አራት ዓመታት በስፋት እየተሰራበት ነው ያለው። እናም ይህንን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀጥሎ የእኛ ድርጅት ነው የሚጠቀሰው። ይህንን ፕሮግራም ተጠቃሚ በመሆኑ አጠቃላይ የድርጅቱ የሂሳብ አሠራር ዘመናዊ በመሆኑ የፋይናንስ አሠራር ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ አስችሎታል። እናም አሁን አብዛኞቹ የልማት ድርጅቶች የእኛን ተቋም ነው መነሻ የሚያደርጉትና ልምድ የሚቀስሙት። ሌላው አጠቃላይ የድርጅቱ ሂሳብ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በውጭ ኦዲተሮች ኦዲት ሲደረግ ከአስተያየት የፀዳ ሪፖርት ነው ያለው። እነዚህ አጠቃላይ አሠራርና ውጤታማነት የሚታይባቸው መገለጫዎቹ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡-በሕትመት ጥራት ረገድ የሚነሳባችሁን ቅሬታ ለመፍታት ምን ያህል ጥረት ተደርጓል? ድርጅቱ አጠቃላይ አሠራሩን ለማዘመን የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎችን በማስገባት ረገድ በመንግሥት በኩል የተደረገለት ድጋፍ ምን ይመስላል?
አቶ ሽታሁን፡- የመንግሥትን ድጋፍ በተመለከተ እንደሚታወቀው ድርጅታችን ስትራቴጂክ ተቋም ነው ተብሎ ከሚጠቀሱ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው። ያም በመሆኑ የመንግሥት እይታ ትኩረት ያለው ነው። አስቀድሜ እንደገለፅኩት አቅሙን ከማሳደግ አኳያ ውጭ የሚታተሙ በሀገር ውስጥ እንዲታተሙ እንዲሁም በአዲስ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ አቅሙን አሳድጎ የተሻለ እንዲሆን መንግሥት በማመኑ በተለይ በዚህ ረገድ የምናቀርበውን በጀት በመፍቀድ ረገድ ድጋፍ ያደርጋል። አጠቃላይ አሠራራችንና እቅዳችንን በተመለከተ በየጊዜው ክተትልና ግምገማዎች ይደረጋሉ።
በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲም ሆነ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አለ። በየጊዜው ሪፖርቶችን እያቀረብን አጠቃላይ አፈፃፀሙንና ያጋጠሙ ችግሮችን በመፈተሽ አመራርና ክትትል እየተሰጠ የሚኬድበት አግባብ አለ። በሌላ መልኩ ደግሞ ድርጅቱ በ1985 ዓ.ም እንደመንግሥት የልማት ድርጅት በአዋጅ የተቋቋመ ነው። ያ ጊዜ ሲቋቋም የነበረው ካፒታል ወደ 8 ነጥብ4 ሚሊዮን ብር ነበር። ከዚያ ወዲህ ግን ካለው የሽያጭ መጠንና ሃሴት አንፃር የተፈቀደው ካፒታል ድርጅቱን የሚመጥን አይደለም በሚል በየጊዜው ጥያቄዎች ይቀርቡ ነበር። ከባንክ ብድር ለመጠየቅም እንቅፋት የሚሆንበት ጊዜ ነበርና ይህንንም በየጊዜው እናቀርብ ስለነበር በ2009 ዓ.ም ላይ ወደ 1ነጥብ5 ቢሊዮን ብር ተደረገ። በተጨማሪም የውጭ ምንዛሬ እንደሀገር ያለ ችግር ቢሆንም በተለይ ቅድሚያ አግኝተን ግብዓቶችን ከውጭ እንድናስገባ በማድረግ ረገድ መንግሥትም ቅድሚያ ድጋፍ እያደረገልን ነው ያለው።
ከጥራት አንፃር ላነሳሽው ጥያቄ ደግሞ የጥራት ችግር የሚከስትባቸው ምክንያቶች የሠራተኛው አቅም፣ የምንጠቀምበት ቴክኖሎጂና ግብዓት የሚወሰን ነው። የሠራኛውን አቅም ለማሳደግ የህትመት ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ተከፍቶ እየተሰራ ነው። በተለይም ደግሞ እንደሀገር ህትመትን በተመለከተ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ተከፍተዋል። ይሁንና ከህትመት ጋር በተያያዘ ሥልጠና እና ትምህርት የሚሰጥ ተቋም የለም። ይሄ እንደሀገር ትልቅ ችግር ነው። ስለዚህ ድርጅቱም ይህንን ችግር በራሴ መፍታት አለብኝ በሚል ኮሌጅ አቋቁሟል።
በዋናነት ኮሌጁ የተቋቋመው የውስጥ ሠራተኞችን አቅም ለማሳደግ ነው። ከዚህ ባለፈ ደግሞ ፍላጎቱ ላላቸውና ሌሎች ማተሚያ ድርጅቶች ውስጥ ለሚሰሩ ሥልጠናና ትምህርት እየተሰጠ ነው የሚገኘው።
ይህ በመሆኑም አሁን ላይ የምናያቸው ውጤቶች አሉ። በሕትመቱ ሂደት ላይ ሠራተኛው በልምድ ያዳበረውን በንድፈ ሃሳብ አስደግፎ በሚያይበት ጊዜ በቀላሉ ምርቱን ጥራቱን ለመጠበቅ የሚያስችልበት ሁኔታ ይታያል። ቴክኖሎጂውን በተመለከተ አስቀድሜ እንደገለፅኩት አብዛኞቹ ረጅም ጊዜ የቆዩ ማሽኖች በመሆናቸው ከእነሱ ጋር የሚያያዙ ችግሮች አሉ። ይህንን በተመለከተ ግን ያው በአዲስ ቴክኖሎጂ በሚተካበት ጊዜ ቀስ በቀስ እየተሻሻለ ይሄዳል ተብሎ ነው የሚታሰበው። በዚህ በጀት ዓመትም የግዢ ሂደት ላይ ያሉ የውጭ ምንዛሬ የሚፈቀድባቸው ወደ 14 የሚሆኑ ማሽኖች አሉ። እነዚህን ማስገባት ብንችል በመደበኛውም ሆነ በምስጢራዊ ህትመት በሁሉም የሚኖሩ የጥራት ችግሮችን የሚቀርፍ ነው የሚሆነው።
ሌላው ከጥራት ጋር በተያያዘ በተቻለ መጠን ድርጅታችን የሚጠቀምበት ግብዓት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ከውጭ በውጭ ምንዛሬ የሚመጣ ነው። ከውጭ የምንገዛው ግብዓት ጥራት ችግር የለበትም። አልፎ አልፎ ግን የውጭ ምንዛሬ ችግር ሲያጋጥም ሥራ መቆም ስለሌለበት በሀገር ውስጥ ያሉ ግብዓቶችን እንጠቀማለን። በዚህ ጊዜ የተለያዩ የጥራት ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። ስለዚህ በእነሱም በኩል የተሻለ ጥራት ያለው ግብዓት ለማምረት አብረን ነው የምንሰራው። የተለያዩ አስተያየቶችን እየሰጠን እንደግፋቸዋለን። በአጠቃላይ የእነዚህ ቁልፍ ጉዳዮች ውጤት ነው በቋሚነት ጥራቱን የጠበቀ ህትመት መስጠት የሚያስችለው። በሂደት ችግሮቹ እየተቃለሉ በመጡ ቁጥር ድርጅቱ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለደንበኞቻችን የሚያቀርብ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- የሰው ኃይሉን አቅም ለማጎልበት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን የድርጅቱን ሠራተኞች ለማበረታታት ምን ያህል ጥረት ይደረጋል?
አቶ ሽታሁን፡– በተቋማችን በአጠቃላይ ሠራተኛውን ከማበረታታት አንፃር በህብረት ስምምነት ሥርዓት አለ። ከዚህ አንፃር ድርጅቱ ለተከታታይ ዓመታት ትርፋማነቱን አስጠብቆ የሚገኝ ድርጅት እንደመሆኑ በየጊዜው ለሠራተኞቹ ዓመታዊ የደመወዝ ጭማሬ፤ ቦነስ እንሰጣለን። በተጨማሪም ሀገር አቀፍ ሥራዎች ያለችግር በሚከናወንት ጊዜ ልዩ ሽልማት በመስጠት ሠራተኛው የሚበረታታበትን ሁኔታ ተፈፃሚ እናደርጋለን። በዚህ በጀት ዓመትም ሁለት እርከን የደመወዝ ጭማሬ፤ የሁለት ወር ደመወዝና ልዩ ሽልማት በሚል ለሠራተኛው ማበረታቻ የሰጠንበት ሁኔታ አለ። እነዚህ በሚሰጡበት ጊዜ ሠራተኛው በየጊዜው ይህንኑ ማስጠበቅ አለበት በሚል የመነቃቃት ስሜት በየዓመቱ የተሻለ ሥራ ለመስራት የሚነሳሳበት ሁኔታ በውጤቱም የምናይ በመሆኑ የበለጠ አጠናክረን የምቀጥልበት ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡-የሕትመት ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የአሳታሚዎችን መጠን እንዲቀንስ ምክንያት እንደሆነ ይነሳል። በዚህ ረገድ ድርጅታችሁ የተፈተነበት ሁኔታ የለም?
አቶ ሽታሁን፡- አሁን እንግዲህ ከዋጋ አንፃር አስቀድሜ እንዳልኩት አብዛኞቹ ግብዓቶች ከውጭ የሚገቡ እንደመሆናው በውጭ ምንዛሬ ነው የሚገዙት። ላለፉት ጥቂት ዓመታት እንደሚታየው የውጭ ምንዛሬው በጣም እየጨመረ መምጣቱ የሕትመት ዋጋም በተመሳሳይ እንዲጨምር አድርጎታል። በሌላ በኩል ደግሞ የወረቀት ዋጋ በየጊዜው እየጨመረ ነው ያለው። እነዚህ ችግሮች ከእኛ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ዋጋውን ከፍ የሚያርጉ ምክንያቶች ናቸው። በተቻለ መጠን ግብዓቶችን በምንገዛበት ጊዜ ሁለት የማይጣጣሙ ሁኔታዎች ቢኖሩም በብዛት በሚገዛበት ጊዜ ዋጋ የሚረክስበት ሁኔታ አለ። ግብዓቱ በብዛት ለመግዛት ግን የውጭ ምንዛሬው ማነቆ የሚሆንበት ሁኔታ አለ። እናም እነዚህን ለማጣጣም ይቸግረናል። ያም ቢሆን በምንችለው አቅም በብዛት ለመግዛት ጥረት እናደርጋለን።
ሌላው ዋጋውን ከሚጨምሩ ምክንያቶች አንዱ በተለይ ከታክስ ጋር የሚያያዝ ነው። የሚገርመው መጽሐፍ ውጭ ሀገር ታትሞ ሲመጣ ከቀረጥ ነፃ ሆኖ ይገባል። እኛ ግን ለመጽሐፍ የምንጠቀምበትን ግብዓት ከውጭ ሀገር ስናስመጣ ለቀለሙም ሆነ ለወረቀቱ ታክስ እንከፍላለን። እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ ዋጋውን ያንሩታል። ስለዚህ በእኛ በኩል ለጋዜጣ የምንጠቀምበት ወረቀት በጣም እየተወደደ ነው ያለው። መጽሐፍ የምናትምበት 60 ግራም ቦንድ ወረቀትም በተመሳሳይ እየተወደደ ስለሆነ ይህን ችግር ለመቅረፍ ለገንዘብ ሚኒስቴር ያቀረብነው ጥያቄ አለ።
ውጭ ያለውን የገበያ ዋጋ መቆጣጠር ባይቻልም ሀገር ውስጥ ለሚገባው በተለይ ታትሞ ሲገባ ያለቀረጥ መግባቱና ያንን ለማተም እዚህ የሠራተኛ ደመወዝም ሆነ ሌሎች ወጪዎች ያሉብን በመሆኑ የህትመት ዋጋው የበለጠ እንዳይንር ታክሱ ላይ ማሻሻያ የሚደረግበት ሁኔታ ቢኖር ጠቃሚ ነው። ይህንን ጉዳይ እየተከታተልን ነው ያለነው። የእናንተን ድርጅት ጨምሮ በመንግሥት ድጋፍ እንዲቀርቡ ለማድረግ እየተጠባበቅን ነው ያለነው።
ሌላው ዋጋ የሚጨምረው ጉዳይ በውስጣዊ አሠራራችን የብቃትና የብክነት ችግር ነው። ይህ እንዳይኖር ከህትመቱ ሥራ ጋር የተያያዙ ለብክነት የሚዳርጉና ጊዜ የሚወስዱ ጉዳዮችን በጥናት እየለን አጠቃላይ አሠራሩን ለማሻሻል የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። በብቃት ችግር ምክንያት የሚኖረውን የዋጋ ጭማሬ ለማስቀረት በእኛ በኩል እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፡-አንዳንድ ደንበኞቻችሁ ህትመቱን በጊዜ ያለማድረስ ሁኔታ መኖሩን ይጠቅሳሉ። በዚህ በኩል ያለውን ችግር ለመቅረፍ ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ሽታሁን፡- በጊዜ ያለማድረስ ችግር ጎልቶ የሚገለፀው ከጋዜጣ ሕትመት ጋር በተያያዘ ነው። የጋዜጣ ህትመት ቅሬታ በተለይም ከመዘግየት ጋር የሚገለፀው ችግር በዋናነት ያሉን ማሽኖች ረጅም ጊዜ የሰሩ እንደመሆናቸው በተለያዩ ምክንያቶች ድንገት ያልተጠበቀ ብልሽት ሊያጋጥም ይችላል። ዕለታዊ ጋዜጦችም ቢሆን እስከመጨረሻዋ ሰዓት ዜና መዘገብ ስለሚፈልጉ ዘግይቶ የመምጣት ሁኔታ አለ።
ዘግይተው ይመጡና ጋዜጣው ደግሞ ጠዋት እንዲወጣ ይፈለጋል። ስለዚህ በሌሊት ፕሮግራም ሁሉም የሚመጡ ጋዜጦችን ለማስተናገድ ያለን የአቅም ውስንነት ችግር ይሆንብናል። በመካከል ደግሞ ማሽኖች ብልሽት በሚያጋጥማቸው ጊዜ ሕትመት የሚዘገይበት ሁኔታ ይኖራል። አብዛኞቹ ደንበኞቻችን ረጅም ጊዜ አብሮ በመስራታቸው የእኛን ችግር የሚረዱ ናቸው። በተለይም ሰው-ሰራሽ ችግር አለመኖሩን ከተረዱ ችግሩን የሚቀበሉበት ሁኔታ አለ። ስለዚህ መዘግየቱንም ሆነ እጥረቱን ለመቅረፍ በገለፅኩት አግባብ የተሻሉ ተጨማሪ ማሽኖችን በምናስገባበት ጊዜ ችግሩ ሙሉ ለሙሉ የሚቀረፍ ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡-ከዚህ ጋር ተያይዞ በምሽት የሚሰሩ ሠራተኞች በደንበኞች ላይ የሚፈጥሩት የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩ ይነሳል። በተለይ ለሚቀርቧቸው የግል አሳታሚዎች የማድላትና ሌላውን ህትመት የማዘግየት ሁኔታ መኖሩ ይነገራል። ይህ ምን ያህል ተጨባጭነት አለው?
አቶ ሽታሁን፡- ይህንን በተመለከተ እንዲሁ በወሬ ደረጃ ይገለፅ እንጂ በተጨባጭ ያለ አሠራር አይደለም። ያንን የምልበት ምክንያት በተለይ የግል ጋዜጣ አሳታሚዎች ናቸው፤ እንዲያውም ቀደም ባሉ ጊዜያትም ሆነ አሁን የሚገልጿቸው ቅሬታዎች ያሉት። በተለይ ለመንግሥት ጋዜጦች ቅድሚያ ትሰጣላችሁ የሚል ቅሬታ ያነሳሉ። ይህንን ቀደም ባሉት ዓመታት ይገለፅ ስለነበረ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ብቻ ብለን ማሽን የገዛንበት ሁኔታ ነበር። በእርግጥ አሁን ሁሉም የሚጠቀሙበት ቢሆንም ይህንን ችግር ለመፍታት ታስቦ ነው በዚያ መልኩ ተገዝቶ የነበረው። ስለዚህ እዚህ ያሉ ሥራ ተከታታዮች በምሽት የሚሰሩ ሠራተኞችን በጥቅም በመደለል ቅድሚያ እንዲሰራላቸው ለማድረግ ሊያስቡ ይችላሉ። ግን እኛ በአሠራር ነው የምንቆጣጠረው። ምክንያቱም እያንዳንዱ ጋዜጣ ተንጠባጥቦ እንጂ በሙሉ አይገባም።
ባለን አሠራር መሠረት በየዕለቱ ለሕትመት የሚገቡ ጋዜጦች ቅጂዎቹ የገቡበት ሰዓት ይመዘገባል። ሥራው የተጀመረበትና ያለቀበት ጊዜ ተመዝግቦ የምንከታተልበት አካሄድ አለ። ሰው በመሰለው ቢገልፅም አሠራሩ ራሱ ከዚያ መስመር ለመውጣት ዕድል የሚሰጥ አይደለም። በዚህ ረገድ ያጋጠመ ችግር የለም፤ በወሬ ደረጃ ግን አንቺም እንዳልሽው ይገለፃል። ያንን ግን ኃላፊዎች በየጊዜው እየተቆጣጠሩ ነው የሚሄዱት። በተጨማሪም የሚባለውን ይዘው አይቀመጡም፤ በጉዳዩ ዙሪያ ሠራተኛውን ያወያያሉ። ያጋጠመ ችግር ካለ ወዲያውኑ ለመፍታት ነው ጥረት የሚደረገው። ከደንበኞች ጋርም መድረኮችን በማመቻቸት ውይይት እናደርጋለን።
በእርግጥ ለሠራተኞቻችን ማበረታቻ እንደምንሰጥ ሁሉ ሲያጠፉም የምንቀጣበት ጠንካራ ሥርዓት ነው ያለን። በተለይም ከጋዜጣ ህትመት ጋር ተያይዞ የሆነ ችግር ቢከሰት ከሥራ ማገድ እስከ ማባረር የሚደርስ ሥርዓት ነው ያለው። ሠራተኛውም ያንን ስለሚያውቅ እንዲህ ዓይነት ችግር ውስጥ አይገባም። ከገባም ከቅጣት አያመልጥም።
አዲስ ዘመን፡-ተቋሙ የሰው ኃይል ልማቱ ላይ እየሰራው ካለው ሥራ ጎን ለጎን የውጭ ምንዛሬ የሚያስቀሩ እንደ ወረቀት ያሉ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ያቀደው ነገር ካለ ቢጠቅሱልን?
አቶ ሽታሁን፡– ወረቀትን በተመለከተ ፐልፕና ወረቀት ፋብሪካ ጋር የምንሰራው ሥራ አለ። በተለይም ይህ ፋብሪካ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ለማሟላት በስፋት ለመስራት አቅዶ እየሰራ መሆኑን ብናውቅም ፐልፑን ከውጭ የሚያስመጣ በመሆኑ በሚፈለገው መጠን ማቃለል አላስቻለውም። ስለዚህ የውጭ ምንዛሬ እጥረት የእነሱም ችግር በመሆኑ በምናስበውና የእኛን ፍላጎት በሚያረካ መልኩ ወረቀቱን አምርተው የሚያቀርቡበት ሁኔታ የለም።
በሌላ በኩል ግን በመሪም ሆነ በስትራቴጂክ እቅዳችን ላይ ድርጅታችን የራሱ የወረቀት ፋብሪካ እንዲኖረው በእቅድ የተያዘበት ሁኔታ አለ። እናም የራሱን ፍላጎት ራሱ አምርቶ መጠቀም የሚችልበት ሁኔታ በቀጣይ እንደእቅድ ተይዟል። ሁኔታዎች ሲፈቅዱ ተግባራዊ ይሆናል። በተለይ ከውጭ የሚመጣውን ወረቀት በሀገር ውስጥ ማምረት የሚያስችል የተፈጥሮ ሀብት አለን። ያንን የተፈጥሮ ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ሁኔታ በመንግሥት በኩል ቢመቻች የሀገር ውስጥ የወረቀት ፍላጎት ማሟላት የሚቻልበት ሁኔታ ይኖራል።
አዲስ ዘመን፡-ከዚሁ ጋር ተያይዞ እናንተም ሳትቀሩ ውጭ ልካችሁ የምታሳትሟቸውና የተለየ የቴክኖሎጂ ጥበብን የሚጠይቁ ምርቶችን ከማምረት አኳያ በመንግሥት በኩል ምን መሰራት አለበት ብለው ያምናሉ?
አቶ ሽታሁን፡- አንቺ የጠቀስሽውም ሆነ በአጠቃላይ ምስጢራዊ ሕትመት ማስፋፊያ ፕሮጀክት በውጭ ባለሙያ ሳይቀር አስጠንተን የተዘጋጀ ፕሮጀክት አለ። ያንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎች፣ የበጀት መጠን ተለይቷል። ስለሆነም ያንን ፈቅዶ ተግባራዊ ማድረግ ነው ችግሩን የሚፈታው። ያንን ተግባራዊ ለማድረግ ችግሩን ሁላችንም እንረዳዋለን። አሁን ባለንበት ጊዜ ግን ደረጃ በደረጃ አስፈላጊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ከቻልን ውጭ ሀገር የሚታተሙ ሕትመቶችን በሀገር ውስጥ በማተም የውጭ ምንዛሬ ወጪያችንን ማስቀረት የሚቻልበት ሁኔታ ይኖራል።
ለምሳሌ የመማሪያ መጽሐፍት ውጭ መታተም አልነበረበትም። ግን የአቅም ችግር በመኖሩ ነው የውጭ ምንዛሬያችንን መታደግ ያልቻልነው። ስለዚህ የተሻለ አቅም ያላቸውን ማምረቻ መሣሪያዎች ያንን ማተም የሚችሉ ለይተን አዘጋጅተናል። ስለዚህ በመንግሥት ተፈቅዶ የውጭ ምንዛሬው ተገኝቶ ማሽኖቹን ገዝተን ማስገባት ከቻልን ውጭ የሚታተሙትን እዚሁ ማተም ይቻላል። እንዳልሽው ግን አጀንዳ ሳይቀር ውጭ ይታተማል። ይህ በጣም የሚያስቆጭ ነው። ግን አሁን አጀንዳም ሆነ ሌሎች የተሻለ ቴክኖሎጂ የሚፈልጉ ህትመቶችን ለማምረት የሚያስችል ዝግጅት እያደረግን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ሊያስተላልፉት የሚፈልጉት መልዕክት ካለ ዕድሉን ልስጥዎት?
አቶ ሽታሁን፡-እንደአጠቃላይ በተለይ ብርሃንና ሰላም ካስቆጠረው ዕድሜ አንፃር አሁን በዚህ ደረጃ ላይ ይገኛል። ማኔጅመንቱም ሆነ ሠራተኛው የዚህ ታሪካዊ የሆነ ድርጅት አካል መሆናችን የሚፈጥርብ ስሜት አለ። በተለይም ካለፈው ትውልድ እኛ ተቀብለን ሥራውን እያስቀጠልን መሆናችን ከፍተኛ የሆነ የኃላፊነት ስሜት ነው የሚሰማን። ስለዚህ ይሄ ድርጅት በተሻለ ደረጃ በቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ሆኖ አሠራሮቹ ዘመናዊ ሆነው ለደንበኞችና ለኅብረተሰቡ ደግሞ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንድንችል ሁላችንም እንድንረባረብ ነው ጥሪ ማቅረብ የምፈልገው።
አዲስ ዘመን፡-ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቻችንና ዝግጅት ክፍላችን ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ሽታሁን፡-እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2014