ኢትዮጵያ በተለይ በአትሌቲክስ ስፖርት በትውልድ ቅብብሎሽ የተጓዙ ጀግኖች ባለቤት ናት። እነዚህ ጀግኖች በኦሊምፒኮችና በዓለም ሻምፒዮናዎች ኢትዮጵያን ወርቅ በወርቅ በማድረግ ችሎታቸውን አስመስክረዋል። በአብሮነት ጉዞ የተገኘው ድል የ“ይቻላል”ን ታሪክ በማቀበል ዛሬ ትውልድ እንዲመሰክርና እንዲማር እያደረገ ይገኛል። ቀደምት አትሌቶች በጉብዝናቸው ወራት ለሀገራቸው ሮጠው ያኖሩትን የድል ታሪክ ትውልድ ሊያወሳው ይገባል። ይህን ድል የብርታትና የጽናት ምሳሌ አድርጎ የራሱን ታሪክ ለመስራት እንዲዘጋጅ ያግዘዋልና፤ ይህን እውነታ መነሻና መድረሻ በማድረግ የአዲስ ዘመን ጋዜጣም ከቀደምት ጀግኖች አንዱ የሆኑትን የቀድሞ አትሌት የ፶ አለቃ ኃይለ ሚካኤል ጃርሶን እንግዳ አድርጓል። የ፶ አለቃ ኃይለሚካኤል በ3 ሺህ ሜትር መሰናከል፣ በ5 ሺህ ሜትር፣ በ10 ሺህ ሜትር በመሮጥ ለሀገራቸው 54 ሜዳሊያዎች ያመጡ ባለውለታ ናቸው። እኛም በርቱዕ አንደበታቸው የተረኩልንንና ከተወዳዳሪነት እስከ አሰልጣኝነት የተሻገረውን የህይወት ገጻቸውን እንደሚከተለው አቅርበነዋል። መልካም ንባብ፤ትውልድና እድገት
ትውልድና እድገቴ በቀድሞ መጠሪያው ምዕራብ ሸዋ ጅባትና ሜጫ አካባቢ ነው። ዕድሜዬ ለትምህርት እንደደረሰም ወላጆቼ በአካባቢያችን በሚገኝ አንደኛ ደረጃ ትምህርት አስገቡኝ። ትምህርቴን ከአንድ እስከ አራተኛ ክፍል ተከታተልኩኝ። ከአራተኛ ክፍል በኋላ ያለውን ደግሞ አዲስ አበባ ነበር የተማርኩት፤ያው የህይወት አጋጣሚ ሆነና ወደ አዲስ አበባ መጣሁ። ትምህርቴንም እዚሁ አዲስ አበባ በሽመልስ ሀብቴ ትምህርት ቤት መከታተል ጀመርኩ። ከአራተኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል በዚሁ ትምህርት ቤት ተምሬያለሁ። የትውልድና እድገቴ ሂደት ይህን ይመስላል።
የስፖርት አጀማመር
ስፖርት ለእኔ ህይወቴ ነው። ገና ልጅ እያለሁ ጀምሮ ነበር የስፖርት ፍቅር ያደረብኝ፤ በትውልድ ስፍራዬም ሆነ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ በሰፈር ውስጥና በትምህርት ቤት በስፖርት እንቅስቃሴ አደርግ ነበር። በተለይ ደግሞ በትምህርት ቤት ውስጥ በልዩ ሁኔታ ስፖርት አዘወትር ነበር። ሩጫውን፣ ጦር ውርወራውን፣ ዝላዩን፣ ቅርጫት ኳሱን እሞክራለሁ። ስፖርት በህይወቴ ውስጥ እስከ እለተ ሞቴ ተከትሎኝ እንደሚሄድ ጭምር ይሰማኛል። ለስፖርቱ ጥልቅ የሆነ ፍቅር ያለኝ ቢሆንም የህይወቴ ጉዞ ከትምህርት ቤት ወደወታደር ቤት ነበር ያረፈው፤ ዘመናዊ ትምህርቴን እስከ 12ኛ ከተከታተልኩ በኋላ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ተቀላቀልኩ። የሀገር ፍቅር ስሜቴና ወኔዬ ከልጅነቴ አብሮኝ ያደገ ነውና ሀገሬን በምን ላገልግል ከሚል ጉጉት ነበር ጦሩን የተቀላቀልኩት።“ሁን ያለው ይሆናል” ነውና የልጅነት ህልሜን በጦሩ ቤት ዳግም አገኘሁት። የስፖርት እንቅስቃሴ ለማድረግ ተመቸኝ። በጦሩ ቤት በሚደረጉ የውስጥ ውድድሮች ላይም በአትሌቲክስ የመሳተፍ አጋጣሚዎች ተፈጠሩ። የልጅነት ህልሜ ከተቀበረበት ተፈንቅሎ መውጣት ጀመረ። የህይወቴ ምዕራፍ ወደሌላ አቅጣጫ ተዛወረ።
በሀይለስላሴም ሆነ በደርግ ጊዜ በጦሩ ቤት ስፖርት በከፍተኛ ሁኔታ ይዘወተር ነበር። በየአካባቢው የነበሩት የጦሩ ክፍሎችም በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጁ የውድድር አውዶች ውጤታማ ቡድኖችን ይዘው በመቅረብ ይታወቃሉ። የውጤት ታሪክ በያዘው ቤት ውስጥ ዳግም የተወለደው የእኔ የስፖርት ህይወት ይሄንኑ መልክ የያዘ ነበር። ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በጦሩ ቤት በተደረገ የውስጥ ውድድር እኔ የመታየት አጋጣሚው አግኝቻለሁ። ያኔ በሀገሪቱ ጠንካራ ተብለው ዛሬም ድረስ በታሪክ ከሚወሱት ቡድኖች አንዱ የሆነውን ክቡር ዘበኛን ለመቀላቀል በቃሁ። ክቡር ዘበኛ ውስጥ ከገባሁ በኋላ ችሎታዬን በሚገባ የማውጣት እድል አግኝቻለሁ። በአጭር ጊዜ ውስጥ አይን ውስጥ ገባሁ። የመጀመሪያው የስኬት በርም ተከፈተ። በ1963 ዓ.ም በሸዋ ሻምፒዮና (ያኔ የሸዋ ጠቅላይ ግዛት የሚባል አስተዳደር ነበር) ውስጥ መመረጤ ነበር ይህንን ያበሰረኝ፤ በዚህ ውድድር በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል መድረክ ላይ የነበረኝ ውጤታማነት በሀገር አቀፍም ሆነ ከአገር ውጪ በሚደረጉ የስፖርት ውድድሮች በመሮጥ ሜዳሊያዎችን እንድሰበሰብ መንገድ ጠርጎልኛል።
የአፍሪካ እና የዓለም አቀፍ መድረክ ተሳትፎና ውጤት
በሀገራችን ስፖርት እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ ታሪክ ባለበት በክቡር ዘበኛ ቤት ውስጥ መቆየቴ በአጭር ጊዜ ከሀገር አቀፍ ወደ አህጉር አቀፍ ውድድር ለመሸጋገር ድልድይ ሆኖኛል። ዓመተ ምህረቱም 1964 ነበር። በሀገር አቀፍ ውድድር በማሸነፌ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተመረጥኩ። ይሁን እንጂ፤ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር በሙኒክ ኦሎምፒክ ለመሳተፍ ከተመረጠው ቡድን ጋር ለመጓዝ እየተሰናዳሁ ባለሁበት ወቅት ከአሰልጣኝ ጋር በተፈጠረ ግጭት ከቡድኑ ውጪ ተደረግሁ። ወደትልቁ የውድድር መድረክ ለመጓዝ የቋመጠው ልቤ፤ በዚያም ለመሮጥ የተነሳው እግሬ በትንሽ አጋጣሚ “ነበር” ሆኖ ቀረ። ይህ መሆኑ ውስጤን ቢረብሸኝም ተስፋ ሳልቆርጥ ልምምድ መስራቴን አላቋረጥኩም። ከአንድ ዓመት በኋላ፤ ማለትም በ1965 ዓ.ም በመላው አፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለመወዳደር ለብሄራዊ ቡድን ተመረጥኩ። ናይጄሪያ ሌጎስ በተካሄደው በዚያ ሻምፒዮና ላይ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ሀገሬን በመድረኩ ወከልኩኝ። በውድድሩ አራተኛ በመውጣት ዲፕሎማ ተሸለምኩ። በሩጫው የገባሁበት ሰዓት ፈጣን የሚባል በመሆኑ ለፓን አፍሪካ ለመመረጥ ያስቻለኝ ነበርና ከአንድ ዓመት በኋላ አልጀርስ ላይ ተወዳድሬ ሶስተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቀኩ። በሻምፒዮናው የነበረኝ ተሳትፎና ውጤት ደግሞ በአትሌቲክሱ የማደርገውን ጉዞ ቀጣይነት እንዲኖረው ያደረገ ነበር።
በአህጉር ደረጃ የነበረኝ የተወዳዳሪነት አድማስ ከፍ ያለና በተለያዩ የዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የመሳተፍ እድሎችም ነበሩኝ። በአሜሪካ አዘጋጅነት በተካሄደውና ከተለያዩ አህጉራት የተውጣጡ ቡድኖች በሚተሳተፉበት ውድድር በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ተሳታፊ ሆኛለሁ። በውድድሩ ሶስተኛ በመውጣት ለአፍሪካም ሆነ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ሜዳሊያ ያጠለቅኩበት አጋጣሚ ከብዙዎቹ መካከል የሚጠቀስ ነው። በአህጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለኝ ተሳትፎና ውጤት ከዚህ አኳያ ታሪካዊ የሚባል እንደሆነ አስባለሁ። በተወዳዳሪነት ዘመኔ በተለየ መልኩ 3ሺህ መሰናክል እውቅና ላትርፍ እንጂ፤ በ5 ሺህ ና በ10 ሺህ ሜትር በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ተወዳድሬያለሁ። በተለያዩ አገራት በመዞር በተወዳደርኩባቸው ጊዜያት ባጠቃላይ 54 ሜዳሊያዎች አግኝቻለሁ።
የአሰልጣኝነት ህይወት
በክቡር ዘበኛ ቤት ውስጥ የጀመረው የተወዳዳሪነት ህይወቴ በተለያዩ የታሪክ ገጠመኞች ታጅቦ እዛው ተዘጋ። ለስፖርቱ የነበረኝ ጥልቅ ፍቅርና ፍላጎት በዚያው እንድዘልቅ አደረገኝ። እናም የተወዳዳሪነት ቆይታዬ ካከተመ በኋላ፤ በዚያው ባሳደገኝ በክቡር ዘበኛ ቤት ውስጥ አሰልጣኝ ሆኜ ቀጠልኩ። በሀገራችን የስፖርት ታሪክ ውስጥ ዛሬም ድረስ ስሙ በሚነሳው በጦሩ ቤት ከባልደረቦቼ ጋር በመሆን ታሪክ ለማስቀጠል ተነሳን። በወቅቱም ማዕከላዊ ኮርን እንዳሰለጥን ተሰጠኝ። በዚያም ውርወራ፣ ዝላይና መሰናክል አሰለጥን ነበር። ከዚያም፤ እድሜዬ ለጡረታ ሲደርስ በ1987 ዓ.ም ጡረታ ተገለልኩ። የአሰልጣኝነት ቆይታዬ ከተወዳዳሪነት ጊዜ ባልተናነሰ ስኬታማ እንደነበር አስባለሁ። ለዚህም በአፍሪካ ሻምፒዮና የወርቅ ጫማ ተሸላሚ የሆነው አትሌት በቀለ ደበሌ የኔ ሰልጣኝ ነበርና እርሱ እንደማሳያ ይጠቀሳል። አትሌቱ ወታደር ሆኖ የተቀጠረ ቢሆንም ለስፖርት የተመለመልኩት እኔ ነበርኩኝ። በቀለን በጊዜው እንዳየሁት በቂ ስልጠናና ክትትል ከተደረገለት ውጤታማ እንደሚሆን እምነት አደረብኝ። እርሱም አላሳፈረኝም በአፍሪካ ሻምፒዮና ላይ የወርቅ ጫማ ተሸለመ። በአሰልጣኝነት ቆይታዬ ሌሎች ውጤታማ አትሌቶችን አፍርቻለሁ። ሀገራችን ስሟና ታሪኳ ብዙም በማይጠቀሰው የእርምጃ ሩጫ ተወዳዳሪ የነበረው ሸምሱ ሀሰን የእኔ ሰልጣኝ ነው። ሸምሱ በተለያዩ አገራት በመሳተፍ ውጤት ማስመዝገቡን ታሪክ ምስክር ነው። በአሁኑ ወቅት በአሜሪካን አገር የሚኖረውን አለማየሁ ሮባን ከትምህርት ቤት መልምዬ አምጥቼ ውጤታማ አድርጌዋለሁ። በዚህም የተነሳ፤ በክቡር ዘበኛ ተጠንስሶ በተወለደው የስፖርት ህይወቴ በአትሌትነትም በአሰልጣኝነትም ስኬታማ ነበርኩ ብዬ በኩራት መናገር እችላለሁ። ከእኔም ሆነ ከሌሎች ቀደምት ስፖርተኞች ስኬት ጀርባ ግን በጦሩ ቤት ውስጥ በመንግስትም ይህን በጦሩ መሪዎች ለስፖርት የሚሰጠው ትኩረት የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝ ሳልናገር አላልፍም።
ታሪካዊ ድል፤ የጦሩ ጀብድ
በጦሩ ቤት ለስፖርቱ ትኩረት ተደርጎ የተጠናከረ ስልጠና ይሰራል ነበር። ያኔ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚከናወኑ ውድድሮች ላይ የአትሌቲክስ ዋንጫ ለአንድ ጊዜም ቢሆን ከክቡር ዘበኛ ወጥቶ አያወቅም። በቡድን ስራ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል። በመሆኑም በአትሌቲክሱ በተለያዩ ርቀቶች ውጤታማ አትሌቶች በማፍራት ረገድ የክቡር ዘበኛን ያክል የነበረ ክለብ የለም ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል። ክቡር ዘበኛ በርካታ ስፖርትኞችን አፍርቷል። ክለቡ ሀገራችንን በዓለም አቀፍ የውድድር አውዶች ላይ ውጤታማ እንድትሆን ያደረገ፤ ሰንደቋንም ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያሰቸለም ጭምር ነበር። ሻምበል ማሞ ወልዴ፣ ሰለሞን በላይ፣ ካሳ ባልቻ፣ ሀይሉ ወልደጻዲቅ ፣የማራቶን ጀግናው ደረጄ ነዲ፣ ለማ ገዳ፣ እነዚህ ሁሉ አትሌቶች ከክቡር ዘበኛ የተገኙ የሀገር ባለውለታዎች ናቸው። ለእነዚህ አትሌቶች ስኬትና ውጤታማነት ደግሞ አሰልጣኞች የጀርባ አጥንት ነበሩ። እንደትውስታም አሰልጣኝና ተቆጣጣሪ የነበሩት ተከስተ አባይ አብረው የሚነሱ ለክለቡ ብቻም ሳይሆን ለሀገር ባለ ውለታ ጭምር ናቸው። እናም ክቡር ዘበኛ የሀገሪቱ የስፖርት ማህጸን ነበር ማለት ይቻላል። አሁን ባለው የሀገሪቱ ስፖርት ላይም አሻራው ይታያል።
የአትሌቲክሱ ጋሬጣዎች
በአሁኑ ወቅት በስፖርቱ ውስጥ የሚታየው የመለማመጃና የመወዳደሪያ ሜዳ ችግር ከፍተኛ ተጽእኖ እያሳደረ ይገኛል። በመንግስት በኩል ይህ ጉዳይ ትኩረት ተደርጎበት ሊሰራ ይገባል። ስፖርቱን በሚፈለገው ደረጃና መልክ ለማከናወን የማዘውተሪያ ቦታ እንደ ልብ ማግኘት አይቻልም። ለምሳሌ፤ የራሴን ተሞክሮ ባነሳ፤ የግል ክለብ አሰለጥን ነበር። ብዙም ሳልገፋበት ማሰልጠኑን በማቆም አቅጣጫዬን ቀየርኩኝ። ምክንያቱም የእኔ የማሰልጠን ፍላጎትና የአትሌቶች የመሰልጠን ፍላጎት ብቻ በቂ አይሆንም። ይልቁንም፤ የተሟላ የማሰልጠኛ ቦታ ያስፈልጋል። የስልጠና ሜዳ በሚፈለገው ደረጃና እንደ ልብ የሚገኝ ቢሆን ያካበትኩትን እውቀቴንና ልምዴን ማጋራት እችል ነበር። ይህ ችግር ከራሴው ተሞክሮ መንሳቴ ነው እንጂ በሌሎች ሙያተኞች በተደጋጋሚ ሲነሳ ይደመጣልና ብሄራዊ ፌዴሬሽኑም ሆነ መንግስት ጉዳዩን በሚገባ ሊያጤኑት ይገባል። ኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ሀገር ሆና አትሌቶች በበቂ ሁኔታ ስልጠና የሚሰሩበት ሜዳ አለመኖሩ ያሳፍራል። አዲስ አበባ ውስጥ አነሰ ቢባል ስምንት የስልጠና ሜዳ ሊኖር ይገባ ነበር። እውነታው ግን ይህ አይደለም። ሌላው ለሀገራችን አትሌቲክስ የቁልቁለት ጉዞ ምክንያት ተደርጎ መወሰድ የሚገባው ልምድና እውቀት ያካበቱ አንጋፋ ስፖርተኞችን መዘንጋት ነው።
በብሄራዊ ፌዴሬሽኑ አሁን የሚገኙት ወጣት አሰልጣኞችና አትሌቶች ልምድ ያካበቱ ሙያተኞችን ሲጠቀሙ/ሲያማክሩ አይስተዋልም። በኦሎምፒክ፣ በአለም ሻምፒዮና ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ሀገርን ያስጠሩ ትንታግ አትሌቶች ባለቤት መሆኗ ይታወቃል። እነዚህን የትናንት ጀግኖች ልምድና እውቀት ከዘመኑ ጋር አዋድዶ መጠቀም ያስፈልጋል። በእርግጥ በአሰልጣኝነቱ ባንመጥን እንኳን፤ ለወጣት አሰልጣኞች ረዳትና አማካሪ በመሆን የቀደመውን ልምድ ማካፈል እንችል ነበር። ያለፍንበትንና የሰራንበትን ማሳየቱ ለመጪው ትውልድ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። በሀገራችን አትሌቲክስ ውስጥ ይህ ባህል ብዙም የለም። አይስተዋልምም። በሌሎች ሀገራት ልምድ ያካበቱ ስፖርተኞችን ከማራቅ ይልቅ ቀርበው እንዲያግዙ፤ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ እንደሚያደርጉ በተለያዩ አጋሚዎች ታዝቤአለሁ። በእኛ ሀገርም ይሄን ልምድ ወስዶ ተግባራዊ ማድረጉ ጥቅሙ የጋራ ነው። በሀገራችን ነባራዊ ሀቅ የቀደሙ አትሌቶች አስታዋሽና እውቅና እያገኙ አይደለም።ይህ አይነቱ ውለታበል አካሄድ ስፖርቱን ገድሎታል የሚል እምነት አለኝ።
የሀገር ባለውለታዎች የጊዜ ክፍያ
በሀገራችን የቀድሞ አትሌቶችን ብዙን ጊዜ አስታውሶ እውቅና የመስጠቱ ዝንባሌ በእጅጉ ትንሽ ነው። በዓለም አቀፍ መድረኮች የአትሌቲክስ ውድድሮች በመሳተፍና በማሸነፍ የሀገራችንን ሰንደቅ አላማ በዓለም ህዝብ ፊት እንዲውለበለቡ ያደረጉ በርካታ የቀድሞ አትሌቶች አሉ። እነዚህ የቀድሞ አትሌቶች አሁንም በህይወት ይገኛሉ። በጉብዝናቸው ወራት የሀገራችንን ስም ያስጠሩትን እነዚህን ባለውለታዎች ፈልጎ እውቅና መስጠትና ድጋፍ ማድረግ ትልቅ ቁም ነገር ነው። ይሁን እንጂ፤ ይህ አይነቱ ሁኔታ በሀገራችን ብዙም ጠንካራ አይደለም። አስታውሶ እውቅና የመስጠት ባህሉ/ልምዱ እምብዛም ነው። ይህ መሆን የለበትም። በእርግጥ በቅርቡ ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ (ምንም እንኳን ቢዘገይም) አስታውሶን ትጥቅና የተወሰነ ገንዘብ ድጋፍ አድርጎልናል። ፌዴሬሽኑ ይሄን ሲያደርግ እኔ እውነቴን ነው ከእንቅልፌ የባነንኩኝ መስሎኛል። “ለካስ ያውቁናል” ነበር ያልኩት፤ ይህ ዓይነቱ ተግባር ሊቀጥል ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 202011
በዳንኤል ዘነበ