ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በትምህርት ላይ እያለሁ አንድ መምህራችን የነገረን ትዝ አለኝ፡፡ የጋዜጠኝነት ሙያ ልዩ ዕይታ ይፈልጋል፤ ነገሮችን ማስተዋልና ማጠያየቅ የግድ ይላል። አለና ይህንንም ለማስረዳት አንድ ምሳሌ ሰጠን፡፡
አንድ የኪነ ሕንጻ ባለሙያ (አርክቴክት) ወይም አንድ መሃንዲስ በከተማ መሃል እየሄደ አንድ አስገራሚ ሕንጻ ቢያይ ትኩረት ሰጥቶ ማስተዋል አለበት፡፡ እንዴት እንደተሰራ ማሰላሰል አለበት፡፡ ከሌላው ሰው በተለየ የሕንጻው ነገር ቀልቡን ሊስበው ይገባል፡፡ እንዴት እንደተሰራ ማወቅ እንኳን ባይችል በአሰራሩ መደነቅ አለበት፤ ወይም ካልጣመው ደግሞ እንዴት እንደዚህ ያበላሹታል ብሎ መናደድ አለበት፡፡ ልብ ሳይለው ካለፈ እሱ መሃንዲስ አይደለም!
ይሄንን ፎቶ በማህራዊ ገጽ ላይ ሳየው ያ መምህሬ ነው ትዝ ያለኝ፤ ‹‹ፌስቡክ ላይ ስንት አስራሚ ነገር እያለ እንዴት በዚህ ትገረማለህ?›› የሚለኝ አይጠፋም! ልክ ነው። ከዚህ በላይ የሚገርሙ ነገሮች አሉ፤ ግን ያ መምህር የነገረንን ነገር ስላስታወሰኝ ነው፡፡ ለዚያውም እኮ ይሄ ፎቶ በእውን ይኑር በፎቶሾፕ የተሰራ ይሁን እርግጠኛ አይደለሁም፤ ዳሩ ግን ከዚህ በላይ የሚገርምም ስላለ በእውን ያለም ሊሆን ይችላል፤ ፎቶሾፕ ከሆነም ለነገር መነሻ ይሆነናል፡፡
መገረም የጠቢባንና የብልሆች ነው፡፡ አንድ ሰው በሆነ ሥራ የሚገረመው አሰራሩን ለማወቅ ካለው መጓጓት የተነሳ ነው፡፡ ለምሳሌ፤ ሕጻናት ‹‹ይሄ ምንድነው? ለምን እንዲህ ሆነ?›› እያሉ ይጠይቃሉ፤ ይህን ሚያስጠይቃቸው ለማወቅ ያላቸው ፍላጎት ነው። በተቃራኒው እኛ አዋቂዎቹ ደግሞ የማናውቀውን ነገር መጠየቅ አንወድም፡፡
በነገራችን ላይ፤ መጠየቅን ነውር ያደረገው ይህ “አራዳ” እና “ፋራ” ሚባል ነገር ነው፡፡ መጠየቅ የፋራነት ምልክት መስሏቸው ፋራ ሆነው የቀሩ አሉ፡፡ ‹‹መጠየቅ ያደርጋል ሊቅ›› የሚለው የአበው አባባል ውሃ በላው ማለት ነው፡፡ ይሄ ችግር ሚታየው ከተማ አካባቢ ነው፡፡ በከተማ ውስጥ የማያውቁትን ነገር መጠየቅ የፋራነት ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። በተቃራኒው ግን፤ የከተማ ነዋሪ ወደ ገጠር ሲሄድ ያለምንም ፍራቻ ‹‹ይሄ ምንድነው?›› እያለ ይጠይቃል፡፡ በእርግጥ ይሄ የሆነበት ምክንያት ገጠር ያለውን ነገር አለማወቅ የማያሳፍር፤ ከተማ ያለውን አለማወቅ ግን የሚያሳፍር መስሎ ስለሚታየን ነው፡፡ ግን ደግሞ የገጠር ነዋሪዎችም እኮ ይስቁባቸዋል (ሙድ ይይዛሉ እንበለው?) ለምሳሌ፤ ቅርብ ጊዜ ወደ ከተማ የገባ ሰው ‹‹ይሄ ምንድነው›› ብሎ ቢጠይቅ ይሳቅበታል፡፡
ነገሩን “የተማሩ ናቸው” ወደሚባሉት እናምጣው፤ የመጠየቅና የመገረም ባህል የለንም፡፡ መገረም የሞኝነትና የ“ፋራነት” ይመስለናል፡፡ መገረም ግን የብልህነት ነው፡፡ መገረም ሲባል ታዲያ ዝም ብሎ ‹‹አጃዒብ!›› እያሉ መገረም አይደለም፤ “ምንድነው!? እንዴት ተሰራ?”… እያሉ ማጠያየቅ እንጂ!
መገረምንና መጠየቅን እንደፋራነት በማየታችን ብዙ ነገሮችን እናበላሻለን፤ በግምት እንሰራለን፡፡ በቀላሉ በመንገድ ላይ ስንሄድ እንኳን ያለውን ክስተት ብንወስድ፤ አካባቢ ሲጠፋብን ላለመጠየቅ ብለን እኛ ከምንሄድበት ወደተቃራኒ አቅጣጫም ልንሄድ እንችላለን፡፡
የጥበብን ሰዎች ብናስተውል ጥበብን ያገኙት ከመገረም ነው፡፡ በተለይ ሰዓሊዎችና ቀራጺዎች በአካባቢያቸው ባሉ ነገሮች ይገረማሉ፡፡ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ሬዲዮ ሲናገሩ እንደሰማሁት፤ ልጅ እያሉ በሰማይ ደመና በሚሰራው ቅርጽ ይገረሙ ነበር፡፡ ደመና በሰማይ ላይ የሚፈጥረውን የተለያየ ዓይነት ቅርጽ እያዩ ‹‹ምንድነው ይሄን ደመና እንዲህ ሚያደርገው?›› ይሉ ነበር፡፡ ይህ መገረማቸው ነው የሰማዩን ደመና ጥበብ ወደ ምድር አውርዶ እርሳቸውን የሸራ ላይ ሰዓሊ ያደረጋቸው፡፡
የገጠር ሕጻናት የጭቃ በሬ ይሰራሉ። ከጭቃ መኪና ይሰራሉ፡፡ ያ ማለት በገሃዱ ዓለም የሚያዩትን ነገር በምናብ ያስቡና አስመስሎ ለመፍጠር ይተጋሉ ማለት ነው፡፡ እኛ ግን አስመስሎ ከመስራት ይልቅ መገረምን እንደፋራነት በማየት እናልፈዋለን፡፡ ለዚህ እኮ ነው የምዕራባውያን ቴክኖሎጂ ለሥልጣኔ ከመሆን ይልቅ ለጊዜ መግደያ ብቻ የሆነን፤
ዶክተር አክሊሉ ለማ እንዴት ለብልሃርዚያ በሽታ መድሃኒት እንዳገኘ ብዙዎቻችን እናስታውሳለን፡፡ ተማሪ ሆኖ ሰዎች በወንዝ ዳር ልብስ ሲያጥቡ ያየው ነገር ነው፡፡ ሰዎቹ ልብስ የሚያጥቡበት እንዶድ በውሃው ውስጥ ያሉትን አካላት ሲገድላቸው ተመለከተ፤ እናም የእንዶድን ብርታት አስተዋለ፡፡ ለካ ይሄ ነገር መድሃኒት ይሆናል ብሎ ተመራመረበት ማለት ነው፡፡ እንዲህ ነው ጥበበኛነት! እርሱ አስተዋይ ስለሆነ ተመራመረበት እንጂ፤ ከእርሱ በፊት እኮ በዚያ ወንዝ ውሃ ብዙ ሰው ልብስ አጥቧል፤ ብዙዎችም ልብስ ሲታጠብ አይተዋል። እንዶዱም ብልሃርዚያ መግደል የጀመረው ያኔ አይደለም፡፡
አስተዋይ ልቦና ይስጠን!
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2011
በዋለልኝ አየለ