በሰፊው ግቢ ውስጥ ከተሰባሰቡት ሴቶች አብዛኞቹ በተለየ ትኩረት እየተወያዩ ነው። ሁሉም ሃሳብና ጨዋታቸው በአንድ ተቃኝቷል። በዚህ ስፍራ አገናኝቶ የሚያነጋግራቸው ቁም ነገር ምን እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቁታል። አጠገባቸው ተገኝታ የሃሳብ አካፋይም ተካፋይም የሆነችው የጤና ባለሙያም ለሚጠይቋት ሁሉ ትመልሳለች። እነርሱም ለጥያቄዎችዋ ምላሽ ይሰጣሉ።
የምክክር ስፍራውን አለፍ ሲሉ ሰፋ ባለ ክፍል በአግባቡ ከተነጠፉ አልጋዎች አጠገብ ይደርሳሉ። የአልጋዎቹ አቀማመጥ እናቶች በአግባቡ ለመወያየት እንዲያመቻቸው ሆነው የተዘጋጁ ናቸው። በአንዱ ጥግ የተቀመጠው ተለቅ ያለ ቴሌሌቪዥን ደግሞ ለመዝናኛና መረጃ ልውውጥ የሚያግዛቸው ነው። እናቶች በየዕለቱ በሚተላለፉ ዝግጅቶች እየተዝናኑ ይማማራሉ።
ከመኝታ ክፍሉ ትይዩ የምግብ ማዘጋጃ ክፍል ይገኛል። በዚህ ስፍራ በአግባቡ የተቀመጠው እህል ከአካባቢው አርሶ አደሮች በበጎ ፈቃድ የተሰበሰበ ነው። የማብሰያ ዕቃዎቹና ለምግብ ፍጆታ የተዘጋጀው አቅርቦትም የተሟላ ነው። ይህ መሆኑ እናቶች በውሏቸው እንዳይቸገሩ አግዟቸዋል። ያሻቸውን ቀምሰውና ከሻይ ቡናው ፉት ብለው መዋል መብታቸው ነው።
ምስራቅ ጎጃም ዞን ሸበል በረንታ ወረዳ የሚገኘው የ«ሞዠን» ቀበሌ ጤና ጣቢያ ሁሌም ቢሆን ከዚህ ልማድ ርቆ አያውቅም። በርካታ እናቶችን አሰባስቦ በአንድ ሲያወያይ ያረፍዳል። እህል ውሃው ተዘጋጅቶ፤ ቡናው ከነቁርሱ ቀርቦ ቁም ነገር በሚወራበት በዚህ ስፍራ ነፍሰጡር እናቶች ያሻቸውን እያነሱ ይወያያሉ። የሚገኙበት ቦታ አንድም ለጤንነታቸው የሚበጅ፤ ሌላም እንደቤትና ጓዳቸው የሚታይ ማረፊያቸው ነው።
እናቶቹ ከያሉበት ተሰባስበው በአንድ ሲውሉ ስሜታቸው አይራራቅም። ሃሳብና ጨዋታቸው ተመሳሳይ ነው። ሁሉም በሆዳቸው ስለያዙት ጽንስ በትኩረት ይወያያሉ። አርቀውም ስለነገው ዕቅድ ይነድፋሉ። እያንዳንዳቸው ስለጤንነታቸው ሲያስቡ በባለሙያዎች የሚታዘዙላቸውን መድሃኒቶች በጊዜውና በአግባቡ መውሰድ አይዘነጉም።
ወይዘሮ ሃይማኖት ደነቀው የ«ስዋ» ተፋሰስ ቀበሌ ነዋሪ ናት። የ«ኩበት» ከተባለችው ጎጥ ተነስታ ሞዠን ቀበሌ ለመምጣቷ ምክንያት አላት። ይህን ስታደርግ መምህሩ ባሏ በደስታ ሸኝቶ ስትመለስም ይቀበላታል። ሃይማኖት የመጀመሪያ ልጇን ነፍሰጡር ናት። ይህን ካወቀች ወዲህ የህክምና ክትትል ታደርጋለች። እሷን መሰል እናቶች ሁሌም ቢሆን ወሩን ጠብቀው ብቻ እንዲመጡ አይገደዱም። ጤና ባልተሰማቸውና ምክር በሚሹ ጊዜም የጤና ባለሙያዎችን ማግኘት ይችላሉ።
ሃይማኖት ከዚህ ቀደም በነፍሰጡሮች ላይ ይከሰት የነበረውን ችግር ታውቀዋለች። የጤና ክትትል ካለማድረግ የተነሳ ስለሚከሰተው አደጋና በወሊድ ጊዜም ስለሚያጋጥም የደም መፍሰስ ዕውቀቱ አላት። ቀደም ሲል በቤታቸው የሚወልዱና ህይወታቸውን የሚያጡ እናቶች ቁጥር በርካታ ነበር። አሁን ግን ያ ታሪክ እንዳይደገም ሁሉም የራሱን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።
ወይዘሮዋ እርግዝናው የመጀመሪያዋ እንደመሆኑ ከመውለዷ ጥቂት ቀናት አስቀድሞ በጤና ጣቢያው አርፋ መቆየት ትፈልጋለች። ለዚህም የጤና ባለሙያዎችና እሷን መሰል እናቶች ከጎኗ ሆነው ይንከባከቧታል። እንደአማኝ አስቀድሞ ወደዚህ መምጣት የከበደውን ያቀልላል። ድንገት ምጥ ቢመጣና አስቸኳይ ርዳታ ቢያስፈልግ ድንጋጤና መዋከብ፣ ድካምና ሩጫ አይኖርም። ለእናቲቱም ሆነ ለልጁ ደህንነት ዋስትና ማግኘት ይቻላል።
ሁሌም ማለዳ በነፍሰጡር እናቶች የሚደምቀው ይህ ግቢ መተሳሰብና መተጋገዝ መለያው ነው። ቀናቸው ለደረሰ ነፍሰጡሮች የሚሰጠው ትኩረት የሚደረገው እንክብካቤ ለየት ይላል። እናቶቹ መውለዳቸው በተሰማ ጊዜም ገንፎ ተገንፍቶና ቡናው ተፈልቶ የመጀመሪያው ደስታ የሚበሰረው በዚህ ስፍራ ነው።
ወይዘሮ አዱኛ ዳምጤ የአንዲት ሴት ልጅ እናት ነች። ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት ይህ ግንዛቤ ስላልነበራት በቤቷ ውስጥ ለመውለድ ተገድዳለች። የዛኔ ያጋጠማትን ስቃይና የደም መፍሰስ መቼም አትረሳውም። በወቅቱ ወደ ጤና ጣቢያ የመሄድ ልምድ ባለመኖሩ በዚያ ሁኔታ ለማለፍ ግድ ብሏት እንደነበር ትናገራለች።
አሁን ግን አዱኛ ያለፈውን ላለመድገም ለክትትል የተገኘችው ቀደም ብላ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ በጤና ጣቢያው አገልግሎት ያገኙ እናቶች ተሞክሮ አግዟታል። ወይዘሮዋ «ልጅ በዕድሉ ያድጋል» በሚለው ተለምዷዊ ብሂል አትስማማም።
«ልጅ ሁሌም ፍላጎቱ ተሟልቶለት ሊያድግ ይገባዋል» ስትል ታምናለች። እሷም የኑሮ አቅሟ ዳብሮ የጎጆዋ ሙላት እንዲቀጥል ትፈልጋለች። ትናንት ያለፈችበትን የችግር ህይወት ልጆችዋ እንዲደግሙት አትሻም። ትምህርቷን እንድታቋርጥ ሰበቡም ያለዕድሜዋ የገባችበት ትዳርና ተከትሎ የመጣው ልጅ መሆናቸው አልጠፋትም። ይህ በመሆኑም ዛሬ ድረስ ይቆጫታል። ሌሎች ምክንያቶች ደግሞ ሰባት ዓመታት ያለ ተጨማሪ ልጅ እንድትቆይ አድርጓታል።
ውሎ አድሮ ግን ይህ አቋሟ ከባለቤቷ አላስማማትም። ወዳጅ ዘመዶችዋም ቢሆኑ ሃሳቧን አልደገፉላትም። ይህን ስታውቅ ወይዘሮዋ ቆም ብላ አሰበች። ትዳሯን መታደግና ኑሮዋን በአግባቡ መምራት ግድ ቢላት፤ የምትወስደውን የወሊድ መቆጣጠሪያ ትታ ለማርገዝ ወሰነች።
አሁን አዱኛ ዘጠነኛ ወሯ ገብቷል። በየጊዜው ቅድመ ወሊድ ክትትል ለማግኘትም ከጤና ጣቢያው ርቃ አታውቅም። ይህ ውሎዋ ደግሞ ከሌሎች መሰሎቿ ጋር አገናኝቷት ልምድ ቀስማለች። ሴቶቹ በተገናኙ ቁጥር ስለትዳርና ስለጎጇቸው ያወጋሉ። ስለልጆቻቸው፤ ስለነገው ህይወታቸውና ስለሚያስቡት ዕቅድ ሁሉ ይወያያሉ። እግረ መንገዳቸውንም ለገጠሟቸው ችግሮች መላና መፍትሄ ያበጃሉ።
ሌላኛዋ ወይዘሮ እማዋይ ዳምጤም በሞዠን ጤና ጣቢያ ለመገኘቷ ምክንያቱ ነፍሰጡር መሆኗን ማወቋ ነው። እማዋይ ክትትሏን ለማካሄድ በጠዋቱ መጀመር እንደሚበጅ ገብቷታል። ውጤቷም የሁለት ወር ነፍሰጡር መሆኗን አመላክቷል። ወይዘሮዋ በከዚህ ቀደሙ እርግዝናዋም የምርመራ ልምድ እንደነበራት ትናገራለች።
እማዋይ አሁን በጀመረችው የእርግዝና ክትትል ይበልጥ ተጠቅማለች። ውስጧን የሚረብሽ ህመም ቢጤ ሲሰማት ያለምንም ቀጠሮ የመምጣት ዕድሉን አግኝታለች። ከአርሶ አደሩ ባለቤቷ ጋር ተማክራ ሁለተኛውን ልጇን ስታረግዝም በሙሉ ፍላጎትና ስምምነት ነበር። ለዚህ እውነት ደግሞ የጤና ባለሙያዎቹ ድጋፍና ሙያዊ ምክር ይበልጥ አግዟታል።
እሷን መሰል ሴቶች ከማርገዛቸው በፊትና በኋላ ማድረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄ ባለሙያዎቹ ቤት ለቤት እየዞሩ ትምህርት ይሰጣሉ። እናቶችም በጤና ጣቢያው በሚያደርጉት ቆይታ ስለህጻናት ክትባትና ጤናማ አስተዳደግ በጥልቀት ይወያያሉ። ይህ መሆኑ እማዋይን ለበለጠ እቅድ አዘጋጅቶ፤ ስለወደፊቱ በጎነት እንድታልም አስችሏታል። ነገን አርቃ የምታስበው ወይዘሮ ዛሬ ከትናንት የተሻለ መሆኑንም አረጋግጣለች።
ሲስተር ሃይማኖት በላይ በሸበል በረንታ ወረዳ የሞዠን ጤና አጠባበቅ ጣቢያ አዋላጅ ባለሙያ ናት። እሷና መሰሎቿ ዘወትር በሚንቀሳቀሱባቸው አራት ቀበሌዎች ነፍሰጡርን በማወያየት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሃላፊነት ይወጣሉ። እንደ ሃይማኖት አባባል፤ እነዚህን እናቶች የጤና ጣቢያው ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረታቸውን የሚጀምሩት በየመንደሩ ከሚያደርጉት የየቀን አሰሳ ነው። ሁሌም ቤት ለቤት በሚደረገው ፍለጋ ያገኟቸውን ነፍሰጡሮች ወደ ማዕከሉ በማምጣት የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ያከናውናሉ።
እናቶችን በጤና ክትትሉ ተሳታፊ ለማድረግ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ተሳትፎ የላቀ ነው። በከፍተኛ ጥረት መተግበር በጀመረው ሂደትም እናቶችንና ጨቅላ ህጻናትን ከሞትና ከከፋ ጉዳት መታደግ ተችሏል። አሁን በሞዠንና ዙሪያ ገባው ቀበሌዎች በቤት ውስጥ መውለድ እንደነውር ይቆጠራል። የእርግዝና ወቅት የጤና ክትትልም እንደ ባህል መለመድ ጀምሯል።
አቶ የሺጥላ ጌትነት የሞዠን ጤና ጣቢያ ሃላፊ ናቸው። በእሳቸው ሃላፊነት የሚመራው ጤና ጣቢያ በእናቶችና ህጻናት ጤና ላይ ያስመዘገበው ውጤት ከፍተኛ ስለመሆኑ ይናገራሉ። ለተመዘገበው ፍሬያማ ውጤት ምክንያቱ በየጤና ኬላው ያለው የዕለት ከዕለት ጥረትና ጠንካራ ተሳትፎ መሆኑን ይገልጻሉ። ለዚህ ደግሞ የሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች አስተዋጽኦ ላቅ ያለ ስፍራ ይሰጠዋል።
በአራቱ ቀበሌዎች በሚደረገው የእናቶች ክትትል በተደራጀና በጤና ኤክስቴንሽን በተዋቀረ ቡድን አስፈላጊውን ሁሉ መከወን የተለመደ ነው። ቅርብ ያልሆኑትንና በረሀ አካባቢ የሚገኙትን እናቶች ተደራሽ ለማድረግም ከመውለዳቸው አስቀድሞ በተዘጋጀላቸው ማረፊያ እንዲቆዩ ይደረጋል።
እናቶች በማረፊያ ክፍሉ ቆይታቸው ስፍራውን ልክ እንደቤታቸው እንዲቆጥሩት ለማድረግም ከምግብ አቅርቦት እስከ ማህበራዊ አንድነት የሚኖረው ትስስር የጠበቀ ነው። አራስዋ በስፍራው ስትገኝ ለህክምና ብቻ አለመሆኑን የሚያመላክቱ እውነታዎች መተግበራቸውም የተለመደ ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ ሁሌም የእናቲቱን ጉዞ ከቤት ወደ ቤት ያደርገዋል።
በጤና ጣቢያው የወለደች እናት ከሃያ አራት ሰአት በፊት ወደቤቷ መመለስ እንደሌለባት በአብዛኛው ማህበረሰብ ዘንድ ይታወቃል። ይህን ዓይነቱን ጥረት ለማሳካትም የጤና ባለሙያው ተሳትፎ በተለየ ትጋት የተሞላ ነው። ዛሬም ሆነ ወደፊት የእናቶችንና የህጻናትን ደህንነት ለመጠበቅ የሚደረገው ተሳትፎ እንደማይቋረጥ ሃላፊው ያረጋግጣሉ። ለዚህም የአካባቢውን ጥንካሬና መተማመን በእማኝነት ይጠቅሳሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2011