የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚቋቋሙባቸው ዋነኛ ዓላማዎች አንዱ የጥናትና ምርምር ስራዎችን መስራትና የማኅበረሰብ አገልግሎት ተግባራትን ማከናወን (Research and Community Service) ነው፡፡ ይህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተግባርም በተቋማቱ በየጊዜው የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች በተግባር ተመንዝረው ለኅብረተሰቡ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የሚችል ፋይዳ እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡
በኢትዮጵያ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያከናወኑና የማህበረሰብ አገልግሎትን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ ተቋማቱ ከሚያከናውኗቸው የጥናትና ምርምር እንዲሁም የማኅበረሰብ አገልግሎት ተግባራት መካከል ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በትብብር የሚያከናውኗቸው ስራዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ሚኒስቴሩ በጀት መድቦ ከተቋማቱ ጋር በትብብር ከሚሰራቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች መካከል ጥቂቶቹ ወደ ተግባር ተሸጋግረው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በሰሜን ሸዋ ዞን፣ ኤፍራታና ግድም ወረዳ ይምሎ ቀበሌ አስተዳደር ያከናወነው የተቀናጀ የዓሳና የዶሮ እርባታ፤ እንዲሁም የማዳበሪያ ዝግጅትና የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክት የዚህ ማሳያ ነው፡፡
ይህ ፕሮጀክት በአነስተኛ መሬት ላይ የዓሳና የዶሮ እርባታ፤ እንዲሁም የማዳበሪያ ዝግጅትና የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የሚከናወንበት፤ በቴክኖሎጂ የታገዘ የተቀናጀ የግብርና ስራ ነው፡፡ የፕሮጀከቱ መሪ ተመራማሪ ዶክተር ገዛኸኝ ደግፌ እንደሚሉት፤ ፕሮጀክቱ የዓሳና የዶሮ እርባታን ጨምሮ የማዳበሪያ ዝግጅት የሚከናወንበትና በትንሽ መሬት ትልቅ ውጤት የሚያስገኝ ስራ በመሆኑ ማኅበረሰባዊ ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በዘልማድ ሲሰራ የቆየው ስራ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ተመጋጋቢ የሆኑ የግብርና ስራዎችን በአንድ ላይ አስተሳስሮ በአጭር ጊዜ ውጤት የሚገኝበት ጥምር ተግባር ነው፡፡
በዓሳና በዶሮ እርባታ ሂደት ከሚያጋጥሙ ችግሮች መካከል አንዱ የዓሳና የዶሮ መኖ ዋጋው ውድ መሆን ነው፡፡ በዚህ የተቀናጀ የዓሳና የዶሮ እርባታ መርሃ ግብር አንዱ ከሌላው ተጠቃሚ በመሆኑ ችግሩን ለማቃለል ያግዛል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ከሚከናወኑ ተግባራት አንዱ የማዳበሪያ ምርት ነው፡፡ ዶክተር ገዛኸኝ ስለ ማዳበሪያው ሲገልፁም፤ ‹‹ከየአካባቢው የተሰበሰበ ቆሻሻ ለትሎች ተሰጥቶ ትሎቹ ቆሻሻውን በመብላት ወደ ማዳበሪያነት ይቀይሩታል፡፡ ይህ ቨርሚኮምፖስት በመባል የሚታወቀው ማዳበሪያ በዓለም ላይ በአልሚነታቸው ከታወቁ የተፈጥሮ ማዳበሪያዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ የማዳበሪያው ኬሚካዊ ይዘት በቤተ-ሙከራ ሲለካ ከሌሎቹ ማዳበሪያዎች ሁሉ የተሻለ ነው›› ይላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፤ ውሃ የመያዝ አቅሙም በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ማዳበሪያው አንድ ጊዜ መሬት ላይ ከተደፋ በኋላ ለረጅም ጊዜ ማዕድናቱን እንደያዘ ይቆያል፡፡ ቨርሚኮምፖስትን በመጠቀም የሚተከሉ አትክልት ከሌሎቹ ፈጥነው ያድጋሉ፡፡ የይምሎ ቀበሌ አርሶ አደሮችም ማዳበሪያውን መጠቀም እየጀመሩ እንደሆነም መሪ ተመራማሪው ይናገራሉ፡፡
መሐመድ ሸህ አሊ የ‹‹ኅብረት በአንድ የይምሎ ወጣቶች የዶሮና ዓሳ እርባታ ማኅበር›› አባልና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በትብብር ባከናወኑት ፕሮጀክት ተጠቃሚ የሆነ ወጣት ነው፡፡ ማኅበሩ አምስት አባላት ያሉት ሲሆን፤ ሁለቱ ከስደት (ሳዑዲ አረቢያ) የተመለሱ ናቸው፡፡
መሐመድ ለሦስት ዓመታት ያህል በስደት እንደቆየና አስተማማኝ የሆነ የኑሮ መሰረት እንዳልነበረው ያስታውሳል፡፡ በመስከረም ወር 2010 ዓ.ም እርሱና አራት ጓደኞቹ በፕሮጀክቱ ታቅፈው ስራውን ከጀመሩ ወዲህ ግን ‹‹እንዲህ መሆኑን ብናውቅ ለስደት አንዳረግም ነበር›› ያስባላቸውን ለውጥ ማየታቸውን ይናገራል፡፡
‹‹በትንሽ መሬት ላይ ዶሮና አሳ እናረባለን፤ አትክልትና ፍራፍሬ እናለማለን፤ ማዳበሪያም እናመርታለን፡፡ የእንቁላል ዶሮዎችን አርብተን በሁለት ዙር ለገበያ ካቀረብነው እንቁላል ካገኘነው ገቢ በማኅበራችን የባንክ አካውንት ከ41ሺ ብር በላይ ቆጥበናል፡፡ የገበያ ችግር የለብንም። ብድርም ከማኅበሩ መውሰድ እንችላለን›› ይላል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፤ ሁለት ጊዜያት የአርሶ አደር መድረኮችን በማዘጋጀት ቀደም ሲል ዶሮም ሆነ ዓሳ ለማርባትና ለመጠቀም ብዙም ፍላጎት ላልነበረው የአካባቢው ሕዝብ ግንዛቤ በመፍጠር ለውጥ እንዳመጡም ያስረዳል፡፡ ለምሳሌ ያህልም ቀደም ሲል ሁለት ወይም ሦስት ዶሮዎችን ብቻ ገዝተው የማርባት ልምድ ከነበራቸው አርሶ አደሮች መካከል ዛሬ አንዳንዶቹ እስከ 300 ዶሮዎች ገዝተው እያረቡ እንደሆነ በመጥቀስ፤
የይምሎ ቀበሌ የእንስሳት እርባታ ባለሙያው መስፍን ጸጋዬ ወጣቶቹ ስላገኙት ውጤት ምስክርነቱን ይሰጣል፡፡ ፕሮጀክቱ የተቀናጀና ሁሉን አቀፍ የግብርና ስራ የሚከናወንበት በመሆኑ ወጣቶቹን ተጠቃሚ ማድረግ እንደቻለ የሚናገረው መስፍን፣ ‹‹የማኅበሩ አባላት እያከናወኑት ያለው ተግባር ለአካባቢው አርሶ አደሮች መነቃቃትን በመፍጠሩ አሁን አሁን ብዙ ዶሮዎችን እያረቡ ያሉ አርሶ አደሮች ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አርሶ አደሮቹ ለስራው የሚያስፈልግ ቦታ እንድንመርጥላቸውና ሙያዊ የምክር አገልግሎት እንድንሰጣቸው እየጠየቁን ነው›› በማለት ፕሮጀክቱ ከማኅበሩ አባላት አልፎ በአካባቢው ኅብረተሰብ ዘንድ በጎ ውጤት እያስገኘ ስለመሆኑ ያብራራል፡፡
የማኅበሩ አባላት አሁን ባገኙት ውጤት ተወስነው የመቀመጥ ፍላጎት የላቸውም፡፡ መሐመድ እንደሚለው፤ በቀጣይ ጊዜያት ስራቸውን በማስፋት ከዚህ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ‹‹ምስጋና ድጋፍ ላደረጉልን አካላት ይሁንና ስራችን ከዚህ ለተሻለ ትጋትና ስኬት አነሳስቶናል፡፡ እኛ በሕይወታችን ላይ ያየነው ለውጥ ለሌላውም እንዲዳረስ የአካባቢው አርሶ አደሮች ቨርሚኮምፖስት ተጠቅመው ምርታቸውን እንዲያሻሽሉ ለማሳየት እቅድ አለን›› በማለት ማኅበራቸው ከአባላቱ በተጨማሪ የአካባቢው ኅብረተሰብም ተጠቃሚ እንዲሆን የሰነቀውን ዓላማ ያስረዳል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር ከሚያከናውናቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች መካከል ወደ ተግባር ተቀይረው ማኅበረሰባዊ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ፕሮጀክቶች ቁጥራቸው ጥቂት መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ፤ ሚኒስቴሩ ባለፉት አራት ዓመታት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ ከ60 በላይ ለሚሆኑ የዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ስራዎች ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው ተጠናቅቀው ወደተግባር የገቡት ግን ጥቂት እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡
እንደርሳቸው ገለፃ፣ በሚኒስቴሩ ድጋፍ ከተከናወኑት ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው የይምሎ ቀበሌ የተቀናጀ የዓሳና የዶሮ እርባታ፤ እንዲሁም የማዳበሪያ ዝግጅትና የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክት በትንሽ ሀብትና በአጭር ጊዜ ውጤት ማምጣት የሚችል ስራ በመሆኑ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ተግባር ነው፡፡ ፕሮጀክቱ አርሶ አደሮች በጓራቸው ከዶሮ፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በተጨማሪ ዓሳ በማርባት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ስለሚያደርግ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ያግዛል፡፡
ፕሮጀክቱን ወደሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት የሚያስችል የአሰራር መመሪያ ስለተዘጋጀ በቀጣይ ጊዜያት ስራው በሌሎች ክልሎች እንደሚተገበርም ጠቁመው፤ የአማራ ክልልም በይምሎ ቀበሌ አስተዳደር የተገኘውን መልካም ተሞክሮ በመቀመር የተቀናጀ የዓሳና የዶሮ እርባታ፤ እንዲሁም የማዳበሪያ ዝግጅትና የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክቱን በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ማስፋት እንዳለበትም ያስገነዝባሉ፡፡
በአጠቃላይ በሚኒስቴሩና በዩኒቨርሲቲዎች ትብብር የሚከናወኑት የምርምር ሥራዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከተቋቋሙባቸው ዓላማዎች መካከል አንዱን የሚያሳኩ በመሆናቸው የኅብረተሰቡን ኑሮ በዘላቂነት እንዲለውጡ ታሳቢ ተደርገው ሊከናወኑ እንደሚገባም ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን ያሳስባሉ፡፡
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝደንት ዶክተር አልማዝ አፈራ መሰል ፕሮጀክቶች ለወጣቶች የሥራ እድል እንደሚፈጥሩና ፕሮጀክቱም ተጨማሪ ተግባራትን ለማከናወን ልምድ የተገኘበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ወደ ተግባር የሚቀየሩ ብዙ የምርምር ስራዎች እንዳሉትና ይህን የተቀናጀ የዓሳና የዶሮ እርባታ፤ እንዲሁም የማዳበሪያ ዝግጅትና የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክት ወደሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት በትኩረት መስራት እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያከናው ኗቸው ጥናቶችና ምርምሮች ወደ ተግባር ተቀይረው በኅብረተሰቡ ኑሮ ላይ ተጨባጭና አወንታዊ ለውጥ እንዲያመጡ ከተፈለገ በጀት መመደብ ብቻ ሳይሆን ምርምሮቹን ለሚያከናወኑ አካላት ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2011
በአንተነህ ቸሬ