የፌዴሬሽን ምክር ቤት በህገ መንግስቱ በክልሎች መካከል የሚፈጠር የወሰን አለመግባባት ለመፍታት፤ በህዝቦች የሚቀርቡ የማንነት ጥያቄዎችን መፍትሄ ለመስጠት፣ የሰላም ዕጦትን የመፍታት፤ የህገ መንግስት አስተምህሮና ሌሎች ተዛማጅ ሃላፊነቶች ተሰጥተውታል። ይሁን እንጂ፤ የተሰጡትን ሃላፊነቶች በተገቢው ደረጃ የመወጣት ችግር እንዳለበት ተደጋግሞ ይነሳል። በዚህም የተነሳ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ችግሮች መፈጠራቸውን ተንተርሶ በብዙዎች ዘንድ ይወቀሳል። በእነዚህ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ የህገ መንግስት አስተምህሮና የሰብዓዊ መብት ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፍረወይኒ ገብረእግዚአብሔርን ቃለ መጠይቅ አድርገንላቸዋል። እንደሚከተለውም አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ ያለውን የሰላም ችግር ለመፍታት ቋሚ ኮሚቴያችሁ ምን እየሰራ ነው?
ወይዘሮ ፍረወይኒ፡- ቋሚ ኮሚቴያችን ከስያሜው ጀምሮ ዴሞክራሲዊ አንድነት፤ የሰላም ግንባታ እና የህገ መንግስት አስተምህሮ እንደሚሰራ ነው የሚያሳየው፤ እነዚህ ስራዎች ተያያዥነት ያላቸው ናቸው። ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ለመፍጠር፤ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና ህገ መንግስቱን ለማስተዋወቅ በቋሚ ኮሚቴያችን ትልቅ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው።
ስራችንን እያከናወንን ያለነውም የህዳር 29ን በዓል በዋናነት ግንዛቤ ለመፍጠር በመጠቀም ነው። በየዓመቱ በዓሉን በመጠቀም ግንዛቤ የሚፈጥሩና የሚያሳድጉ ስራዎችን እንሰራለን። የተለያዩ ጽሁፎች በምሁራንና በፖለቲካ መሪዎች እየተዘጋጁ ለህብረተሰቡና ለምክር ቤት ይደርሳሉ። መቶ ሚሊዮን ህዝብ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ማስተማር ስለማይቻል ፤ በፎረሞችና በተለያየ አደረጃጀቶችም በኩል ህገ መንግስቱን ለህብረተሰቡ የማስተዋወቅ ስራ እናከናውናለን። በእነዚህ አደረጃጃቶችም የአሰልጣኞች ስልጠና በመስጠት ወደ ህዝቡ ተደራሽ የማድረግ ስራም እየሰራን ነው። ከዚህም በተጨማሪ፤ የህገ መንግስት አስተምህሮ በዴሞክራሲ ተቋማት በኩል ተደራሽ እንዲሆን እናደርጋለን። እንዲያም ሆኖ ግን፤ ህገ መንግስቱን በህዝብ የማስረጽ ክፍተት እንዳለ እያየን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ህገ መንግስቱን በህዝብ ውስጥ ማስረጽ ካልቻላችሁ ታዲያ ምንና እንዴት ለመስራት አቅዳችኋል?
ወይዘሮ ፍረወይኒ፡- ይህን ችግር ለመፍታት የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የትምህርት ዘርፍ እና ሌሎች ባለድርሻ ተቋማት የተሳተፉበት የህገ መንግስት አስተምህሮ ስልት ተቀይሷል። ስልቱንም ተግባራዊ ለማድረግ አስተምህሮቱን የሚመራና የሚያከናውን ተቋም እንዲቋቋም ለማድረግ አዋጅ ተዘጋጅቶ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩል ለእንደራሴዎች ምክር ቤት እንዲጸድቅ ገብቷል። በመሆኑም ይህ ችግር በቅርብ ጊዜ ይፈታል የሚል እምነት አለኝ። ይህ ሲሆን ለዴሞክራሲና ለሰላም ግንባታ ትልቅ ሚና ይኖረዋል።
አዲስ ዘመን፡- የህገ መንግስት አስተምህሮ ተቋም ምን ምን ጉዳዮችን ይሰራል?
ወይዘሮ ፍረወይኒ፡- ተቋሙ በማዕከል ደረጃ ትልቅ ሆኖ እንዲቋቋም ነው የተፈለገው፤ በውስጡ የተለያዩ የልህቀት ማዕክል ይኖሩታል። የትምህርት ሚኒስቴር አንዱና ዋናው ተዋናይ ነው። ምክንያቱም ሩብ ሚሊዮን የሚሆኑት ዜጎች ያሉት በትምህር ቤት ነው። በስነ ምግባርና ስነዜጋ ትምህርት ለእነዚህ ዜጎች ስለህገ መንግስቱ ማስተማርና ማስረጽ ይገባል። የስነ ዜጋ ትምህርትም ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተሻሻለ ነው። የዴሞክራሲ ተቋማት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና እንባ ጠባቂ ተቋም ናቸው። ምክር ቤቶች እና የሚዲያ ተቋማት ህገ መንግስቱን በማስረጽ ረገድ ሰፊ ስራ ያከናውናሉ። የሲቪክና የሙያ ማህበራት መብታቸውና ግዴታቸውን እንዲከበር ይሰራል። የጸጥታና የፍትህ ተቋማትም ህጉን ለማክበርና ለማስከበር ትልቅ ስራ ያከናውናሉ። እነዚህንና ሌሎች ተቋማትን አደራጅቶ በመስራት የልህቀት ማዕከል በመሆን ሰፊ ተግባር ይሰራል። በአጠቃላይ ህገ መንግስቱን የማወቅና የማሳወቅ ስራ ያከናውናል። ህገ መንግስቱን ከማስረጽ ባለፈም በአገሪቱ ሰላምና ጸጥታ እንዲሰፍንም ይሰራል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ከሚታየው ችግር አንፃር በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት አለ?
ወይዘሮ ፍረወይኒ፡- ዴሞክራሲያዊ አንድነት በብዙ መንገድ ሊገለጽ ይችላል። ለአንድነታችን ችግር የሆነ የብሄር ብሄረሰቦች ጭቆናና ማንነት ያለማግኘት ችግር ነበር። ይህ መፍትሄ አግኝቷል። ዛሬ ሁሉም ብሄሮችና ብሄረሰቦች ማንነታቸውና እኩልነታቸው እውቅና አግኝቷል። እስካሁን 76 ብሄር ብሔረሰቦች በፌዴሬሽን ምክር ቤት ተመዝግበዋል። እነዚህ ሁሉ ብሄራዊ ማንነታቸው ታውቆላቸዋል ማለት ነው። ይህ ማለት ግን፤ ሌሎች ጥያቄዎች የሉም ማለት አይደለም። ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ያልመጡ ተሟጥጠው ያልተፈቱ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ።
ከዚህም በላይ፤ ብሄር ብሄረሰቦች ማንነት ማግኘት ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ፤ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን እንዲያሳድጉ ተደርጓል። ማንነታቸውን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲገልጹና እንዲያስተዋውቁ ዕድል ተፈጥሯል። አንዱ ብሄር የራሱን ከማሳወቅ ጎን ለጎን የሌሎችንም እንዲያውቅና አክብሮ እንዲኖር የሚያስችሉ ስራዎችን ሰርተናል።
ሌላው፤ የዴሞክራሲያዊ አንድነት መገለጫው ህዝቦች በየደረጃው ውክልና ማግኘታቸው ነው። ምክር ቤቶች የህዝቦች ፍላጎት የሚገለጽባቸው ናቸው። በፌዴሬሽን ምክር ቤት እንኳን ብናይ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች እኩል ውክልና ከማግኘታቸው በተጨማሪ በአንድ ሚሊዮን ህዝብ ተጨማሪ አንድ ተወካይ አላቸው። በዚህም ምክር ቤቱ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ፍላጎት የሚንጸባረቅበትና ውሳኔ የሚያልፍበት ነው ማለት ይቻላል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በተመሳሳይ በህጉና በሥርዓቱ መሰረት ይወከላሉ። የክልል ምክር ቤቶችም በተመሳሳይ ሁኔታ ተደራጅተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ክልሎች ርስ በርሳቸው የሚደጋገፉበትና የሚተዋወቁበት ሥርዓት ተቀይሷል። በተመሳሳይ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር የጋራ የምክክር መድረክ አላቸው። በቅርብ ጊዜ በመቀሌ አንድ የምክክር መድረክ እናካሂዳለን። ከዚህ በፊት ብዙ ምክክሮች አካሂደናል። በመሆኑም ክልሎች ልምዳቸውን የሚለዋወጡበትና ችግሮቻቸውንም የሚወያዩበት ሥርዓት አለ።
አዲስ ዘመን፡- እነዚህ የዘረዘሯቸው ተቋማትና ስራዎች በኢትዮጵያ ለምን ዴሞክራሲያዊ አንድነትን አላመጡም?
ወይዘሮ ፍረወይኒ፡- ስራዎቹ ጉድለት የለባቸውም ማለት አይደለም። ጉድለቶችን ለማረም የፌዴራልና የክልል መንግስታት ህጋዊ አሰራር እንዲኖራቸው፤ ግንኙነታቸውም የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረው ለማድረግ አዋጅ ተዘጋጅቶ ወደሚኒስትሮች ምክር ቤት ተልኳል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከተመለከተው በኋላ ለእንደራሴዎች ምክር ቤት ቀርቦ ይጸድቃል የሚል እምነት አለኝ። ይህ ዴሞክራሲያዊ አንድነታችንን ቀጣይነት ባለው አግባብ ሊያጎለብትልን የሚችል ነው።
የህግ ማዕቀፉ አንዱ ክልል ከሌላው ጋር ያለውን ችግር ቁጭ ብሎ ሊወያይ የሚያስችል ሥርዓት ይዘረጋል። የክልሎች፣ የህግ አውጭዎች፣ የህግ አስፈፃሚዎች፣ የህግ ተርጓሚዎች እና የዘርፍ ተቋማት መድረኮችን በመፍጠር ዴሞክራሲያዊ አንድነታችንን ያጠነክራሉ። ችግሮች ሲፈጠሩ በእንጭጩ ለመፍታትም ያስችላል። ጥሩ ተሞክሮዎቻችን እያጎለበትን፤ አንዱ አንዱን ረግጦ ማለፍ ሳይሆን ርስ በርስ ተደጋግፎ ለመሄድ ያስችላል። አዋሳኝ ክልሎች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች የጋራ ፕሮጀክቶቻችውን በጋራ ይፈጽማሉ። ተመሳሳይ ተቋማት አብሮ ለመጠቀም የሚያስችል አካሄድ ይፈጥራል። የጋራ ችግሮቻቸውን በጋራ የሚፈቱበት ሥርዓት ይዘረጋል።
በአጠቃላይ አሁን ላይ የድርጅቶች ፖለቲካዊ ግንኙነትና የመንግስታት ግንኙነት በሚፈለገው ደረጃ እንዳልሆነ እያየን ነው። መልካም እሴቶችን ለማጠናከር ይሰራል። በአንዳንድ አካባቢዎች በተወሰኑ ልሂቃንና ቡድኖች አነሳሽነት ጫናና የሰዎች ማፈናቀል ይታያል። ይህን አስተሳሰብ በመግዛትም በተወሰኑ ዜጎች የመቃቃር ሁኔታ ይታያል። እነዚህን ዴሞክራሲያዊ አንድነታችንን የሚሸረሽሩ አስተሳሰቦችን ለማስታረቅ ፖለቲካ ከባቢውን ማስተካከል ያስፈልጋል። ይህ ሲስተካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ትናንት የነበረ ዛሬም ያለ ወደፊትም የሚቀጥል ስለሆነ አብሮነቱ ይስተካከላል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን በአገሪቱ ያለው መቃቃር የተፈጠረው በፖለቲካ ልሂቃንና የተወሰኑ ዜጎች ብቻ ነው? የህዝቡ መጠላላትና መጠላለፍስ? መገፋፋቱና መገዳደሉስ?
ወይዘሮ ፍረወይኒ፡- ችግር ያለበት ልሂቅ ሄዶ የሚወሸቀው ብሄሩ ውስጥ ነው። እንደዚህ አይነት አካሄዶች ናቸው በህዝብ ውስጥ መቃቃር የፈጠሩት፤ በማህበረሰቡ ዘንድ ችግር አለመኖሩን የምታየው በአንድ ብሄረሰብ አባላት ላይ ችግር ሲፈጠር የአካባቢው ህብረተሰብ ‹‹በመጀመሪያ በእኔ ልጅ ላይ ጉዳት አድርሰህ ነው ከዚያ በኋላ እርሱን የምትጎዳው›› ይላል። ይሄ ማለት እሱን ከምትጎዳው እኔን ጉዳኝ የሚል ነው። ይህ ጥሩ እሴታችን በህዝቡ መካከል ጠንካራ ግንኙነት መኖሩን የሚያመለክት ነው። ይህን ሚዛን አስይዞ መሄድ ይገባል። እንደዚህ አይነት ችግር በሁሉም አካባቢ የለም። ህዝብ አብሮ የኖረ፤ የተዋለደ እና ብዙ ነገር አብሮ ያሳለፈ ነው።
ችግሩ ያለው በልሂቃን መካከል ነው። የልሂቃኑን ችግር ስንፈታ የተሳሳተ አመለካከት ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ካሉ ችግሩ ይፈታል የሚል እምነት አለኝ። በማህበረሰቡ ውስጥ በአንዳንዶች ዘንድ አሁንም በጎ ያልሆነ አመለካከት ግን አይኖርም ብለን አንወስድም። ልሂቃኑ ሲስተካከሉ ግን ማህበረሰቡም ወደ ቀልቡ ይመለሳል። ምክንያቱም ማህበረሰቡ የተዋለደ፣ የተጋመደ፣ የተዛመደ ስለሆነ የማይለያይና የማይበጣጠስ ነው። ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ጫፍ አብሮ የኖረና ሊለያይ የማይችል ነው። ስለዚህ ችግር የሚፈጥሩ ልሂቃንን እያስተካክልን በሄድን ቁጥር ሁሉም ችግሮች እየተፈቱ ይሄዳሉ። ታዲያ፤ የተወሰኑ ጫፍ የወጣ አመላካከት ያላቸው ሰዎች አይኖሩም ግን አይባልም። አብዛኛው ማህበረሰብ ግን በአብሮነት የሚያምን ነው። እየተጎዳና ችግር እየደረሰበትም ጭምር የእኔ ወንድም የሚል ህዝብ ነው።
እኛ መድረኮች ፈጥረን ስናወያይ ማህበረሰቡ የሚያነሳው ይህንን ነው። በጌዲዮና በጉጂ መካከል ያለውን ማህበረሰብና አባገዳዎች ስናወያይ መለያየት እንዳማይችሉና የጋራ የግጭት አፈታት ስልት ጭምር እንዳላቸው ነው የሚያወሩት፤ ችግር የፈጠረው ማነው ስትል ሄዶ ሄዶ የሚያርፍው ውስን ልሂቃን ላይ ነው። በሁሉም አካባቢዎች ተመሳሳይ ችግር ነው የሚያነሱት፤ በተወሰኑ ሊህቃን የተሳሳቱ አይኖሩም ማለት ባይቻልም፤ ማህበረሰቡ ግን ያለው በአንድነት ነው። እናም ልሂቃኑ ሲስተካከሉ የተሳሳቱት ይታረማሉ የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለመሆኑ የተሰጣችሁን ሰላም የማስፈንና የህገ መንግስት አስተምህሮ ሃላፊነት በትክክል ተግባራዊ አድርጋችኋል?
ወይዘሮ ፍረወይኒ፡- በክልሎች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ያለው ግንኙነት እንዲስተካከልና የተፈጠሩ ግጭቶች እንዲፈቱ ሰርተናል፤ እየሰራንም ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች በተለያዩ ሁኔታዎች ምክንያት በሚፈለገው መጠን ማካሄድ ባንችልም፤ በርካታ ስብሳባዎችን አካሂደናል። ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓታቸውን ተጠቅመው ግጭቶቻቸ ውን እንዲፈቱ ለማድረግ ተሰርቷል። ምክር ቤቱም የክልሎችን የባህላዊ የግጭት አፈታት ስልት ለመቀመር እየሰራ ነው። ከዚህ በተጨማሪ፤ ግጭት ከመፈጠሩ በፊት ለመከላከል የሚስችል ጥናት እያደረግን ነው። ተጋላጭነትም ለመተንተን እየተሰራ ሲሆን፤ በዚህም ላይ ውይይት አድርገን ለመፍታት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን እየሰራን ነው። እነዚህ ዴሞክራሲ አንድነታችንን የሚያጠናክሩ አንኳር አንኳር ጉዳዮችን እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- አንዱ ለግጭት መንስዔ እየሆነ ያለው የፌዴሬሽን ምክር ቤትና ክልሎች ከማንነት ጋር ያሉ ጥያቄዎችን በአግባቡ ያለመመለሳቸው ጉዳይ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ምን እየሰራችሁ ነው?
ወይዘሮ ፍረወይኒ፡- ይህ ጉዳይ የራሱ ቋሚ ኮሚቴ አለው። ጥልቅ መረጃ ከዚያ ማግኘት ይቻላል። ሌሎች የግጭት መንስኤ የሚሆኑ ጉዳዮች ቢኖሩም የማንነት ጉዳዮች የግጭት መንስዔዎች ናቸው የሚለው ትክክል ነው። እነዚህንም ለማስተናገድ ምክር ቤቱ በህገ መንግስቱና በአዋጅ የተሰጠውን ሃላፊነት እየተወጣ ነው። በህጉ መሰረት የማንነት ጉዳዮች በመጀመሪያ በክልል ምክር ቤቶች በየደረጃው ምላሽ እየተሰጣቸው መምጣት አለባቸው። በክልል ምክር ቤቶች ምላሽ ካልረኩ ወይም በሁለት ዓመት ውስጥ ምላሽ ካላገኙ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መምጣት ይችላሉ። በዚህ ሂደት አልፈው መልስ ያላገኙ የሉም።
አዲስ ዘመን፡- የሰላም የታጣውና ዴሞክራሲዊ አንድነት የጠፋው ፌዴሬሽን ምክር ቤት የማንነትን ጥያቄ ባለመመለሱ ነው የሚሉ ሰዎች አሉ። የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?
ወይዘሮ ፍረወይኒ፡- እኛ እንደዚያ አይነት ግምገማ የለንም። ይህ የሚመነጨው በአንድ በኩል ከግንዛቤ ማነስ ነው። በክልል ምክር ቤት ሳይቀርብ በቀጥታ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚቀርብ ጉዳይ/አቤቱታ አለ። ይህንን ግንዛቤ አስይዘን ወደ ክልል የምንመልስበት ሁኔታ አለ። አንዳንድ ምክር ቤቶች ደግሞ በቶሎ ምላሽ ያልሰጡ አሉ። እነዚህ አቤቱታዎች ጊዜውን ጠብቀው ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አልመጡም። ከክልል ምክር ቤቶች ጋር በተደረገ አንድ የጥናት መድረክ ለረጅም ጊዜ ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጣቸው ከክልሎች ጋር የጋራ መግባባት ተደርሷል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ ካልሰጡ ግን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገብቶ ምላሽ እንደሚሰጥ ተገልጿል። በአጠቃላይ ግን ህጋዊ አሰራሩን ጠብቀው የመጡና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያልመለሳቸው የማንነነት ጥያቄዎች የሉም።
አዲስ ዘመን፡- ከአስተዳደራዊ ወሰን ጋር በተያያዘ አገሪቱን ሊበትን የሚችል ችግር እንዳለ ነው የሚታየው፤ ይህን የመፍታት ሃላፊነታችሁን በምን ደረጃ እየተወጣችሁ ነው?
ወይዘሮ ፍረወይኒ፡- በሁለት ክልሎች መካከል አለመግባባት ካለ በመጀመሪያ ሁለቱ ክልሎች ቁጭ ብለው የሚፈቱበት ሥርዓት አለ። ሁለቱም ክልሎች መፍታት ካልቻሉ፤ ሁለቱም ወይም ከሁለቱ አንዱ መፍታት አለመቻላቸውን ጠቅሶ ጥያቄ ሲያቀርቡ/ብ ነው ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩን ለማየት የሚገባው፤ አሁን ባለው ሁኔታ ክልሎች ከአቅማችን በላይ ነው ብለው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያስገቡት ጥያቄ የለም። ከዚህም ጋር ተያይዞ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ ያለ፤ በክልል ምክር ቤቶች መታየት የሚገባው ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ይመጣል። ይህም የግንዛቤ ችግር ነው። ሲመጡም ማብራሪያ እየሰጠን መልሰናል። በዚሀ ረገድ ቀደም ሲል የመጣው የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል ጉዳይ ነው። እሱም በአስፈፃሚው እንዲታይና እንዲፈታ ተሰማምተ ዋል። ምክር ቤቱም የተደረገውን የመግባባቢያ ስምምነት አይቶ እውቅና ሰጥቷል። ከዚህ ውጭ ግን በህጉ መሰረት የመጣ የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ/አቤቱታ የለም። ከግንዛቤ አንፃር የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ስልጣንና ሀላፊነት ካለማወቅ ነው። ይህ የእኛ ግንዛቤ ያለማስጨበጥ ችግር ነው። በቀጣይ ይህንን ችግር በማስተማር እንፈታዋለን።
አዲስ ዘመን፡- አንዱ ስራችሁ ግጭቶች ከመፈጠራቸው በፊት መከላከል ነውና አቤቱታ ሲደርሳችሁ በህጉ መሰረት ሂደቱን ጠብቆ አልመጣም ብላችሁ ዝም ነው የምትሉት?
ወይዘሮ ፍረወይኒ፡- የሰላም ኮንፍረንስ የምናካሂደው በማህበረሰቡ ውስጥ ያለው ችግር እንዲፈታ ነው። ህብረተሰቡ ውስጥ ዛሬ ያልፈነዱ፤ ነገር ግን ነገ ሊፈነዱ የሚችሉ ችግሮች ወጥተው እንዲፈቱ ነው ኮንፍረንስ የምናካሂደው፤ ህዝብ ከተቀራረበ ራሱ ለችግሩ መፍትሄ ያስቀምጣል። የምናወያየው እነዚህን እምቅ ችግሮች ለመፍታት ነው። በዩኒቨርሲቲዎችም ትምህርት እንሰጣለን። ይህን የምናደርገው የዜጎች መብት መጠበቅ አለበት ከሚል መነሻ ነው። በሃላፊነታችን ሳንገደብ ከሌሎች ተቋማት ጋር ሆነን እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ክልሎች ሚናቸውን እየተወጡ አይደለም። ሚናቸውን እንዲወጡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምን ያህል ሃላፊነቱን ተወጥቷል?
ወይዘሮ ፍረወይኒ፡- ይህን ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ብታነሳው ጥሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የፌዴሬሽን ምክር ቤት በርካታ ስራዎች አሉት። ለዚህ የሚመጥን የሰው ሃይልና በጀታችሁ ምን ያህል ነው?
ወይዘሮ ፍረወይኒ፡- እንደ ምክር ቤት ስንገመግም ትልቁ ማነቋችን የሰው ሃይል ነው። ይህ ከበጀትም ከሌሎች ጉዳዮችም ጋር ይያያዛል። ይህን ለማስተካከል ምክር ቤቱ እየሰራ ነው። በሰው ሃይል ለማጠናከርና በተግባር የተፈተኑ ባለሙያዎችን የሚሰብ ለማድረግ እየሰራን ነው። የግጭት አመላካች ካርታ ለመስራት ታስቦ በበጀት ችግር ለረጅም ጊዜ ቆይቷል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል አሰራር ቀርጾና ከማስተካከያው ጋር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀጥታ አቅርቦ ለማስጸደቅ እየሰራ ነው። የሰው ሃይሉንና የበጀቱን መጠን የእኔ ሃላፊነት ስላልሆነ ጽሕፈት ቤቱ ቢገልጥልህ ጥሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አዲስ የተቋቋመው የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ኮሚሽን የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ስልጣን ይጋፋል ይባላል። እንደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አቋማችሁ ምንድን ነው?
ወይዘሮ ፍረወይኒ፡- ይቅርታ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታ ገብቷል። ወደ ህገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ ቀርቧል። ለአቤቱታው ግን ስርዓቱን ጠብቆ ምላሽ ይሰጣል። የህገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ በቀጥታ ምላሽ ሊሰጥ ወይም አቤቱታው ወደኛ ሊመጣም ይችላል። እኔም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል ስለሆንኩ የአስተሳሰብ ተጽዕኖ እንዳላደርግ መጠንቀቅ እፈልጋለሁ። ስለዚህ እዚህ ሀሳብ ባልሰጥ ጥሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ቃለ ምልልስ አመሰግናለሁ።
ወይዘሮ ፍሬወይኒ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2011
በአጎናፍር ገዛኸኝ