ኢትዮጵያውያን አንድነታቸው ጎልቶ ከወጣባቸው ጊዜያት ሁሉ ተነጥሎ እንደ ምሳሌ የሚነገረው በ1888 ከጣልያን ወራሪ ጋር የተደረገው የአድዋ ጦርነትና ድል ነው። አዎን ከዚያ ቀደም አርባና ሃምሳ በማይሞሉ ዓመታት ውስጥ በየአካባቢው በነበሩ ነገስታት እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ባይነት ሳይስማሙ ቀርተው እርስ በርስ ጦር ይማዘዙ ነበር። ይሁን እንጂ፤ ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው የጋራ አካፋይ ነበራቸው። አገር የሚባል!
እናም የተለያዩ ስልቶች ተጠቅሞ ቆይቶ፤ በመጨረሻ ጦርና ሰራዊቱን አዘጋጅቶ ኢትዮጵያን ለመውረር የመጣውን የኢጣልያ ጦር በአንድ ሆኖ በመዋጋትና የአገርን ሉዓላዊነትና የህዝቦቿን አንድነት በማስከበር ሁሉም በአንድነት ቆሟል።
ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን የሀገር ጉዳይ ሲነሳ አንዳችም ልዩነት አይታይባቸውም ነበር። ለእነርሱ አገር ማለት፤ ኢትዮጵያ ማለት አንድና አንድ ብቻ ነበረች፤ ናትም። በዚህም ምክንያት የወቅቱ መሪ ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ህዝባቸው ጦር ሰብቆና ስንቁን ሰንቆ፤ በሰጡት የቀጠሮ ቀን፤ ባሉት ቦታ ከትቶ እንዲጠብቃቸው አዋጅ ሲያስነግሩ የህዝቡ ምላሽ አንድ ዓይነት ነበር። የአገሩና የድንበሩ መደፈር ከዙፋኑ በላይ ነበር የቆረቆረው፤ በወቅቱ የነበረው የመጓጓዣና የመገናኛ አውታር እጅግ አስቸጋሪ ቢሆንም የወራት መንገድ በእግሩ ተጉዞ ክተት ወደተባለበት ወረኢሉ ለመድረስ ግን አንዳችም አላገደውም ነበር።
የአገር ፍቅር እንደሰብዓዊ ግንኙነት በቃል ብቻ የሚገለጽ አይደለም። የያኔዎቹ ኢትዮጵያውያን ጀግኖችም የሀገር ፍቅራቸውን ደም በማፍሰስ፣ አጥንት በመከስከስና መተከያ የሌለው ክቡር ሕይወታቸውን በመስጠት ገልጸዋል።
አገራቸው ስትደፈር፤ መሪያቸው ጥሪ ሲያቀርብ “እኔ…”አላሉም “እኛ አለን” ብለው ነበር በአንድ የተሰለፉት። ምናልባት በዘመን ትሩፋት የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች እና ዘመናዊ በምንባልበት በአሁኑ ወቅት ልናደርገው አይደለም ልናስበው በሚያጠራጥረን ሁኔታ እኒያ የዚያን ዘመን አባቶች የአስተሳሰብ ስልጣኔ አሳይተውናል።
የኢጣሊያ ወራሪ ኃይል የሰሜኑን የአገሪቱ ክፍል ወርሮ ወሰኑን ወደ መሀል ለማስፋፋት ባሰበበት ወቅት የታጠቀው ዘመኑ የደረሰበትንና አቅሙ የፈቀደለትን የጦር መሳሪያ ነበር። በአንጻሩ ኢትዮጵያውያን የታጠቁት እጅግ ኋላቀር መሳሪያ ቢሆንም፤ የሰነቁት የአገር ፍቅር እና የአልደፈርም ወኔ ነበርና ከአራቱም አቅጣጫዎች ተምሞ ለአገሩ ዘብ ቆመዋል። ያኔ ኢትዮጵያውያንን እገሌ ከእገሌ ሳይባል በአንድ ያቆማቸውና እስከአፍንጫው ከታጠቀው ወራሪ ኃይል ጋር በግንባር ያፋጠጣቸው የአገር ፍቅራቸውና የነጻነት ቀናኢነታቸው ነበር። እንጂማ፤ ዛሬ የሚባለው ሁሉ ያኔም ነበር። ዛሬ የሚጠራው ያኔም ይጠራ ነበር። መቋጠሪያው ውሉ ግን አንድ እና አንድ ሲሆን እሱም አገር ብቻ ነበር!
የአገር ፍቅር ፆታ አይለይም፤ ብሔር አይጠይቅም፤ ዕውቀትና ሙያ አምጡ አይልም። መመራመርና መፈላሰፍም የግድ አይልም። ይህ ከውስጥ የሚመነጭ አክብሮት የሚገለጽበት የውዴታ ስሜት ነው። እናም አባቶቻችን በቁሳዊ ስልጣኔ ኋላቀር ቢሆኑም በአስተሳሰባቸው የዘመኑና የረቀቁ በመሆናቸው ጦርነት ገጥመው ድል አደረጉ። የድላቸው መሰረት ደግሞ በአገር ፍቅር ስሜት በአንድነት መቆማቸው ነው።
ይህ አንድነታቸው ያስመዘገበው ድል ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪቃውያንም ዓይን መክፈቻ የምስራች ነበር/ነው። በርግጥም የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ብቻ አይደለም። ይልቁንም የመላው ጥቁር ህዝብ ድል ነው። ዛሬም 123ኛው የድል መታሰቢያ ቀን ሲዘከር የአባቶቻችን አንድነታቸውና የሀገር መውደድ ስሜታቸው አብሮ ይታሰባል።
የአድዋ ድል የአንድነትና የሀገር ፍቅር ስሜት ውጤት ነው። ይህ ውጤት ደግሞ ሁሉም በቅኝ ግዛት ጥላ ስር የነበረና ለነጻነት የሚታገል የዓለም ህዝብ የተጋራውና የሚጋራው የብርሃን ቀንዲል ነው። ዛሬ ከአንድ መቶ ሃያ ዓመታት በላይ ሲዘከር የኖረውን የአድዋ ድል ማሰብ ያለብን ወደልቦናችን ተመልሰን መሆን አለበት። ለመለያያ ሰበብ እየፈለግን ያጋደምነውን የልዩነት መስመር አሽቀንጥረን በመጣል ዳግም ልንዋደድ፤ መልሰን በአንድ ልንቆም ይኖርብናል። ያለስምምነት አንድነትና ህብረት፤ ያለአንድነትና ህብረት ደግሞ እድገትና ብልጽግና አይታሰብም።
እኛ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ወቅት ከምንም በላይ አንድነትና ህብረት ያስፈልገናል። እንደቤተሰብ፤ ልጅ ወልዶ ለማሳደግ ከፈለግን፤ እንደዜጋ በየአቅጣጫው ወጥተን ገብተን ለመስራት ከተመኘን ከምንም በላይ አገር በምትባል ትልቅ ጥላ ስር በህብረት ልንሰባሰብ ይገባል።
ወጣቶች ሀገርን ከቋንቋ በላይ ሊያውቋትና ሊገነዘቧት፤ ተፋቅረው ሊንከባከቧት የግድ ይላል። ይሄ ደግሞ የሁሉም ሃላፊነት ነው። ትምህርት ቤቶች በስነምግባርና በስነዜጋ ትምህርት ከምንምና ከመቼውም ጊዜ በላይ ስለሀገር ሊያስተምሩ ይገባቸዋል። መንግስትና ሁሉም ያገባኛል ባይ ተቋማት አንድነትን፤ በጋራ መቆምን ሊሰብኩና ሲያሳውቁ ይገባል።
የአድዋ ድል በእኛ በኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በአፍሪካውያንም ዘንድ የነጻነትና የአልደፈርም ባይነት ተምሳሌት ነውና በጀመርነው ድህነትን የማጥፋት አገራዊ ዘመቻ በአንድ ቆመን ድሉን ልንደግመው ይገባል። በልዩነታችን ደምቀንና አንድነታችንን በሚያጎሉ አገራዊ ትሩፋቶች ታጅበን ያማረና የሰመረ ነገን ለተተኪዎች እንድናስተላልፍ ቅድሚያ ለአገር፤ ቅድሚያ ለህብረት ማለት ተገቢ ነው እንላለን።
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2011