አዲስ አበባ፡– በሸገር ከተማ አስተዳዳር ከበዓል ጋር ተያይዞ የሚያጋጥም የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም እንዳይኖር አስቀድሞ እየተሠራ መሆኑን የሸገር ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ገለጸ።
የሸገር ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚደንት መጋቢ ስርዓት ቀሲስ ታዬ ለታ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በዓላት በመጡ ቁጥር የሚያሳስበው የአቅርቦት እና የፍላጎት አለመመጣጠንን ተከትሎ የሚከሰት የዋጋ ጭማሪ ነው።
አሁን ላይ ችግሩን ለመፍታት ከነጋዴው እና ከንግድ ቢሮ ጋር በተቀናጀ እየተሰረ እንደሆነ ያመለከቱት ፕሬዚደንቱ፤ ነጋዴዎች በተለይ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ቀድሞ በማስገባት ገበያው እንዲረጋጋ የማድረግ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች የአቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥምና አላስፈላጊ ጭማሪ እንዳይደረግባቸው ነጋዴዎች በተለያዩ መድረኮች ስልጠና እያገኙ እንደሆነ ጠቅሰው፤ የሚሰጡት አገልግሎት ለራሳቸው ማህበረሰብና ለዜጋቸው መሆኑን ተረድተው ምርቶችን በተገቢው መንገድ ለማቅረብ እየሰሩ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
የኦሮሚያ የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የመግዛት ዓቅማቸው ዝቅተኝ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ባዛሮችን ማዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ ምርቶች ፤ እንደ ዘይት እና ሱኳር ያሉ መሰረታዊ ሸቀጦች እጥረት እንዳያጋጥም ምክር ቤቱ ላለለፉት ዓመታት ሲሰራ እንደቆየም ገልጸዋል።
ንግድ ምክር ቤቱ ትልቅ ዓላማ ያነገበ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ከሀገር ውጭ በአሜሪካ እና በጀርመን ኤክስፖዎቹን ማካሄዱን አመልክተዋል፤ ከበአላት ጋር ተያይዞ ሸማቹ ማህበረሰብ ሸቀጦች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገበያይ ስርዓት በመዘርጋት አመርቂ ውጤቶች እያስመዘገበ ይገኛል ብለዋል።
ውጭ ሀገር የሚገኙ የዲያስፖራ አባላት ሀገር ውስጥ ገብተው በተለያዩ የስራ ዘርፎች እንዲሳተፉ እያደረገ መሆኑንም፤ አፖሎ የተባለ ትልቅ ካምፓኒ ዘመናዊ የሪልስቴት ለመገንባት ከምክር ቤቱ ጋር ሰፊ ውይይት ማደርጉንና ጥናቱን አጠናቆ ለማስረከብ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የወተት ምርትን ለሸገር እና ለአዲስ አበባ ከተማ ለማቅረብ በከብት እርባታ እና በወተት ተዋፅኦ ምርት መሰማራት የሚፈልጉ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ባለሀብቶች እንደቀረቡም ገልጸዋል።
ማህበረሰቡ የማይጠቀምበት ንግድ ጤናማ አይሆንም ያሉት ፕሬዘዳንቱ ፤ ህገወጥ ንግድ እና በአቋራጭ ለመክበር የሚደረግ እንቅስቃሴ ጎጂ መሆኑን በመረዳት ነጋዴው ምርቶችን አስቀድሞ በማቅረብ ህብረተሰቡ በዓሉን በደስታ እንዲያከብር በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 ቀን 2017 ዓ.ም