የተሻለች ሀገር ፈጥሮ ማስቀጠል የትውልዱ ትልቁ የቤት ሥራ ነው !

የአንድ ሀገር የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በትውልዶች ቅብብል ውስጥ በሚኖር የእሴት ግንባታ ነው። ይህን ታሳቢ በማድረግም ሀገራት የቀደሙ ተሻጋሪ እና አዲስ አሻጋሪ እሴቶችን በሁለንተናዊ መልኩ በመጠበቅ እና በመፍጠር ሀገር እንደሀገር በተሻለ መንገድ ሕልውናዋ ተጠብቆ እንዲቀጥል በስፋት ይሠራሉ። ይህም የሠላማቸው፣ የሥልጣኔያቸው እና የነገ ተስፋቸው መሠረት እንደሆነ ይታመናል።

ለዚህም በትምህርት ሥርዓታቸው፣ በባሕል እና በሃይማኖታዊ አስተምህሯቸው፣ ለቤተሰብ እና ለማኅበረሰባዊ ማንነት ግንባታ ትልቅ ቦታ ሰጥተው ይንቀሳቀሳሉ። ብዙ ሀብት፤ ሰፊ ጊዜ ሰጥተው ይሠራሉ። ይህም አጠቃላይ የሆነው ማኅበራዊ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮቻቸው ጤናማ እንዲሆን መሠረት የጣለ ነው።

እኛም ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር የብዙ ሺህ ዘመን የሀገረ መንግሥት ታሪክ ባለቤቶች ነን ብለን አፋችንን ሞልተን የምናወራው፤ ሀገርን እንደሀገር አቁመው ማስቀጠል ያስቻሉ ማኅበረሰባዊ እሴቶች ባለቤቶች በመሆናችን ነው። እነዚህ እሴቶቻችን በአንድም ይሁን በሌላ ከትውልድ ወደ ትውልድ እያሻገሩ ዛሬ ላይ አድርሰውናል።

በርግጥ በየዘመኑ የተነሱ የተዛቡ አስተሳሰቦች የመጣንባቸውን መንገዶች በብዙ መንገጫገጮች የፈተኑን እና እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ ያስከፈሉን ናቸው። ትናንትን ማሻገራቸው አንድ ነገር ሆኖ፤ ትናንትን ከዛሬ ጋር አስታርቀን መሄድ አለመቻላችን፤ የእሴት ግንባታችን ከየዘመኑ አስተሳሰብ ጋር ተሳስሮ አለመሄዱ የችግሮቻችን አንዱ መገለጫ ነው።

በተለይም ከቅርብ ጊዜ አንስቶ አጠቃላይ በሆነው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መስተጋብሮቻችን ውስጥ እየተስተዋሉ ያሉ የተዛቡ አስተሳሰቦች አጠቃላይ በሆነው የትውልዶች ግንባታ ውስጥ ትልቅ ፈተና ሆኖ የመገኘቱ እውነታ የአደባባይ ሚስጥር ነው።

የተከተልናቸው እና እየተከተልን ያለነው ከማኅበረሰቡ መንፈሳዊ፣ ባሕላዊ እና ማኅበረሰባዊ እሴቶች በተቃርኖ የቆሙ የፖለቲካኢኮኖሚ አስተሳሰቦች፤ አስተሳሰቦቹ የፈጠሩት ግራ መጋባት ተከታታይ ትውልዶችን ብዙ ያልተገባ ዋጋ አስከፍለዋል። በትውልድ ግንባታ ውስጥ የአስተሳሰብ ክፍተት በመፍጠር ዛሬም ባልተገባ መንገድ ዋጋ እንድንከፍል እያደረጉን ነው

ግለሰቦች እና ቡድኖች በፈጠሯቸው የተዛቡ የፖለቲካኢኮኖሚ እሳቤዎች ትናንት በዓለም አቀፍ ደረጃ የምንታወቅባቸው እሴቶቻችን አደጋ ውስጥ ወድቀው፤ ዓለምን ባስደነገጠ መንገድ ከማንነታችን በተቃርኖ በቆሙ ተግባራት ብዙ ዋጋ ከፍለናል።

ባልተገቡ ትርክቶች ወንድም በወንድሙ ላይ እንዲነሳ፤ ልጅ በአባቱ ላይ እንዲጨክን ተደርጓል። የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ባልተገባ መልኩ በአደባባይ የተዋረዱበት አንገት የሚያስደፉ ክስተቶች ተፈጥረዋል። ሀገርን እንደሀገር የሚያፈርሱ የጥፋት አስተሳሰቦች አካል ገዝተው ታይተዋል።

ይህ የብዙዎችን ልብ የሰበረ፣ አንገት ያስደፋ እውነታ ዛሬም በተለያዩ የሀገራቱ አካባቢዎች እየተስተዋለ ነው። ትናንት አባቶቻችን በብዙ መስዋዕትነት ያስረከቡንን ሀገር ሕልውና አደጋ ውስጥ ከትቶ ብዙ ዋጋ እንዳላስከፈለን፤ ዛሬ ደግሞ የሕዝባችን የሠላም እና የመልማት ጥያቄ ተግዳሮት ሆኖ ከፊታችን ቆሟል። ሀገርን እንደሀገር ያቆሙ ማኅበራዊ እሴቶቻችን ከመሸርሸር ባለፈ ለመጪዎቹ ትውልዶች ብሩህ ነገዎች ተግዳሮት ሆኗል።

የትኛውም ግለሰባዊ ሆነ ቡድናዊ ጥቅም፤ ጥቅም ሆኖ ሊቀጥል የሚችለው ከሁሉም በላይ ሀገር እንደ ሀገር መቆም ስትችል፤ ትውልዶችም ሀገርን መሸከም የሚያስችል የአስተሳሰብ መሠረት ሲኖራቸው ብቻ ነው። ይህ መሆን ባልቻለበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል ተብሎ የሚታሰበው ተጠቃሚነት ሀገር አፍርሶ፤ ከፍርስራሽ ውስጥ መኖር ነው።

ይህ ደግሞ አሁን ባለበት ዓለም አቀፍ እሳቤ ከጠላት ሳይቀር የማይታሰብ፤ ከፍጹም መታወር እና ኅብረሰባዊ ጥላቻ የሚመነጭ ነው። ከአዕምሮ ጤነኝነት ጋር አብሮ የሚታሰብ፤ የእያንዳንዱን ዜጋ ትኩረት የሚሻ እና ፈጥኖ መንቀሳቀስ የሚጠይቅ ሀገራዊ አጀንዳ ነው።

ለዚህ ደግሞ እንደሀገር ዛሬ ላይ ላደረሱን ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ እሴቶቻችን ዋጋ መስጠት፤ እነዚህን እሴቶቻችንን ከዛሬ ጋር አጣጥመን ለምንፈልገው እና ተስፋ ለምናደርገው ነገ አቅም እንዲሆኑን መግራት ያስፈልገናል። ዛሬን በሚሸከሙ፣ ነገን በተሻለ ተስፋ መቀበል በሚያስችሉ ዘመኑን በሚዋጁ አስተሳሰቦች ሊቃኙም ይገባል

ይህን እውን በማድረግ ሂደት ሁሉም በተለወጠ ማንነት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል። ወላጆች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ መምህራን፣ ምሑራን፣ የፖለቲካ ልሂቃን ኃላፊነት የሚሰማው፣ ከራሱ እና ከማኅበረሰቡ አሻጋሪ እሴቶች ጋር የታረቀ ትውልድ በመፍጠር የሚጠበቅባቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል።

ይህን ማድረግ ከቻልን እንደሀገር እየተፈተንባቸው እና ብዙ ዋጋ እየከፈልንባቸው ያሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮቻችን ተሻግረን ከራሳችን አልፈን ለመጪዎቹ ትውልዶች የተሻለች ሀገር ፈጥረን ማስቀጠል እንችላለን። ይህንን ማድረግም የዚህ ትውልድ ትልቁ የቤት ሥራ ነው!

 አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You