ዜና ሐተታ
ሐና አልቤ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከአርባ ምንጭ አዲስ አበባ ስትመጣ መልካም ሕልምን ይዛ ነው፡፡ በወሬ ዝናቸውን እንደምትሰማው የሀገሯ ልጆች ሠርታ የመለወጥ፣ ለብሳ የመዋብ ዓላማ ነበራት፡፡ እሷን ጨምሮ ሰባት እኩዮቿ መሐል አዲስ አበባ ሲደርሱ የተቀበላቸው ዘመድ ወዳጅ አልነበረም፡፡ ሰባቱም የሚገቡበት ቤት የላቸውምና የመጀመሪያ ማረፊያቸው የጎዳና ጥግ ሆነ::
ዕለቱን በእንግድነት የተቀበሏቸው የጎዳና ልጆች ፊት አልነሷቸውም:: ካላቸው አካፍለው ከለበሱት ገፈው በሠላም አሳደሯቸው:: ማግስቱን ለሰባቱ ባልንጀሮች የመጣ ሲሳይ አልነበረም:: አብረዋቸው ካደሩት ልጆች ጋር ተመሳስለው የመጀመሪያዋን ቀን በልመና ሊያሳልፉ ግድ ሆነ ::
ቀናት እየጨመሩ ጊዜያት መግፋት ሲይዙ ያሰቡት ዕቅድ ቀርቶ ኑሮ አዳራቸው ጎዳና ላይ ሆነ:: ሥራና ዓላማ ይሉት ግብ ተረሳ:: ሕይወታቸው በልመናና ሱስ ተገለጠ:: ጎዳና ላይ ሕይወት በእጅጉ ይለያል ትላለች ሐና::
በልቶ ማደር፣ ለብሶ ማማር ብርቅ ነው:: ሁሌም የእናት ቤት እንጀራ፣ የዓውዳ ዓመት ወግ ይናፍቃል:: በዚህ ቦታ የጎረቤት፣ የወዳጅ ዘመድ ፍቅር ሩቅ ነው:: ሐና እና ጓደኞቿም በዚህ እውነታ ሊያልፉ ግድ ሆኗል:: በተለይ ዓውዳ ዓመት ደርሶ ዕለቱ መከበር ሲጀምር የሁሉም ሆድ ይሸበራል:: የሚያዝን የሚተክዘው ይበዛል ነው ያለችው::
አብዛኞቹ ዓመታትን በጎዳና ቢገፉም ይህን ጊዜ እንደዋዛ ማለፍ ይቸግራቸዋል:: በዓውዳ ዓመት እንደ ልጅነታቸው የሚገዛላቸው አዲስ ልብስና ጫማ፤ የቤት ጓዳቸው ሙላት፣ የሰፈርተኛው ልማድና ወግ ዛሬ ትዝታቸው ሆኗል:: እንጀራና ዶሮው፣ ዳቦና ጠላው፣ በግና ቅርጫው፣ ቡና፣ ቄጤማና ዕጣኑ በዓይናቸው ውል እያለ እንደሚቸገሩ ታስታውሳለች::
ዓውዳ ዓመትን በአይረሴ ትዝታና ባዶነት ማለፍን የማይሹ የጎዳና ልጆች ታዲያ ሁሌም ደስታን ለመፍጠር መላ ዘዴው በእጃቸው ነው:: ቀኑን በፍቅር ለማለፍ የራሳቸውን ዓውዳ ዓመት ማድመቅን ያውቁበታል:: በአቅማቸው ውሰጣቸውን አስደስተው ብዙኃኑን ለመምሰል ጎዳናን ከመኖሪያ ቤት ወግ አይለዩትም:: እንደ አንድ ቤትና ቤተሰብ የአቅማቸውን ለማሟላት የቻሉትን ይጥራሉ:: ሐናና ጓደኞቿ ለዓመታት ይህን እውነት በራሳቸው ዓለም ሲያጣጥሙት ቆይተዋል::
ዓውዳ ዓመት በመጣ ቁጥር የጎዳናው ድባብ ይለወጣል:: የአስፓልት ጥጎች፣ የመንገድ ላይ ጠርዞች በቄጤማና አበቦች ይደምቃሉ:: ዕጣን ሰንደሉ፣ ፈንድሻ ከሰሉ ስፍራውን እንደ መልካም ሳሎን ያስውቡታል:: ቤት ያፈራው ዳቦ፣ ቆሎና ቂጣ ለታዳሚው ይታደላል:: ከተገኘ ጠላና ጠጁም ይቀርባል:: በ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› ምኞት በፍቅር ጽዋ ተሞልቶ ሁሉም በእኩል ይቃመሳል::
የእንጀራና ወጡን ጎዶሎ ለመሙላት በየቤቱ የሚለምኑት በእነሱ አጠራር ‹‹ተመላሽ›› ለውሏቸው በቂ ነው:: እሱን በፍቅር ተጎራርሰው በደስታ ይውላሉ:: እነሐና የቁርጥ ሥጋ አምሮታቸውን በትዝታ ብቻ አያልፉትም:: ‹‹ቻቻ›› ብለው በሚጠሩት የመዋጮ ልማድ ያላቸውን አጋጭተው ቅንጥብጣቢ ሥጋ እንደሚገዙ::
ዕለቱን ቤተክርስቲያን ለመሳለም አንድ ነጠላ ለብዙዎች በቂ ነው:: ተራ በተራ እየለበሱ የወጉን ማድረስ ልማዳቸው ነው:: በዚህ ቀን የዕምነት ሃይማኖት ልዩነት አይታወቅም:: ሁሉም በእኩል ከማዕዱ ይካፈላል:: በጎዳና ለነገ ይደር፣ ይቆጠብ ይሉት ልማድ ፍጹም ነውር ነው::
ፌቨን ታደሰ የአዳማ ልጅ ናት:: በጎዳና ኑሮ ከማለፏ በፊት በርካታ ውጣ ውረዶችን ተሻግራለች:: እናቷን በሞት ያጣችው ገና የአስር ዓመት ልጅ ሳለች ነበር:: ቀጣይ ሕይወቷን ለመምራት አዲስ አበባ በአክስቷ ቤት ለመማር ሞክራለች:: ዕድሜዋ ከፍ ሲል ግን ወደ ቤሩት ሄዳ ለመሥራትና ራሷን ለመቻል ፈለገች:: ተሳካላት::
ፌቨን ከዓመታት በኋላ ራሷን ጎዳና ላይ አገኘችው:: በስፍራው ለመገኘቷ ዋና ምክንያት አብሯት የቆየው ከባድ ሱስ ነበር:: ይህ ልማዷ ከሥራ ዓለም አራቃት፣ ከሰዎች አገለላት:: በሕገ ወጥነት ተይዛ ሀገሯ ስትመለስ ማረፊያዋ የወዳጅ ዘመድ ቤት አልነበረም:: ጎዳና ተቀበላት:: ኑሮዋ የመንገድ ጥግ ሆኖ ጊዜያትን ገፋች::
ፌቨን በጎዳና ሕይወት ክፉና ደግ አይረሴ ትዝታዎች አሏት:: ከሁሉም ግን ዓውዳ ዓመት ሲመጣ ከጓደኞቿ ጋር የምታሳልፈውን መልካም ጊዜ አትዘነጋውም::
ዛሬ ፌቨንና ሐና የ‹‹ነገዋን ተሐድሶ ክህሎት ማበልፀጊያ›› ማዕከልን ተቀላቅለዋል:: ይህ እውነት ከጎዳና ሕይወት አርቆ የነገ ሕልማቸውን ሊፈታ እውነትነቱ ተቃርቧል:: አሁን የትናንቱ አስከፊ ኑሮ ‹‹ነበር›› ተብሎ አልፏል:: ሁለቱም ዛሬ ላይ ሆነው ትናንትን ሲያስቡት ለነገ ሕይወታቸው እንዲተጉ ያበረታቸዋል::
ወጣቶቹ በማዕከሉ አስፈላጊውን ተሐድሶ አልፈው በመረጡት ሙያ መሠልጠን ጀምረዋል:: የዛሬው ዓውዳ ዓመታቸው በጣራ ስር እንጂ በጎዳና ጥግ አይደለም:: ለሁለቱም የቀድሞው ዓመት በዓል ያለፈ ትዝታ ነው:: የትናንቱ የጎዳና ዓውዳ ዓመት፣ ለጎዳና ልጆች ትዝታን አሻግሮ፣ ዛሬን አቀብሎ በነበር:: አልፏልና::
ነገ ደግሞ በሥራ ተሰማርተው ሕይወታቸው ተቀይሮ በራሳቸው ቤት እንደሚያከብሩት ተስፋ ሰንቀዋል:: የጎዳና ሕይወት ተሰናብተው ማዕከሉ እንደገቡ ሁሉ ነገ ደግሞ ማዕከሉን ቆይታቸው አጠናቀው አዲስ ሕይወት አዲስ ሥራ እንደሚጀምሩ ተስፋ ማድረጋቸውና ይህም እውን እንደሚሆን ነው የነገሩን::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 25 ቀን 2017 ዓ.ም