ኢትዮጵያ እንደ ሀገር፤ ኢትዮጵያውያንን እንደ ሕዝብ ከሦስት ሺህ ዘመናት የተሻገረ ታሪክ ያላቸው ባለታሪኮች ናቸው ሲባል፤ የታሪካቸውን ተሰናስሎ፣ የሥርዓተ መንግሥቱን ቀጣይነት፣ የባህልና የቱሪዝም አቅም የሚሆኑ ተፈጥሮም የሕዝቦች የጥበብ አሻራም የቸሯቸው አያሌ መገለጫዎች ያሏቸው ጭምር ስለመሆናቸው የሚገለጥበት የተረክ ውቅር አለ::
ይሄ የተረክ ውቅር ታዲያ፣ በተረት ተረት የተወረሰ ሳይሆን፤ በሚገለጥ እውነት፣ በሚጨበጥም ሕያውነት የሚረጋገጥ ነው:: ይሄ ተጨባጭነቱ ደግሞ ተራኪዎችን ልበ ሙሉ፤ ተግባሪዎችንም ባለ ዐሻራ ትውልድ ያደረገ፤ ከትናንት እስከ ዛሬም በትውልዶች ቅብብሎሽ ውስጥ ደምቆ የዘለቀ ከፍታን ያጎናጸፈም ነው::
ይሄ የኢትዮጵያ እውነትም ሆነ የኢትዮጵያውያን የኑሮ ዐሻራ ታዲያ፤ አንድም እውነቱን የመግለጥ ስንፍና እና እውነትን ያለመረዳት አላዋቂነትን ታክኮ፤ ሁለትም እውነትን በመግለጥና ታሪክን በማደስ ውስጥ የትናንቱ ታላቅነት የዛሬውን ግብር ያሳንሳል ከሚል ታሪክ ጠል ምልከታ ተሸብቦ ሳይገለጥ ተዳፍኖ ኖሯል::
ከ2010ሩ ሀገራዊ ለውጥ ማግስት፣ በተለይም እንደ ሀገር እየተተገበረ ከሚገኘው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ጋር በተያያዘ፤ እንደ ሀገር ያሉ አቅሞች ተሰባስበውና ተደምረው የብልፅግናው ጉዞ ማሳለጫ እንዲሆኑ የግድ አለ:: እናም ሀገር ያላት አቅምና ሀብት፣ እውቀትና ታሪክን የመሳሰሉ የማደጊያና የመበልጸጊያ መንገዶች ሁሉ መፈተሽ ጀመሩ::
ለምሳሌ፣ እንደ ሀገር ለሚፈለገው ሀገራዊ የልማት ግብ፤ አንድ መንገድ (ለምሳሌ ግብርናው) ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ ማሳካት እንደማይቻል ይታመናል:: ለዚህም፣ ማዕድን፣ ዲጂታላይዜሽን፣ ቱሪዝም፣ ግብርናን የመሳሰሉ ዘርፎች ላይ ያሉ አቅሞችን መደመር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል::
በመሆኑም በአስር ዓመቱ እውን እንዲሆን ለሚጠበቀው ግብ አቅም ሆኖ ከተመረጡ ዘርፎች አንዱ ቱሪዝም ነው:: እንደ ሀገር ደግሞ የቱሪዝሙን አቅምነት ከፍ የሚያደርጉ አያሌ ሀብቶች አሉ:: ይሁን እንጂ እንደ ሀገር ቀደም ሲል እነዚህን ሀብቶች ከመለየትና ከማልማት፣ ከመጠበቅና የኢኮኖሚ አቅም ከማድረግ አኳያ እዚህ ግባ የሚባል ሥራ ሳይሠራ ቆይቷል::
ከለውጡ ማግስት ግን አንዱ ትኩረት ተደርጎ ከተሠራባቸው ጉዳዮች መካከል እነዚህን የቱሪዝም አቅሞች የመለየት፣ የማልማትና የገቢ አቅም የማድረግ ጉዳይ ነው:: በዚህ ረገድ ሀብትነታቸው ሳይሆን የቆሻሻ ማዕከል ሆነው የመታየት እድላቸው ከፍ ብሎ የነበሩ ከአዲስ አበባ እስከ ክልል ያሉ ሥፍራዎች፤ ከቤተ መንግሥቱ ቅጥር እስከ ወንዝ ዳርቻዎችና ጥቅጥቅ ደኖች ያሉ ገጽታዎችን መቀየር ተችሏል::
በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባላቸው ከፍ ያለ እይታ ምክንያት፤ በገበታ ለሸገር ጀምረው እስከ ገበታ ለትውልድ በዘለቀው መንገዳቸው በርካታ ሀብቶችን ለይቶ ማልማት እና ታሪክንም፣ ገጽታንም፣ የቱሪዝም አቅምንም መግለጥ፤ ዘርፉንም የኢኮኖሚው አቅም ማድረግ ተችሏል::
የአንድነት ፓርክ፣ የወዳጅነት አደባባይ፣ የእንጦጦ ፓርክን የመሳሰሉት በገበታ ለሸገር፤ ጎርጎራ፣ ኮይሻ እና ወንጪ ደንዲን የመሳሰሉት በገበታ ለሀገር፤ እንዲሁም ሌሎች በገበታ ለትውልድ ማሕቀፍ ተይዘው እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ለዚህ ሕያው ምስክር ናቸው::
ከሰሞኑ ነባር ማንነቱን በአዲስ ገጽታ ይዞ ተደማሪ ድምቀትና ታላቅነትን እንዲገልጥ ሆኖ የተሰናዳው የብሔራዊ ቤተ መንግሥት እድሳት ሥራም የዚህ የሀገርን ታሪክ የማክበር፣ ገጽታዋንም የመግለጥ፣ የቱሪዝም ዘርፉንም ከፍ ወዳለ ምዕራፍ የማሸጋገርና ዘርፉን የኢኮኖሚው አዕማድ የማድረግ ተግባር ማሳያ ነው::
ምክንያቱም፣ በብሔራዊ ቤተ መንግሥቱ ውስጥ ለጥቂቶች እይታ ብቻ (ያውም ጥቂት ገጹን) ተገድቦ የኖረውን ታሪክና ሀብት፤ ለሕዝብ እይታ እንዲበቃ ያደረገ ሆኗል:: ኢትዮጵያ የታሪኳን መንገድ እንድትገልጥ፤ የሥልጣኔዋን ጣሪያ እንድታሳይ፤ የሥርዓተ መንግሥቷን ጉዞ እንድትናገር፤ የነጻነትና አርዓያነት መንገዷን እንድታስረዳ የሚያስችልም ነው::
ይሄ ደግሞ ታሪክን የሚወድድ፣ በታሪኩ የሚኮራ፣ ታሪኩንም የሚያውቅ፣ ለታሪክና ለባለታሪኮችም ክብርና ፍቅር ያለው፤ በጥቅሉ ኢትዮጵያን የሚወድድ፣ ኢትዮጵያውያንንም በሚመጥናቸው ልክ ለማኖር የሚተጋ መሪና ትውልድ እሳቤና ተግባር ነው:: የተዳፈነውን የሚገልጥና የቱሪዝም መንገዱን ብርሃን ከሚያደርግ ትውልድ፤ አቧራውን አራግፎ ደምቆ የሚታይ ዐሻራን ከሚያኖር መሪ፤ የታሪክ ከፍታን በመግለጥ ውስጥ ከፍ ያለ ታሪክን ለማኖር ከሚታትር መንግሥት ቅን እሳቤ ተወልዶ የተተገበረ ታላቅ ሥራ ነው::
ለዚህም ነው የተደበቁት አቅሞች እየተገለጡ፤ በክፉ ትርክት የተዳፈኑ ከፍታዎች ዳግም እየታደሱ፤ የግለሰብና ቡድኖች የግል ሀብት መስለው ይታዩ የነበሩ የወል ሀብቶች ዳግም የሕዝብ ሀብትነታቸውን እንዲጎናጸፉ እየሆኑ ያሉትታሪክን ያደሰ፣ የሀገር ገጽታን እና የቱሪዝም ጠቀሜታን ታሳቢ ያደረገ መልካም ተግባር! ከዚህ አኳያ የለውጡ ማግስት መንገድን ከፍ አድርገው ካሳዩት ተግባራት መካከል አንዱ የሆነው የብሔራዊ ቤተ መንግሥት እድሳትም ታሪክን ያደሰ፣ የሀገር ገጽታን እና የቱሪዝም ከፍታን ያቀናጀ መልካም ተግባር ነው!
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 ቀን 2017 ዓ.ም