መጪውን የቱሪዝም ወቅት በሚገባ መጠቀም ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ለቱሪዝም ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መሆኑ ይታወቃል። በእዚህም የቱሪዝም ሀብቶቿን መጠቀም የሚያስችሉ መዳረሻዎችን በማልማት፣ በዩኔስኮ መመዝገብ ባለባቸው የቱሪዝም ሀብቶች ላይ በመሥራት፣ ለቅርሶች ጥገና በማድረግና በመሳሰሉት ላይ ስትሠራ ቆይታለች፤ በዚህም ተጠቃሽ ውጤቶችን አግኝታለች።

በእዚህም የውጪ ቱሪስቶችን ቁጥር ለመጨመር፣ ቆይታቸውን ለማራዘም እንዲሁም የሀገር ውስጥ ቱሪዝምንም እንዲሁ እንዲጨምር ለማድረግ፣ ከጎብኚዎች የሚገኝ ሀብትንም ለማሳደግ እየተሠራ ነው። ለእዚህ ደግሞ የቱሪዝም መሠረተ ልማት መዘርጋት ብቻውን በቂ ላይሆን ይችላል። ቱሪስቶች የሀገሪቱን የቱሪዝም መስኅቦች ይበልጥ ለመጎብኘት የሚያስችሏቸውን አዳዲስ የቱሪዝም መሠረተ ልማቶችንና መዳረሻዎችን እንዲተዋወቁ፣ እንዲጠቀሙ ማድረግ ላይም መሥራት ያስፈልጋል።

ለእዚህም በሀገሪቱ ከፍተኛ ቱሪስቶች የሚገኙባቸውን ሃይማኖታዊና ባሕላዊ በዓላት በሚገባ መጠቀም ይገባል። ከዚህ አኳያ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት ያለባቸውን እንደ መስከረም፣ ታኅሣሥና ጥር የመሳሰሉትን ወራት በሚገባ መጠቀም ላይ መሥራትን የልማቱ አካል አድርጎ መሥራት ተገቢ ነው።

ሀገሪቱ በቱሪዝም ዘርፍ ደምቃ ከምትታይባቸው ወቅቶች መካከል የሚጠቀሱት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በመጪዎቹ ሳምንታት በድምቀት የሚከበሩት የገና እና ጥምቀት ከተራ በዓላትን ለእዚህ ዓላማ ማዋል ይገባል።

እንደሚታወቀው በዓላቱ በመንፈሳዊ በዓልነታቸው በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በደማቅ ሥነሥርዓት ይከበራሉ። በተለይ የገናን በዓል በላልይበላ እንዲሁም የጥምቀት በዓልን በጎንደር በርካታ የእምነቱ ተከታዮች፣ ከመላ ሀገሪቱና ከውጭ ሀገሮች የሚመጡ ቱሪስቶች ጭምር በስፍራዎቹ በመገኘት ያከብሯቸዋል።

በተለይ በመላ ሀገሪቱ በአደባባይ በሚከበረው የጥምቀት በዓል ከዋዜማው አንስቶ በሚከበረው በዓል ከፍተኛ መጠን ያለው የእምነቱ ተከታይ የሚገኝ ከመሆኑ በተጨማሪ በዓሉን ብለው አያሌ የውጭ ሀገር እንዲሁም ሚሊዮኖች የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች በዓሉ በሚከበርባቸው መላ የሀገሪቱ አካባቢዎች ድረስ በመዝለቅ የበዓላቱ ታዳሚ እንደመሆናቸው መጪው ወቅት ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት የሚታይበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

ቤተክርስቲያኗ ሁሌም እንደምታደርገው በዓሉን በደማቅ ሥነሥርዓት ለማክበር ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን ታካሂዳለች። የሀገሪቱም የክልሎች እንዲሁም የየአካባቢዎቹ አስተዳደሮች በዓላቱ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሠላም እንዲከበሩ ልዩ ዝግጅት ይዘጋጃሉ።

የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የክልል፣ የዞን እና ወረዳ የቱሪዝም አደረጃጀቶች፣ የቱሪስት ድርጅቶች፣ ሆቴሎች፣ ወዘተ. በዓላቱን ሲሉ ወደ ሀገሪቱ የሚመጡ፣ በዓላቱ ወደሚከበሩባቸው አካባቢዎች የሚጓዙ ምዕመናንንም ሆነ ጎብኚዎችን በዓሎቹን በሠላም እንዲያከብሩ ጐብኚዎቹም ጉብኝታቸውን እንዲያካሂዱ ለማድረግ ከወዲሁ ዝግጅት እያደረጉ ናቸው። አንዳንዶቹም ምን ያህል እንደተዘጋጁ ከወዲሁ እየገለጹ ይገኛሉ።

የጥምቀት ከተራ በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች የተመዘገበ መሆኑም ይታወቃል። ይህም በዓሉ በየዓመቱ በደማቅ የሚከበር በመሆኑ ላይ ተጨማሪ ድምቀትና ትልቅ ስፍራ እንዲያገኝ የሚያደርገው እንደመሆኑም በበዓሉ ላይ የሚታደሙ የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ እንዲመጣ እንደሚያደርግ ይታሰባል። በየዓመቱ የሚደረጉ ዝግጅቶችም ይህን የሚመጥኑ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

በመንፈሳዊ በዓሉ አከባበር ሥነሥርዓት ላይ የእነዚህ የውጭ ቱሪስቶችና በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በብዛት መገኘት ይህ ወቅት ሀገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ሀገር ቱሪስ ቶችን የምታስተናግድባቸው ወቅቶች እንዲሆ ን አድርጎታል።

ባለፉት ዓመታት የቱሪዝም ዘርፉ አደረጃጀቶች በዓላቱ በድምቀትና በሠላም እንዲከበሩ ለማድረግ ሲያከናወኑ ከቆዩት ተግባር መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው። ዘንድሮም ይሄው ነው መከናወን ያለበት። የቱሪስቶች ቁጥር ይበልጥ እንዲጨምር ለማድረግ በእነዚህ በዓላት ወቅት ወደ ሀገሪቱ የሚመጡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የውጭ ቱሪስቶች በሀገሪቱ የተገነቡ የቱሪስት መሠረተ ልማቶችን እንዲጠቀሙ፣ እንዲጐበኙ ማድረግ ላይ በእዚህ ወቅት በትኩረት መሠራት ይኖርበታል።

የዚህ ፋይዳው ብዙ ነው፤ የመጡትን ቱሪስቶች በሚገባ በማስተናገድ በገቢ ተጠቃሚ መሆን፣ ቱሪስቶቹ ስለኢትዮጵያ በቂ መረጃ ይዘው እንዲሄዱ ማድረግ፣ ከዚህም ባሻገር በዚህ ጉዟቸው ቱሪስቶቹ በኢትዮጵያ ቆይታቸው የተመለከቷቸውን የዘርፉን ለውጦች ወደ መጡበት ሀገር ሲመለሱ በማስተዋወቅ ሌሎች ቱሪስቶች ወደ ሀገሪቱ እንዲመጡ ማድረግ ላይ እንዲሠሩ ለማድረግ የቱሪዝም አደረጃጀቶች ይህን ምቹ ሁኔታ በሚገባ መጠቀም ይኖርባቸዋል።

በአዲስ አበባ የተገነቡትን የአንድነት፣ የእንጦጦ እንዲሁም የወዳጅነት ፓርኮችን፣ የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየምንና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ወደ ገበያው የገቡ እንደመሆናቸው ቱሪስቶቹ በራሳቸው ሊጎበኟቸው ይችላሉ ተብሎ ሊታሰብ ይችላል። ቱሪስቶቹ እነዚህን ስፍራዎቹ በልዩ ትኩረት እንዲጎበኟቸው በማድረግ የተከናወኑትን ግዙፍ የቱሪስት መሠረተ ልማት ሥራዎች በሚገባ ማሳየት ይቻላል። ሀገሪቱ እድሳት ሲደረግለት የቆየውን ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ከትናንት በስቲያ አስመርቃለች፤ ይህም ሌላው የቱሪዝም ዘርፉ አንድ አቅም ሆኖ መጥቷል። ሌሎች በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች በመንገድ ላይ ናቸው። ሁሉም ያሉበትን ደረጃ ማስተዋወቅም ይገባል።

በኮሪደር ልማቱ የተከናወኑ ተግባሮች በግልጽ የሚታዩ ቢሆኑም ቱሪስቶቹ ተዘዋውረው እንዲጎበኟቸው በማድረግ ላይ ቢሠራ ጎብኚዎች ወደ መጡበት ሀገር ሲመለሱ ሀገሪቱ ምን ያህል ለጎብኚዎች ምቹ ስለመሆኗ ማስገነዝብ፣ በዚህም እነዚህን ሥራዎች በማስተዋወቅ በቀጣይ የሚመጡ የውጭ ቱሪስቶችን ቁጥር ከፍ ማድረግ ያስችላል!

አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You