‹‹እናት…እናት ዳቦ ግዥልኝ… አባት ማስቲካ ግዛኝ››

በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻችን ውሰጥ ወላጅ እና አሳዳጊ ያጡ ሕጻናትን በየጎዳናው ማየት የተለመደ ነው። አንጀታቸው ታጥፎ፤ ከንፈራቸው ደርቆ፤ እግሮቻቸው በጸሃዩ ግለት እና በአቧራው ቆስለው፤ በወላጅ ፍቅር ልባቸው ተሰብሮ በየጥጋጥጉ በክረምት ዝናቡ፤ በበጋ ፀሃዩ ሲፈራረቅባቸው ማየትም አዲሳችን አይደለም።

በተለይ በክረምት ባልበላ አንጀታቸው አህያ የማይችለው ዝናብ ሲቀጠቅጣቸው ማስተዋሉ እጅግ አንጀት የሚበላ ጉዳይ ነው። ያልተገደበ ነጻነት አለን ብለው ቢያምኑም፤ ይሄ ነጻነት ግን ማስተዋል በሌለበት እድሜ እንደመሆኑ ሕይወትን ሊያበላሽ ብሎም ወዳልተፈለገ የሕይወት መስመር ሊወስድ አንደሚችል ከማንም አይሰወርም።

”ይሄው ነጻነት ተብዬ” አብዛኞቹ የጎዳና ሕጻናት ወደ ሱስ እንዲያመሩ መንገድ ይከፍትላቸው። በርግጥ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ቢኖሩም ዋነኛው ግን ኃላፊነት የሚሰማው ከልካይ ማጣታቸው ነው። ጠዋት ሲነሱ ምን እንደሚያደርጉ ምን እንደሚበሉና እንደሚጠጡ የሚያስብላቸው፤ ስለእነርሱ የሚሟገት እና አለኝ የሚሉት ደራሽ ወገን የላቸውም።

ብዙዎቹ ጎዳና ላይ ያሉ ሕጻናት ስለ ነገ አያውቁም። ከእንቅልፋቸው ሲነቁ ተማምነውት የሚነሱት እጆቻቸውን የሚዘረጉላቸውን ደጋግ ልብ ያላቸው ሰዎች ነው። በለስ ሳይቀናቸው ከቀረ እና ደጋግ ያልናቸው ሰዎች ከሌሉ ጦማቸውን ውለው ያድራሉ። ጎዳናው ለጎዳናነት ብቻ ስለተሰራ ለነሱ ሲርባቸው ምግብ፤ ሲጠማቸው ውሃ፤ ሲበርዳቸው መሸሸጊያ ሊሆንላቸው አይችልም።

የምኖረው እና የምሰራው በመሃል ከተማ በመሆኑ በየዕለቱ ውሎዬ እንዲህ ያሉ ልጆችን የማግኘት ዕድሌ ሰፊ ነው። ፊታቸው ገርጥቶ አንጀታቸው ታጥፎ ሳይ ልቤ ያዝናል። እንደ ሰው ያለኝን ሰጥቼአቸው ባልፍም የኔ ሽርፍራፊ ሳንቲም ሕይወታቸውን በሚፈለገው ደረጃ እንደማይቀይር ስለምረዳ አዝናለሁ።

አሁን አሁን ደግሞ በስፋት እንደምናየው ዩኒፎርም የለበሱ ‹‹እናት ዳቦ ግዥልኝ..እ.እ አባት ማስቲካ ግዛኝ›› የሚለውን ቃል በአሳዛኝ የፊት ገጽታ አጅበው የሚያሰሙ የሕጻናት ቁጥር በርክቷል።

በየጎዳናው ዩኒፎርም የለበሱ እና ነግደው ለውጠው ቤተሰብ ለማስተዳደር አይደለም በእጃቸው በቅጡ መጉረስ ይችላሉ ተብሎ የማይገመቱ ሕጻናት፤ ሰው በተሰበሰበበት እና በየታክሲ መያዥያው የማስቲካ ግዙኝ ጥያቄ ለአላፊ ለአግዳሚው ሲያሰሙ ይስተዋላል። ይህ ብቻ አይደለም፤

‹‹እናት የቤት ኪራይ ጎድሎብኝ ነው… እናቴ ባትቸገርብኝ እኮ አላስቸግርሽም ያለሽን ስጭኝ›› የሚሉ ሕጻናት በየጥጋጥጉ ወዲያ ወዲህ ይላሉ። ሕጻናቱ አነሱም በዛም የሚኖሩት ቤትና አሳዳጊዎች አሏቸው።

ታዲያ በእነዚህ ሕጻናት ዙሪያ አንድ ጥያቄ ማንሳት አለብን፤ እውነት እነዚህ ልጆች ተቸግረው ነው? ወይስ ቤተሰቦቻቸው አስገድደዋቸው? አልያም ልጆቹ ገንዘብ ለምደው እና በአቻዎቻቸው ተገፋፍተው ነው? የሚለው መመለስ አለበት። ጥናት ስላላደረኩ ይሄ ነው ማለት አልችልም።

ከቢሮዬ ስወጣና ወዲያ ወዲህ ስል በተደጋጋሚ የማገኘው አንድ እድሜው ቢበዛ ሰባት ዓመት የሚሆን ልጅ አለ። ሁል ግዜ ጥያቄው አንድ ነው ‹‹የቤት ኪራይ ሙሉልኝ›› አንድ ቀን ጠጋ ብዬ አወራሁት እውነት የቤት ኪራይ ጎድሎብክ ነው? ወይስ ምንድነው? አልኩት።

ይሄንን ልል የቻልኩት በኔ ምልከታ የቤት ኪራይ በወር አንዴ የሚከፈል ነው። ልጁን ደግሞ የማየው በየዕለቱ ነው። ከልጁ ያገኘሁት መልስ ግን አስደንግጦኛል። ልጁ የሚኖርበት ቤት በየቀኑ የሚከፈልበት መኖሪያ ነው። እያልኩት ያለሁት አልጋ ቤት አይደለም። በቋሚነት የሚኖርበት ቤት ነው።

ቤተሰቦች እንዳሉትና እሱ ሁልግዜ ለምን ገንዘብ ከሰዎች እንደሚጠይቅ ጠየኩት። ‹‹ከትምህርት ቤት ስወጣ ሁልግዜ እለምናለሁ። እኔ ብቻ ሳልሆን ሁለት ወንድሞቼ በየእለቱ ከትምህርት ቤት ስንወጣ እንለምናለን። እናታችን መልካም ፊት የምታሳየንና እራት የምትሰጠን ብዙ ብር ስንሸቅል ነው። ካልሆነ ግን ራት ”ወፍ አለኝ…” ይሆናል ›› አለኝ ።

በልጁ ንግግር እጅግ አዝኛለሁ። አንዲት እናት ምን ቢቸግራት? ወይስ ምን ያህል ብትጨክን ነው ልጆቿን ከማስለመን አልፋ ምግብ የምትሰጠው ባመጡት ገንዘብ ልክ ሊሆን የቻለው። እንዳልኳችሁ ልጁ ልጅ ነው።

በየቀኑ ከሚያጋጥሙት ስድብ፤ ጩኸት እና መገፋትን እንዴት ተቋቁሞ እየኖረ እንዳለ አስደነቀኝ። እንደነገረኝ ከሆነ ወላጆቹ ያወጡለት ስም ቢኖረውም ትምህርት ቤት የሚለምነው ልጅ እየተባለ ነው የሚታወቀው። ስሙ ተሽሮ ሥራው ስሙ ሆኗል።

ወደ አይምሮዬ የመጣው ነገር ይሄ ልጅ ሲያድግ ምን አይነት ሰው ይሆናል? የሚለው ነው። ሥነ አዕምሮ ባለሙያዎች ሰዎች በልጅነታቸው የሚያዳብሩት (ዴቨሎፕ) የሚያደርጉት ባህሪ አለ። ይሄ ደግሞ ልጆች ተገቢውን ፍቅር እና እንክብካቤ ካላገኙ ነገሮችን ከራሳቸው ጋር በማያያዝ በራስ መተማመናቸውን እንዲያጡ እና መጥፎ ባህሪያትን እንዲያዳብሩ ያደርጋል።

በዝርዝር ለማስረዳት ያክል ላለፉት 17 ዓመት በሥነልቦና ሕክምና ሀገሯን ስታገለግል የኖረችውን ትዕግስት ዋልታንጉስ ሀሳብ ልዋስ። በአንድ መድረክ ላይ ስለ የአእምሮ ቁስለት (ትራውማ) ስትናገር፤ ‹‹ልጆች ነገሮችን የሚመዘግቡት በጥቁርና ነጭ ቀለም ነው። ማለትም አንድ ልጅ ቤተሰቦቹ ፍቅር የሚያሳዩት ልጁ ያስደሰታቸው ቀን ብቻ ከሆነ፤ ሕጻኑ የሚወደደው ሰዎችን ባስደሰተ ግዜ ብቻ ስለሚመስለው ዘመኑን በሙሉ ለመወደድ ሲል እራሱን ሳይሆን፤ ሰዎች የሚፈልጉትን እየሆነ ይኖራል ›› ።

ወደ ተነሳሁት ታሪክ ስመለስ ይሄ ትንሽዬ ልጅ ሲያድግ ምን አይነት ልጅ ይሆን? የዚህን ልጅ ብቻ አነሳሁት እንጂ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናት ጎዳናው ላይ በመዋላቸው ምን አይነት ሥነልቦና ያላቸው ልጆች ሊሆኑ እንደሚችሉ ጥናት መደረግ ያለበት ይመስለኛል።

ሀገር የምትቀጥለው በትውልዷ ነው። ትውልድ ላይ መስራት ካልቻልን ሊከሰት የሚችለውን ማወቅ ለኛ ለኢትዮጵያውያን ከባድ አይደለም። በትውልዶች መካከል ራስ ወዳድና ሀገር ጠል በሆኑ ሰዎች የሰዎች ሕይወት መጥፋት እና የንብረት መውደም ሲደርስ በዘመናችን አይተናል።

ሰዎች የተሰጣቸው ነው የሚመልሱት። ፍቅር ስንሰጣቸው ፍቅር፤ ጥላቻን ስንዘራባቸው መሪር በቀልን ይመልሳሉ። በቋሚነት ጎዳናው ላይ የሚኖሩ ልጆችም ሆኑ በከፊል ጎዳናውን ለሚያውቁ ሕጻናት ከፍቅር ይልቅ በንቀትና በጥላቻ መታየትን፤ ከመወደድ ይልቅ ሌባና ወሮ በላናቸው የሚሉ እሳቤዎችን፤ ከመፈለግ ይልቅ መገፋትን በየእለቱ የሚያስተናግዱ ናቸው። መቼም የዘራውን ለሚያውቅ ገበሬ ሰብልህ ሲደርስ ምን ታጭዳለህ? አይባልም።

በጎዳና ላይ የሚኖሩ ልጆች ለጤና ጉዳት፤ ለከፋ ጽዩፍ ባህሪያት እና ለጥቃት ተጋላጭነትን ጨምሮ ብዙ ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል። የጎዳና ተዳዳሪዎች በመኪና አደጋ ለሚመጣ የአካል ጉዳት፣ ለኤችአይቪ/ኤድስ፣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች፣ ለተላላፊ በሽዎች፤ ያልተፈለገ እርግዝና፣ ውርጃ እና የአባላዘር በሽታዎች ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ነው።

ሃይ ባይ ከልካይ በማጣታቸው እና በበዛ ነጻነታቸው ከሁሉም ለከፋውና ለችግሮች መነሻ ለሚሆነው የአደንዛዥ እፅ ሱስ ያጋልጣቸዋል። በየጎዳናው ጡት እና ጡጦ ከተው በኋላ በሃይላንድ ማስቲሽ እና ቤንዚን መሳብ የተለመደ ነው። በየትራፊክ መብራቱ አይኖቻቸው ደፍርሶ፤ ከንፈሮቻቸው ዝናብ ያጣ መሬት መስሎ፤ እግሮቻቸው ተሰነጣጥቀው እና ልብሶቻቸው ነትቦ ”እናት ዳቦ ግዥልኝ ወይም የምሳ ጎድሎብኝ ነው ሙይልኝ” የሚሉ ሕጻናትና ወጣቶችን ማየት የለመድነው ነው።

ብዙ የጎዳና ልጆች የተለያዩ ሱሶች ተጠቃሚዎች ቢሆኑም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በከፍተኛ ሁኔታ እየተስተዋለ ያለውና ከአብዛኛው የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች እጅ ላይ የምንመለከተው ማስቲሽ የሚባል መርዛማ ኬሚካሎችን የያዘ አደንዛዥ ነገርን ነው። ነገን ማየት ከቻሉ፡ እነኝህ ሕጻናት ናቸው ነገ ሀገሪቷን የሚረከቡት።

በአንድ የሥራ ጉዳይ ያነገርኳቸው ሦስት በአስራዎቹ መጀመሪያ ላይ ያሉ ልጆች ማስቲሹን የሚወስዱት ራሳቸውን ከብርድ እና ከረሃብ ለመከላከል እንደሆነ አጫውተውኛል። ታዲያ ግን ማስቲሽ የጤና እክል እንደሚያመጣ ታውቁታላቹ ስል ላነሳሁት ጥያቄ መልሳቸው “አዎ እናውቃለን” ነበር።

እስኪ ምን ሊያደርግ ይችላል? ስላቸው አንጀት እንደሚያጣብቅ ጉሮሮ ላይ ችግር እንደሚፈጥር ተቀባብለው አስረድተውኛል። እንደውም ከመካከላቸው አንዷ ከዚ በፊት በሩጫ ጎበዝ እንደነበረችና ማስቲሹን መውሰድ ከጀመረች በኋላ ግን ጥቂት ስትሮጥ ትንፋሽ እያጠራት መሆኑን አስረድታኛለች።

ይህ ከሆነ ታዲያ ለምን ማስቲሽ ትወስጃለሽ ለሚለው ጥያቄዬም፤ ሌሊት ሌሊት አጥንት ድረስ የሚዘልቀውን ብርድ አቅም በሌለው አካሏ መቋቋም ሲያቅታት በእርሷ እድሜ ያሉ የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች ማስቲሹን ብትወስድ ብርድ እንደማያገኛት አስረድተው እንዳስጀመሯት ነገረችኝ። አሁን ላይ ግን ማቆም ብትፈልግም እንዳቃታት አስተዛዝና አጫወተችኝ።

ሌላኛዋም ‹‹ስተወው እንቅልፍ እንቅልፍ ይለኛል የገዛ ራሴን ጭንቅላት መሸከም ያቅተኛል። ጥሩ እንዳልሆነ አውቃለሁ ግን ለመተው አቅም አጣሁ። ለዚህ ሱስ በቀን ከ60-120 ብር እናወጣለን። ማስቲሹን በምንስብበት ወቅት (እነሱ ሰንጦዝ ይሉታል) የተለያዩ ዓይነት ቀለማትና አስፈሪ ነገሮች ይታዩናል። የምንደርበው ልብስ ባይኖረንም ብርድ አይሰማንም፤ መጣላት መደባደብ ያሻናል፤ ለመስረቅ ድፍረት እናገኛለን››።

በመጨረሻም ምን ቢደረግላቹ አሁን ካላቹበት ሱስ መላቀቅ ያስችላቹኋል? ለሚለው ጥያቄዬም ‹‹መልካም ሰዎች ብናገኝ መማር በጣም እንፈልጋለን። መጠለያ ብናገኝ በተለይ ባህሪያችንን መረዳት ከሚችሉ ሰዎች ጋር የመኖር ፍላጎት አለን። ሰዎች ቢያቀርቡንና ጓደኛ ቢያደርጉን ደስ ይለናል” ነው ያሉኝ

በጎዳና ላይ መኖር መሰረታዊ ከሆኑት ምግብ ልብስ እና መጠለያ በተገቢው እና በበቂ ሁኔታ የማይሟሉበት ነው፤ እነዚህ ነገሮች አለመሟላታቸው በራሱ ከባድ የሆነ ሥነ ልቦናዊ ተጽእኖ የሚያሳድር ነው። በዛው ልክ ጎዳና ላይ ሚኖሩ ልጆች ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ይጋለጣሉ። ከዚህ ቀደም በተደረገ ጥናት ጎዳና ላይ ካሉ ሕጻናት መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ቢያንስ አንድ ሱስ እና የአእምሮ ጤና እክል እንዳለባቸው ተረጋግጧል። ቁጥሩ ቀላል አይደለም ከዚ ጋር ተያይዞ ወንጀሎች ይፈጸማሉ።

አደንዛዥ እጽ እና አነቃቂ እጽ በመባል ሱስ አምጪ የሆኑ ዕጾች በሁለት ይከፈላሉ። የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች በአሁኑ ሰዓት በስፋት የሚወስዱትን ማስቲሽ ስናይ የሚመደበው ከአደንዛዥ እጾች መካከል ነው። ነገር ግን ቁጥራቸው በማስቲሽ ተጠቃሚዎች ልክ ባይሆንም ልጆቹ ሌሎች ሱስ አምጪ የሆኑና ለጤና እጅግ ጎጂ የሆኑ እንደ ቀለም ማቅጠኛና ቤንዚን የመሳሰሉትን ይወስዳሉ።

ጎዳና ላይ ላሉ ልጆች ማስቲሽ ተጠቃሚ መሆን ግን እንደ ምክንያት ልንወስደው የምንችለው፤ ጉዳዩ በሕግ የማያስጠይቅ መሆኑ ነው። ለምሳሌ ሻጭም ከተጠያቂነት ነጻ ሆኖ ይሸጣል ተጠቃሚ የሆኑት ሕጻናትም ያለ ክልከላ ይሸምታሉ። ሌላኛው ለጉዳዩ መስፋት ምክንያቱ ዋጋው ቅናሽ መሆን እና ለማግኘት ቀላል መሆኑ ነው። ነገር ግን እነኚህ ልጆች በየአደባባዩ ሲገዙት፤ ሲሸጡት እና ሲስቡት ሲታዩ እንደሕገወጥ ተግባር ሊወሰድ ይገባል። በችርቻሮ የሚሸጡትንም ተጠያቂ ማድረግ በይደር የሚተው አይደለም።

ሕጻናቱ ጉዳዩን ቀለል አድርገው መውሰድ ይጀምሩና መውጣት ያቅታቸዋል። ይህም የሚሆነው አንዴ ሰዎች ሱስ አምጪ የሆኑ ዕጽዎችን መውሰድ ሲጀምሩ ሱሱን ለመውሰድ ያለማመዱት አዕምሯቸውን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯቸው ሱሱ እነሱን ማዘዝ ስለሚጀምርና ስለሚቆጣጠራቸው ነው።

ማስቲሹን በሚወስዱ ሰዓት ጥሩና ጥሩ ያልሆነን ትክክልና ትክክል ያልሆነን ነገር የሚለየውን የአእምሮ ክፍል ስለሚቆጣጠረው በአጠቃላይ በትክክል የማሰብና የመወሰን ችሎታን ይጎዳል። ልጆቹ ለማቆም በሚሞክሩበት ሰዓት የተለያዩ አካላዊ፤ ስሜታዊ፤ ስነልቦናዊ ጫናዎችን ያስከትልባቸዋል። ይህንን ጫና መቋቋም ካልቻሉ ተመልሰው ወደ ቀድሞው እሽክርክሪት ይገባሉ።

ከማስቲሽ ሱስ ለመውጣት ጊዜ ይፈልጋል። በሚተውበት ጊዜ ድብርት ስለሚከሰት ለዛ የሚረዱ መድሃኒቶችን መውሰድና የሚከታተላቸው ሰው እና የአእምሮ ጤና ሕክምና ባለሙያ ያስፈልጋል። እነዚህን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ልጆችን ከጎዳና አንስቶ ወደ ተስተካከለ የኑሮ ሁኔታ ለማምጣት ሥራ ስንሰራ የልጆቹን ሁኔታ፤ ስለሚወስዱት ሱስ አምጪ እጾች፤ ስሜቶችም ጭምር በደንብ ለይቶና እቅድ ነድፎ ማስቀመጥ ያስፈልጋል።

አዲስ አበባ ላይ ብዙ ግዜ በዘመቻ ልጆችን ከጎዳና ላይ የማንሳት ሥራዎች ተካሂደዋል። ነገር ግን የሚፈለገውን ያክል ለውጥ ማምጣት የሚቻለው በበቂ ሁኔታ የልጆቹን ሥነ ልቦና መረዳት የሚችሉ ባለሙያዎች እና የሥነ ልቦና ምክክሮች በአስፈላጊ ሁኔታ መስጠት ሲቻል ነው። ማኅበራዊና ሥነልቦናዊ ድጋፎች፤ የአእምሮ ጤና ሕክምና ተካተው ሊሰሩባቸው ይገባል።

ልጆቹን በታጠረ ግቢ ብቻ ማኖር ለብቻው ውጤት አያመጣም። በተጨማሪም ችግሩን ከስሩ ለማድረቅ ሁሉም ልጆች በየትምህርት ቤቶቻቸው የአቻ ግፊትን መቋቋም የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ መሰጠት አለበት። አሁንም በልመና ላይ ተግባር ላይ ለተሰማሩ ልጆች ለወላጆቻቸው ተገቢውን የኦኮኖሚ አቅም መገንባት እና የሥራ እድል መፍጠር ያስፈልጋል።

ልጆቹ አሁን ላይ ማስቲካ ግዥኝ በሚመስል መንገድ ልመናን መማራቸው ለቀጣይ ሕይወታቸው ቀውስ ስለሚሆን ልመናን የሚጸየፉ እና እንደነውር የሚቆጥሩ ትውልዶችን ለማፍራት በትምህርት ፖሊሲው ውስጥ ተካቶ መሰጠት አለበት። ጎዳናው ላይ የሚኖሩ ሕጻናትና ወጣቶች ለሕገወጥ ዝውውር እና ለፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ እንዳይሆኑ ለማድረግ የሚመለከተው መሥሪያቤት ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል።

ማኅበረሰቡም ለረሃባቸው ማስታገሻ ምግብ ሳይጥል ለቁሩ መሸሸጊያ ልባስ ሳያቀብል ማስቲሽ ተው ማለት ብቻ ሳይሆን በሚችለው ሁሉ ሕጻናቱን በመደገፍ ከጎዳና ማንሳት አለበት።

መክሊተ-ወርቅ

አዲስ ዘመን  ታኅሣሥ 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You