ሁሉም ዘመን አለው፤ የሚነግስበት፣ የሚበረታበት፣ ከሌላው ልቆ የሚወጣበት። ለሰው ልጅ ይህ የብርታት ዘመኑ ወጣትነት ነው። ልክ እንደሰው ልጅ አንዳንድ በሽታዎች የሚገኑበት ዘመን አላቸው። ያላወቃቸውን የሰው ልጅ በብዛት የሚያጠቁበት፤ የተያዘው ላይ የሚበረቱበት፤ ያልተያዘው የኔስ ተራ መች ይሆን ብሎ የሚርድበት ጊዜ አላቸው። በ1990ዎቹ በሀገራችንም ሆነ በዓለማችን የኤችአይ ቪ ወረርሽኝ የሰው ልጅ ሕልውናን የተፈታተነበት ወቅት ነበር።

ያኔ አብዛኛው ማኅበረሰብ በስማ በለው ስለቫይረሱ ከሚሰማው መረጃ ውጭ ብዙም ግንዛቤ አልነበረውም። ቫይረሱ የአብዛኛውን ቤት አንኳኩቶ ገፈት ቀማሹ በዝቶ በየአካባቢው የሀዘን ድንኳን የበዛበት ወቅት ነበር። ያኔ ወላጅ አልባ ሕጻናት በዝተዋል፤ በርካቶች የሚወዱትን አጥተዋል። ለሀገር ብሎም ለቤተሰብ ተስፋ የነበሩ ወጣቶች ለቫይረሱ ተጋላጭ ሆነዋል። ያኔ ታዲያ የቫይረሱ ግስጋሴ ሲበረታ ወጣቶች በየአካባቢው በክበባት በመደራጀት ለራሳቸውም ግንዛቤን ከመጨበጥ ተሻግረው ሌሎችን ወደ ማንቃት ተሻግረዋል። በሂደትም በሀገራችን በርካታ የወጣት ጸረ-ኤድስ ክበባት ተቋቁሟል። ከመሰል ወጣቶች ስብስብ መሃል የእሸት ጸረ-ኤድስ ክበብ አባላት ይገኙበታል።

ክበቡ ሲጀመር ዋነኛ ትኩረቱ የዘመኑ ትኩሳት የነበረው ኤችአይ ቪን መከላከል ላይ ነበር። ለዚህም በሙዚቃ፣ በድራማ፣ በአቻ ለአቻ ውይይቶች ሰፊ ሥራን ሰርቷል። ያኔ በበጎ ፈቃደኝነት የሚንቀሳቀሱት የክበቡ አባላት የሚያስፈልጉ እቃዎችን ከቤታቸው እያመጡ ጊዜና እውቀታቸውን ያለስስት እያዋጡ የበኩላቸውን አበርክተዋል። ከቆይታ በኋላ ክበቡ እሸት የወጣቶች ማኅበር ተባለ። በሂደት ከኤችአይቪ በተጨማሪ የወጣቶች የሥነ-ተዋልዶ ጤና ላይም መስራት ጀመሩ። ወጣቶቹ በራሳቸው ጥረት ሲፍጨረጨሩ ያዩ አጋዥ ድርጅቶች የወጣቶቹ እንቅስቃሴ ትኩረታቸውን ሳበው። የክበቡ መስራች አባላት አጋዥ ድርጅቶቹ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ሕጋዊ ድርጅት ሆነው መመዝገብ እንዳለባቸውና የድርጅት ቅርጽ መያዝ እንዳለባቸው አወቁ። እ.አ.አ በ2001 እሸት ችልድረን ኤንድ ዩዝ ዴቨሎፐመንት ኦርጋናይዜሽን በሚል ሥያሜ አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው ሕጋዊ ተቋም በመሆን ተመዘገበ፡፡

የእሸት ችልድረን ኤንድ ዩዝ ዴቨሎፐመንት ኦርጋናይዜሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ታረቀኝ ድርጅቱ ከብዙ አካላት ጋር በትብብር የሰራበትና የድርጅቱ ዋነኛ መታወቂያ የወጣቶች የሥነ-ተዋልዶ ጤና ላይ የሰሩት ሥራ መሆኑን ይናገራል። ለወጣቶች፣ ለሕጻናት እና ለሴቶች ልማት መስራት የድርጅቱ ዋነኛ ትኩረት ነው። ከክበብነት የተነሳው ድርጅቱ በየትምህርት ቤቱና በተለያዩ አካባቢዎች ክበባትን በማቋቋምና በመደገፍ ክበባቱ ወጣቱን እንዲደርሱ ሰርተዋል። የሥነ-ተዋልዶ ጤና ፕሮግራሞች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር የአቻ ለአቻ መማማር ላይ እንደሰሩና የተወሰኑ ወጣቶችን በማሰልጠን የሰለጠኑት ለሌሎች የሚደርሱበትን ሁኔታ ያመቻቹ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ማብራሪያ የወጣቶች ሥነ- ተዋልዶ ጤና ጉዳይ ብዙ ፕሮጀክቶች ከብዙ አካላት ጋር በትብብር የሰሩበት የድርጅቱ ትልቁ ፕሮግራም ነው። እሸት በዋናነት መከላከል ላይ በማተኮር ወጣቶች ለሥነ- ተዋልዶ ጤና ችግሮች እንዳይጋለጡ ሳይንሳዊ የሆነና ወቅቱን የጠበቀ መረጃን ተደራሽ ያደርጋል። አስቀድሞ ወደ አደጋ እንዳይገቡ የአቻ ለአቻ ትምህርቶችን፣ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ ሚኒሚድያዎችን በመጠቀም መረጃዎቹን ተደራሽ ያደርጋል። ይህን አልፈው አደጋ ውስጥ ሲገቡ ለወጣቶች የሚመች የሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ያግዛል። ድርጅቱ ለዚህ የሚሆን የሕክምና ተቋም ባይኖረውም ከሕክምና ተቋማት ጋር አብሮ ይሰራል።

ያልተፈለገ እርግዝና እሱን ተከትሎ ጥንቃቄ የጎደለው ጽንስ ማቋረጥ፣ በአባላዘር በሽታዎች መያዝ ወጣቶች በአብዛኛው እነዚህን አገልግሎቶች ፈልገው ወደሕክምና ተቋማት እንደሚሄዱ ጥናቶች መጠቆማቸውን የሚናገሩት አቶ ሲሳይ፤ ድርጅታቸው ወጣቶች ለእነዚህ ችግሮች እንዳይዳረጉ እንደሚሰራ ነው የጠቀሱት። ከዚህ አልፎ ችግር ውስጥ ሲገቡ ጥንቃቄ የጎደለው ጽንስ ማቋረጥና ሞት እንዳይከሰት አገልግሎቱን በተገቢው መልኩ በጤና ተቋማት የሚያገኙበትን ሁኔታ ያመቻቻል። ለዚህም ከጤና ተቋማት ጋር በቅርበት እንደሚሰራና እንደአስፈላጊነቱ ለጤና ተቋማቱ የአቅም ግንባታ ሥልጠናና ግብአት አንደሚያሟላ ያስታውሳሉ፡፡

በአዳማና በአሰላ የታዳጊዎች ማረፊያ “ሴፍ ስፔስ” አላቸው። ሥራው የተጀመረው በጥናት መሆኑን የሚናገሩት ሥራ አስኪያጁ አዳማ ከተማ ላይ ታዳጊ ሴቶች ምን አይነት ችግር አለባቸው የሚል ጥናት በማጥናት መጀመሩን ያስረዳሉ። በዚህም ከታዳጊዎቹ ከተለዩ ችግሮች መካከል ከጥቃት ነጻ የሆነ የመወያያ፣ የመጫወቻና ልምድ የመቀያየሪያ ቦታ አለመኖር አንዱ ነው። ለዚህም አብዛኛው ቦታዎች በወንዶች የተያዙ መሆናቸውን በመጥቀስ ለአብነትም ፑል ቤትን ያነሳሉ። “ፑል ቤት ደፍራ የምትሄድ ሴት ብትኖር እንኳን ትንኮሳ ይደርስባታል። በተመሳሳይ የእምነት ቦታዎች ትምህርት ቤቶች ከጥቃትና ከትንኮሳ ነጻ አይደሉም፡፡” ይላሉ። ከጥናቱ በመነሳት በአዳማ ከተማ አራት የታዳጊ ሴቶች ማረፊያ (ሴፍ ስፔስ) ተከፈተ። ማረፊያዎቹ ሁለቱ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሲሆኑ ሁለቱ ከትምህርት ቤት ውጭ ናቸው።

የማረፊያ ክፍልና የሞዴስ መቀየሪያ ያላቸው ናቸው። ታዳጊዎች እርስ በእርስ ሀሳብ የሚለዋወጡበት ምቹ ቦታም ነው። አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት ተማሪዎች የወር አበባ ሲመጣ ወደቤት ይሄዱ ነበር። ነገር ግን አገልግሎት መስጠት ከተጀመረ በኋላ ተማሪዎች በክፍሎቹ ሞዴስ ቀይረው ወደ ትምህርታቸው መመለስ እንደቻሉ ያስረዳሉ። በአዳማ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተገነቡት ሴፍ ስፔሶች ከትምህርት ቤቱ ክፍል በመጠየቅ የተሰራ ነው። በዛም ክፍሎቹን የማሳመር እቃዎችን የማሟላትና ሥልጠና የመስጠትና ሥራ በድርጅቱ አማካኝነት ተሰርቷል፡፡

በአርሲ አራት “ሴፍ ስፔሶች” የተቋቋሙ ሲሆን እነዚህ እሸት ከአጋር አካላት በተገኘ ድጋፍ የገነባቸው በመሆኑ ሰፋ ያለ ይዞታ እንዲኖራቸው ተደርጓል። በዚህም የመታጠቢያና የመጸዳጃ አገልግሎትን አካተዋል። ማረፊያዎቹ ተማሪዎቹ የሚስባቸው ሄደው የሚዝናኑበት እንዲሆኑ ትኩረት የተሰጣቸው ሲሆን በውስጣቸው አጋዥ መጽሀፍትና ሌሎች መጽሀፍት፣ ቲቪ፣ የጠረጴዛ ቴኒስና ሌሎች ጨዋታዎችን መጫወት የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ከወረዳ ዘጠኝ እስከ ወረዳ 12 ባሉት አራት ወረዳዎች እሸት ለረዥም ጊዜ የወጣቶች ሥነ-ተዋልዶ ላይ ሠርቷል። አሁንም በመስራት ላይ ይገኛል። ከዚህ ቀደም በአምቦና በሸዋ ሮቢት ፕሮጀክት ነበር። አሁን አፋር ክልል የትግራይና የአፋር አዋሳኝ ላይ የምትገኝ አብአላ ወረዳ ላይ እየሰራ ነው። በእዛ ሴቶች የምግብ ዋስትናቸው የተረጋገጠ እንዲሆን አካባቢው ግጭት የነበረበት ቦታ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሴቶች ተጎጂ ስለሆኑ በአካባቢው የተጎዱ ሴቶች የምግብ ዋስትናቸው እንዲረጋገጥ ለማድረግ እየሰራ ነው፡፡

ድርጅቱ ሱስን መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ሲሆን በተለይ የወጣቶች ሱሰኝነትን መከላከል ላይ ያተኩራል። ወጣቶች በሥራ ማጣትና ተስፋ በመቁረጥ ለሱስ ይጋለጣሉ የሚሉት አቶ ሲሳይ ይህ እንዳይሆን ሥራ ፈጠራ ላይ እንደሚሰሩ ይናገራሉ። ድርጅቱ ሱስ ውስጥ የገቡ ወጣቶች ወደማዕከል ገብተው ከሱስ ነጻ እንዲሆኑ ሱስ ውስጥ ያልገቡ ግን እና ተጋላጭ የሆኑ ወጣቶች የሱስ አስከፊነትን አስመልክቶ ሥልጠና ይሰጣል። ድርጅቱ ጫት ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ የሚናገሩት ሥራ አስኪያጁ የዚህ ምክንያትም መጠጥና ሲጋራ በመገናኛ ብዙሃን እንዳይተዋወቅ፣ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ እንዳይጨስ የሚከለከል ሕግ መውጣቱን በመጥቀስ ጫትን በተወሰነ መልኩ የሚገድብ ሕግ እንዲወጣ ድርጅታቸው ከሌሎች ጋር በመሆን መስራቱን ይናገራሉ። ሆኖም ይህ ሕግ በተወሰነ መልኩ ቢዘጋጅም እስካሁን ሕጉ እንዳልወጣና ድርጅታቸው ሕግ ሊወጣ እንደሚገባ እንደሚያምንና ለዛም እንደሚሰሩ ያስረዳሉ።

በቅርቡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሕግ መሻሻልን ተከትሎ ሰላም ላይ በስፋት እየሰሩ መሆኑን የሚናገሩት ሥራ አስኪያጁ በየጊዜው የሀገራችን ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን በማንሳት ወጣቶች የሰላም ዘብ እንዲሆኑ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ። በተለይ አሰላ አካባቢ አልፎ አልፎ ግጭቶች መኖራቸውን በማንሳት ድርጅቱ በአሰላ ፕሮጀክት ቀርጾ እንደሚንቀሳቀስና በአካባቢው ከሚገኙ የሀይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ስንቄዎች ጋር በመተባበር በአካባቢው ሰላም እንዲመጣ የበኩላቸውን አስተዋዕኦ ማበርከታቸውን ይናገራሉ። ድርጅቱ በሰላም ዙሪያ በሰራው ሥራ በርካታ እውቅና ማግኘቱን ይጠቅሳሉ። “በተለይ በሰላም ዙሪያ በሰራነው ሥራ ከአፍሪካ ሕብረት ያገኘነው እውቅና የምንኮራበት ነው” ይላሉ። አፍሪካ ሕብረት በመላው አፍሪካ ያሉ ድርጅቶችን አወዳድሮ ከሦስት ሀገራት ሦስት ድርጅቶችን ሲመርጥ አንዱ መሆናቸው ትልቅ ማበረታቻ ሆኗቸዋል። እሸት ወጣት የሰላም አምባሳደሮችን በመፍጠርና በማሰልጠን ለሰላም ማስከበር አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ማመቻቸታቸው ያስመረጣቸው ሥራ ነው፡፡

እሸት በአጋርነት የሚያምን ድርጅት ነው የሚሉት አቶ ሲሳይ ብዙ ጥምረቶች ውስጥ በአባልነት መንቀሳቀሳቸውና በንቃት መሳተፋቸውን ማሳያ መሆኑን ይናገራሉ። ለአብነትም ከ400 በላይ ድርጅቶችን ባቀፈው ሲሲአርዲኤ፣ በሥነተዋልዶ ጤና ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ሕብረት በሆነው ኮንሰርቲየም ኦፍ ሪፕሮዳክቲቭ ሄልዝ አሶሴሽን፣ ሥነ-ሕዝብ የአካባቢ ጥበቃና የጤናን ጉዳይ ላይ የሚሰራ ፖፕሌሽን ሄልዝ ኤንድ ኢንቫይሮመንት ኮንሰርቲየም፣ ዩዝ ኔትወርክ ፎር ሰስቴነብል ዲቨሎፕመንት የሚሰኝ በወጣቶች የተመሰረተ ኔትወርክ ውስጥ፤ ሰላምን ለማምጣት በወጣቶች የተመሰረተው ኡቡንቱ ፒስ ቢውልዲንግ አሊያንስ ውስጥ ከአባልነት አንስቶ በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለግላሉ። ሜን ኢንጌጅ ኢትዮጵያ 27 ድርጅቶችን በአባልነት የያዘ ንቅናቄን ድርጅታቸው በስትሪም ኮሚቴ ሰብሳቢነት እንደሚመራ ያነሳሉ። የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የወንዶች ተሳትፎ ወሳኝ ነው በማለት እንደሚንቀሳቀሱ ይናገራሉ። የጾታ ጥቃት አድራሾቹ በአብዛኛው ወንዶች ስለሆኑ የጾታ እኩልነትን ለማምጣት ሴቶች ላይ ብቻ መስራት ሳይሆን ወንዶች ላይም መስራት ይገባል። ወንዶችም የሴቶችን መብት እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ ለማድረግ እንደሚንቀሳቀሱ ያስረዳሉ፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ማብራሪያ የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ በሀገራችን በግጭት ጉዳት በደረሰባቸው ትግራይ፣ አማራና አፋር ክልል ተዘዋውረዋል። በዚህም በርካታ ወጣቶች የአካል ጉዳት አጋጥሟቸው ተመልክተዋል። የሰላም እጦት ዋና የችግሩ መንስኤ በመሆኑ ለቀጣይ ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳይፈጠር ሰላም ላይ ትኩረት ሰጥተው የመስራት እቅድ አላቸው፡፡በተለይ ሀገራዊ ምክክር፣ ትጥቅ ማስፈታትና በመሰል ጉዳዮች ላይ ወጣቶች ድምጻቸው እንዲሰማ ትኩረት ሰጥተው ይሰራሉ። እስካሁን በሀገራችን ከሰላማዊ ንግግር ውጭ በርካታ አማራጮች ተሞክረው ውጤት አላመጡም። አሁን ወጣቶች በንግግር ችግሮችን ለመፍታትና ጥያቄ ሲኖራቸው በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገርን እንዲለምዱ ለማድረግ ይሰራል። እሸት አባል በሆነበት ኡቡንቱ ፒስ ቢውልዲንግ አሊያንስ አማካኝነት ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ወጣቶችን በማሰባሰብ ወጣቶች ለሀገራዊ ምክክር እንዲቀርብ የሚፈልጉትን አጀንዳ በራሳቸው በወጣቶቹ እጅ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዲቀርብ ማድረግ ችለዋል።

ድርጅቱ አብዛኛው እንቅስቃሴው ከውጪ ለጋሽ ድርጅቶች ጋር የተያያዘ ስለሆነ እንደልብ ለመንቀሳቀስ የሚቸገርበት ሁኔታ መኖሩን የሚያነሱት አቶ ሲሳይ፤ በተወሰነ ድርጅት ጥገኛ ላለመሆን ከተለያዩ አጋዥ ድርጅቶች ጋር መስራትን እንደአማራጭ የያዙት መሆኑን ይናገራሉ። በቀጣይም ድርጅቱ የራሱን ገቢ የሚያመነጭበትን አማራጮች እቅድ አውጥተው ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ይገኛሉ። ከግንዛቤ ፈጠራ ሥራ በተጨማሪ አስፈላጊ ግንባታዎችን መገንባት ሲያስቡት የቆዩት መሆኑንና በቅርቡ ከሴፍ ስፔስ በተጨማሪ ጤና ጣቢያን መደገፍ መቻላቸውን ይገልጻሉ። የፕሮጀክታቸው አካባቢ በመሆኑ በተደጋጋሚ የማየት እድል የነበራቸውንና በውስጡ የተሟላ አገልግሎት ያልነበረውን ከአሰላ ወጣ ብሎ የሚገኘው ጢጆ ከተማ የሚገኘውን የጢጆ ጤና ጣቢያ ጉድለት ማሟላት ችለዋል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ ጤና ጣቢያው የተሟላ ቁሳቁስ እና የመብራት አገልግሎት ያልነበረውና በዚህም የተነሳ የሚሰጠው አገልግሎት የተዳከመ መሆኑን በማስተዋላቸው ለማገዝ ይፈልጉ ነበር። አብሮአቸው የሚሰራ ድርጅት ሲያገኙ ለእናቶች አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ተጨማሪ ክፍሎች ገንብተዋል፤ የሕክምና እና የቢሮ እቃዎችን ማሟላት ችለዋል። በዚህም በአካባቢው ካሉ ጤና ተቋማት አልትራሳውንድ ያለው የጤና ተቋም መሆን ችሏል። በዚህም በአካባቢው ከሚገኙ የጤና ኬላዎች በሪፈራል ሰዎች የሚታከሙበት ሆኗል። የመብራቱን ችግር ለመቅረፍ የሶላር ሲስተም በመግጠም የውሃ መስመሩ ተስተካክሏል።

ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት መስጠት ይገባል የሚሉት አቶ ሲሳይ ድርጅቱ በተመሰረተበት ወቅት ያኔ ወጣቶችን በአንድ ቦታ መሰብሰብ ይቻል እንደነበር ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት ወጣቶችን ኑ ከማለት ይልቅ አብዛኛው ወጣት እጁ ላይ በሚገኘው ሞባይል መጠቀም ይገባል። ለዚህም ሁለት የሞባል አፕሊኬሽኖችን አበልጽገዋል። አንደኛው አዶዬ ሲሰኝ ድርጅቱ በአዳማ በሚንቀሳቀስበትን አካባቢ አንዲት ሴት ጥቃት ቢደርስባት የት መሄድ እንዳለባት በቂ መረጃ ይሰጣል። ጥቃት የደረሰባት ታዳጊ ምን ማድረግ እንዳለባትና የት መሄድ እንዳለባት እንዲሁም አስፈላጊ ስልክ ቁጥሮችን የያዘ የሞባይል አፕሊኬሽን ነው። የአፕልኬሽኑ ተጠቃሚዎች ስለሥነ-ተዋልዶ ጤና መረጃም ያገኛሉ። በተመሳሳይ ሀዋሳ ታቦር ሰብ ሲቲ ላይ ያሉ አገልግሎቶችን የሚያሳይ ኢንጆኔ የተሰኘ የሞባይል አፕሊኬሽን ለምቷል። ሁለቱም አፕሊኬሽኖች በትንሽ ሞባይል ኔትወርክ እንዲሰሩና አንዴ ስልክ ላይ ከተጫኑ አለዳታ እንዲሰሩ ተደርገው መበልጸጋቸውን ይናገራሉ። እሸት በሰላም ዙሪያ፣ ታዳጊ ሴቶች ላይ የሚሰራውን እና የሴፍ ስፔስ ሥራውን አጠናክሮ የማስቀጠል እቅድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡

ቤዛ እሸቱ

 

አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You