አዲስ አበባ፦ በየአደባባዩ መንገድ ዘግተው የሚነግዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ስርዓት የማስያዝ ስራ እየተሰራ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ መደበኛ ያልሆነ ንግድ ስርዓት ማስያዝ ዳይሬክቶሬት አስታወቀ።
የዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳኛቸው ሉሌ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑና የቀበሌ መታወቂያ ያላቸውን በመለየት በየአደባባዩ በመንገድ ላይ ንግድ የተሰማሩ ዜጎችን ስርዓት የማስያዝ ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ዳይሬክቶሬቱ ደንብና መመሪያ ወጥቶለት ከተቋቋመ አስር ወር ሲሆነው፤ በዚሁ ጊዜ ውስጥ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ዕቅድ አዘጋጀቶ ወደ ስራ ገብቷል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በተያዘው የአጭር ጊዜ ዕቅድም በመዲናዋ በአስሩም ክፍለ ከተማ በዘርፉ የተሰማሩ 58 ሺህ ስድስት የመንገድ ላይ ነጋዴዎችን መመዝገቡን ተናግረዋል።
ከነዚህም መካከል በደንብና በመመሪያው መታቀፍ የሚችሉ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑና የቀበሌ መታወቂያ ያላቸውን 32 ሺህ 735 የመንገድ ላይ ነጋዴዎች ተለይተዋል። ከነዚህም ውስጥ በአስር ወር ውስጥ 16ሺህ 718 የመንገድ ላይ ነጋዴዎችን ወደ ስርዓት በማስገባት በተወሰነላቸው ቦታና ሰዓት የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር/ቲን ነምበር/ አውጥተውና እንደ ንግድ ፈቃድ የመለያ ባጅ ተሰጥቷቸው እንዲሰሩ ተደርጓል።
የተቀሩትንም እንዲሁ ወደ ንግድ ስርዓቱ የማስገባት ስራ ከተጠናቀቀ በኋላ ቀጣዩና የመጨረሻው ዕቅድ የሚሆነው ነጋዴዎቹን በመደገፍ፤ የገበያ ትስስር በመፍጠር፤ ቁጠባ እንዲቆጥቡና ሀብት እንዲያፈሩ በማድረግ እስከ ሁለት ዓመት ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል። ከሁለት ዓመት በኋላ ግን ሙሉ በሙሉ ወደ መደበኛ ንግድ እንደሚሸጋገሩ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በዘርፉ የተሰማሩት ነጋዴዎች በተወሰነላቸው ሰዓትና በተለየላቸው ቦታ ብቻ የሚሰሩ እንጂ በቦታው ላይ በአጣናም ይሁን በድንጋይ የመገንባት መብት የላቸውም። በተሰጣቸው የሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠቅመው ወደ መደበኛ ነጋዴነት መሸጋገር አለባቸው ይህ ካልሆነ ግን መደበኛና ግብር ከፋይ የሆነውን ነጋዴ ማዳከም ይሆናል። ስለሆነም መደበኛው ነጋዴ ሳይጎዳ፤ ለትራፊክ ፍሰቱም እንቅፋት ሳይሆኑ በተወሰነላቸው ጊዜና ቦታ ብቻ ሰርተው ከሁለት ዓመት በኋላ መሸጋገርና ለሌሎች ቦታ መልቀቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2011
በፍሬህይወት አወቀ