የተወለዱት በደቡብ ኢትዮጵያ ከአርባ ምንጭ ከተማ ወጣ ብላ በምትገኝ ጉማይዴ በተባለች ወረዳ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ትግራይ ክልል በሚገኙት ኲህያ እና ሳምሬ በተባሉ ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ደግሞ በአርባ ምንጭና ሃዋሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተምረዋል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በጥሩ ውጤት በማለፍ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ውጤት ቢኖራቸውም በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን መማር ሳይችሉ ይቀራሉ፡፡
ይልቁንም በማዕድን ሚኒስቴር ስር ለአጭር ጊዜ በተነደፈ ፕሮጀክት ውስጥ ተቀጠሩ፡፡ በዚህም ስራ ግን ብዙ አልገፉም፤ በሞያሌ በኩል ወደ ኬኒያ ተሰደዱ፡፡ በኬኒያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ከተማ ለስድስት ወራት ከቆዩ በኋላ ወደ ዩጋንዳ አቀኑ፡፡ ለስደተኞች የሚሰጠውን የትምህርት እድል በመጠቀም በአካውንቲንግ ዲፕሎማቸውን ያዙ፡፡ ዩጋንዳ በነበራቸው ንቁ ተሳትፎ አሜሪካ የመሄድ እድል አገኙ፡፡ በአሜሪካው ሩዝቤልት ዩኒቨርሲቲ ገብተውም በአስተዳደር ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ሰሩ፡፡
የዛሬው የዘመን እንግዳችን ምንም እንኳን ለኑሮ ሲባል ዜግነታቸውን ቢቀይሩም ላለፉት 36 ዓመታት ቀልባቸውም ሆነ መንፈሳቸው ከኢትዮጵያ ተለይቶ አያውቅም ነበር፡፡ መለስ ቀለስ እያሉ ሃገራቸው በምትፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ ቀድመው በመገኘት ሃላፊነታቸውን ሲወጡ ነው የቆዩት፡፡ በሚኖሩባት ሀገርም ሆነ ወደ ትውልድ ስፍራቸው በመመላለስ ኢትዮጵያን በሚመለከቱ ጉዳዮች ሁሉ በመሳተፍ ለሀገራቸው ዘብ ቆመዋል፡፡
እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት መንግስታት መካከል ድልድይ በመሆን ግንኙነታቸው እንዲጎለብት ሰርተዋል፡፡ በአሜሪካ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ በማስተባበር ለሀገሩ እድገት ተቀናጅቶ እንዲሰራ አስተባብረዋል፡፡ ለአብነትም የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የዲያስፖራውን ማህበረሰብ በማስተባበር ከፍተኛ መጠን ያለው የቦንድ ግዢ እንዲፈፀም ያበረከቱት አስተዋፅኦ ተጠቃሽ ነው፡፡
ይህንን ጥረታቸውን የያው የኢትዮጵያ መንግስትም ራሱ ከሚሾማቸው ዲፕሎማቶቹ እኩል ሀገራቸውን ወክለው እንዲሰሩ መረጣቸው፡፡ የአሜሪካ መንግስትም የግለሰቡን ንቁ ተሳትፎ እና በጎ አስተዋፅኦ በመመልከት ሁለቱን ሀገራት የሚያገናኙ የክብር አምባሳደር በማድረግ እውቅና ሰጧቸዋል፡፡ በዚህ መሰረትም ከሁለት አስርተ-ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ማህበረሰብን በመወከል የስደተኞች አስተባባሪ ሆነው ሰርተዋል፡፡ በተጨማሪም የአሜሪካ ምርጫ ቦርድ ሰራተኛ የሆኑት እኚሁ ግለሰብ ታዲያ በቅርቡ የተመሰረተውን የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች የተግባር ምክርቤት አባል በመሆን በውጭ የሚኖረው ዜጋ ለሃገሩ ልማት አስተዋፅኦ እንዲያበረክት የማስተባብር ስራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ከሰሞኑም አዲስ ዓመትን አስታከው ወደሀገራቸው ከገቡ ከ500 በላይ የሚዘልቁ ዲያስፖራዎች አንዱ ናቸው፡፡ ዲያስፖራው በኢትዮጵያ ባለው ቆይታ ለመከላከያ ሰራዊት የደምና የገንዘብ ልገሳ እንዲያደርግ ብሎም የታላቁ ህዳሴ ግድብ በአካል ጭምር በመጎብኘት ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል በማስተባበር ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእንግዳችን ከክቡር አምባሳደር በፍቃዱ ተረፈ ጋር በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገናል፤ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ ምንም እንኳን ዜግነትዎን ቢቀይሩም ከሶስት አስርተ-ዓመታት በላይ ለኢትዮጵያ ዘብ በመቆም ብዙ መስራቶት ይጠቀሳል። በተለይም ያለአንዳች ክፍያ በተጨባጭ የኢትዮጵያ ምስለኔ ሆነው ሲሰሩ የነበሩበት የተለየ ምክንያት ካሎት ያስረዱንና ውይይታችንን እንጀምር?
የክብር አምባሳደር በፍቃዱ፡- እኔ ይህንን የማደርግበት የተለየ ምክንያት ወይም ተልዕኮ ስላለኝ አይደለም። ብቸኛው ምስጢር ሃገሬን ከልቤ ስለምወድ ነው። መንግስት ሊለዋወጥ ይችላል፤ እኔ ግን የየትኛውም መንግስት ደጋፊ አልነበርኩም። ወይም ደግሞ የፓርቲ አባል አይደለሁም። ግን ካለው መንግስት ጋር በመሆን ለሀገሬ የሚገባኝን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለብኝ ስለማምን ነው በምችለው ሁሉ ድጋፍ ሳደርግ የነበረው።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ አጋጣሚ የክብር አምባሳደር ተብለው የተሾሙበትን ሁኔታ ያጫውቱን?
የክብር አምባሳደር በፍቃዱ፡– በመሰረቱ ማንም ከሀገሩ የወጣ ሰው ለሀገሩ አምባሳደር ነው። እኔም ያንን በማመኔ ነው ከሀገሬ ወጥቼ በቆየሁባቸው ዓመታት በሙሉ ያለማንም ጎትጓችነትና አስገዳጅነት ስለሀገሬ ስሟገትና ለሀገሬ እድገት ስለፋ ነው የቆየሁት። እርግጥ ነው ማንኛውም ሰው የክብር አምባሳደር መሆን የሚችለው የመጣበት ሀገርም ሆነ አሁን ያለበት ሀገር ይወክለናል፤ ይጠቅመናል ብለው እምነት ሲጥሉበት ነው። እኔም በዚያ መስፈርት አልፌ ነው ይህንን ማዕረግ ማግኘት የቻልኩት።
ከዚህም ባሻገር ይህንን ማዕረግ በሀገሪቱ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ፤ ልዩ ተሰጥኦ ያለው እንዲሁም ለሁለቱም ሀገር ጠቃሚ አገልግሎት መስጠትና የተመሰከረለት መሆን ይገባል። በዚህ መሰረት ለእኔ የተሰጠኝ ሃላፊነት በመንግስት ተወክሎ ከሄደው አምባሳደር ጋር ተመሳሳይ ነው። ልዩነታችን እኔ በበጎ ፈቃድ የማገለግል እንጂ ደመወዝተኛ አለመሆኔ ነው። እሱ በማይገኝባቸው የትኛውም መድረኮች ላይ እሱን ወክዬ የመሳተፍና በሙሉ ስልጣን የማገልገል ሚና አለኝ። ከእኔ ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ በተለያዩ ቦታዎች እያገለገልን ያለነው አራት ሰዎች ነን። በነገራችን ላይ የክብር አምባሳደር ሆነሽ ስትሰሪ የሁለቱንም ሀገራት ህልውና የማስጠበቅ ሃላፊነት አለብሽ።
አዲስ ዘመን፡- የአሜሪካና የኢትዮጵያ አሁናዊ ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱ ይነሳል። እርሶ እንደ አንድ የኢትዮጵያ ተወካይ ግንኙነቱ ወደዚህ ደረጃ እንዳይደርስ ሃላፊነታችንን ተወጥተናል ብለው ያምናሉ?
የክብር አምባሳደር በፍቃዱ፡- በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳሽው። እርግጥ ነው፤ የአሜሪካና የኢትዮጵያ ግንኙነት ዛሬ የተጀመረ አይደለም። ከመቶ ዓመታት በላይ የዘለቀ ነው። ግንኙነቱም በዲፕሎማሲ ብቻ የተወሰነ አይደለም። በተለይም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አልፎ ለጥቁር ህዝቦች ተወካይ ሆና ነው የግኑኝነታቸው አግባብ የቀጠለው። ይህ አሁን የመጣ አይደለም። ላለፉት መቶ ዓመታት በዚህ ደረጃ ነበር በአሜሪካም ሆነ በመላው የምዕራቡ ዓለም ተከብራ የቆየችው።
በተለይም አሜሪካ የራሷን ደህንነት ለማስጠበቅና ሽብርተኝነት ለማስወገድ በምታከናውናቸው ስራዎች ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ መናገሻ አድርጋ ነው ስትጠቀምባት የቆየችው። ለዚህም ነው ማንኛውም የአሜሪካ ባለስልጣን አፍሪካ መጥቶ ኢትዮጵያን ሳይጎበኝ የማይሄድ የነበረው። በአጠቃላይ እነዚህ ሁኔታዎች የሁለቱን ሀገራት አብሮ ለመስራት የነበራቸውን ፍላጎትና መከባበር ነበር የሚያሳየው። አሁን ግን ያንን ሁሉ ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ኋላ የመተው ዝንባሌ ነው በአሜሪካኖቹ በኩል የሚታየው። በፍጹም ኢትዮጵያ እንዳልነበረች ተደርጎ የመቁጠር ሁኔታም ይታያል። አሁን ላይ ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት የዋለችውን ውለታ የዘነጉት ነው የሚመስሉት። ይህ ሁሉ ውለታዋ ተረስቶ ዛሬ ግን ከጠረጴዛ ዙሪያ አልፎ ማዕቀብ ደረጃ መድረሱ በበኩሌ በጣም ያሳዝነኛል።
አንቺ ከጠየቅሽኝ ጥያቄ አንፃር ማዕቀቡን ለማስጣል ብዙ ሙከራ ተደርጓል። እየተደረገም ነው። ሙከራዎች አልቀሩም። ነገር ግን ህወሓትም ሆነ ሌሎች የኢትዮጵያ ጠላቶች በአሜሪካ ኮንግረስ ውስጥ በገንዘብ የተቀጠሩ ጉዳይ አስፈፃሚዎች ያሏቸው መሆኑ የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ከእለት ወደ እለት እየሻከረ እንዲሄድ ሰርተዋል። ይህንን የሚያስፈፅሙት ጉዳይ አስፈፃሚዎች ከተራ ስልጣን ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያለ ሃላፊነት ላይ የተቀመጡ ናቸው። አሁን ላይ እንደሰማሁት ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል የተዘጋጀው ሰነድ ለፊርማ ፕሬዚዳንቱ ጠረጴዛ ላይ ነው ያለው። ይህ ሁሉ እየተደረገ እንግዲህ ገንዘባቸውን ከፍለው ኢትዮጵያን ለማጠልሸት በሚሞክሩ የህወሓት ሃይሎች ነው። በመሰረቱ ህወሓትና ብዙዎቹ የአሜሪካ ባስልጣናት ባለፉት 27 ዓመታት የነበራቸው ግንኙነት ቀላል አይደለም። ያም ሆኖ ኢትየጵያ ግን ከሃያላን ሃገራቱ ጎን ቆማ ለአለም ሰላም ስትሰራ ነበር የቆየችው። ኢትዮጵያ በዚህ ደረጃ አለምአቀፍ ተቀባይነት እንዲኖራት የተደረገው በተሰራው የዲፕሎማሲ ስራ ነው። አሁን ላይ ግን ያ ሁሉ ተረስቶ ዶክተር አብይ ከመጣ በኋላ ነገሮች ተለወጡ።
አዲስ ዘመን፡- ይቅርታ ይህንን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
የክብር አምባሳደር በፍቃዱ፡– ግንኙነታቸው የሻከረበት ዐብይ ምክንያት ወቅታዊና ሊጠየቅ የሚገባው ጥያቄ ነው። እንግዲህ ከኢትዮጵያ ጋር እዚህ ደረጃ ሊያደርሳቸው የቻለው ባለፉት 27 ዓመታት በተሰራው ዲፕሎማሲ ስራ ነው። ከቀጠናውም ሆነ ከአህጉር ወጥቶ በአለም ላይ ተሰሚነታችን ትልቅ ነበር። እርግጥ የዲፕሎማሲ ስራው በቅርብ አልተጀመረም። አስቀድሜ እንዳልኩሽ ከመቶ ዓመት በላይ የነበሩ መሪዎች ሁሉ የኢትዮጵያን ትልቅነት አስመስክረዋል። አሁን ለየት የሚያደርገው ነገር ከአሜሪካ መንግስት ጋር በቅርበት ይሰራ የነበረው ሃይል ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጎን በመሰለፉ ነው።
በነገራችን ላይ ምዕራባውያን ሉዓላዊነትሽን የሚጋፉት የውስጥ ጥንካሬሽን እያዩ ነው። ኢትዮጵያ በአለም መድረክ ላይ ጠንካራ ሀገር ነች። ያ ሁኔታ የማይመቻቸው አሉ። ሌላው ሃገር ላይ ጣልቃ ገብተው በአስተዳደር ብቻ ሳይሆን በብሔር፤ በሃይማኖትና በመሳሰሉት ነገሮች እየገቡ የራሳቸውን የበላይነት ያሳያሉ።
እስካአሁንም እያሳዩ ነው። ኢትዮጵያ ላይ ግን አልቻሉም። በታሪክም የነበሩትም ሆነ አሁንም ያሉት መሪዎች በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ አልተደራደሩም። እጅ የሰጠ የለም። እናከብራቸዋለን፤ መከበርም እንፈልጋለን። እነሱ ግን የሚፈልጉት የራሳቸውን አስተሳሰብ ማስረፅ ነው። እንደእድል ሆኖ ኢትዮጵያ ላይ አጀንዳቸውን ማስፈፀም አልተቻላቸውም። ይህንን እድል አላገኙም። አሁን ደግሞ በሀገር ውስጥ በተነሳው የርስበርስ ጦርነት መንገድ አግኝተው እኛን ለመበታተን ያላዳረጉት ነገር የለም። ዛሬ ሀገራችን እሳት ዳር ላይ ነው ያለችው። ይሄ የሁላችንንም ውስጥ የሚያቃጥል ጉዳይ ነው።
አሜሪካም ሆነ ሌሎች ሀገራት በውስጥ የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅመው ቢገቡም የፈለጉትን ማድረግ አልቻሉም። የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ጠንካራ ነው። ‹‹የፈለገ ነገር ይቀራል እንጂ ህልውናዬን አልሰጥም›› የሚል መሪ ነው ያለን። ይህ ለኢትዮጵያ ከሚሰጠው እርዳታ በላይ ነው። እርዳታቸው ከሉዓላዊነታችን የሚበልጥ አይደለም። ክብርና ነፃነታችን ከምንም በላይ ነው። እኛ ነፃ ስለሆንን ነው ዛሬም ድረስ በነፃነትና በራስ መተማመን ዜጎችንን በዓለም ላይ የሚንቀሳቀሱት። ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን ብታዬ አሁንም ድረስ ተፅዕኖ አለባቸው።
በመሰረቱ በአፍሪካ ሀገራት ላይ የሚያደርጉት ጫና ዛሬ የመጣ አይደለም። ከቀኝ ግዛት ቢለቋቸውም በእጅ አዙር ዛሬም እያስተዳደሯቸው ነው የሚገኙት። ኢትዮጵያ ላይ ግን ይህንን ማግኘት አልቻሉም። አሜሪካም ሆነ የአውሮፓ ሃገራት በዚህች ሃገር ላይ አጀንዳቸውን እውን ማድረግ አልቻሉም። ይሄ ነው ዛሬ እዚህ ላይ ያደረሰን። ለምዕራባውያኑ ዛሬም አልተሸነፍንም። እርግጥ ነው ጦርነት ከፍተውብናል። እርስበርሳችን እንድንዋጋ አድርገውናል። እንደዚያም ሆኖ በሚፈልጉት መጠን ሊያተራምሱን አልቻሉም። ምክንያቱም የእኛ ህዝብ ትልቅ ነው። ታጋሽ ነው። አልበገር ባይ ነው። የእኛ ህዘብ ስንዴያቸው ሆነ መድሃኒታቸው ይቅር እንጂ ክብሩን ነው የሚያስቀድመው።
ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያ ፈረሰች ሲሉ እኮ ሶስት ዓመት ሊሞላ ነው። አንዴ ሲያቃጥሉ፤ አንዴ ደግሞ እርስበርስ ሲያባሉን፤ ሌላ ጊዜም ‹‹ያልተመረጠ መንግስት ነው›› በማለት ትርምስ ሲፈጥሩ ነው የቆዩት። ኢትዮጵያ ህዝብ አይስማማም ብለው ተስፋ አድርገው ለመበታተናችን ቢሰሩም ያሰቡት አንዱም ሳይሆን ነው የቀረው። እንዳውም ምርጫውም በሰላም ተጠናቀቀ። አሁንም በየበዓሉ ትርምስ ለመፍጠር ቢሞክርም አንዱም አልተሳካላቸውም። ይሄ የሚያሳይሽ ህዝቡ ካለው መሪ ጋር ተማምኖ ሀገሩን ለማሳደግ መቁረጡን ነው። እርግጥ ነው ዛሬም ድረስ ልዩነቶች አሉን። ግን ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው አንድነታቸውን አስመሰከሩ። ሰሙኑን ያየነው የመንግስት ምስረታ ይህንን የሚያረጋግጥልን ከመሆኑም ባሻገር ኢትዮጵያ ትሞታላች ብለው ላለሙ እጅግ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው።
በነገራችን ላይ አሜሪካ ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያን ምርጫ አላፀደቀችም። ይህ ሁኔታ በግሌ እንደ አሜሪካዊነቴ በጣም የሚያሳፍረኝ ነገር ነው። እንደ ኢትዮጵዊነቴ ደግሞ የሚያኮራኝ ተግባር ነው። በመሰረቱ አሜሪካ አፀደቀችው አላፀደቀችው በኢትዮጵያ ላይ የሚፈይደው ነገር የለም። ዋናው ህዝቡ ያመነውን የመረጠበት መሆኑ ላይ ነው። አሁንም የህዝቡን ቅቡልነት ያገኘ የመንግስት ምስረታ ነው የተካሄደው። ኢሬቻም ሆነ የመስቀልም በዓል በፍቅርና በሰላም መካሄዳቸው ህዝቡ አሁንም እንደቀድሞ በአንድነት ተከባብሮ መኖር የሚፈልግ ሰላም ወዳድ መሆኑን ነው። የመንግሰት ምስረታው እውን መሆን የኢትዮጵያን መፍረስ ለቋመጡ አካላት ውድቀት ነው።
ሌላው አብይ ጉዳይ ኢትዮጵያውያን ዛሬም አንድነታቸውንና ሉዓላዊነታቸውን አስጠብቀው መቆየት እንደሚሹ ያረጋገጡበት ጉዳይ ነው። ዶክተር ዐቢይ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ችግር ተከትሎ ያወጁትን የክተት አዋጅ መላው ኢትዮጵያዊ ተቀብሎ ዘምቷል። አሁን ላይ የሰሜኑን ጦርነት ለመግታት ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም አስተማማኝ የሆነ የመከላከያ ሃይል ለማፍራት እድል ሰጥቶናል። ይህ የሚያሳየው ህዝብና መንግስት አብረው መሆናቸውንና እየተናበቡ መሆኑን ነው። የሕዝብ ጉዳይ ነው። ዲያስፖራውም ቢሆን የቦታ ርቀት እንጂ በመንፈሱም ሆነ በአስተሳሰቡ ለሀገሩ ያለው ፍቅር በተግባር የሚገለፅ ነው። በፖለቲካ፣ በሃይማኖት፣ በብሔርና በቋንቋ ልዩነቶች ሊኖሩን ይችላሉ። ልዩነታችን እንደጠበቀ ሆኖ በሀገራችን ጉዳይ ላይ አንድ ነን። በጋራ ለመስራትና ችግሩን ለመጋፈጥ ዛሬ እኔን ጨምሮ በርካታ ዲያስፖራዎች ወደ ሀገራችን መግባታችን የዚሁ ማሳያ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ግን ደግሞ በተደጋጋሚ የሚነሳ ጉዳይ አለ። ይኸውም የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ህብረት የለውም የሚል ነው። ያም ደግሞ ለሀገሩ መሰረታዊ ለውጥ ተጨባጭ ድጋፍ ለማድረግ እንዳላስቻለው ይገለፃል። እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
የክብር አምባሳደር በፍቃዱ፡- እንዳልሽው ልዩነቶቻችን በአደባባይ ጎልተው የታዩበት አጋጣሚዎች እንዳሉ እሙን ነው። በዚህ ላይ በምን መልኩ መከራከር አስፈላጊ አይደለም። ከሁሉ በላይ የሚያሳዝነው ግን የሃሳብ ልዩነቶቻችን እንዳሉ ሆነው በባዕድ ሀገር እስከ ባንዲራ ማቃጠል የተደረሰበት ሁኔታ ነው። በእኔ በኩል በጎሳ መለያየታችን ሃገራችን እስከመካድ ያደርሰናል ብዬ አላምንም። እርግጥ ፖለቲካም ሆነ ሃይማኖት የተከበሩ ነገሮች ናቸው። እስካሁን እየጎዳን ያለው ባለፉት 27 ዓመታት የተዘራው የዘር ፖለቲካ ምክንያት ነው። አሁን ላይ ዲያስፖራው አላስተሳስር ያለው የዘር ካንሰር ነው። ሁሉም በየጎጡ የሚሰለፍበትና ልዩነታችን በአደባባይ ጎልቶ የታየበት ነው።
አሁን ላይ አይን ያወጣውና ወደ ጥላቻ የተቀየረው ይህ የዘር ካንሰር ነው። ያ ሁሉ የተከበረው ባህል ተረስቶ በአስነዋሪው ፖለቲካ ሳቢያ በድጋፍና በተቃውሞ ጎራ ተሰልፈን ነው ያለነው። ተከፋፍለናል። ይሄ ካንሰር ህወሓት ሃገሪቱን መምራት ከጀመረ ወዲህ የተፈጠረ በሽታ ስለመሆኑ ምንም የሚያጠያይቀን አይደለም። አሁን ላይ አሁን አዲስ የተመሰረተው መንግስት ይህንን ካንሰር ለማስወገድ ከልቡ ይሰራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁኝ። አሁን ላይ በየሃገሩ ያለው ዲያስፖራ ይዞት የሚወጣው ባንዲራ አሁን ላይ የደረስንበትን የመከፋፋል በሽታ በተጨባጭ የሚያሳይ ነው።
አንዱ አምበሳ ያለበትን፤ ሌላው ልሙጡን አንዱ ደግሞ ባለኮከቡን ይዞ ይወጣል። በመሰረቱ አንዲት ሀገር አንድ ባንዲራ ነው የሚያስፈልጋት። እኔ ካለኝ ሃፊነት አንፃር አንዱ ስሟገትበት የቆየሁበት ጉዳይ የዚሁ ባንዲራ ነገር ነው። በምሳተፍበት መድረክ ሁሉ ሁሉንም የሚያግባባ ባንዲራ እንዲኖረን ጠይቄያለው። በነገራችን ላይ ይህ የባንዲራ ጉዳይ አሁን በህይወት ያለነው ሰዎች ብቻ ሳይሆን የወደፊቱን ትውልድ ውዝግብ ውስጥ የሚከት ነው። አሁን ላይ እኮ ልጆቻችን ለሚጠይቁን ጥያቄ እንኳን መልስ የለንም። በአጠቃላይ ያን ሁሉ ችግር የፈጠረው ያለፈው መንግስትና ህገ-መንግስቱ ነው።
በውጭ የምንኖር አብዛኞቻችን ዘንድ ውስጣችን ከፍተኛ የሆነ መከፋፋል አለ። ከዚያም አልፎ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ በትግራይ ውስጥ ባለው ጦርነት ውጭ ያለነው አብረን ተደጋግፈን ችግሩን ከመቅረፍ ፋንታ በቤተክርስቲያን ውስጥ እንኳን ልዩነቶቻን ጎልተው እየወጡ ነው። ባይገርምሽ በቀጥታ ለእኔ መጥቶ ‹‹ኢትዮጵያዊ አይደለሁም›› ያሉኝ የትግራይ ተወላጆች አሉ። ይሄን ስስማ እጅግ በጣም ነው ያዘንኩት። ሰፋ አድርገው እንዲያስቡና ነገ የሚፀፅታቸውን ነገር እንዳያደርጉ ብዙ ለምኜያቸዋለሁ። እርግጥ ነው፤ እንዲህ የሚሉት ሰዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ ናቸው። አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ዝም ብለው የሚኖሩ ቢሆን በሃገራቸው ላይ አይደራደሩም። እዚህ ካለው ኢትዮጵያዊ እኩል እንጂ ያነሰ አይደለም የሚያስቡት። ኢትዮጵያ ስትጎዳ እንጎዳለን፤ ኢትዮጵያ ስትስቅ አብረን ነው የምንስቀው።
አስቀድሜ እንዳልኩሽ ዛሬ እኛ እዚህ የተገናኘነው ከወገናችን ጋር ደስታውን ብቻ ሳይሆን ችግሩን እንካፈል በሚል ነው። ከ500 በላይ የሚሆኑ ዲያስፖራዎች አባይ የእኛ መሆኑ ለማረጋገጥ ነው የመጣነው። በውጭ ያሉ አካላት በጉዳይ አስፈፃሚዎቹ ሴራ እንዳይታለሉ ምስክርነት ያለው ነገር ይዘን ለመሄድ ነው እዚህ የተገኘነው። ከዚያም ባለፈ በሌሎች ሃገራት የምቀናውን ኢንቨስትመንትን በተጨባጭ ለማምጣት የሚያስችል ስራ ለመስራት ነው ያቀድነው። ሌላው ይቅርና ጎረቤታችን ኬኒያ እንኳን በዲያስፖራው ሪሚታንስ ነው ኢንቨስትመንቷን ማሳደግ የቻለችው። በመሰረቱ ከኬኒያ በእጥፍ የሚበልጥ ዲያስፖራ አለን። ግን ሪሚታንሱን በአግባቡ ያለመጠቀማችን ነው ሀገራችንን በሚገባ ማሳደግ ያልቻልነው። ይህንን ሁሉ ዲያስፖራ እያለን ዛሬም ከረጂ ሃገራትና ደርጅቶች ስንዴ መለመን ባልተገባን ነበር።
በቂ ሃብት፣ እውቀትና እድሉ ያላቸው ዲያስፖራዎች አሜሪካ ውስጥ አሉ። በመሆኑም ያለውን የልዩነት ግድግዳ ሰብረን ተቀራርበን መስራትና ህዝባችንን ከድህነት ማውጣት ይጠበቅብናል። እርግጥ ነው ዛሬም ሆነ ትናንት በየሚዲያው ሳይጮሁ ውስጥ ለውስጥ ሃላፊነታቸውን የሚወጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን አሉ። ሆኖም የህወሓት ተላላኪዎች ከእኛ የሚሻሉት ባለፉት 27 ዓመታት በሰበሰቡት ገንዘብ ተጠቅመው ጉዳይ አስፈፃሚዎችን በመቅጠር ነጩ ቤተመንግስት ድረስ መግባት በመቻላቸው ነው። ይሄ ደግሞ ለዘላለም የሚዘልቅ አይደለም። አሁን ላይ መንግስት ተመስርቷል። ካቢኔም ተመርጧል። ስለዚህ ወደ ስራ ይገባል። ስራ ላይ ነን፤ አብረን እናስተካክለዋለን። እሳቱንም እናጠፋዋለን። ስናጠፋ ግን ለአንድ ጊዜ አይደለም። እስከወዲኛው ነው። ችግሩን ላይደገም እናልፈዋለን። ጥሩ ጥሩ በተሰራው ላይ እየገነባን የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የኢትዮጵያን ትልቅነት እናስቀጥላለን።
አዲስ ዘመን፡- በዲፕሎማሲው ረገድ በመንግስት በኩል ሊሰሩ ይገባል የሚሉት ነገር ካለ አያይዘው ቢጠቅሱልን?
የክብር አምባሳደር በፍቃዱ፡- እንዳልኩሽ ኢትዮጵያውያኖች ዲፕሎማሲ መስራት እንችላለን። አሳይተናልም። አሁን ግን ላለፉት ሶስት ዓመታት ዲፕሎማሲው ተዳክሟል እንኳ ባይባልም ግን ዘግይቷል። ያለፉት 27 ዓመታት በዘርና በቤተሰብ ነበር ዲፕሎማቶችን ሲሾሙ የነበሩት። በነገራችን ላይ አንድ አምባሳደር ሲሾም በዚያ ሰዓት ያለ መሪ ያገለግለኛል ብሎ የሚያምንበትን ነው የሚሾመው። ነገር ግን ከተሾመ በኋላም ቢሆን ስለዲፕሎማሲ እውቀት ሊያጎለብት ይገባል። የሚሄድበትን ሃገር ባህል ቋንቋ ማወቅ ይጠበቅበታል። ከአምባሳደር በታች ግን የሚሾሙት ዋነኛ ሃላፊነት ያለባቸው ዲፕሎማቶች ናቸው መሆን የሚገባቸው። እነኚህ ሰዎች የሚመደቡት በእውቀታቸውና በልምዳቸው ተመዝነው ነው ሊሆን የሚገባው። ይህ ካልሆነ በጣም ብዙ ችግር ይፈጥራል። ያም ቢሆን ሰው ከስራ ይማራል።
በዚህ ረገድ ቅሬታ ያለኝ እነዚህ ሰዎች መመደባቸው ችግር ባይኖርበትም ከመምጣታቸው በፊት እዛው ስልጠና ሊሰጣቸው ይገባል የሚል እምነት ስላለኝ ነው። በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ እስከ ሹፌር ድረስ ከዚህ ይሄዳሉ። አሁንም ቢሆን መሄዳቸውን ጠልቼ አይደለም። ግን መሰረታዊ የሚባሉ እውቀቶቸ ሊኖሩት ይገባል ባይ ነኝ። ግን በእኛ ሀገር ሲደረግ የነበረው በቤተሰብና በጥቅማጥቅም የተሳሰረ ምደባ ነው። ዛሬ ላይ አሜሪካ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ብትደውዬ መልስ አይሰጥሽም። ስልክ የሚያነሳ የለም። ይህ ችግር የኖረ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ከአምባሳደሩ ጋር ቁጭ ብዬ ተነጋግሪያለሁ።
የሰው ሃይል የለንም የሚል ምላሽ ነው የተሰጠኝ። በመሰረቱ ስልክ የሚያነሳው አካል ለሚቀርብለት ጥያቄ በተገቢው መልኩ ቋንቋውን አውቆ የማይሰራ ከሆነ አለማንሳቱ ነው የሚደገፈው። የኤምባሲው ማህበራዊ ትስስር ገፅ ላይ የእኔ ስልክ በመኖሩ በየቀኑ ይደወልልኛል። እኔ ሙሉ ቀን የምሰራበትና ደመወዝ የምከፈልበት ስራ ስላለኝ በስራ ሰዓቴ አላነሳውም። መልስ የምሰጣቸው ከስራ በኋላ ነው። ይህ በራሱ የሚፈጥረው ችግር አለ። አሁን እንዳውም ቴክኖሎጂ ምቹ ስለሆነ ዲፕሎማቱ ነው መስራት ያለበት። ይህንን የምነግርሽ በቅሬታም ነው፤ በተስፋም ነው። ያ ግን አልፏል። ከእንግዲህ በኋላ ከዚያ ተምረን ስራችንን ማሻሻልና ዲፕሎማሲያችን ማሳደግ ይገባናል።
አዲስ ዘመን፡- እንደ አጠቃላይ አሁን ላይ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ያዩታል?
የክብር አምባሳደር በፍቃዱ፡- እንደ እኔ እምነት ኢትዮጵያ ያለችው መስቀለኛ መንገድ ላይ ነው። ጥሩና ብሩህ ተስፋ ከፊቷ ይታያል። የዚያኑ ያህል ደግሞ ብዙ ስራ ይጠበቅባታል። በተለይ በዚህ በሰላም ላይ ያለው ችግር አሁን ከመንግስት ምስረታው በኋላ በመጀመሪያ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራ ጉዳይ ነው የሚሆነው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። መንግስት ሆደ ሰፊ እና ትዕግስተኛ መሆን አለበት። እየተጎዳም ስራውን መስራት ይጠበቅበታል። ይህንን ደግሞ ይሰራል ብዬ አምናለሁ። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ላለፉት 27 ዓመታት የተሰሩት ጥሩ ስራዎች እንዳሉ ሁሉ በጣም አስከፊ የተባሉ በደሎችን ፈፅመዋል። በዘር ያለ እውቀት ስልጣን ላይ መውጣት፤ የአሰራር ጉድለት በስፋት ነበር። ያንን ለማስቀረት አሁንም ብዙ ስራ ይጠይቃል። ይህም ታዲያ የመንግስት ስራ ብቻ አይደለም። የሁላችንም ሃላፊነት ጭምር ነው።
ይህንን ስራ ደግሞ በአንድ ወር ወይም በስድስት ወር የምንጠብቅ ከሆነ አይሆንም። ግን ተስፋ ሳይቆረጥ ከአሁኑ ጀምሮ ስራ መሰራት አለበት። በውጭ በኩል በተለይ የባንዲራ ጉዳይ አሳሳቢ ነው። ምክንያቱም ዲያስፖራውን አለያይቶ ያቆየው ጉዳይ በመሆኑ ነው። ስለሆነም መንግስት ለዚህ ጉዳይ ትኩረት እንደሚሰጠው ተስፋ አደርጋለሁኝ። የህዝቡን የልብ ትርታ በማድመጥ ምላሽ ይሰጡናል ብዬ አምናለሁኝ። በህዝበ ውሳኔም ሆነ በሆነ አሰራር መላ ሊያበጁለት ይገባል።
ሌላው ደግሞ ዲያስፖራውና የሀገሪቱ ህዝብ በሁለት መልክ መታየት የለበትም። ብዙዎቻችን በሰው ሃገር የተሰደድነው የተሻለ ህይወት ፍለጋ ነው። ሁላችንም ግን ሰርተን ሀገራችንን መለወጥ ነው የምንሻው። ይህንን በሚገባ መገንዘብ ይገባል። አንድ ዲያስፖራ ቢመጣ ቢያንስ በወር አምስት ሺ ዶላር ያጠፋል። ይህም ለሀገሪቱ ባለባት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ትልቅ ችግር ፈቺ ነው። በመሆኑም ዲያስፖራው በመንከባከብና ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ሀገርን ማሳደግ ይገባል። በነገራችን ላይ ውጭ የሚኖሩትን ባሉበት ሃገር መንከባከብ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ይህንን ማድረግ ስንችል ነው ዲያስፖራው በተጨባጭ ለሀገሩ ዘብ የሚቆመውና የአምባሳደርነት ሚናውን የሚወጣው።
ከዚህ ጋር አያይዤ መጥቀስ የምፈልገው ነገር የህዳሴው ግድብ ከተጀመረበት ጀምሮ ዲያስፖራውን በማስተባባር ከፍተኛ መጠን ያለው ቦንድ ግዢ ፈፅመናል። እኔ በግሌ እንኳን ከ200 ሺ ዶላር በላይ ቦንድ ነው ሽጬ ለአባይ ያስገባሁት። በጠቅላላው ወደ 600 ሚሊዮን ዶላር ነው በሁለት ዓመት ውስጥ ያስገባነው። የአሜሪከ መንግስት እስከሚያስቆመን ድረስ ገንዘብ ስናሰባስብ ነው የቆየነው። አሁንም እዛ ቦንድ ባንገዛም እዚህ የመጣነው 500 ዲያስፖራዎችን በሙሉ ቦንድ እንዲገዙ እየቀሰቀስን ነው ያለነው። ይሄ ቀላል አስተዋፅኦ አይደለም። አሁንም ሀገሩን ከዚህ በላቀ ማገልገል የሚፈልግ ዲያስፖራ አለ። በመሆኑም አዲሱ መንግስት ካለንበት ሃገር ሆነን በዘመናዊ መንገድ የገንዘብ ድጋፍ የምናደርግበትን ምቹ ሁኔታ ቢፈጥር የተሻለ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ሊያስተላልፉት የሚፈልጉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጦት?
የክብር አምባሳደር በፍቃዱ፡– ስለሰጠሽኝ እድል በጣም አመሰግናለሁ። እኔ በተለይ ለዲያስፖራው የማስተላልፈው መልዕክት ሀገራቸውን ለማሳደግ የየበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ነው። በጎ አድራጎት ከዶክትሬት ዲግሪ ከማግኘትም በላይ እርካታ የሚያሰጥ ነው። በመሆኑ በጎነት መልሶ የሚከፍል መሆኑን ደግሞ እኔ በህይወቴ አይቼ የምመሰክረው ነገር ነው። እኔ በስደት በሄድኩበት ሃገር እንኳን በበጎነት የሰራኋቸው ስራዎች ናቸው አሁን ላለሁበት ደረጃ ከፍተኛ ድጋፍ ያረጉብኝ። ባለሁበት ሀገር በምርጫ እስከመወዳደር ድረስ እድል ያገኘሁት በበጎ አድራጎት በማደርጋቸው ተግባራት አማካኝነት ነው። ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጀምሮ ከብዙ የአሜሪካ ባለስልጣት ጋር የመቀራረብ እድሉን አግኝቻለሁ። ይህ በማቀርባቸው ሃሳቦች ሁሉ ተቀባይነት እንዲኖረኝ አግዞኛል። በመሆኑም የሁሉም ዲያስፖራ ባለበት ሀገር ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የሀገሩን ተቀባይነት ከፍ ሊያደርግ ይገባል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡-ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ።
የክብር አምባሳደር በፍቃዱ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መስከረም 29/2014