የመግባቢያ ብያኔ፤
መዛግብተ ቃላት “አዋጅ”ን የሚበይኑት “በመንግሥት የሚደነገግና በይፋ ለሕዝብ የሚገለጥ ሕግ፣ ደንብ፣ ውሳኔ” በማለት ነው አዋጅን መደንገግና ማስነገር የመንግሥት ዋነኛ ሥልጣነ መብት ሲሆን፤ አዋጁን መታዘዝና መተግበር ደግሞ የሕዝብ ኃላፊነትና ግዴታ ነው አንድን አዋጅ የማስፈጸም ሥልጣን የሚሰጠው የመንግሥታዊ አካል ማንነትም በግልጽ ይወሰናል አዋጁን አንታዘዝም የሚሉ “እምቢተኞች” የሚዳኙበት ጉዳይም በሚደነገገው አዋጅ ውስጥ በዝርዝር ይሰፍራል ማንኛውም አዋጅ ለሕዝብ የሚደርሰው በጽሑፍ ሲሆን አዋጁን በደነገገው የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊ ፊርማና ማኅተምም የመጽናት ግዴታ አለበት “በዚህ ስልጡን ዘመን” መንግሥታዊ አዋጆች ለሕዝብ ጆሮ እንዲደርሱ የሚደረገው በተለያዩ የብዙኃን መገናኛዎች አማካይነት ስለሚሆን የተደራሽነት ችግሩ ፈተና አይሆንም
በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ የነበረው የአዋጅ ነገራ ዘዴ በእጅጉ የተለየና ለዛሬው “ዘመንኛ” ትውልድ ምናልባትም ፈገግ ሊያስደርግ ይችል ይሆናል ከሰው ቁመት እኩል የገዘፈ ነጋሪት የተሸከሙ አዋጅ ነጋሪዎች ወይንም ቃለ ዐዋዲዎች በርቀትና በቅርበት በሕዝብ መካከል እየተገኙ የአዋጁን ቃል ያደርሱ ነበር ሕዝብ የሚሰበሰብባቸው ምክንያቶች ገበያ፣ ሸንጎ፣ አፈርሳታና አውጫጭኝ ወዘተ. ሊሆኑ ይችላሉ
“አዋጅ! አዋጅ! የደበሎ ቅዳጅ! የሰማህ ላልሰማህ አሰማ!” በማለት የሰሚዎቻቸውን ቀልብ ከሳቡ በኋላ መንግሥታዊውን አዋጅ በጎላ ድምጽ ያስተላልፋሉ ቃለ ዐዋዲዎች ለምን “የደበሎ ቅዳጅን” በንግግራቸው ውስጥ እንደሚሰነቅሩ ለጊዜው ከንባቤ ምክንያቱን ማግኘት ስላልቻልኩ መረጃው ያለው አንባቢ ቢያሳውቀን ለዕውቀት ይበጀናል ሲወራረድና ሲወራረስ የመጣውን ይህንን ነባርና ባህላዊ የቃል ማስረጃ ለዋቢነት የጠቀስኩት እንደወረደ መሆኑ ስለዚሁ ምክንያት ነው
ለአብነት እንዲያግዝ መስከረም 11 ቀን 1901 ዓ.ም ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ወንጀለኛ ስለሚቀጣበት ሕግና ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከተውን አዋጅ ያስነገሩት በሚከተለው የመግቢያ መንደርደሪያነት ነበር “ስማ! ስማ! መስማሚያ ይንሳው! ያድባርን ያውጋርን ጠላት ስማ! ስማ! መስሚያ ይንሳው የማርያምን ጠላት ስማ! ስማ! መስሚያ ይንሳው የጌታችንን ጠላት” (ዝክረ ነገር፤ ብላቴን ጌታ ማኅተመ ስላሴ ወልደ መስቀል፤ ገጽ 71) በአዋጁ ውስጥ ለምን የማስፈራሪያና የርግማን ቃላት እንደተደረደሩበት ብርቱ ጥናት ስለሚያስፈልገው ይህንንም ሃሳብ የጠቀስኩት እንዳለ በጥሬው ነው
አጠቃላይና ዋናው የነገረ አዋጅ አስኳል ነጥብ አዋጅ የመደንገግ ሥልጣን ያለው መንግሥት መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል የአዋጅ ጉዳይ የመንግሥት ስልጣን ከሆነ ዘንዳ በዚህ ጽሑፍ ርዕስ ስለምን “አዋጅ የመደንገጉ ሥልጣን” ለሕዝብ ተላልፎ ሊሰጥ ቻለ? አንባቢያን ይህንን ጥያቄ ቢጠይቁ መብታቸው ነው “ሕዝብ” አዋጅ ተቀባይ እንጂ እንደምንስ በቃለ ዐዋዲ አማካይነት አዋጅ ደንግጎ ከመንግሥት ጆሮ ማድረስ ይቻላል? የሚል መከራከሪያ ቢቀርብም ትክክል ነው እናስ ርዕሱ የቀረበው ምን መልዕክት ለማስተላለፍ ተፈልጎ ነው? ዋናውና ተፈላጊው ጥያቄ ይሄ ስለሆነ ወቅታዊውን የሀገራችንን ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች እየጠቃቀስኩ “ሕዝብ አዋጅ የሚያውጀው በምን ምክንያትና ዘዴ ነው?” የሚለውን ጥያቄ ወደ ማብራራቱ ልዝለቅ
“ንጉሥ ቢለማ፤ ሀገር ይሰማ!”
ሀገራዊ ብሂሎች በአብዛኛው ዕድሜያቸው የሰነበተ ስለሚሆን ይዘታቸው ለዛሬው ዐውድ ላይመጥን ይችል ይሆናል ለምሳሌ ከላይ ባለው ሕዝባዊ አነጋገር ውስጥ “ንጉሥ” የሚለው ቃል የሚወክለው የመንግሥቱን ሥርዓትና ገዢዎችን ሲሆን “ሀገር” የተሸከመው ሰፊ ጽንሰ ሃሳብ ደግሞ ሕዝብን ለመግለጽ ነው የአባባሉ ፍቺም የሚከተለውን የመሰለ ይዘት ይኖረዋል “የተሻለ መንግሥታዊ ሥርዓት ከቆመና ፍትሕና ርትዕ ካልተጓደለበት ሕዝብ በመንግሥት ለሚደነገግለት አዋጅም ሆነ ለሚተላለፍለት ትዕዛዝ ታዛዥና ተገዢ ይሆናል” ማለት ነው በአንጻሩም ሕዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ ከሆኑ እንኳን መደማመጥና መቀባበል ይቅርና ውጤቱ ሌላ ስለመሆኑ “ሀገር ቢያብር ንጉሥ ያስቸግር” የሚለውን ተቃራኒ ብሂል ማስታወስ ይቻላል
ይህ ማለት ግን የሀገሪቱ ሕዝብ በምልዓትና በአንድ ልብ ተባብሮና በአንድ ገጽ ተናቦ የመንግሥትን ትዕዛዝና አዋጅ በሙሉ አሜንታ ተቀብሎ ይተገብራል ማለት አይደለም ከብስል ንፍሮ ጥቂት ያልበሱ ጥሬዎች፣ ከታረመ ማሳም አረም እንደማይጠፋ ሁሉ ከሕዝብ መካከልም አሳማኝ ምክንያት ኖሮትም ይሁን ሳይኖር ለተቃውሞ የሚፈጥን፣ በእምቢታ የሚጨክንና ለአድማ የሚፈጥን ወገን መኖሩ የተለመደና የሚጠበቅም ነው ጥያቄውን አገላብጠን እንየው “ብዙኃኑ ሕዝብ” የመንግሥትን ትእዛዝና አዋጅ ማክበሩና መተግበሩ እንደተጠበቀ ሆኖ “ሕዝብስ አዋጁን ለመንግሥት የሚያደርሰው እንዴት ነው?” መሠረታዊው ጥያቄ ይኼ ነው
የሕዝብ አዋጅ ዝምታ ነው፤
ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ፈጸሙ የተባለውን አንድ በተለምዶ ተደጋግሞ የሚጠቀስ ታሪክ እናስታውስ ንጉሠ ነገሥቱ በሕዝባቸው ላይ ተደጋጋሚ ግብር መጣላቸውን በመደበኛ አዋጅ አስነገሩ ይባላል አዋጁ በተነገረ ማግሥት በዘመኑ ቋንቋ “ጆሮ ጠቢዎቻቸውን” አሰማርተው “ሕዝቡ ስለ ተነገረው አዋጅ ምን ምላሽ እንደሰጠ” እንዲያጣሩ በሕዝቡ ውስጥ አሰማሩ ከተሰበሰበው መረጃ የተገነዘቡት ነገር ሕዝቡ በማጉረምረምና በተቃውሞ እየተንጫጫ ንጉሡን እያማ መሆኑ ተገለጸላቸው ይሄን ጊዜ ንጉሡ “እንግዲያውስ ሕዝቤ ግብሩ ከበደበት እንጂ ክፉ አላሰበብንም” በማለት ድጋሚ ሌላ አዋጅ አውጀው በሕዝቡ ላይ የግብር ጫና በማክበድ “ድጋሚ ሰላዮቻቸውን” በሕዝቡ መካከል በማሰማራት የሁለተኛ ዙር ግዳጅ ሰጧቸው
መልዕክተኞቹ ይዘው የመጡት ውጤት ከበፊቱ ተቃራኒ ነበር ሕዝቡ ምንም ተቃውሞም ሆነ ቅሬታ ሳያቀርብ ዝም ማለትን እንደወሰነ ሪፖርት የቀረበላቸው ጠቢቡ ንጉሥ እንዲህ አሉ ይባላል ሕዝብ በመንግሥት ላይ ተቃውሞውን፣ ቅሬታውንና ማጉረምረሙን ሳይፈራና ሳይሳቀቅ በይፋ ከገለጸ ክፉ ያለማሰቡ መገለጫ ነው ነገር ግን ሕዝብ በዝምታና አንደበቱን ሸብቦ ለተቃውሞም ሆነ ለቅሬታ እምቢኝ ካለ ክፉ አስቧልና መጠንቀቅ ይገባናል ስለዚህ የተጫነባቸው የግብር አዋጅ እንዲሻር ወሰኑ ይባላል ግሩም ምሳሌ ነው የመንግሥት አዋጅ በሕዝብ የዝምታ አዋጅ ተገለበጠ ይሏል እንዲህ ሲሆን ነው ወይንም “አዋጁን በአዋጅ” ማለትም ይቻላል ሕዝብ ተስማምቶና በአንድ ልብ ተግባብቶ የሚደነግገው አዋጅ ከመንግሥት የአዋጅ ድንጋጌ የሚለየው በዝምታና በቃል አልባ ኩሪፊያ መሆኑ ዋና መገለጫ ነው
አዲሱ የብልጽግና መንግሥታችን ሆይ!
የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደምን ቸርና መልካም ሕዝብ እንደሆነ ለመንግሥታችን ይጠፋዋል ብለን አንገምትም በርግጥም ብሩክ ሕዝብ ነው መከራ ሲወቅረው “በቀን ያልፋል ትእግሥት” እየተጽናና ውሎ ይገባል እንጂ ለአመጽ ተነሳስቶ እንደ ሌሎች ሀገራት እሳትና ጭድ ይዞ ከማለዳ እስከ ማምሻ ውሎውን አደባባይ አያደርግም ቢሮክራሲው “የደም እንባ ሲያስነባው” በሆድ ይፍጀው ብስለት ችሎ ያልፈዋል እንጂ “ቡራ ከረዩ እያለ” ጎዳና ላይ ወጥቶ ለአመጽ አይተባበርም
ትናንት ከእርሱ መካከል ወጥተው የተሾሙለት “ገዢዎቹ” በእብሪትና በትዕቢት ቁልቁል እያዩ ቢሯቸው ገብቶ ብሶቱን እንዳይተነፍስ እያዳፉ ሲገፈትሩት “ግዴለም! ቀን ያልፋል” እያለ ታዝቧቸው ያልፋል እንጂ አታካራ ገጥሞ ያለ አቅሙ ለቡጢ አይቸኩልም የኑሮ ቋጥኝ ከብዶ ሲያንገዳግደውም “እርሱ የከፈተውን ጉሮሮ እርሱው ይዘጋዋል” እያለ ቢያገኝ በልቶ ቢያጣ ተደፍቶ ያድራል እንጂ “ዘገር እየነቀነቀ” ይዋጣልን በማለት ከመንግሥት ጋር እልህ አይጋባም
የሕዝብ አዋጅ ዝምታ ነው ኩርፊያውንም የሚገልጸው በዝምታ ነው ሲብስበት ግን የሚያደርገውን ያውቅበታል ዐራት ዐሠርት ዓመታት ነግሦ የኖረው ፊውዳላዊ ሥርዓት በሕዝብ ቁጣ ተገርስሶ የወደቀው ከብዙ ትዕግሥት በኋላ “ዝምታው” ሲበረታበት ነበር ዝምታው ቋንቋ ሆኖ ንጉሡን ወደ ኅሊናቸው ሊመልሳቸው አልቻለም ስለዚሀም ፍጻሜያቸው እንደምናውቀው ሆኖ ተጠናቀቀ
ወታደራዊ መንግሥትም እንዲሁ በዝምታ የጀገነው የሕዝብ አዋጅ አልገባው ስላለ ችሎ ችሎ በገነፈለበት እለት የደረሰበትን ፍጻሜ እናስታውሳለን የትህነግ መራሹ “መንግሥታዊ” የውንብድና ቡድንም እንዲሁ የሕዝብን ዝምታ እንደ ፍርሃት ሲቆጥር ቢኖርም “የግፉ ጽዋ በሞላ ዕለት” እንደምን ተልከስክሶ እንደተዋረደ የትናንት ታሪክ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ያልተደመደመ ክስተት ነው
የሕዝብ የዝምታ አዋጅ የሚገለጠው በቁጣ በትር ብቻ ሳይሆን በፍቅርና በአቃፊነት ጭምር ነው አንዳንድ ያልመሸባቸውን ማሳያዎችን እንጠቃቅስ ስድስተኛው ብሔራዊ ሀገራዊ ምርጫ እንዳይሳካና እንዲኮላሽ በውስጥና በውጭ ጠላቶች ያልተሴረና ያልታቀደ የተንኮል ዝግጅት አልነበረም ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ቢቻል በአመጽ ካልተቻለም በክሽፈት ጀንበሯ እንድታዘቀዝቅ ብዙ ሴራ ተጎንጉኖ ነበር ይህ ጨዋ ሕዝብ “ሙያ በልብ ነው” የሚለውን ነባር ብሂል እንደ መርህ በመውሰድ “በዝምታ አዋጅ” ምርጫው ያለምንም ኮሽታና የጎላ ችግር እንዴት እንደሰመረ እኛ መራጮችም ሆንን ተመራጩ መንግሥት በሚገባ እናስታውሳለን
ሕዝብ ልብ ለልብ የሚናበበው የትሥሥሩ ቁርኝት በእጅጉ የጠበቀ ስለሆነ እንጂ ብዙ ፖለቲከኞች ሰራነው በሚሉት ድርጅታዊ ብልሃት እንዳይደለ ልብ ሊባል ይገባል እርግጥ ነው መንግሥታዊ ስልቶችና አሰራሮች ዋጋ የላቸውም ማለት እንዳይደለም ሊሰመርበት ይገባል
በሦስት ዓመቱ የሽግግር ወቅቶች እጅግ በርካታ የረቀቁ ሀገራዊ ቀውሶች በአሸባሪው ቡድን አማካይነት ሲፈጸሙ ሕዝቡ የዝምታ አዋጅ አውጆ “በቆይ ግዴለም!” መታገሱ የጨዋነቱ ማሳያ አንዱ አብነት ነው እንጂማ ግፍ የዋሉበት፣ መከራ ያሳዩት፣ የዘረፉትና የገረፉት በደጃፉ እየተሹለከለኩ ሲወራጩ እያስተዋለ በትእግሥት ባላለፈ ነበር የእኛን ሕዝብ ውበት የምናደንቀው ቀልባችንን ሰብሰብ አድርገን የጎረቤት ሀገራትን ተሞክሮ ስናስታውስ ነው
ብልጽግና ፓርቲ አዲሱን መንግሥት አዋልዷል ትልቅ ሀገራዊ ድል ስለሆነ ሕዝቡንም ሆነ መንግሥትን እንኳን ደስ አለን ማለቱ ተገቢ ነው እርግጥ ነው በብዙ ጉዳዮች መንግሥት ለሕዝቡ ይበጃል የሚላቸውን በርካታ አዳዲስና የሚሻሻሉ አዋጆችን በቅርቡ እንደሚደነግግ ይታመናል ይህ መንግሥታዊ ስልጣኑ ስለሆነ በአሜንታ ልንቀበለው ግድ ይላል
ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ዛሬም ድረስ ሕዝቡ በዝምታ ቋንቋ ያወጃቸው በርካታ አዋጆች ምላሽ እንዳላገኙ ጨከን ብለን ከመንግሥት ጆሮ ብናደርስ ተገቢ እንደሆነ እናምናለን በቀበሌ፣ በወረዳ፣ በክፍለ ከተማና በበርካታ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ አንድን ጉዳይ ለማስፈጸም ያለውን መጉላላት ሕዝቡ ጮኾ ጮኾ ሰሚ ስላጣ ትክት ብሎት የዝምታ አዋጅ አውጆ አፉን በመሸበብ እህህን ምርጫው አድርጓል ሃሜት ሳይሆን ጉዳይን ፈጥኖ ለማስፈጸም የሚቻለው በአንድ የሀገራችን ቋንቋ መናገር የሚቻል ከሆነ ብቻ ነው
በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይሄ ጉዳይ ይጠፋዋል ብሎ ማሰብ ራስን መሸንገል ነው የሕዝብ የዝምታ አዋጅ ገንፍሎ ገደቡን ከጣሰ አክብሮ የመረጠውን መንግሥት ማስደንገጡ ስለማይቀር አዲሱ መንግሥት በአዲስ አስተሳሰብ ራሱን ቢፈትሽ ይበጃል
የሀገሪቱ የፍትሕ ሥርዓት ልክ እንደ እመቤት ሆይ ፍትሕ (Lady Justice) ዓይኑ ተሸፍኖ ሕዝብ በየጓዳው እምባውን እየረጨ በዝምታ አዋጅ ራሱን ስላቀበ ተስፋ የተጣለበት መንግሥታዊ ሪፎርም ይህንን ተቋም የመጀመሪያ ሥራው አድርጎ “ቢሰራው” ጥቅሙ የጋራ ነው – ለመንግሥትም ለሕዝብም የሕዝብ ኩርፊያ በአደባባይ ከሚገለጥባቸው ሥፍራዎች መካከል የትራንስፖርት መናሃሪያዎችን አይቶ ብቻ ፍርድ መስጠት ይቻላል
ለሕዝብ የዝምታ አዋጅ ጥሩ መገለጫና ማሳያው ይህ ዘርፍ ስለሆነ መንግሥታችን ሆይ “አዋጁን በአዋጅህ” የምታቃናበት አንዱ ተቋም ይህ ነው ዝናብ አናቱን እየቀጠቀጠና የፀሐይ ንዳድ እየከካው “በዝምታና በአርምሞ ሠልፉን ሳያዛንፍ” በዝምታ አዋጁ ከራሱና ከፈጣሪ ጋር ብሶቱን እየተጨዋወተ ቀን የሚገፋ ሕዝብ ከሕዝባችን በስተቀር በየትኛው የዓለም ክፍል ይገኝ ይሆን? የዕለት እንጀራውንና ኑሮውን ግፈኞች በዋጋ ንረት ሲጠበጥቡት “ቀን ያልፋል እያለ” በዝምታው አዋጅ ጸንቶ የሚኖር ሕዝብስ ከእኛ በስተቀር ማን ይጠቀሳል
የብልጽግናው መንግሥታችን ሆይ! ሕዝቡ በችግሩ ላይ ያወጃቸው የትዕግሥትና የዝምታ አዋጆች የትዬለሌ እንደሆኑ አንተም ሆንክ እኛ አይጠፋንም በሕዝቡ ላይ የተደራረበው የዝምታ አዋጅ አንድ ቀን ገንፍሎ የሚወጣ ከሆነ ለእኛም ለአንተም ስለማይበጀን የተሸከምከውን ስም ኑርበት ስምህን ያሸከምካቸውን “ልጆችህንም” በአግባቡ እንዲያስተዳድሩ እግር በእግር ተከታተልልን
የፈረንሳዩ ንጉሥ የናፖሊዮን ቦናፓርቲ ታሪክ ለመደምደሚያ ሃሳብ ይመጥን ይመስለናል ናፖሊዮን ከወታደሮቹ ጋር በተፋፋመ ውጊያ መካከል ከጠላት ጋር እየተፋለመ እያለ አንዱ ፈሪ የእርሱ ወታደር ሞትን ሽሽት ፈረሱ ላይ ተቀምጦ ወደ ኋላ ሲፈረጥጥ አይቶ ኖሮ ወታደር አስልኮ በማስያዝ ፊቱ አስቀርቦት እንዲህ ሲል ጠየቀው ይባላል
“ስምህ ማነው?” ወታደሩም “ጌታዬ ስሜ ናፖሊዮን ይባላል” – “ጉድ ነው! ማን አልከኝ?”- “ጌታዬ ናፖሊዮን እባላለሁ!” – “ለምን መሸሽ ፈለግህ?” – “ ጌታዬ ፈርቼ ነው” – “እንግዲያውስ አልቀጣህም፤ ወይ ስሜን መልስ ወይ እንደ እኔ እንደ ናፖሊዮን ጀግና ወታደር ሁን” የብልጽግናው መንግሥታችን ሆይ! ለምትሾማቸው ሁሉ ይህንን መሰል መልዕክት አድርስልን ወይ ያበልጽጉን ካልሆነላቸውም ያዋስካቸውን የብልጽግና ስም መልሰው እንዳሻቸው ይሁኑ የሕዝብ አዋጅ ዝምታ ነው ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 29/2014