ታላቂቱ ሀገር ኢትዮጵያ ዙሪያዋን በአደገኛ እሾህ እንደተከበበች ጽጌረዳ ትመሰላለች። ጽጌረዳዋን ላያት ለተመለከታት መዓዛ ገጽታዋ ይማርካል። አላፊ አግዳሚው እሷን በቀላሉ አይቶ ማለፍን አይሻም። በርካቶች አንገታቸውን አስግገው ሊቃኝዋት ይሻሉ። ብዙዎች እጃቸውን አርዝመው ሊነኳት፣ ሊቆርጧት ይፈልጋሉ። ጽጌረዳዋ ግን በዋዛ አትገኝም፣ ዕልፍ አዕላፉን እንዳማለለች፣ ሺዎችን እንደማረከች በጽናት ትቆያለች።
ዛሬም የኢትዮጵያ አሁናዊ እውነታ ህልምና ቅዠት የሆነባቸው ጠላቶቿ አይሞከሬውን አጥር አልፈው ለመግባት ያስባሉ። እንደሾህ ዙሪያዋን በጀግኖች የተከበበች ድንቅ አገርን ዋጋ አቅልለውም የዘመናት ታሪኳን ለመናድ ያልማሉ። ኢትዮጵያ ግን ዛሬም እንደውቧ ጽጌረዳ በእሾህ አጥር ተከባለች። ድንበሯን ጥሰው መስመር እንለፍ ለሚሉ ልበ ተራሮች ማርከሻ የሆኑ ክንዶቿ ሀያልነትም እንደጠነከረ ነው።
ኢትዮጵያን በጉልበት ታግለው እንጣል ያሉ ታሪካዊ ጠላቶቿ ከእግሯ ስር ተንበርክከዋል። የሽንፈት ጽዋቸውን ከተጎነጩ በኋላም ዕንቅልፍ ይሉት በዓይናቸው ዞሮ አያውቅም። ሌት ተቀን የሚመኟትን ድንቅ አገር ከእጃቸው ሊያደርጉ በአቋራጭ መንገድ ሲያሳብሩ፣ ፍላጎታቸውን በገሀድ ሲያሳዩ ኖረዋል።
ኢትዮጵያን ላለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት በግፍ ሲያሰተዳደር የቆየው የህወሓት መንግስት ለነዚህ ሀይሎች ፍላጎት ቀኝ እጃቸው ሆኖ ቆይቷል። ይህ አገር ቸርቻሪ ቡድን የራሱን ጥቅም ከማስጠበቅ ያለፈ ስለወገን አክብሮትና ፍቅር ኖሮት አያውቅም።
ከሶስት ዓመታት በፊት በተባበሩ የህዝብ እጆች ስልጣኑን የተነጠቀው ህወሓት መንግስት ሆኖ አገር ሲያስተዳድር ያልፈጸመው የግፍ ድርጊት አልነበረም። የጭቃ ላይ እሾህነቱ ይበቃን ባሉ አትዮጵያውያን ታላቅ ተጋድሎ ስርዓቱ ከተገረሰሰ በኋላም አገር የማፍረስ አዲስ ውጥን ቀምሮ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
አሸባሪው ህወሓት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እንደዕብድ ውሻ መክለፍለፍ፣ መባዘኑን ቀጠለ። ለእስትንፋሱ መኖር ሳንባ ከሆኑለት ምዕራባውያነ ጉያ ለመወሸቅም የቀደመው አልነበረም። ከባህር ማዶ ያሉት የልብ ወዳጆቹ ከሀገርና ህዝብ ይልቅ የሽብርተኛ ቡድኑን፣ ትኩሳት ለመለካት አለንህ አሉት። እነሱ ደግሞ ለጥፋት ቡድኑ ሰፊ አመኔታን ለመቸር በቂ ምክንያት ነበራቸው።
ራስ ወዳዱ አሸባሪው ህወሓት ለዓመታት የፍላጎታቸው ርካብ፣ የደም ዝውውራቸው ወፍራም ስር ሆኖ ቆይቷል። ለዘመናት በእነሱ ሀሳብና ፍላጎት ሲመራና ካሻቸው መንገድ ሲያሻግሯቸውም ኖሯል። ሁለቱም በእከክልኝ ልከክልህ መርህ ቋንቋና ስሜታቸው በአንድ ተጋምዶ፣ በእኩል ተዛምዶ ዘልቋል።
ድንገታዊ ሀገራዊ ለውጥ ዕውን ከሆነ በኋላ ግን ታላቂቱ ኢትዮጵያ የሆነባትን አሳፋሪ ተግባር ላትመለስበት እምቢኝ፣ አሻፈረኝ አለች። ለሰፊው ህዝብ ነጻነትና እኩልነት የተከፈለው መስዋዕትነት ትርጉም ይኖረው ዘንድም በጠንካራ አቋሟ ጸናች።
ይሄኔ ቡድኑም ጨምሮ ቁርጠኝነቷን ያስተዋሉ ምዕራባውያን በውሳኔዋ ስጋት ገባቸው። ከአቋሟ ትወርድ ትንሸራተት ዘንድም ዙሪያ ገባዋን መነቅነቅ ስራቸው ሆነ። ኢትዮጵያን ግን ከቆራጥነቷና፣ ከጠበቀ የውሳኔ ጽናቷ የመለሳት አልተገኘም።
ለዓመታት ከአገራችን ጉያ ተወሽቀው ሀብት ንብረቷን የዘረፉ ቀማኞች የአገራዊ ለውጡ ተአምራዊ ጅማሬ ክፉኛ አስደነገጣቸው። ይሄኔ አገር በማፍረስ ተግባራቸው ሊመክሩ የተንኮል እቅድ ወጠኑ። ትልማቸውን ዕውን ለማድረግም መቀሌ ገብተው መሸጉ። ከመርዛማ ሀሳባቸው አንደኛው ደግሞ በትግራይ ክልል አስገዳጅ ምርጫን ማካሄድ ነበር።
ይህን ውጥን የተረዱ ባለውለታ አገራት አሁንም ከጎናቸው በመቆም ኢትዮጵያን ለማሸማቀቅ ሞከሩ። ለምርጫው እውቅና ይሰጠው ዘንድም ተጽዕኖ ለመፍጠር ትጋታቸውን አሳዩ። ኢትዮጵያ ግን ይህ አይነቱ ተልካሻ ሀሳብ ፈጽሞ አላሰጋትም። በትግራይ ለተካሄደው የማንአለብኝ ምርጫና ለተከተለው አስቂኝ ውጤት ቦታ እንደማትሰጥ ግልጽ አቋሟን አስታወቀች።
የነ አሜሪካ ዓይን ያወጣ ተጽዕኖ ሳይቀዛቀዝ አረመኔው የህወሓት ቡድን በገዛ ወገኑ ላይ የሸረበውን የሰሜን ዕዝ ጥቃት ተግባራዊ አደረገው። ከተቃውሞ ይልቅ ዝምታን የመረጡት የህወሓት ወዳጆች በጥቃቱ ጉዳይ አንዳች ባለመተንፈስ ማንነታቸውን በገሀድ አሳዩ። ኢትዮጵያ ግን የህልውና ዘመቻውን በቁርጠኝነት ጀመረች። የአሸባሪው የቀኝ እጆች ጉምቱ ባለስልጣናትን ጨምሮ በርካታ የጥፋት ሀይሎችን ህልም አመከነች።
አሁንም የነጮቹ ጥቁር ልብ ከተንኮል ስራ አልጸዳም። ረጃጅም እጆቻቸው በአባይ ጉዳይ ዘልቀው ያገባኛል ለማለት ፈጠኑ። ይህ ከተራ ሀሳብ በላይ የሆነ ውጥን የኢትዮጵያን ህጋዊ መብት በግልጽ የሚጋፋ ሆነ። ኢትዮጵያ እንደወንጀለኛ ተቆጥራ ያለወጉ በመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ፊት ቀረበች።
ይህ መሆኑ ብቻ ጠንካራውን አገር አልበገራትም። እንደውም ጥንካሬዋ ጎልብቶ ማንነቷን አሳየች። በሳልነቷ ፍሬ ያዘ። ትዕግስተኛነቷ በጀመረችው መንገድ እንድትቀጥል አጸናት። ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ህብረት አሰመልሳ ዳግም ችሎት አሰየመች። ይህ አጋጣሚ የነግብጽን ወስጠት አስደገጠ። ለዚህች ድንቅ አገር ታላቅ ድል፤ ውድቀቷን ለሚሹት ደግሞ አንገት የሚያስደፋ ሆነ።
ዙሪያ ገባውን የከበቧት የውስጥና የውጭ ጠላቶቿ ፈጽሞ አልተኙላትም። ጊዜ እየቆጠረ በሚሰየመው የጸጥታው ምክር ቤት ፊት ሊሞግቷት ቀጠሮውን ደጋገሙት። ኢትዮጵያ በቁርጠኝነቷ እንደጠነከረች፣ በማይረግበው አቋሟ እንደጸናች ዘለቀች። በሌላ ተንኮል ያልተሳካላት አሜሪካም አጋጣሚውን በብርቱ ፈለገችው። ‹‹ላደራድራችሁ›› በሚል ሰበብ ቁጭቷን ልትወጣ በማሰብ።
የድመት መነኩሴ መሆኗን ጠንቅቃ የተረዳችው ኢትዮጵያ ግን አመሏን እንደማትረሳ ቢገባት በጠነከረው አቋሟ ጸናች። በማንአለብኝነት በዓለም አደባባይ የተሞገተችው ሀገራችን አሁንም አሸናፊነቱን አላጣችም። እነ ሩሲያና ቻይና ከጎኗ ቆሙ። በመሰል ሀገራትም ዘንድ ሙሉ ልብ ተቸራት።
እነ አሜሪካ ለውጥናቸው ያልተንበረከከችውን ኢትዮጵያን በእጃቸው ለማስገባት የሚያደርጉት ሩጫ ፍጻሜ አላገኘም። አፍሪካዊቷ አገር እንደ መሰሎቿ በይሁንታ ሸብረክ ያለማለቷ ክብራቸውን እየነካው ነው። ይህ አይነቱ እውነት ምዕራባውያኑን ጭምር ማትከን ፣ ማበሳጨት ይዟል።
የድርድሩን መልክ ቀይረው ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ማዛመድ የፈለጉት ሀይሎች ስራቸውን ቀጥለዋል። ኢትዮጵያ በተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛነቱን ካወጀችለት የጥፋት ሀይል ጋር የጠረጴዛ ውይይትን እየፈለጉ ነው። ይህ ከቃላት በላይ የሆነ ድፍረት የሀገራችንን አቋም አልሸረሸረም። በምክንያታዊ ማሳያዎች ለሀሳባቸው ተገዢ እንደማትሆን ቁርጥ ውሳኔዋን አስታወቀች።
ይህ ቁርጠኝነት በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብነትን የለመዱትን አሜሪካና ምዕራባውያንን ሴራ የሚያጋልጥና እርቃናቸውን የሚያስቀር ሆነ። ዕንቅልፍ የለሾቹ ሀገራት ኢትዮጵያን ጠልፎ የሚጥል ወጥመድ መሸረባቸውን ቀጠሉ። ማዕቀብ ለመጣል፣ ብድር ለመከልከል፣ እርዳታ ላለመስጠት ብዙ መከሩ፣ ተማከሩ።
ኢትዮጵያ በጀመረችው የህልውና ዘመቻ እውቅና መስጠት ሞታቸው የሆነው አካላት ለአሸባሪው ይሁንታን ለመቸር ቅርብ ሆኑ ። በየቀኑ ለሚፈጸመው ኢሰብአዊ ድርጊት በዝምታ አፋቸውን ሸብበውም ለቡድኑ ትንፋሽ መቀጠል አቅም ሆኑ።
በኢትዮጵያ ምድር ለተለያዩ የሰብአዊ አገልግሎቶች እግራቸው የረገጠ አንዳንዶች ከመጡበት ዓለማ ውጭ ሲንቀሳቀሱ እንደቆዩ ታወቀ። አልሚ ምግቦች በመለገስ፣ መገናኛ ሬዲዮ በመስጠት፣ ሀሳብና ምክር በማካፈል ለሽብርተኛው ቡድን አጋር መሆናቸውን አሳዩ።
የረድኤት ሰራተኞቹን ህገወጥ ድርጊት በንቃት ስትቃኝ የቆየችው ኢትዮጵያ ከቁርጥ ውሳኔ ለመድረስ የማንም ምክር አላሻትም። በውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ ገብተው ሲንቀሳቀሱ የቆዩትን ሰባት የውጭ አገር ዜጎች ከሀገሯ ለማስወጣት ከቁርጥ ውሳኔ ደረሰች። ይህ ውሳኔ የመንግስታቱ ድርጅትን ጨምሮ በርካታ አገራትን ማስደንገጡ አልቀረም።
በ72 ሰዓታት ከአገር እንዲወጡ ከተወሰነባቸው ሰባት የረድኤት ሰራተኞች መካከል ከከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ የነበሩ ይገኙበታል። እንዲህ አይነቱ ቁርጠኝነት በብዙዎች ዘንድ ያልተለመደ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ አንቶንዮ ጉተሬዝን ጨምሮ በርካቶች መደናገጠቸውን ገለጹ። ኢትዮጵያ ግን ከእነሱ ልብ መደንገጥ ይበልጥ ለራሷና ለዜጎቿ ደኅንነት ስጋት መሆናቸውን ገልጻ ውሳኔዋን ዕውን አደረገች።
እነሆ! በታላቅ ፈተና ውስጥ ያላቸው ታላቂቱ አገር አሁንም እንደ ጽጌረዳዋ በአደገኛ፤ አሾሆች ተከባለች፣ ዛሬም በርካታ ጠላቶቿ ዙሪያ ገባዋ ቆመዋል። ሀያላን መንግስታት በክንዳቸው ሊደቁሷት ማስፈራራታቸውን ቀጥለዋል። ጦርነት፣ መፈናቀልና ችግር አብረዋት ዘልቀዋል።
ኢትዮጵያ ግን በአዲስ ምዕራፍ አዲስ የለውጥ ጎዳና ላይ ትገኛለች። ግፈኛውን የህወሓት አገዛዝ ታሪክ ያደረገው አዲስ መንግስት ተመስርቶም የተስፋ ብርሃን ፈንጥቋል። የጠላቶች ክንድ ቢበረታ፣ የሀያላን ፍላጎት ቢያይል ጥንካሬዋ አይጎድልም። ማንነቷ አይሻርም። አዎ! እናት አገር ኢትዮጵያ ቆራጥነቷ ይቀጥላል። በጀግንነት ዘመኗን ዋጅታ በታላቅ ስሟ ትጓዛለች።
ከአትጠገብ
አዲስ ዘመን መስከረም 29 ቀን 2014 ዓ.ም