ኢትዮጵያ በታሪኳ የተለያዩ መንግስታትን አይታለች። ከአጼው ስርዓት ጀምሮ እስከ ለውጡ መንግስት ዋዜማ ድረስ በተለያዩ የመንግስትና የፖለቲካ ፍልስፍና ውስጥ አልፋለች። በዚህ ሁሉ የመንግስታት መለዋወጥ ውስጥ ኢትዮጵያ የሚለው ስም ትልቅ ጉዳይ ሆኖ ከትላንት እስከ ዛሬ መጥቷል። ቅሉ ግን ኢትዮጵያዊነትን በሚገባው ክብር ልክ በተገቢው መንገድ ያስኬደ አንድም አለመኖሩ ነው።
በተለይ ከለውጡ መንግስት በፊት ያሉት ሁለቱ መንግስታት ማለትም ደርግና ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ታሪክ የተበላሸ ፖለቲካን በማራመድ ቀዳሚዎች ነበሩ ማለት ይቻላል። በተለይ የኢህአዴግ መንግስት የዛሬዋን ኢትዮጵያ አበላሽቶና አወላግዶ ለመፍጠሩ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ ድርጅት ነው።
በሚያራምደው የብሄር ፖለቲካ ኢትዮጵያዊነትን በዘርና በቋንቋ ከፋፍሎ ኢትዮጵያውያን በጠላትነት እንዲተያዩ ከማድረግ ባለፈ የፈየደው አንድም ነገር አልነበረም። በዚህ የመንግስት የትላንት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ውስጥ እኔነት እንጂ እኛነት አልነበረም። ኢትዮጵያዊነት ስፍራ ከማጣቱ በላይ ለዘመናት ተዋዶና ተከባብሮ የኖረን ማህበረሰብ በሴራ ፖለቲካ ሲያባሉት ነበር።
ዛሬ ላይ መከራ የሆኑብን ችግሮቻችን ከዚህ የመንግስት ስርዓት ውስጥ የተፈጠሩ ናቸው። እነዚህ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶቻችን በለውጡ መንግስት እስኪስትካከሉ ድረስ ከዚህ የመንግስት አወቃቀር ውስጥ የተሰሩ ነበሩ። ኢትዮጵያዊነትን ለማድመቅ የተነሱ እንዳሉ ሁሉ ኢትዮጵያዊነትን ለማደብዘዝ ታጥቀው የተነሱ እንደ ህወሓት አይነት ራስ ወዳድ ቡድኖች የተነሱበት ሰሞን ላይ ነን።
ኢትዮጵያዊነትን ከቀለሙ..ካበጁና ከመለሱ የህዝብ ባለውለታዎች ውስጥ አንዱ የለውጡ መንግስት ነው። የለውጡ መንግስት ካለፉት የፖለቲካ ስርዓቶች ሁሉ በተለየ መልኩ የኢትዮጵያን ጥቅም ያስከበረ የኢትዮጵያውያንን ጥያቄ የመለሰና ሁሉን ባሳተፈ መልኩ እንቅስቃሴ እያደረገ ያለ የለውጥ ሀይል ነው።
ለዚህ ምሳሌ እንዲሆን ደግሞ የሰኔ አስራ አራቱን የምርጫ እንቅስቃሴና ውጤት ማየት ይቻላል። ሰኔ አስራ አራት ለሁላችንም ታሪካዊ ቀን ነው። የብዙዎቻችንን ጥያቄ የመለሰና ለብዙዎቻችን የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ ነበር። ብዙዎቻችን ያጣነውን ፍትህ፣ ያጣነውን ዲሞክራሲ የመለሰ እንዲህም ነበር። ኢትዮጵያውያን በአንድ ስሜት የለውጡን መንግስት የደገፉበትና የተቀበሉበት ታሪካዊ ቀን ነበር ማለት ይቻላል።
በዚሁ ቀን የለውጡ መንግስት በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ለሚመጡት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያን እንዲመራ በሙሉ ድምጽ ተቀባይነትን አግኝቷል። ይሄን የምርጫ ውጤት መሰረት አድርጎ የመንግስት ምስረታ ተካሂዷል። ከፍ ብዬ እንዳልኳችሁ የለውጡ መንግስት የህዝብ መንግስት ነው። የለውጡ መንግስት የአንድነት መንግስት ነው። ከምርጫ በፊትም ሆነ ከምርጫ በኋላ እያሳየው ያለው ትጋት ህዝብን ያስቀደመና ሀገርን መሰረት ያደረገ ነው። ይሄ ደግሞ ሁላችንም የምናውቀው መሬት የወረደ ሀቅ ነው። ከምርጫ በፊት ምርጫውን የሚያሸንፍ ከሆነ ኢትዮጵያን በታማኝነትና በታላቅ ትጋት እንደሚያገለግል ተናግሮ ነበር።
በምርጫው የሚሸነፍ ከሆነም ያሸነፈውን ፓርቲ አክብሮና አድንቆ ስልጣኑን ያለ ምንም ነውጥ እንደሚያስረክብ ይሄንንም ከለውጡ መንግስት አፍ ሰምተን ነበር። ከዚህ በላይ ለውጥ አለ ብዬ አላስብም። ከዚህ በላይ ለሀገርና ህዝብ መቆርቆር አለ ብዬ አላምንም። ያለፉት መንግስታቶቻችን ምርጫን በተመለከተ ምን አይነት አስተሳሰብ ያራምዱ እንደነበር ሁላችንም የምናውቀው ሀቅ ነው።
ተፎካካሪ ፓርቲን በተመለከተ ከመንግስት የሰማነውና እየሰማነው ያለው ነገር የምንናፍቃትን ኢትዮጵያ ለመፍጠር የመጀመሪያ እርምጃ እንደሆነ ነው የምረዳው። መንግስት ለህዝብ የሰጠው ድንቅ ስጦታ እንደሆነም ማመን ጀምሬያለሁ። ይሄ ለእኛ ብርቅም ድንቅም ነው። ተፎካካሪ ፓርቲን በምርጫ አሸንፈኸኛልና እንኳን ደስ አለህ ብሎ መቀበል በእኛ ሀገር ያልተለመደ ነው። ያልተለመደ ብቻ አይደለም የማይታሰብም ነበር። ምክንያቱም ባለፉት የምርጫ ስርዓት አጭበርብሮና አወናብዶ ስልጣን መያዝ እንጂ ስልጣን ማስረከብ ስለማናውቅበት ነው።
አይደለም ሽንፈትን በጸጋ ተቀብሎ አሸናፊን ፓርቲ ወደ ስልጣን ማምጣት ቀርቶ እንዲህ የሚወራበት የፖለቲካ ስርዓት አልነበረንም። ወደ ጉዳዬ ልመለስና የሰኔ አስራ አራቱን የህዝብ ድምጽ መሰረት ባደረገ መልኩ አሸናፊው ፓርቲ አዲስ መንግስትን መስርቷል። የመንግስት ምስረታው ደግሞ ከዚህ በፊት ባልነበረና ባልተለመደ ለሁላችንም ተስፋ ሰጪ በሆነ መልኩ በምርጫ የተሸነፉ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማሳተፍና ወደ ስልጣን በማምጣት ተካሂዷል።
ይሄ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ ለውጥ ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ሲያሳድድ እንጂ ሲያቀርብ አላየንም። ሲያገልና ሲያስር፣ ሲያዋርድና ሲያሳድድ እንጂ ለጋራ ጥቅም አብሮ በመስራት ሲተባበር አላየንም። የተለየ ሀሳብና የተለየ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ሀገራችን ላይ ምን እንደነበሩ ሁላችንም የምናውቀው የአደባባይ ሀቅ ነው።
የዘንድሮው የመንግስት ምስረታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ያለፈውን አዳፋ የፖለቲካ አካሄድ ሽሮ በአዲስና እጅግ አዋጪ በሆነ አካሄድ የሚመሰረት ነው። የለውጡ መንግስት እየሄደበት ያለው መንገድ ምን ያክል ለሀገራችን ጠቃሚና ዋጋ ያለው እንደሆነ ይሄን ማየቱ ብቻ በቂ ነው እላለሁ። ሌሎችን በማግለልና በማራቅ ለውጥ አይመጣም። ለውጥ የአንድነት ውጤት ነው። ኢትዮጵያን ባሉ ስለ ኢትዮጵያ በሚጮሁ ድምጾች የሚፈጠር ነው።
ሀገራዊ ሀሳቦች አንድ ላይ ተደምረው የሚፈጥሩት ነው። አዲስ የተመሰረተው መንግስት ደግሞ በዚህ እውነት ውስጥ የቆመ እንደሆነ ከላይ የጠቀስኩላችሁን እውነታዎች ምስክሮች ናቸው። ካለፈው በበለጠ የኢትዮጵያውያንን ጥያቄ የሚመልስበት እንደሚሆን የሁላችንም እምነት ነው። እንደ ሀገርም እንደ ህዝብም ያሉብንን ችግሮች ተመልክቶ ለጋራ ጥቅም በጋራ የሚሰራ የመንግስት መዋቅር ነው ።
ባሳለፍናቸው ሶስት ዓመታት ውስጥ የታየው ለውጥና የአንድነት መንፈስ ህዝብ በመንግስት ላይ ያሳደረው እምነት ምን ያክል እንደሆነ የሚያሳይ ነው። መንግስትም ህዝብ የሰጠውን አደራ በበቂና በአስተማማኝ መንገድ በመተግበር የኢትዮጵያን ህዝብ ወደፊት እንደሚያራምደው በሰራውና እየሰራው ባለው መልካም ስራ ማረጋገጥ ይቻላል።
የለውጡ መንግስት አላማ አንድ ሀገርና አንድ ህዝብ መገንባት ነው። በአሸባሪው ህወሓት የስልጣን ዘመን የከሸፈውን አንድነት፣ የጠፋውን ፍትህና ዲሞክራሲ መመለስ ነው። ከምንም በፊት ሀገርና ህዝብን ያስቀደመ ፖለቲካዊ እሳቤ በእያንዳንዳችን ውስጥ መፍጠር ነው። ለለውጡ መንግስትም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ካለፈው ይልቅ የሚመጣው ጊዜ የተሻለና ብሩህ ይመስለኛል።
ከፊታችን በብርሃን የተሞሉ የኢትዮጵያን መነሳት የሚያበስሩ የተስፋ ምልክቶች አሉ ። ከመስከረም በኋላ አዲስ ዓመትን ታኮ በኢትዮጵያ ምድር የአንድነትና የአብሮነት ጸሀይ እንደምትወጣ እምነቴ ነው ። የመንግስት ምስረታው ኢትዮጵያ የተጓዘችበትን ትላንትናዊ ጎዳና በማጤን ከፊቷ የተጋረጡባትን መሰናክሎች የምታልፍበትን ዘዴ በመዘየድ፣ ከዛም በኋላ ባለው ጉዞዋ የምትደርስበትን የለውጥና የከፍታ ስፍራ መሰረት ያደረገ ነው።
አዲሱ መንግስት የህዝብ መንግስት ነው። በህዝብ ተሳትፎ ስልጣን የያዘ፣ በህዝብ ይሁንታ መንግስት የሆነ አሁንም በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ የተመሰረተ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ያለፉት መንግስታት ያልመለሱለት በርካታ ጥያቄዎች ነበሩት። የፍትህ፣ የዴሞክራሲ ሌላም ሌላ ጥያቄዎች። እኚህ ጥያቄዎች በለውጡ መንግስት መልስ የተሰጠባቸው ናቸው።
ሀገር ለሚመራው ህዝብ የታመነና የቀረበ መንግስት ትሻለች። አሁን ህዝብ ያገኘው ይሄንን ነው። በዚህ የመንግስትና የህዝብ ውህደት ውስጥ የሚመሰረተው መንግስት ምን አይነት እንደሚሆን መገመት አይከብድም። ከዚህ በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ ህዝብ ከመንግስት መንግስትም ከህዝብ የሚጠቀሙበት የጋራ አሰራር ይፈጠራል። ያለፉት ሶስት ዓመታት በብዙ ለውጥና በብዙ ተግዳሮቶች የተሞሉ ነበሩ። ለውጡን የፈጠረው የአዲሱ መንግስት የአስተሳሰብና የፖለቲካ ፍልስፍና ሲሆን ተግዳሮቱን የፈጠረው ደግሞ ባለፈው መንግስት በተሰራው ተንኮልና ደባ የተነሳ ነው።
መንግስት ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ቢገባ አሁን ካየነው የበለጠ ለውጥ እናይ ነበር እላለሁ። ግን ያለፈው መንግስት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ያስቀመጠው የጥላቻና የመገፋፋት ፖለቲካ መንግስት በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ እንዳይገባ እክል ሲፈጥርበት ቆይቷል። አሁን ላይ እያየነው ያለው ለውጥና ብልጽግና መንግስት በአሸባሪው ህወሓት የፖለቲካ ሴራ ያደፈ ኢትዮጵያዊነትን በመመለስ ሂደት ውስጥ የፈጠረው ነው።
መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጣ በአሸባሪው ህወሓት የሴራ ፖለቲካ የተተበተበችን ውል አልባ ሀገር ነው የተረከበው። ይሄን አዳፋ መልክ ማጽዳት ነበረበት። ይሄን የሴራ ፖለቲካ ማክሸፍ ነበረበት።፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ነው ሁላችንም ተስፋ ያደረግናትን ኢትዮጵያ ለማየት የበቃነው። መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአዲሱ መንግስትም የተለየ ጊዜ ነው። ከፊታችን ለእኛ የሚሆኑ በርካታ ገጸ በረከቶች አሉ። የምንግዜም የጋራ ጠላታችን የሆነውን አሸባሪውን ህወሓት አሸንፈን በአንድነት የምንነሳበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።
ጊዜው መንግስት በተለየ ኃይል በተለየ የፖለቲካ አወቃቀር ወደ ስልጣን የሚመጣበት ወቅት ነው። ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከመገለል ወደ ተሳትፎ፣ ከመታሰር ወደ ስልጣን የመጡበት የተለየ ዓመት ነው። በዚህ የጋራ ውህደት ውስጥ፣ በዚህ የመንግስትና የተፎካካሪ ፓርቲ ቅንጅት ውስጥ የሚፈጠረውን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ማሰብ ይከብዳል ብዬ አላስብም። የሀሳብ ፖለቲካ ዋጋው ምን ያክል እንደሆነ ሳይገባን ኖረናል። በሀሳብ የበላይነት ኢትዮጵያን እንገባ የሚል ድምጽ የሰማነው በለውጡ መንግስት ዋዜማ ላይ ነው። የለውጡ ዋዜማ ብዙ ነገር ይዞልን መጥቷል። ዛሬም ድረስ እንኳን ይሄን ሁሉ ለውጥ ያየነው በለውጡ ዋዜማ ላይ በሰማነው የመደመር ፍልስፍና ነው።
በሀሳብ የበላይነት የሚያምን መንግስትና ህዝብ ያስፈልገናል። እስከዛሬ ሀሳብ አልነበረንም። እስከዛሬ በሀሳብ የበላይነት የሚያምን መንግስትና ህዝብ አልነበረንም። ሀሳብ ገድለን ሀገር ስንመራ ነበር። የግለሰቦችን ሀሳብ አፍነን በጽሞና ውስጥ ለመራመድ ስንሞክር ነበር። እስከዛሬ ሀሳብ ከሌለው ልብና መንግስት ውስጥ ሀሳብ ስንጠብቅ ኖረናል።
ቢሯችን በር ላይ ለይስሙላ የሀሳብ መስጫ ሳጥን አስቀምጠን ህዝብና ትውልድ ስናደናግር ነበር። የለውጡ መንግስት ይሄን ሁሉ ቀይሮታል። ሀገር በሀሳብ የበላይነት እንደምትገነባ ስላወቀ በድንቅ ሀሳብ ድንቅ ሀገርና ህዝብ በመፍጠር ላይ ነው። ባለፈው ስርዓት ውስጥ ሀሳብ ቦታ አልነበረውም። ጥቂት ግለሰቦች ብቻ እንዲናገሩ የተፈቀደበት ሁኔታ ነበር፤ ይሄ በመሆኑም ጥቂት ሰዎች እየተጠቀሙ ብዙሃኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን በከፋ ድህነት ውስጥ ሲማቅቅ ነበር ።
ሀሳብ የሌለባት ሀገር ስልጣኔ የላትም። ሀሳብ የሌለው ማህበረሰብ ወደፊት ፈቀቅ አይልም። ሀሳብ ለምንም ነገር ያስፈልገናል። የለውጡ መንግስት በሀሳብ የተሞላ፣ ለሀሳብ ቅድሚያ የሚሰጥ፣ የግለሰቦችን ሀሳብ የሚያከብር ነው። አሁንም በአዲስ ሀሳብ በአዲስ ኃይል እየመጣ ነው። ከዚህ ኃይል ጋር ተደራጅተን ሀገራችንን ወደፊት ማራመድ ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው እላለሁ። በአዲሱ የመንግስት አዲሷንና በሁሉ ነገሯ የተሳካላትን ኢትዮጵያ እንደምናይ እምነቴ የጸና ነው። አበቃሁ ቸር ሰንብቱ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2014