ኢትዮጵያውያን በነቂስ ወጥተው ይበጀኛል ያሉትን መንግስት መርጠዋል። ይህን ተከትሎ ከቀናት በፊት በታላቅ ስነ ስርዓት አዲስ መንግስት ተመስርቷል። በዚህም አብላጫውን ድምፅ ያገኘው የብልፅግና ፓርቲ መንግስት የመመስረት ድርሻውን ወስዶ የቤት ስራውን አጠናቋል። አዲሱ አመራር በተለይም ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ ፖሊሲዎችን ለማሻሻል፣ ፀጥታውን አስተማማኝ ለማድረግ፣ በተለይ በኢኮኖሚ ዘርፉ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ቃል ገብተዋል። በተለይ ብልሹ አሰራርና “ሌብነትን” በስሙ በመጥራት በዚህ ጉዳይ ላይ ምህረት የለሽ እርምጃ እንደሚወሰድ ግልፅ አድርገዋል። አስፈፃሚዎች ይህን ተገንዝበው ከብልሹ አሰራርና ሌብነት እጃቸውን ሰብስበው የመረጣቸውን ህዝብ እንዲያገለግሉ የስራ መመሪያም ሰጥተዋል።
በአገራችን በርካታ ተቋማትን ዘርፎ በብልሹ አሰራርና የአመራር ቁርጠኝነት ማነስ፣ የመመሪያና ማስፈፀሚያ ህጎች ሽንቁር የተተበተቡ መሆናቸው ይነሳል። ከእነዚህ ተቋማቶች ውስጥ ደግሞ የኢንቨስትመንት ዘርፉ ተጠቃሽ ነው። ይህ ዘርፍ ለአገር ኢኮኖሚ እድገት ካለው ከፍተኛ ጠቀሜታ አንፃር በጥብቅ አመራርና በተጠና ፖሊሲ መመራት እንዳለበት ይታመናል። ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ በሚፈለገው መጠን “የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ” ከማሳደግ አኳያ ሊወስድ የሚገባውን የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ አልቻለም። ዋንኛው ማነቆም ዘርፉን በእውቀት የመምራትና ውስብስብ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን አለመፍታት እንደሆነ ይጠቀሳል።
ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው አዲስ በተመሰረተው መንግስት ቁልፍ መዋቅራዊ ለውጥና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ሊደረግባቸው ከሚገቡ ዘርፎች መካከል የኢንቨስትመንት ዘርፍ አንዱ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ይህን ዘርፍ የማሻሻልና ይበልጥ የማዘመን ስራ ሰርቶ አገር እንድትጠቀም የማድረግ ተግባር ግዜ ሊወስድ አይገባም። ከዚህ አንፃር የሚከተሉትን ምክረ ሃሳቦች ለመስጠት እወዳለሁ።
አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ
ኢትዮጵያ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭና በርካታ ክፍት ሴክተሮች መኖራቸው ይታወቃል። ይህን አማራጭ የአገር ውስጥም ሆነ የውጪ አገር ግለሰቦች፣ ኩባንያዎች፣ እንዲሁም አገራት እንዲያውቁት የማስተዋወቅ ስራዎችን መስራት ተገቢ ነው። በዋናነት መዋለንዋያቸውን በአገራችን ልዩ ልዩ አካባቢዎች በማፍሰስ ዘርፉን የሚያነቃቁ ባለሃብቶችና ኩባንያዎች ይህን እድል ማየት እንዲችሉ ስትራቴጂዎችን ነድፎ መንቀሳቀስ ይገባል። በተለይ ኢንቨስተሮችን የሚያሸሽ ውስብስብ ህጎችን፣ የአሰራር ስርዓቶችን በኤክስፐርቶች በሚመራ የጥናት ቡድን በመለየት ማስተካከል እንዲሁም ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ለነዚሁ የዘርፉ ባለሃብቶች በተለያዩ አማራጮች ማስተዋወቅ ይገባል። ይህን በጠንካራ ህግና ስርዓት ከመምራት ባሻገር በተለያዩ የመንግስት ኢንቨስትመንት ጉዳይ ላይ የሚሰሩ መስሪያ ቤቶችን በጠንካራ መዋቅርና አመራሮች ማደራጀት ተገቢ ይሆናል።
የነበሩትን መመርመር፣ ማበረታታትና ማቆየት
በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ የአገር ውስጥና የውጪ ባለሃብቶች መኖራቸው ይታወቃል። እነዚህ ግለሰቦች፣ ተቋማትና የተለያዩ አገራትን የወከሉ የኢንቨስትመንቱ አካላት ሃብታቸውን አፍስሰው ኢኮኖሚውንና የአገር ግንባታ ሂደቱን በመደገፍ ላይ ይገኛሉ። ከምንም በላይ ለስራ አጡ የስራ አማራጭ ፈጥረው መንግስት ላይ ያለውን ጫናም እያቃለሉና እሴት እየጨመሩ እንደሆነ ይታመናል። ስለዚህ በትክክለኛው መንገድ ህግና ስርዓትን ተከትለው የሚሰሩ ኢንቨስተሮችን ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር ማበረታታት ቀጥተኛ ድጋፍ ማድረግ፣ ያሉባቸውን ማነቆዎች ለመፍታት በግልፅ መመካከርና የመፍትሄ እርምጃ ማመንጨትና መተግበር ከመንግስት ይጠበቃል።
በሌላ መልኩ የመንግስትን የኢቨስትመንት አማራጭ ተጠቅመው ለማልማት መሬትና የገንዘብ ብድር ወስደው ወደ ትግበራ ስራ ውስጥ ያልገቡ አካላት እንዳሉ በተለያየ ግዜ ሰምተናል። ብልሹ አሰራርን ተከትሎ የሚመጣ ክፍተትን ተጠቅመው የአገር ሃብት የሚያባክኑ ትክክለኛ የኢንቨስትመንት ስራ ውስጥ ለመግባት የሚፈልጉ አካላትን አማራጭና እድል የዘጉ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድም ከአዲሱ መንግስትና አመራሮች የሚጠበቅ ይሆናል። ከዚህ አንፃር የህግ ክፍተቶችን ተጠቅመው ሌብነት ውስጥ የገቡትንና ከተጠያቂነት የሸሹትን መስመር ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ይህን ሂደትም በጠንካራ ምርመራና የህግ ማእቀፍ መምራት ያስፈልጋል።
ምቹ የመሰረተ ልማት ግንባታ
ኢትዮጵያ ተዝቆ የማያልቅ ሃብት፣ ሰርቶ የማይደክመው ሰፊ የሰው ሃይል ያላት አገር ነች። ይሁን እንጂ ለአንድ አገር እድገት ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ ሁለቱን ሃብቶቻችንን ማቀናጀትና በተገቢው መንገድ መምራት ባለመቻላችን ምክንያት መጠቀም የሚገባንን ያህል አንዲሁም ኢትዮጵያን ልናሳድግ በሚገባን ፍጥነትና ልክ ልናሳድግ አልቻልንም። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ በቀላሉ ልናመቻቸው የሚገባው የመሰረተ ልማት ጉድለት በተጨማሪ የሚነሳ ጉድለት ነው። መንግስት ኢንቨስተሮችን ለመሳብ በቅድሚያ የተሟላ መሰረተ ልማት ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል።
ይህን ሳያደርግ መዋለ ንዋያቸውን ሊያፈሱ የሚችሉ ባለሃብቶችን አንጋጦ መጠበቅ “ላም አለኝ በሰማይ…” እንደሚባለው አገርኛ ብሂል አይነት ነው። በመሆኑም የመንገድ፣ የኢንንዱስትሪ ፓርክ፣ የኢነርጂ ብሎም መሰል አስፈላጊ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን አስቀድሞ በፍጥነትና በጥራት ማዘጋጀት ይጠበቅበታል። ይህን ወሳኝ ሃላፊነትም አዲስ የተመሰረተው መንግስት “የቅድሚያ ቅድሚያ” ሰጥቶ እንደሚሰራው እንጠብቃለን።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ላይ ኢትዮጵያ እጅግ አበረታች ሂደቶች ላይ እንደምትገኝ ማንሳቱ ተገቢ ቢሆንም የሃይል አቅርቦት፣ የሃይል መቆራረጥ፣ የመንገድና መሰል የመሰረተ ልማት ጉዳዮች ላይ ግን አሁንም እጅግ በርካታ ማነቆዎችና ብልሹ አሰራሮች መኖራቸውን መረዳት ተገቢ ይሆናል። ከዚህ አንፃር መንግስት ልዩ ትኩረት እዚህ ላይ ማድረግ ቢችል ፈጣን መፍትሄ ለመስጠት አይቸገርም የሚል እምነት አለኝ።
የፀጥታ ችግር
በአንድ አገር ኢንቨስትመንት እድገት ላይ “ሰላምና ፀጥታ” ቁልፍ ድርሻን ይይዛሉ። ሰላም ከሌለ ኢንቨስትመንት የለም፤ በተቃራኒው ሰላማዊ አገር ውስጥ ፈጣን የኢንቨስትመንት እድገት ይመዘገባል። ይሄ የማይካድ ሃቅ ነው። ስለዚህ ከምንም ነገር በላይ አዲስ የተመሰረተው መንግስት በአገሪቱ ላይ ያሉትን “የፀጥታና አለመረጋጋት” ጉዳዮች በግዜ መፍታት ይኖርበታል። ለኢንቨስተሮችም ዋስትና መስጠት ይጠበቅበታል። በተለይ አዲስ ለሚመጡ ባለሃብቶች ይህን መሰል ዋስትና መስጠት ከምንም ነገር በላይ መቅደም ይኖርበታል የሚል ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል።
“የኢንቨስትመንት ሴክተሩን ወደሚቀጥለው ደረጃ ከፍ ለማድረግ ለአለም ባለሀብቶች በራችንን ክፍት በማድረግ፣ በዘመናዊ ኢንደስትሪ ፓርኮቻችን፣ በብዙ የኢንቨስትመንት አማራጮቻችን እንዲሁም በዘርፈ ብዙ የኢንቨስትመንት ሴክተሮቻችን ተግተን በመስራት ወደአቀድንበት ለመድረስ እንተጋለን” የሚለውን የመንግስት እቅድ ለማሳካት ከላይ ያነሳናቸው ዝርዝር ማነቆዎች ላይ የፖሊሲ፣ የአሰራር ስርዓት እንዲሁም የአመራር ቁርጠኝነት በተገቢው መንገድ መሻሻሉን ማረጋገጥ ይኖርብናል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መስከረም 28 ቀን 2014 ዓ.ም