አንዳንድ ቀናት በአዎንታም በአሉታም ለታሪክ የታጩ የተመረጡ የተሾሙ ይመስላል። አርብ ለስቅለት። እሁድ ለትንሳኤ። ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሀገር ከጀርባ የተወጋችበት የተከዳችበት ጥቁር ቀን አርብ እንደሆነችው። በአንጻሩ አንዳንድ ቀናት አሉ ተለይተው ለዙፋን ለአክሊል የተጠሩ እሁድ የሚሆኑ።
መጀመሪያም ትንሳኤም የሚሆኑ። ሰኞ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም ከእነዚህ ቀናት አንዷ ናት። በጥንታዊው የኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ መጽሐፍ ያስገለጠች። ልብ አርጉ አዲስ ምዕራፍ አላልሁም። አዲስ ምዕራፍ የአሮጌው መጽሐፍ አካል ስለሆነ። ይቺ ታሪካዊ ቀን የአዲስ መጽሐፍ አዲስ ምዕራፍ እንጂ የአሮጌ መጽሐፍ አዲስ ምዕራፍ አይደለችም።
ምርጫውም ከቀደሙት አምስት ምርጫዎች በፍጹም የተለየ 1ኛ ምርጫ እንጂ 6ኛ ምርጫ አልነበረም። የመንግስት ምስረታውም የዚህ አዲስ ምርጫ ውጤት ስለሆነ 6ኛ የመንግስት ምስረታ ሳይሆን 1ኛ የመንግስት ምስረታ ነው። ታላቁ መጽሐፍ አዲስ ወይን በአዲስ አቁማዳ እንዲል። እንደ ሙዚቃ አዝማች በዚሁ ጋዜጣ በዚሁ አምድ ደግሜ ደጋግሜ ለመግለጽ እንደሞከርሁት ይቺ ታሪካዊ ቀን ወሳኝ መታጠፊያ critical juncture ናት። አዎ ! ሀገራችን እስከ ዛሬ ከመጣችበት መንገድ ወደ ቀኝ ማለትም ወደ ነጻነት ዴሞክራሲያዊነት አሳታፊነት ፍትሐዊነት ርዕታዊነት ሰላም ፍቅር ብልጽግና ወደሚያመራው ረጅም መንገድ ታጥፋለች። የጠቅላይ ሚንስትሩ የበዓለ ሲመት ንግግርም ይሄን መታጠፊያ ሪቫን ቆርጦ በይፋ የሚያውጅ ነበር። በተጨማሪም የአዲሱ ትውልድ ራዕይ ፍኖተ ካርታ road map የተበሰረበት ልዩና ታሪካዊ ቀን ነው። ይህ ብስራት በጠቅላይ ሚንስትሩ በየሀገራት መሪዎች እንዲህ ይፋ ሆኗል።
በዚች ታሪካዊ ቀን ማለዳ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መስራች ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሰየሙት ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤ ከሰዓት በመስቀል አደባባይ በርካታ የአፍሪካ መሪዎችና አያሌ የአዲስ አበባ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች በተገኙበት የበዓለ ሲመት ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር የአዲሲቱን ኢትዮጵያና የአዲሱን ትውልድ ፍኖተ ካርታ፤ ሀገሪቱ በቀጣይ የምትመራበትን አቅጣጫና የቆመችባቸውን አእማድ ወይም ፍኖተ_ካርታ አመላክተዋል።
ሀገራችን ነጻ ጥንታዊ ታሪካዊ የግዛት አንድነቷንና ሉዓላዊነቷን ጠብቃ መኖሯ የቆመችበት የማይናወጥ መሠረት መሆኑን፤ የማትደራደርባቸው ቀይ መስመሮች መሆናቸውን እና አሁን የገጠማትን ፈተና በአሸናፊነት እንደምትወጣ እንዲህ አረጋግጠዋል። “በኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ግልጽና ተዓማኒ ምርጫ ተካሂዶ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያገኘ መንግሥት ምስረታ ላይ ስለደረስን እንኳን ደስ አለን፡፡ ኢትዮጵያ ጠላቶቿን ድል አድርጋና ችግሮቿን ተሻግራ አንገቷን ቀና አድርጋ የምትጓዝበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና በምታደርገው ጉዞ የወዳጆቿን አጋርነት ትሻለች። ነገር ግን ሉዓላዊነቷን እና ነፃነቷን በሚነካ ማንኛውም ጉዳይ ላይ ድርድር አይኖራትም፡፡ ኢትዮጵያ ከፊት ለፊቷ ያለውን ቆሻሻ አስወግዳ አቧራውን ጠርጋ ወደ ብልጽግና ትጓዛለች።”
ጠቅላይ ሚንስትሩ በማስከተልም መንግስታቸው እንደ ቀደሙት አገዛዞች የተለየ ሀሳብ የሚያራምዱ ግለሰቦችንም ሆነ ተፎካካሪዎች አይናችሁ ለአፈር የሚል በአይነ ቁራኛ የሚከታተል የሚያሰቃይ የሚገርፍ የሚገድል የሚያስር የሚያሳድድ የሚገፋ የሚያገል ወዘተረፈ ሳይሆን አካታችና አሳታፊ እንደሚሆን በፍኖተ ካርታው እንዲህ ጠቁመዋል። ”በምርጫው የተመዘገበው ድል የአንድ ፓርቲና የመንግስት ብቻ ሳይሆን እንደ ህዝብ በአንድነት ያሸነፍንበት መሆኑን ተገንዝበን ወደ ከፍታው ምዕራፍ በአንድነት መጓዝ አለብን። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት የአሸናፊዎች ብቻ እንዳይሆን መንግሥታቸው ሁሉን አካታችና አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲሰፍን በቁርጠኝነት ይሰራል። የኢትዮጵያ ህዝብ በምርጫው ሂደት ለመፍጠር የተሞከሩትን እንቅፋቶች አኩሪ በሆነ መንገድ ተወጥቶታል፡፡”
በዚሁ ፍኖተ ካርታ ቀጣናዊ አፍሪካዊ አንድነት ምስራቅ አፍሪካንም ሆነ አህጉሩን የሚገጥሙ ችግሮች ለመመከትም ሆነ በጋራ ለመልማት በአንድነትና በሕብረት መቆም የግድ መሆኑን ገልጸዋል።”ውድ አፍሪካውያን እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ከሚያጋጩን ነገር ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ነገር ብዙ ናቸው፤ አንድ ከሆን ጠላቶቻችን ከንስር ፊት እንደቆመች ድንቢጥ ናቸው። ጥቅሟን የምታስጠብቅ አህጉር እንድትኖረን በህብረት ጥረት ማድረግ አለብን። “ካሉ በኋላ ስለ ኢትዮጵያ መጻኢ እድልም ያላቸውን ርዕይ እንዲህ አመልክተዋል።
“ቀጣዮቹ አምስት ዓመታትም ኢትዮጵያ ከፍ የምትልበት ገናናው ስሟ በዓለም በስፋት እንዲናኝ የምታደርግበት፤ አሁን የተጋረጡብንን ችግሮች የምንወጣውም በጋራ በመስራት ነው። የውስጥ ሽኩቻችን ለጠላቶቻችን ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጥር መጠንቀቅ አለብን፡፡ ለአፍታ እንኳ ሳንዘናጋና ሳናንቀላፉ ለአገራችን ህልውና ደህንነትና ብልጽግና በቁርጠኝነት እንሰራለን። “የዋጋ ግሽበቱና የኑሮ ውድነቱ በመንግስታቸው ትኩረት እንደሚሰጠውም ቃል ገብተዋል።”ለዘመናት የተከማቹ የመጡትን የኢኮኖሚ ችግሮች ለማሸነፍ በአንድነት መነሳት ይኖርብል። መንግሥታቸው የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራቸው ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው የዋጋ መናርን መቆጣጠር ነው።”
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ መንግስታቸው በትጋት እንደሚሰራም አስታውቀዋል። ከሃዲዎች በፈፀሙት የእብሪት እርምጃ ምክንያት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተከሰተው ግጭት አገራችን እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ከፍላለች። ያጋጠሙን የውስጥ ጠላቶች ኢትዮጵያ ጠል የሆኑ አረመኔዎች ናቸው። በዚህም ጦርነቱ ወደን ሳይሆን ተገደን የሀገራችንን ህልውና ለማረጋገጥ የገባንበት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ለአገራቸው ህልውና እና ሰላም በጽናት በአንድነትና በጀግንነት የቆሙት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የመከላከያና የፀጥታ አካላት ውለታ አይረሳም። ኢትዮጵያን በማድነቅ ስሟን ደጋግመው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዝብ ያለኝን ታላቅ አክብሮትና ምስጋና እገልጻለሁ ብለዋል።
ኢትዮጵያ የገጠማትን የውስጥ ችግር እንደምትፈታ ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሮቹ ለመፍታትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት መድረክ እንደሚካሄድ፤ “የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን ለማጥበብ አካታች ብሔራዊ የውይይት መድረክ እናካሂዳለን፤” የሚካሄደው ውይይት በኢትዮጵያውያን እንደሚመራና የኢትዮጵያ ወዳጅ አገሮች ደግሞ በዚህ ውስጥ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።”ችግሮቻቸውን ተመካክረው ይፈታሉ ብለው የሚያምኑብንን ያካተተና በኢትዮጵያውያን የሚመራ ሁሉን አቀፍ የውይይት መድረክ እናካሂዳለን፤” ሲሉ አገረጋግጠዋል።
ፓን አፍሪካኒዝም ከጥልቅ እንቅልፉ በተቀሰቀሰበት በዚህ ታሪካዊ ቀን፤ በበዓለ ሲመቱ የታደሙ የሀገራት መሪዎች ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል። በቀጠናው ሰላምና ፀጥታ እንዲረጋገጥ ኢትዮጵያ ለምታከናውነው ተግባር ኬንያ ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትቆም፤ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አፍሪካ ቀንድ ቀጠናዊ ሰላም ጉዳዮችና በኢትዮጵያ የሰላምና የፀጥታ ሥራዎች ላይ ሀገሪቱ በምታደርገው የሰላም ግንባታና መረጋጋት ተግባራት የኬንያ መንግሥትና ህዝብ አብሮ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሀገራት በአውሮፓውያን ያለመገዛትን ያስተማረች፣ ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የነፃነት እናትነትን ያሳየች ሀገር ነች። እናት ደግሞ ሰላምና መረጋጋት ካልተስተዋለባት ልጆቿና ጎረቤቶቿ ሰላም አይሆኑም። በመሆኑም ለኢትዮጵያ ሰላም መስራትና ከጎኗ መቆም ግዴታችን ነው ብለዋል። የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በበኩላቸው በኡጋንዳ በብሔር ፖለቲካ የተነሳ በርካታ ችግር ውስጥ ገብታ እንደነበር አውስተው ከዚህ ችግር ለመውጣት ብዙ ፈተናዎችን ማለፋቸውን ጠቁመዋል። በብሄር የተነሳ የተፈጠረውን የፖለቲካ ፍላጎት አለመጣጣም ወደ ጎን በመተው ኡጋንዳ በአንድነት እና በሀገር ጥቅም ላይ የተመሰረተ ፖለቲካን ማራመድ መጀመሯን ገልጸዋል። ኢትዮጵያውያንም ከጎሳና ከማንነት ፖለቲካ ይልቅ በአንድነት እና የሕዝብን ጥቅም የሚያከብረውን መንገድ መከተል እንደሚገባቸውም ምክራቸውን ለግሰዋል።
የጅቡቲ ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ፤ ኢትዮጵያ ባሳለፈቻቸው ረጅምና አስደናቂ የታሪክ ጉዞ ለገጠሟት ፈተናዎች እጅ ሳትሰጥ በአንድነትና በጽናት በመቆም በድል የማሻገር ልምድ ታሪክ ያላት አገር መሆኗ በእጅጉ እንኮራባታለን። በዓለም መድረክ የአፍሪካውያን ኩራትና ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ከሆነችው ከኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደትንና መቻቻልን ለመቅሰም መጥተናል። የሶማሊው ፕሬዚዳንት መሀመድ አብዱላሂ ፎርማጆ በበዓለ ሲመቱ ላይ እንደተናገሩት ኢትዮጵያና ሶማሊያ ጠንካራ ሁለትዮሽና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዳላቸውና ሶማሊያ ለምስራቅ አፍሪካ እድገት ሁሌም ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ትሰራለች።
የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር፤ደቡብ ሱዳን ዛሬ ላይ የደረሰችው የኢትዮጵያ እገዛ ስላልተለያት ነው። ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ ስንሆን የምንጠለልባት ታላቋ እናታችን ናት ብለዋል። በበዓለ ሲመቱ ላይ ከተገኙት መሪዎች ውስጥ አንዱ የሆኑት የናይጀሪያው ፕሬዚዳንት ሞሀመድ ቡሀሪ እንደተናገሩት ሀገራቸው በተለያዩ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ፍላጎት አላት። ከዶክተር ዐቢይ አህመድ ጋር በመሆን አገሪቱ ያላትን የኢኮኖሚ አቅም በመጠቀም ኢንቨስትመንቶችን ታስፋፋለች ብለዋል።
መጭው ዘመን ለኢትዮጵያ ብሩህ ይሆናል!!!
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 27/2014