የኢትዮጵያ ፖለቲካ የዘመናት ጉዞ በመገፋፋት እና አንዱ አንዱን በማስወገድ ላይ የተመሰረተ የመንግስት ሥርዓትን እያስተናገደ ዘልቋል። አሸናፊና ተሸናፊ ስሜት ላይ የተቋጠረው ይህ ሂደት እስከ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ማብቂያ ድረስ ለአንዲት አገር ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ጥቅምና ፍላጎት በጋራ ከመስራት ይልቅ፤ ስልጣንን ተቆጣጥሮ ለራስ ዝናና ጥቅም መሽቀዳደም ዋና መገለጫው ነበር።
በተለይ በለውጡ ሂደት ከስልጣን ተወግዶ ወደ ተራ ሽፍታነትና አሸባሪነት የተቀየረው ህወሓት የመንግስት ስልጣኑን በበላይነት ተቆጣጥሮ በቆየባቸው 27 ዓመታት የስም የፌዴራል መንግስት አወቃቀር እና የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን የመዘርጋት ትርክት ይኑረው እንጂ ቃል እና ተግባር ሳይገናኙ ቆይተዋል። በዚህ ሂደትም ለጋራ አገር በጋራ መስራት ቀርቶ፤ ስርዓቱ የሃሳብ ብዝሃነትን ማስተናገድ ተስኖት የፖለቲካ ድርጅቶችና ፖለቲከኞች ለስደት፣ ለእስርና ለከፋ እንግልት ሲዳረጉ ቆይተዋል።
ለይስሙላ የሚደረጉ ምርጫዎችም ቢሆኑ የህዝብ ድምጽ የሚከበርባቸው ሳይሆን፤ ለአንድ ፓርቲ ጥቅምና ህልውና ሲባል ኮሮጆ የሚገለበጥባቸው እና የ100 በመቶ ድምጽ የሚገኝባቸው ነበሩ። በዘመነ ኢህአዴግ ከተከናወኑ አምስት ምርጫዎች መካከል የተሻለ የምርጫ ፉክክር ታይቶበታል የሚባለው ምርጫ 97ም ቢሆን፤ መጨረሻው ከህዝብ ፍላጎትና ይሁንታ ውጪ ሆኖ ብዙዎች የታሰሩበት፣ የተሰደዱበት እና ወጣቶች የህይወት ዋጋ የከፈሉበት ሆኖ ለታሪክ የሚጠቀስ ጠባሳን ጥሎ አልፏል።
ከለውጡ ማግስት እንደ አገር የተያዘው፣ እንደ መንግስትም የተጀመረው አቅጣጫ ግን ይሄን ታሪክ የቀየረ፤ የህዝብን በምርጫ የማመን ተስፋ ከፍ ያደረገ፤ ተፎካክሮ በመሸነፍም ሆነ በማሸነፍ ውስጥ ፓርቲ ሳይሆን አገር አሸናፊ ሆናለች ብሎ የመግለጽን ታላቅነት ያረጋገጠ፤ ለጋራ አገር በጋራ ተቀራርቦ መስራትን በተግባር የገለጠ ሆኗል።
የለውጡ ኃይል ወደስልጣን ከመጣ ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሲገለጽ እንደነበረው ሁሉ፤ በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ዜጎችም ሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን እንወክላለን ብለው የሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ ቅድሚያ ለአገርና ህዝብ ሰጥተው መነጋገር እና በጋራ መስራት የሚቻልበትን እድል ተፈጥሯል። ይሄን መነሻ በማድረግም በቀደመው ስርዓት ተገፍተው የተሰደዱ፣ የታሰሩ፣ በሽብር የተፈረጁ እና ነፍጥ አንግተው ጫካ የገቡ ኃይሎች ወደአገራቸው እንዲገቡ እና በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ሆኗል። በተቋማት ላይም ሪፎርም ተከናውኗል።
በህዝብ ዘንድ አመኔታን አጥተውና ከህዝብ ይልቅ የመንግስት ጠበቃ ሆነው የነበሩ ተቋማትን ሪፎርም በማድረግ ሂደት ውስጥ የምርጫ አስፈጻሚው ተቋም የሪፎርም ስራ ተጠቃሽ ሲሆን፤ ይሄን ተከትሎም በኢትዮጵያ ታሪክ የዴሞክራሲን መሰረት የሚጥል ነጻ፣ ግልጽ፣ ፍትሃዊ እና ቅቡልነት ያለው ምርጫን ለማካሄድ የሚያስችሉ እርምጃዎች ተወስደዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገርና ህዝብ ጉዳይ ላይ ተቀራርበው የሚመክሩበት እና በጋራ የሚሰሩበት እድል እንዲፈጠር ተደጋጋሚ መድረኮች ተካሂደዋል።
ከዚህ ሁሉ በኋላ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ያገባናል የሚሉ ፓርቲዎች የተሳተፉበት፤ በርካታ የግል ተወዳዳሪዎችም የተሳተፉበት ምርጫ ሂደት ተጀመረ። ስድስተኛው አገራዊ ምርጫም በኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ እስከ ሌሊት ሰባት ሰዓት ድረስ ድምጽ የሰጠበት ነበር። ይህ ምርጫ ታዲያ እንደ ቀድሞዎቹ ምርጫዎች የፓርቲ አሸናፊነትን፣ የቃላት ጦርነት እና በደጋፊዎች ሁከት የታጀበ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያን አሸናፊነት የተበሰረበት፤ ለአሸናፊዋ ኢትዮጵያም ሁሉም በጋራ ሰርቶ ውጤት ያገኘበት፤ ቀጣይ ኢትዮጵያን በማሻገር ሂደት ውስጥ ሁሉም በጋራ ሊሰራ ቃል የገባበት ነበር።
በዚህ ምርጫ ህዝብ በነጻነት ወጥቶ ድምጽ ሰጥቷል፤ በምርጫውም ብልጽግና ፓርቲ መንግስት መመስረት የሚያስችለውን ድምጽ ማግኘቱን ምርጫ ቦርድ ይፋ ከማድረጉ በፊትም ሆነ በኋላ የተፎካካሪ ፓርቲዎች የህዝብን ድምጽ አክብረው የሚንቀሳቀሱ መሆኑን፤ ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን አሸናፊነት፣ ለነገ የተሻለ የዴሞክራሲ ስርዓትን ለመትከል ትልቅ ውሳኔ መሆኑን ገለጹ። ውጤት በታወቀ ማግስትም የአሸናፊው ፓርቲ ፕሬዚዳንት “ህዝብ ድምጹን ሰጥቶን ብልጽግና ያሸነፈ ቢሆንም፤ አሸናፊዋ ኢትዮጵያ ናት፤ ሆኖም አሸናፊዋን ኢትዮጵያን የማሻገሩ ኃላፊነት የብልጽግና ብቻ ሳይሆን የሁሉም አካል ድርሻ እንደመሆኑ፣ ብልጽግና አካታች መንግስት ይመሰርታል” ሲሉ ቃል ገቡ።
ይህ ቃል ብዙዎችን ያስደሰተ፣ እንደ አገር ለመገንባት የሚፈለገውን የአንድነት መንፈስ እንደሚያጠናክር እና የተሻለች ኢትዮጵያን በመፍጠር ሂደት ውስጥ ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም እምነት የተያዘበት ሆነ። ከለውጡ ማግስት የተጀመረው የአሳታፊነት ጉዞ ታዲያ፤ ከምርጫው ማግስት በተመሰረተው መንግስት ውስጥም በርካታ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት እና ግለሰቦችን ያሳተፈ፤ በካቢኔነትም ያቀፈ ነበር።
በዚህ ረገድ በክልሎች የተጀመረው አካታች የመንግስት ምስረታ ሂደት፤ ትናንት ይፋ ሆነ በምክር ቤት በጸደቀው የፌዴራሉ መንግስት ካቢኔ ሹመት ውስጥም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ሚኒስትር በመሆን ካቢኔውን እንዲቀላቀሉ ሆኗል። ይህ የሚያሳየው የለውጡ ሂደት የጋራ የሆነችን አገር በጋራ የመገንባት ሂደትን እውን በማድረግ ረገድ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፤ የፓርቲ አሸናፊ ወይም ተሸናፊ መሆን በአገር ግንባታ ሂደት ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ አለመኖሩን፤ ይልቁንም በሃሳብ ልዩነት ውስጥ ያለ አንድነትን ተጠቅሞ ለአገር ጥቅም በጋራ ለመስራት የሚያግድ ነገር አለመኖሩን ያረጋገጠ ነው።
በዚህ መልኩ በሚኒስትርነት ደረጃ የተገለጠው የመንግስት መዋቅር አካታች ጉዞ፤ በሚኒስትር ዴኤታነት እና ሌሎችም እርከኖች ላይ የሚቀጥል መሆኑም ተነግሯል። ይሁን እንጂ ሁሉም ልብ ሊለው የሚገባ አብይ ጉዳይ አለ። ይሄም ስልጣንና ሹመት ለራስ ክብርና ዝና ሳይሆን ለአገርና ህዝብ ብልጽግና ሲባል ዋጋ ከፍሎ መስራትን የሚጠይቅ ኃላፊነት መሆኑን መረዳት ነው። በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በፓርላማው ፊት ለእነዚህ ሹመኞች የሰጡትን አደራና ማሳሰቢያ ማስታወሱ ተገቢ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሳሰቢያነት ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል አንዱና ቀዳሚው የተሿሚዎቹ ዋና ተልዕኮ ሌብነት እና ልመናን ማጥፋት መሆኑን ተገንዝበው፤ ራሳቸውን ከሌብነት አቅበው ሌብነትም መዋጋት እንደሚገባቸው፣ ለማኝ የትም እንደማይደርስ ተገንዝበውም በራስ አቅም ውጤት ማንጣት ላይ ትኩረት አድርገው መስራት እንደሚገባቸው ያሳሰቡበት ነው። ሌላው ጉዳይ ተሿሚዎች የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች እንጂ የብሔር ተወካይ አለመሆናቸውን አውቀው ከብሔር አጥር በመውጣት ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን እያሰቡ ሊሰሩ የሚገባ መሆኑን ያስገነዘቡበት ነው።
ሌላው ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትሩ በካቢኔው ውስጥ ለተካከቱ የተፎካካሪ ፓርቲ ሰዎች የሰጡት ማሳሰቢያ ነው። ይሄም የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተቋምን መምራት እና ተቋምን መቃወም የተለያዩ መሆናቸውን መገንዘብ እንደሚኖርባቸው፤ ኃላፊነት ሲሰጣቸውም ለይስሙላ ሳይሆን ከፍ ያለ አበርክቷቸውን እንዲወጡ በሚጠይቃቸው መልኩ መሆኑን እና እነርሱም ይሄን አውቀው ለጋራ አገር አብሮ መስራትን ለሚቀጥለው ትውልድ ማሳየት በሚያስችላቸው ልክ መስራት እንደሚገባቸው ያሳሰቡበት ነው። በተመሳሳይ መልኩ የካቢኔ ውቅሩ ብዝሃነትን ያማከለ እንደመሆኑ እያንዳንዱ የተቋም አመራር ጭንቅላትና ልቡን ክፍት አድርጎ በነጻ ፍላጎት በጋራ መስራት እንደሚጠበቅበት በጥብቅ ያስገነዘቡበት ነው።
እንደ አጠቃላይ ለውጡ እና ለውጡን ተከትሎ የተወሰዱ እርምጃዎች፤ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫም በኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ባህልን፤ ቃልንም በተግባር ማዋልን አሳይቶናል። የመገፋፋት ጉዞንም በመተጋገዝ ቀይሮ ተፎካካሪዎችን በግብዣ የመንግስት አካል አድርጓል። እናም በቃል የተነገረ አካታችነት በተግባር ተገልጧል፤ የሚጠበቀው ኃላፊዎች ኃላፊነታቸውን እንዴት ይወጡት ይሆን የሚለው ሲሆን፤ ይሄን አውቆ በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስና መስራት ደግሞ ከእነርሱ ይጠበቃል።
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን መሰከረም 27 ቀን 2014 ዓ.ም