የመንደርደሪያ ብያኔ፤
የአንድ ትውልድ ዘመን ስንት ዓመት ነው? ሃያ አምስት? ሃምሳ? ሰባ ወይንስ ሰማንያ? የዘመኑን ትውልድ የሚወክለው የማሕበረሰብ ክፍልስ በዋነኛነት የትኛው ነው? ታዳጊዎች? ወጣቶች? ጎልማሶች ወይንስ አዛውንቶች? … እነዚህ እንቅብ ሙሉ የመከራከሪያ ጥያቄዎች በዘመናት መካከል በተሟጋቾች አንደበት ሲቀባበሉ ቢኖሩም የነጠረ የጋራ ስምምነት ላይ ስላልተደረሰባቸው ዛሬም ድረስ በሃሳብ ደረጃ ጥሬ እንደሆኑ ዘልቀዋል::
እኔም ጉዳዩን እንደ አዲስ ቀስቅሼ ሙግቱን ማጋጋል ስለማልፈልግ ለዚህ ጽሑፍ ድጋፍ እንዲሆነኝ ብቻ የራሴን ብያኔ (working definition) በመስጠት የአንድን ትውልድ ዘመን በመንግሥታት የዕድሜ ቆይታ ልክ ወክዬ ማሳየቱን መርጫለሁ:: የተዥጎረጎረውን የሀገራችንን ቀደምት ሥርዓቶች በሙሉ ለመዳሰስ የጋዜጣው ውሱን ገጽ ስለማይፈቅድልኝ የመረጥኳቸው ከወዲህ ያሉትን የቅርቦቹን ሦስቱን ማለትም የዓፄውን፣ የደርግንና የህወሓት/ኢህአዴግን መንግሥታትን ብቻ ይሆናል:: አንድን ትውልድ ለመወከል ገና ዳዴ በማለት ላይ ያለው የብልጽግና ፓርቲ መሩ መንግሥታዊ ሥርዓት የመዳረሻችንና የማጠቃለያችን ማረፊያ ስለሆነ ዋነኛው ትኩረታችን በታሪክ ላይ ብቻ መንጠልጠል ሳይሆን ነበሩን እውነታ በጥቂቱም ቢሆን ለመዳሰስ ይሞከራል::
ትውልድ የሚወከለው በየሥርዓተ መንግሥታቱ በነበሩት ዜጎች ድምር ውጤት የመሆኑ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ ለዚህ ጽሑፍ ዐውድ የተመረጠው በአፍለኛው ዕድሜ ላይ የሚገኘው ወጣቱ የማሕበረሰብ ክፍል ነው:: በዚሁ ጥቅልና የጸሐፊው አቋም (Columnist Liberty) ብያኔ መሰረት የየሥርዓተ ዘመኑን ትውልድ የመለያ ባህርያትና ሥነ ልቦናውን እንደሚከተለው በወፍ በረር ቅኝት ለመዳሰስ ይሞከራል::
የዓፄው ዘመን ኢትዮጵያዊ ወጣት – “ልጆቹ”፤የግርማዊ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ወጣቶች ሥርዓቱን ለመለወጥ ያደረጉት ትግልና የነበራቸው ጉጉትና ናፍቆት በዝርዝር ታሪኮች ተጽፎ የተላለፈልን ስለሆነ ጠለቅ ብዬ አልዳስሰውም:: በአጠቃላይ ምልከታ ይገለጽ ከተባለ ግን የዘመኑ ወጣት በእጅጉ ስክነትና ትዕግሥት ይጎድለው ስለነበረ የተረጋጋ አልነበረም:: የለውጥ ፈላጊነቱ ነበልባል ስሜት ከሚንቀለቀለው የወጣትነት ዕድሜው ጋር ተዳምሮ መክነፍ እንጂ መርጋት አልሆነለትም:: ሥርዓቱን በጅምላ ከመቃወምና ንጉሡን ከመንቀፍ ውጭ የፍላጎቱ መዳረሻና ግቡ ምን እንደነበረ እንኳን በሚገባ የተገነዘበ አይመስልም::
ከሀገሩ ጉዳይ ጎን ለጎንም የራሱን ትግል ሳይቋጭና ከውጤት ሳያደርስ ለአፍሪካ የአርነት እንቅስቃሴዎችና ለዓለም ጭቁን ሕዝቦች ድምጽ ካልሆንኩ እያለ የትግል ስልቱንና ርእዩን አደበላልቆ ሲዋዠቅ እንደነበርም ይታወሳል:: ይከተለው የነበረው የሀገሪቱ “የአይዲዮሎጂ ብፌ” እና “የአርአያ ትግል ተምሳሌቶቹ” በአብዛኛው የሌላ ሀገር ባዕዳን “አብዮተኞች” ስለነበሩ የትውልዱ አቋም “የአራምባ እና የቆቦን” ያህል ተራርቆ ነበር:: በተለምዶ ካልሆነ በስተቀር አራምባና ቆቦ በምናስበው ደረጃ ልክ የተቃራኒ አድማስ ጥግ ዳርቻዎች ያለመሆናቸውን ልብ ይላል::
በሌላ ጎኑም ይኼው የዓፄው ዘመን ወጣት የሀገሩ ፍቅር በውስጡ የሚንተከተክ ብቻ ሳይሆን ለእርሱ “ኢትዮጵያ” የተሰኘችው ሀገሩ የነፍሱ ዝማሬና የህልሙ ፍቺ መክሰቻ ተወዳጅ እናቱ ነበረች:: ቋንቋም ሆነ ብሔር ወይንም ሌላ የልዩነት መለዮ በእርሱ እምነት ውስጥ ምንም ስፍራ አልነበራቸውም:: እርሱ ለኢትዮጵያ የምር ልጅ መሆኑን ማመኑ ብቻም ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሙትላት ቢባል እንኳን አንድያ ነፍሱን ለመስጠት የሚሳሳ አልነበረም::
እጅግ አስገራሚ ከሆነው ፅኑ የሀገር ፍቅር ስሜቱና ከሥነ ልቦናው ውቅር ውስጥ ተፈልቅቆ የወጣለት የወል ስምና መታወቂያ “ልጆቹ” የሚል ነበር:: የሥርዓቱ አስኳል የነበሩት ንጉሡም ሆኑ ልዑላንና መኳንንቱ፣ የፀጥታ አስከባሪዎችና ወላጆችም ሳይቀሩ ወጣቶቹ “ሲያብዱም” ሆነ ሲያጠፉ አለያም ሲያለሙም ሆነ ሲገነፍሉ መታወቂያቸው “ደግሞ ልጆቹ ተነሳባቸው” የሚል ነበር:: ልጆቹ ረበሹ፣ ልጆቹ አድማ ጠሩ፣ ልጆቹ ተመረቁ፣ ልጆቹ እንዲህና እንዲያ አደረጉ ወዘተ. እየተባሉ ሲጠቀሱም “ልጆቹ” በሚል የቅጽል መለያነት ነው:: ሀገራቸው እናት እነርሱም ያለ ልዩነት ልጆች ለመሆናቸው ከማሳያዎቹ ውስጥ አንዱ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል::
የማሕበረሰቡ የሥነ ልቦና ውቅር በዋነኛነት ይህንን ይመስል እንጂ “ልጆቹ” የሚለው መለያቸው በብዙ ዘርፍ ተተንትኖ ጊዜው ሲፈቅድ ወደፊት በዝርዝር ይብራራል:: በዘመኑ የብሔራዊ መዝሙር ውስጥ ሳይቀር “ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ በልጆችሽ!” የሚለው ሀገረግና ጽንሰ ሃሳብ በራሱ ይህንኑ የሚደግፍ ይሆንን ያሰኛል::
የዘመነ ደርግ ወጣት – “ያ ትውልድ”፤የዚህን ዘመን ወጣት በአጭር ገለጻ እንበይነው ከተባለ “አንዱ ማገዶ ሌላኛው እሳት” ሆነው በፖለቲካ ትርምስምስ
ሲያጠፉና ሲጠፋፉ የኖሩ ነበሩ ብሎ መጠቅለል ይቻላል:: “ያ ትውልድ” የሚለው ኋላ-መጥ ስያሜ ወቅቱን በሚገባ ይገልጽ ይመስለናል:: በቀይና በነጭ ቀለማት የተወከሉ የአመለካከትና የአይዲዮሎጂ ልዩነቶች፣ “እናቸንፋለንና እናሸንፋለን” የሚሉ የፀጉር ስንጠቃ ክርክሮች አላግባባ ብሏቸው ሟችና ገዳይ በመሆን አጠፋፋቸው እንጂ አልጠቀማቸውም::
ለሀገራቸው የነበራቸው ትልቅ የጋራ ርዕይ እንደ ባሉን የተወጠረ ቢሆንም ግዝፈቱ የሟሸሸው መደማመጥ አቅቷቸው እርስ በእርስ በመጠፋፋት ነበር:: ሩቅ አዳሪ ቅርብ አዳሪ በመሆንም “ያ ትውልድ” ዓላማ የለሽ ሆኖ እንደ ተወርዋሪ ኮከብ ህልሙና ርዕዩ ሳይፈታለት ብልጭታውን አሳይቶ ሊከስም ግድ ሆኗል::
የዚህ ትውልድ የአጥፊና ጠፊነቱ ህፀፆች እንደተጠበቁ ሆነው በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነቱ ላይ ግን በፍጹም የሚደራደር አልነበረም:: እርግጥ ነው ሥርዓቱን ለመጣል ሲባል ከአንዳንድ ተጻራሪ ኃይላት ጋር አልፎ አልፎ ትብብር ማድረጉን ታሪክ ሊሸሽገው አይችልም:: በህቡዕና በግላጭ የተጠለለባቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ሳይቀሩ ይሰየሙ የነበረው የኢትዮጵያን ስም ባማከለ ፍቅር ነበር:: ለማሳያነት ጥቂቶቹን ብቻ እናስታውስ፡- ኢሕአፓ (የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ)፣ መኢሶን (የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ)፣ ኢጭአት/ኢጭአፓ (የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ፓርቲ)፣ በተለያዩ ፓርቲዎች ኅብረት የተመሰረተው ኢማሌዲኅ (የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒንስት ዲሞክራሲያዊ ኅብረት)፣ የገዢው መንግሥት ፓርቲ እንኳን ሳይቀር ኢሠፓ (የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ) ወዘተ. መባሉን ማስታወስ ይቻላል::
በየፓርቲዎቹ መዝሙሮችም ሳይቀር ኢትዮጵያ ዋና ተጠቃሽ ነበረች:: “ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ቅደሚ” የሚለው የዘመኑ ብሔራዊ ሙዝሙርም ቢታወስ አይከፋም:: ፍጻሜው ሳያምር ቀረ እንጂ የደርግ መንግሥት ይዞ የተነሳው ቀዳሚ መፈክር ሳይቀር “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚል እንደነበር አይዘነጋም:: “የ60ዎቹ ትውልድ፣ አጥፊና ጠፊው ትውልድ፣ እንደ ሻማ ቀልጦ ያለቀው ትውልድ ወዘተ.” በመባል የሚታወቀው “ያ ትውልድ” እርስ በእርሱ እየተፋለመ ራሱን አክስሞ ይለፍ እንጂ “ኢትዮጵያ” ለእርሱ ዋና ጉዳዩና ኢትዮጵያዊነቱም ክብሩ እንደነበር ማንም ሊክድ አይችልም:: የ“ያ ትውልድ” ዘመን ነግቶለት የመሸው በዚህ አይነት ትራጀዲ ተጠናቆ ነበር::
የዘመነ ህወሓት/ኢህአዴግ “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ”፤ይህ ዘመንና ሥርዓቱ ለትውልዱ ውክልና የሚበቃ የሞራል ብቃት አልነበረውም:: የሚመሰለውም “በመርዝ ብልቃጥ” ተምሳሌትነት ነው:: የሥርዓቱ ዋነኛው “ሞተር” የነበረውና በአሁኑ ወቅት “ሀገር ካልገነጠልኩ” እያለ ከትውልድ፣ ከታሪክና ከህሊናው ጋር እየተጋጨ ያለው አሸባሪና ጦረኛ ቡድን በዋነኛነት ሲሰራ የኖረው ወጣቱን ትውልድ በተለየ ሁኔታ፣ ሕዝቡን በአጠቃላይ ዕቅድ ለማኮላሸት እንጂ ሀገር ለመገንባትና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማስቀደም አልሞ አልነበረም::
ቡድኑ ገና ከማለዳው ደርግን አስወግዶ በትረ ሥልጣኑን እንደጨበጠ የወሰደው ቀዳሚ እርምጃ ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያን ራሷን አክስሞና አፈራርሶ ብቻውን ለመግነን ነበር:: ከጫካ ማኒፌስቶ እስከ ሽግግር መንግሥቱ ቻርተር፣ ብሎም በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ሳይቀር ሲነሰንስ የኖረው መርዝ የኢትዮጵያን መልክ የሚያደበዝዝ ተግባር እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው::
መላው የኢትዮጵያ ወጣት እንዲቀረጽ ሲሰሩ የኖሩትም በራሳቸው ወጣቶችና በቀዳሚ ታጋዮቻቸው አማካይነት “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” የሚለውን የግፋቸውን የሥነ ልቦና ሌጋሲ በወጣቱ ውስጥ ለማስረጽ ነበር:: “በተራራ ከፍታና ነቅናቂነት” የመሰሉትን ርካሻ የሥነ ልቦና ችግኝ ኮትኩቶ ለማሳደግ የሞከሩትም በብዙ ሀገራዊ ጉዳዮች ውስጥ በማካተት እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም::
ቀዳሚ ሥራቸው ያደረጉትና “ተራራውን አንቀጥቃጭ” ያሉት ትውልድ እንዲተዋወቅ የፈለጉትም ሀሰት የገነነበት ተከታታይ መጻሕፍትን በዚሁ ርዕስ ሥር በርከት ባሉ ቅጾች በማሳተምና በገፍ በማሰራጨት ነበር:: በዚህም ዘዴ ነባር ኢትዮጵያዊ ዕሴቶች፣ ባህሎችና ወጎች፣ በጽናት ተገንብቶ ለዘመናት የኖረው የኢትዮጵያዊነት መገለጫ በጥቂት ግለሰቦች ተሸፍኖ እንዲገንን በጽኑ ተሰርቶበታል:: ብሔረሰቦች በራሳቸው ቅጥር ታጥረው የጎሪጥ እንዲተያዩም አጥብቆ ስለተሰራበት እነሆ የመራራውን ጉሽ ውጤት ሀገሬ ለመጎንጨት ግድ ብሏታል:: ኢትዮጵያዊነትን በአሃዳዊነት፣ የብሔረሰቦችን የእኔነት መለያ ሳይቀር ባዋረደ ስልት “ትምክህተኛና ምንትስ” እያሉ ሲዘሩ የኖሩት አረም ያስከተለው ጥፋትም የሚዘነጋ አይደለም::
እውነታው ይህንን ይመሰል እንጂ እነርሱ ባልገመቱት መልኩ የኢትዮጵያ መላው ወጣቶች ከእነርሱ የተራሮች አንቀጥቃጭነት የውሸት ትርክት ከፍ ያለና ሀገራዊ መናበብ የተደረገበት “ሥር ነቀል ትግል” በማቀጣጠል ይህ ግፈኛ ሥርዓት ተፈንግሎ ሊወገድ ግድ ብሏል:: “የኮፈሷቸው የትምክህት ተራሮቻቸው ተነቃቅለውም” ወደመጡበት የደደቢት በረሃና ዋሻዎች ተሰደው ቅስማቸውና አቅማቸው ተሸምድምዷል:: “ያዳቆነ ሰይጣን…” እንዲሉም ይሄው የበረኸኛነት ልክፍተኛነታቸው አልለቅ ብሏቸው በጀግናው የሰሜን ዕዝ ሠራዊታችን ላይና በሰላማዊ ዜጎችና ክልሎች የፈጸሙትና እየፈጸሙ ያሉት ክህደትና ወረራ ምን መልክ እንደነበረውና እንዳለው እያየንና እየሰማን ስለሆነ ወደፊት ክስረት ያስተናገዱበት ድፍረታቸውና የተዋረዱበት የሽንፈታቸው ቅሌት በዝርዝር ሲገለጥ ለመላው ዓለም ማስተማሪያ መሆኑ አይቀርም::
የዘመነ ብልጽግና ወጣት – መደፈር የጎፈነነው ጀግና ትውልድ፤የቀዳሚው የህወሓት ሥርዓት በዘራው እኩይ እንክርዳድ ምክንያት ከሁለት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ወጣቶች በየብሔረሰቦቻቸው ቋንቋ ስያሜና አደረጃጀት ተሰባስበው ሥርዓቱን ከመታገል ጎን ለጎን በተሳሳተ የጠላት ቅስቀሳ በመታለል ብዙ ሀገራዊ ጥፋቶች ማስከተላቸው አይዘነጋም:: እያደር ግን ስህተታቸው ሲገባቸውና የጠላት እኩይ ሴራ ፍንትው ብሎ እየተገለጠላቸው ሲሄድ እነዚያው የሀገሪቱ ወጣቶች በፍጥነት ራሳቸውን ከእውነታና ከአዲሱ የሀገራዊ ለውጥ ጎን በማሰለፍ ታሪክ መስራታቸው ሁሌም ሲዘከርላቸው የሚኖር ታላቅ ተግባር ነው::
በብሔር ተቧድኖ ለተሳሳተ ዓላማ መሳተፍን እርግፍ አድርገው የራሳቸውን ቋንቋና ባህል ከማክበር ጎን ለጎን ወደ ታላቁ የኢትዮጵያ ክብር መሰባሰባቸው በእጅጉ የሚያስገርምና ለውጡን ልብ ብሎ ለተከታተለ ሰው “እንዴት ሆኖ” የሚያሰኝና የሚስደንቅ ክስተት ነው:: የአሸባሪውን የትህነግ ቡድን ለመመከትና ወረራውን ለመቀልበስ ከሠፈር እስከ ድንበር፣ ከስንቅ እስከ ብርቅ ነፍስያ እየከፈሉ ያሉት መስዋዕትነትም ዘለዓለማዊ ክብር የሚያሰጠው ነው::
የዘመነ ብልጽግና ወጣቶች የሀገራቸውን ከፍታ ማረጋገጫ ዋነኛ ርዕይ ከግብ ለማድረስ እየፈጸሙት ያለው የበጎ ተግባር አገልግሎቶችም እጅግ የሚያበረታቱና የሚያስመሰግኑ ናቸው:: ብልጽግናው ቁሳዊ በረከት የሚያስከትል ብቻም ሳይሆን በአእምሮ መታደስንም ስለሚያጠቃልል የነገይቱን ሀገራቸውን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የቆሙት በትክክለኛው ጎዳና ላይ ነው:: የዛሬዎቹ የኢትዮጵያ ወጣቶች ትግላቸውና ተግዳሮታቸው የበዛ ቢሆንም በአሸናፊነት ለመወጣት ቁርጠኞች እንደሆኑ በብዙ ተግባራቸው አረጋግጠዋል:: በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ በዲሞክራሲ ሥርዓት የቆመውን መንግሥታቸውን ለመደገፍ ያሳዩት ቁርጠኝነትም ለሌሎች ሀገራት የዕድሜ እኩዮቻቸው ትምህርት የሚሆን ነው::
ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ምርጫዋን አሳክታ ሕዝቡ ይሁንታ የሰጠው መንግሥት እንዲመሠረት ዋነኛውን ድርሻ የወሰዱት ወጣቶቻችን ስለሆኑ በዚህም አኳያ ደማቅ ታሪክ አስመዝግበዋል:: ምድራቸውን በልምላሜ፣ ሕዝባቸውን በብልጽግና ለማስዋብና የሀገራቸውን የወየበ ፊት ለማደስ በቁርጠኝነት የትውልድ ተረኛነቱን አደራ ተቀበለው እያሳዩ ያሉት ዘርፍ ብዙ አርአያነት የሚደነቅና የሚወደስ ነው ብሎ መጠቅለሉ ሳይሻል አይቀርም:: የነገይቱ ኢትዮጵያ ብሩህ መልክ የተሳለው ታሪክ እየሰሩ ባሉት በዛሬዎቹ ወጣቶቿ ሰሌዳ ላይ ስለሆነ ለአሸናፊነቷና ለብልጽግናዋ ምንም የሚያጠራጥር ስጋት አይኖርም:: ኢትዮጵያ ሆይ ተስፋ የተጣለበትን መንግሥትሽን ስለመሰረትሽና የዲሞክራሲን መሠረት ስለጣልሽ እንኳን ደስ አለሽ:: ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2014