ሰላም ውድ የአዲስ ዘመን ቤተሰቦች፤ እንደምን ቆያችሁ፤ ባለፈው ሳምንት የፍረዱኝ አምድ ዝግጅታችን በአደራ ተሰጥቶ በኋላ ወደቀበሌ እንዲዞር ተደረገ በተባለና በምትኩ ተወስዶ ነበር ስለተባለ የቀበሌ ቤት እና በዚሁ ዙሪያ ስለተነሳ ክርክር አስመልክተን የጉዳዩን ባለቤት ቅሬታና በዚህ ዙሪያ ህጉ ምን ይላል በሚል ሰነዶችን አገላብጠን ያገኘነውን መረጃ ይዘን መቅረባችን ይታወሳል:: ታሪኩን ለማስታወስ እንዲረዳችሁም በቅድሚያ ከባለፈው ሳምንት መግቢያ ጥቂት እናስታውሳችሁ::
“አቶ ጌታቸው ከበደ ወንድምጊዜ ይባላሉ:: ነዋሪነታቸው በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ነው:: የአቶ ከበደ ወንድም ህጋዊ ወራሽ ናቸው:: ከ2007 ዓ.ም በፊት በተለምዶ አዲሱ ገበያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት የቤት ቁጥ 077 ይኖሩ ነበር:: ከ2007 ዓ.ም በፊት በጉለሌ ከፍለ ከተማ ይኖሩበት የነበረው ቤት አባታቸው አቶ ከበደ ወንድምጊዜ ቃሊቲ የነበራቸውን ቤታቸውን በአደራ ለመንግስት በመስጠት በማካካሻነት እንደተቀበሉት ይናጋራሉ::
በ2004 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰነድ አልባ ቤቶች ጋር በተያያዘ የወጣን መመሪያ ተከትሎ የአቶ ከበደ ወንድምጊዜ ልጅ እና ህጋዊ ወራሽ የሆኑት አቶ ጌታቸው ከበደ «አባቴ ለመንግስት በአደራ የሰጠውን ቤት ይመለስልኝ »ሲሉ መንግስትን ይጠይቃሉ:: ይሁን እንጂ አባታቸው በአደራ ለመንግስት የሰጡትን ቤት የአቃቂ ቃሊቲ፣ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤቶች ልማት አስተዳደር ፅህፈት ቤት እና የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፅህፈት ቤት ሊመልሱልኝ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው “የተፈጸመብኝን በደል ህዝብ አይቶ ይፍረደኝ “ ሲሉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አቤት አሉ::”… በክፍል ሁለት ዝግጅታችንም የዚህን ቀጣይና የመጨረሻ ክፍል ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ቆይታ::
የአቃቂ ክፍለ ከተማ ቤቶች ልማት አስተዳደር ምላሽ
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል በአቃቂ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ቡድን መሪ የሆኑትን አቶ ዳኛቸው ገብረ ሚካኤል “ማካካሻ ቤት የሚሰጠው ምን ሲሆን ነው?” ሲል ጠየቀ:: አቶ ዳኛቸው የማካካሻ ቤት መመሪያን ጠቅሰው እንደተናገሩት ማካካሻ ቤት የሚሰጠው ያልተወረሰ ቤት መኖሩ ሲረጋገጥ እና ከሚመለከተው አካል በአደራ ያስረከቡበት ቅፅ ወይም የሰነድ ማረጋገጫ ሲገኝ ነው:: አንድ ሰው በአደራ ቤቱን ለሚያስተዳድር ህጋዊ አካል ሲያስረክብ ራሱን የቻለ የማስረከቢያ ቅፅ አለ:: የቅጹም 004 በመባል ይጠራል::
በ2004 ዓ.ም የጉለሌ ክፍለ ከተማ ከአቶ ጌታቸው(አቤቱታ አቅራቢው) አባት በቀድሞ ስሙ በቃሊቲ ከተማ በአሁኑ መጠሪያው ወረዳ ሶስት የሚገኝን ቤት ለመንግስት ባስረከቡ ጊዜ የጉለሌ ክፍለ ከተማ በማካካሻነት ቤት እንደሰጣቸው የሚገልጽ ደብዳቤ ለአቃቂ ክፍለ ከተማ ይልካል:: ይህን ደብዳቤ ዋቢ በማድረግ የአቃቂ ክፍለ ከተማ ለወረዳ ሶስት ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ለአቃቂ ክፍለ ከተማ በተላከው ደብዳቤ መሰረት የአቶ ጌታቸው ከበደ አባት በአደራ የሰጡትን ቤት ለልጃቸው ለአቶ ጌታቸው እንዲመለስ አዝዞ ነበር:: “በዚህ ላይ ምን ይላሉ? “ ሲል የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የቤቶች ልማት አስተባባሪ የሆኑትን አቶ ዳኛቸው ገብረ ሚካኤልን ጠየቀ::
ስለዚህ ቤት ጉዳይ መነሳት ያለብን ከአቤቱታ አቅራቢው ማመልከቻ ነው የሚሉት አቶ ዳኛቸው፤ አቤቱታ አቅራቢው የሚፈልገው በጉለሌ ክፍለ ከተማ በማካካሻ የተያዘው ቤት እንዲሰጠው ወይስ የአደራ ቤቱን እንዲመለስለት ነው የሚፈለገው ? የሚለውን ማጥራት እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ:: ከዚህ ጋር ተያይዞ አቤቱታ አቅራቢው በማመልከቻው የጠየቀው በጉለሌ ክፍለ ከተማ በማካካሻነት የተሰጠው ቤት እንዲጸናለት ነው:: የማካካሻ ቤት ለማግኘት ከፈለገ ደግሞ መጠየቅ ያለበት የአቃቂ ክፍለ ከተማን ሳይሆን የጉለሌ እንደሆነ ይገልጻሉ:: ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል አቤቱታ አቅራቢው በማመልከቻ የጠየቁት ማካካሻ ቤቱን ሳይሆን አባታቸው በአደራ የሰጡትን ቤት እንደሆነማስረጃዎችን በማቅረብ ለአቃቂ ክፍለ ከተማ የቤቶች አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ዳኛቸው አስረዳ::
ማረስረጃውም የአቃቂ ክፍለ ከተማ በቁጥር አስ/ቃ/ክ/ቤ/ልማ/810/2004 በቀን 07/08/ 2004 ዓ.ም በአቃቂ ክፍለ ከተማ ለወረዳ ሶስት የተጻፈ ነው:: ማስረጃውም እንዲህ ይላል፡- «ጉዳዩ የማካካሻን ቤት ይመለከታል:: በቁጥር ጉ/ክ/ከ/ቤ/ማስ//አ/2008/2004 በቀን 24/07/2004 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ለአቶ ከበደ ወንድምጊዜ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ቁጥር 077 የሆነ የመንግስት ቤት በማካካሻ የተሰጣቸው መሆኑን እና ስለማካካሻ ቤት አሰጣጥ ሁኔታ የሚገልጽ ዝርዝር መረጃ አያይዘው ልከውልናል:: በመሆኑም ግለሰቡ በወቅቱ በወረዳችሁ ያለውን የግል ቤት በማስረከብ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የማካካሻ ቤት ስለመውሰዳቸው በተገለጸው መሰረት የግል ቤታቸው በምርጫቸው መሰረት መመለስ የሚቻል መሆኑን እየገለጽን ከጉለሌ ክፍለ ከተማ የተላከልን ዝርዝር መረጃ የላክን መሆኑን እንገልጻለን:: »
ነገር ግን የጉለሌ ክፍለ ከተማ በጻፈው እና የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ደግሞ ወረዳ ሶስትን በአደራ የተያዘውን ቤት እንዲመልስ የሚያስገድደውን የትዕዛዝ ደብዳቤ እንደማይቀበሉት አቶ ዳኛቸው ይናገራሉ:: ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ከስድስት ወር በላይ ስለጉዳዩ ማጣራት ተደርጎበት የአቃቂ ቃሊቲ ቤቶች ልማት አስተዳደር የጻፈውን ደብዳቤ “ለምን አይቀበሉትም?” ሲል ጠየቀ:: አቶ ዳኛቸውም ትዕዛዙ የተጻፈው እኔ በሌለሁበት ጊዜ ነው ሲሉመለሱ:: ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም “በመንግሰት መዋቅር የተሰራን ነገር እርሶ ነበሩ አልነበሩ ምን ይቀይረዋል” ሲል ጠየቀ:: ነገር ግን አቶ ዳኛቸው ደብዳቤውን እንደማይቀበሉት ደግመው በመናገር አረጋገጡልን::
በጉለሌ የሚገኘው በቤት ቁጥር 077 በተመዘገበው ቤት ውስጥ አቶ ከበደ ወንድምጊዜ ቢሞቱም ቤተሰቦቻቸው ሲኖሩበት ነበር የሚሉት አቶ ዳኛቸው፤ ነገር ግን ሲኖሩበት የነበረው ቤት በማካካሻነት የተገኘ ባለመሆኑ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ከአቶ ከበደ ወንድም ጊዜ ጋር ከቤቱ ጋር ተያይዞ ምንም አይነት ውል ስላልፈጸሙ የአቤቱታ አቅራቢው የማካካሻ ቤት ጥያቄ እንደማይስተናገድ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ሲገልጽ አቤቱታ አቅራቢው ሌላ እድል ለመሞከር ወደ አቃቂ ቃሊቲ በመምጣት «በአደራ አባቴ የሰጡትን ቤት ይመለስልኝ »ሲሉ መጠየቃቸውን ይናገራሉ::
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም አቶ ዳኛቸው የተናገሩት ስህተት መሆኑን በማስረጃዎች አስደግፎ ሞገተ::
ይህን ተከትሎ አቶ ዳኛቸው «እሺ ስለጉዳዩ አስረዳኝ ሲሉ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልን ጠየቁ:: »የአዲስ ዘመን ዝግጅት ከፍል እንዲህ ሲል አስረዳ «በ2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሰነድ አልባ ቤቶች ጋር ተያይዞ መመሪያ መውጣቱን ተከትሎ አቶ ጌታቸው ከበደ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የሚኖሩበት ቤት በማካካሻነት የተረከቡት እንደሆነ በማስረዳት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ደግሞ በአደራ ያስያዙት ቤት መኖሩን በማስገንዘብ በአደራ ያስያዙትን ቤት ለማስመለስ ይረዳቸው ዘንድ የማካከሻ ቤት የሰጣቸውን የጉለሌ ክፍለ ከተማን መረጃ እንዲሰጣቸው ጠየቁ:: ጉለሌ ክፍለ ከተማ የሰጣቸውን መረጃ ዋቢ በማድረግ አቤቱታ አቅራቢው ወደ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መጥተው ስለጉዳዩ አስረዱ::
አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማም በጉዳዩ ላይ ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ጋር በርካታ ደብዳቤዎችን በመላላክ መረጃዎችን ተለዋወጠ:: ከዚህ በኋላ የአቃቂ ቃሊቲ ከፍለ ከተማ ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ባገኘው ሰነድ መሰረት «በአደራ የተያዘው ቤት ይመለስላቸው» ሲል በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ለሚገኘው ለወረዳ ሶስት ጻፉ:: ወረዳ ሶስትም በአደራ ከአቶ ጌታቸው አባት የተረከቡት ቤት ሶስት ቦታ ተከፍሎ ሶስቱም የቤት ቁጥር ስለተሰጣቸው «እንዴት አድርገን እንመልስ» ሲል ለክፍለ ከተማው ገለጸ:: ክፍለ ከተማውም እንደወረዳ ሶስት ሁሉ ስለተቸገረ ጉዳዩን ወደ አዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ጽህፈት ቤት መራ:: አሁን አቶ ዳኛቸው (የቡድን መሪው) እየነገሩኝ ያለው ሂደት ግን ከዚህ ሂደት በኋላ የአቤቱታ አቅራቢውን ጥያቄ መመለስ ሳትችሉ በቀራችሁ ጊዜ አቤቱታ አቅራቢው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ከሰወዱት በኋላ ስለተፈጠረ ነገር ነው:: » ሲል አስረዳ::
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል አያይዞም አቤቱታ አቅራቢው ጉለሌ ክፍለ ከተማን የማካካሻ ቤት ይሰጠኝ ብለው ከጠየቁ ማካካሻ ቤት እንዲሰጣቸው የጠየቁበትን ሰነድ “ ሊያሳዩኝ ይችላሉ?” ሲል የቡድን መሪውን አቶ ዳኛቸውን ጠየቀ:: የቡድን መሪው ግን የተጠየቁትን ሰነድ ማቅረብ አልቻሉም ::
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ጉዳዩ ሲጀመር ወደነበረው የመጀመሪያው ምዕራፍ መልሶ አቶ ዳኛቸውን እንዲህ ሲል ጠየቀ «በ2004 ዓ.ም ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ያገኛችሁትን መረጃ ዋቢ አድርጋችሁ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሶስት የሚገኘውን በአደራ ቤት የተወሰረው ቤት ለአቤቱታ አቅራቢው ለመስጠት ተስማምታችሁ ነበር:: ነገር ግን ከቤቶች ቁጥር መሰጠት ጋር ተያይዞ እንዴት መመለስ እንዳለባችሁ በተቸገራችሁ ጊዜ አቤቱታ አቅራቢው ደግሞ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በወሰዱት ወቅት ቀደም ሲል የአቤቱታ አቅራቢው ቤት እንዲመለስ እያላችሁ ስትጻጻፏቸው የነበሩትን ሰነዶች በመካድ ስለጉዳዩ ሙሉ መረጃ የለም በማለት በፍርድ ቤት ተከራከራችሁ:: በ2005 እና 2007 ዓ.ም በተካሄደው የፍርድ ቤት ክርክር አቤቱታ አቅራቢው ተሸነፉ:: “ስለዚህ ምን ይላሉ ?” » ሲል ጠየቀ:: “በወቅቱ አቤቱታ አቅራቢው አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ ስላልቻሉ ነው ክርክሩን የተሸነፉ።” ሲሉ አቶ ዳኛቸው መለሱ:: መረጃ ያለው በክፍለ ከተሞች እንጂ እንዴት ከአንድ ግለሰብ ሙሉ መረጃ እንዲያመጡ ይጠበቃል:: ውድ አንባቢያን እዚህ ላይ ፍርዱን ለእናንተው ትተናል::
ከፍርድ በኋላ በ2011 ዓ.ም በአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሶስት የሚገኘው የአደራ ቤት ለአቤቱታ አቅራቢው እንደሚገባቸው በመግለጽ እንደገና ለአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ጻፈ:: “በዚህ ላይ ክፍለ ከተማው ምን ይላል” ሲል የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል አቶ ዳኛቸውን ጠየቀ:: አቶ ዳኛቸውም “ወረዳው ምን አገባው” ሲሉ መለሱ::
ከሰነዶች ያገኘነው ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት በ2011 ዓ.ም በአቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሶስት የአደራ ቤቱ ለአቤቱታ አቅራቢው እንደሚገባቸው በገለጸ ማግስት የአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ጉዳዩን ለመመልከት ኮሚቴ አዋቀረ:: ውሳኔዎችን ወስኖ ለቤቶች አስተዳደር ምክትል ሃላፊ መራው:: ምክትል ሃላፊውም ወደ ህግ ክፍል መሩት:: የህግ ክፍሉም ለአቤቱታ አቅራቢው ቤቱ እንደማይገባቸው ውሳኔ አስተላለፈ::
ጉዳዩ ወደ ህግ ክፍሉ ከመመራቱ በፊት ገና ከጅምሩ ኮሚቴ ተዋቅሮ መረጃ በሚሰበሰብበት ወቅት ከኮሚቴዎቹ መካከል አንዱ እንደነበሩ የሚገልጹት አቶ ዳኛቸው፤ ቤቱ በአዋጅ 47/67 መወረሱን ይናገራሉ:: ለዚህም እንደማስረጃ ያቀረቡት ደግሞ በአደራ በተሰጠው ቤት ተከራይተው የሚኖሩ ሰዎችን ቃለ መጠየቅ በማድረግ ያገኙትን መረጃ ዋቢ በማድረግ እንደሆነ ያስረዳሉ:: ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም “አሁን ላይ ቤቱን ተከራይተው የሚኖሩ ሰዎች ምን አልባት ከቤቱ እንዳይወጡ በመስጋት የሚሰጡት ምላሽ ምን ያህል ታማኝ ሊሆን ይችላል ስንል” አቶ ዳኛቸውን ጠየቅን:: ስለጉዳዩ ሁነኛ መረጃ ስለሌለ ለማጣራት በአደራ ቤቱ ውስጥ ተከራይተው የሚኖሩ ሰዎች የሚሰጡትን የምስክርነት ቃል ለመጠቀም መገደዳቸውን ይናገራሉ::
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአቤቱታ አቅራቢው አባት ባቀረቡት ቅጽ ላይ እንደተመላከተው ሶስት ትርፍ ቤት እንደነበር ያሳያል የሚሉት አቶ ዳኛቸው፤ የነዋሪዎችን ቃለ መጠየቅ እና የአቤቱታ አቅራቢው አባት ያቀረቡትን ሰነድ የሚመለከት ማንም ሰው ቤቱ ተወርሷል ወደሚል ድምዳሜ መድረሱ የማይቀር መሆኑን ይገልጻሉ:: ነገር ግን ከሶስቱ ቤት ውጭ ያለ ያልተወረሰ ቤትም ሊኖር ይችላል:: ይሁን እንጂ አሁን ላይ በግቢው ውስጥ ስድስት ቤቶች በመገኘታቸው የተነሳ ያልተወረሰው የትኛው ቤት እንደሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ መሆኑን አመላክተዋል::
እነዚህን እና መሰል ስልቶችን ተጠቅመው ስለቤቶች ማጣራት ካደረጉ በኋላ በወረዳ ሶስት በአደራ ተሰጠ የተባለው ቤት ትርፍ በመሆኑ መንግስት የወረሰው እንጂ በአደራ ያልተሰጠ መሆኑን መግባባት ላይ በመደረሱ ቤቱን መመለስ አግባብነት እንደሌለው ኮሚቴው መወሰኑን አቶ ዳኛቸው ይናገራሉ::
ይሄን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም “ቤቱ በአዋጅ ተወርሷል ብለው ያምናሉ?” ሲል አቶ ዳኛቸውን ጠየቀ:: አቶ ዳኛቸውም ያለምንም ጥርጥር ተወርሷል ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ:: የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም በ1968 ዓ.ም የቃሊቲ ከተማ እና የአዲስ አበባ ማዘጋጃ የጻፈው ደብዳቤ እንደሚያመላክተው ቤቱ በማካካሻ መንግስት የተረከበው እንጂ ተወርሷል አይልም:: ስለዚህ “እናንተ ከምን ተነስታችሁ ተወርሷል ልትሉ ቻላችሁ?”:: ስንል አቶ ዳኛቸውን ጠየቅን:: አቶ ዳኛቸውም ከአዋጁ በኋላ ቤቱ ተከራይቶ እንደነበር የሚያሳዩ ሰነዶች መኖራቸውን ገልጸው፤ የቃሊቲ ከተማ እና የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ በ1968 ዓ.ም የጻፉትን ደብዳቤ እንደማይቀበሉት ይናገራሉ::
የሚጣረሱ ሁለት ሰነዶች ውድ አንባቢያን ሰነዶች የቱንም ያህል አንደሚጣረሱ ለማሳየት ደብዳቤዎችን እንደወረዱ አቅርበናቸዋል::
ሰነድ አንድ፡- ቁጥር፡- አቃ/ቃ/ክ/ቤ/ል/አስ/1925/11
ቀን፡05/06/2011 ዓ.ም
ለአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ/መን/ቤ/አስ/ጽ/ቤት
አዲስ አበባ
ጉዳዩ፡- የማካካሻ ቤት ጥያቄን በተመለከተ ይሆናል!
አቶ ጌታቸው ከበደ ወንድምጊዜ የወላጅ አባታቸው የሆነውን እና በውርስ ያገኙትን ቤት በዚህ በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ በወረዳ 3 የቤት ቁጥር 395-400 ድረስ የሆናቸውን ቤቶች ከቅጽ 003-1 እስከ 003-8 ባለው የመረካከቢያ ሰነድ አስረክበው በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 በማካካሻ የተሰጠ ቤት የነበረ ሲሆን ይህ የተሰጣቸው ቤት ከዚህ ቀደም ካስረከቡበት ቤት ጋር ተመጣጣኝ ያልሆነ በመሆኑ የቀድሞው ቤታቸው እንዲመለስላቸው በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 የሚገኘውንና በአቶ ከበደ ወንድምጊዜ የተመዘገበው መኖሪያ ቤት ቁጥር 077 በወይዘሮ ማዕሩ ገብረ ክርስቶስ ስም ተመዝግቦ እንደሚገኝ ምላሽ የተሰጣቸውና የተገለጸላቸው መሆኑን ባቀረቧቸው መረጃዎች ልንረዳ ችለናል::
ለዚህም 1ኛ/ በቁጥር 1172 /1750/67 ህዳር 9 ቀን 68 ዓ/ም በአቃቂ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት ለጉለሌ ወረዳ ቀበሌ 01/01/04 የህብረት ስራ ማህበር ጽ/ቤት ሐምሌ 19 ቀን 67 ዓ/ም በወጣው አዋጅ መሰረት ቤቱን ያስረከቡበት ቅጽ ከ003-1 እስከ 000-8 ተራ ቁጥር 8/ስምንት/ ገጽ ተሞልቶ የተላከ ደብዳቤ መኖሩ፧ ሁለተኛ/ በቁጥር 3371/1750/67 ነሀሴ 27 ቀን 1967 ዓ.ም የአቃቂ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት ለጉለሌ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ በአቃቂ ከተማ ውስጥ በወር 20 ብር የሚከራየውን ቤታቸውን በአዋጁ መሰረት ማስረከባቸውንና በምትኩ ከኪራይ ለመዳን እንዲችሉ ያስረከቡበትን ደብዳቤ ማግኘታችን፤ ሶስተኛ/ በቁጥር ጉ/ክ/ከ/ወ/7/ዲ/ግ/አስ/1395/04 በቀን 19/07/2004 ዓ/ም የጉለሌ ክ/ከ/ወ/7/ ዲዛይንና ግንባታ አስ/ጽ/ቤት ለጉለሌ ክ/ከተማ ቤ/ማስ/የስ/ሂደት በጻፈው ደብዳቤ በወረዳችን ክልል ውስጥ በንኡስ ቀበሌ 04 የቤት ቁጥር 077 ያለው መረጃ ለአቶ ከበደ ወንድምጊዜ ከአቃቂ ክፍለ ከተማ የቤት ቁጥር የሌለውን ቤት በአዋጅ ተወርሶ ያስረከቡ መሆኑና በወረዳቸው ክልል ውስጥ የሚገኘው የቤት ቁጥር 077 ኪራዩ ተካክሶላቸው ምንም ኪራይ ሳይከፍሉ በማካካሻ ቤትነት የተሰጣቸው መሆኑን፤ አራተኛ/ በቁጥር ጉ/ክ/ከ/ወ/ግ/ከ/ቤ/ል/314/07 በቀን 27/05/2007 ዓ.ም የጉለሌ ክ/ከ/ወ/7/ኮን/ቤ/ል/ጽ/ቤት ለጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ለንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ በወረዳቸው በቀድሞ ቀበሌ 04 የቤት ቁጥር 077 በአዋጅ ቁጥር 47/67 መሰረት ተወርሶ በመንግስት ቤትነት ተመዝግቦ ለአቶ ከበደ ወንድም ጊዜ የተከራየ ሲሆን የቤት ኪራዩም 20 ብር መሆኑን ተገልጾ የተመዘገበ መኖሩ፧ በመሆኑም የወረዳ 3 መን/ቤ/አስ/ጽ/ቤት በቀን 04/06/2011 ዓ/ም ባደረገው የፕሮሰስ ካውንስል ስብሰባ የአቶ ጌታቸው ከበደ ማመልከቻ መሠረት በማድረግ መረጃዎቹን ሁሉ የማጥራት ስራ ሰርተናል::
ስለዚህ አንደኛ ከላይ የገለጽናቸውና ሌሎች ያልተገለፁ በርካታ መረጃዎችን በማየት፤ ሁለተኛ በአካል ወርደን ያየናቸውና በአሁኑ ሰዓት ተከራይ የሚገኝባቸው የቤት ቁጥር 395-400 ድረስ የሚገኙ ሰባት መኖሪያ ቤቶች ህጋዊ የኪራይ ውልና ደረሰኝ ይዘው የሚኖሩ መሆናቸው ከወረዳችን ማይክሮ ግብር ከፋዮች ቅ/ጽ/ቤት መረጃዎችን አግኝተናል::
በመሆኑም አመልካቹ ከላይ የተገለጹትን ቅደም ተከተሎችን ያካሄዱትን በመመልከት የማካካሻ ቤቱን እንዲያገኙ ፕሮሰስ ካውንስሉ የወሰነ ሲሆን፤ የክፍለ ከተማው መን/ቤ/ል/አስ/ጽ/ቤት ለባለጉዳዩ አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያመቻችላቸው እንጠይቃለን:: ሲል የወ/3/መን/ቤ/አስ/ጽ/ቤት ይጠይቃል::
ውድ አንባቢያን ይህንን ሰነድ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት አስተዳደር ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ዳኛቸው ወረዳ ምን አገባው ሲሉ አጣጥለውታል::
ሰነድ ሁለት
የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ፤ ጥር 30/አአ/ቤ/ል/አስ/ቢ7/ቀን16/11/13 ዓ.ም ለአቶ ጌታቸው ከበደ
አዲስ አበባ
ጉዳዩ፡- የአቶ ጌታቸው ከበደ አቤቱታን
ይመለከታል፤
አቶ ጌታቸው ከበደ በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ወረዳ 03 የቤት ቁጥር ከ395 እስከ 400 ድረስ የተዘረዘሩበት ቤቶች ለወላጅ አባቴ ለአቶ ከበደ ወንድምጊዜ በአደራ መንግስት እያስተዳደራቸው የሚገኝ ሲሆን አሁን ቤቱ እንዲመለስልኝ በሚል ለቢሮአችን በቀን 22/03/2013 ዓ.ም በተፃፈ ማመልከቻ ጠይቀውናል:: በዚሁ መሠረት የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ለአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በቁጥር 14/አአ/ቤ/ል/አስ/ቢ 867/13 በቀን 8/06/13 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ በጽ/ቤቱ የህግ ክፍል በጉዳዩ ላይ የወጣውን የህግ አግባብነት ጭምር በማካተት ክፍለ ከተማው መልስ እንዲሰጥበት አሳውቋል:: ክፍለ ከተማውም በቁጥር አቃ/ቃ/ክ/ከ/ቤ/አ/ጽ/ቤት/4047/2013 በቀን 21/10/2013 ዓ.ም የሚከተለውን መልስ ሰጥቷል::
አንደኛ በክፍለ ከተማችን በወረዳ 03 በቤት ቁጥር 395 – 400 ያሉት ቤቶች በአዋጅ ቁጥር 47/67 መሠረት የተወረሱ እንጂ ቤቶቹ በአደራ የተሰጡ ስለመሆናቸው የሚያሳይ ማስረጃ የሌለ መሆኑ፣ ሁለተኛ አቶ ጌታቸው ከበደ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአቃቂ ቃሊቲ ምድብ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 3185/05 በቀን 22/2/2006 ዓ.ም በእነዚሁ ቤቶች ጉዳይ የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ/አስተዳደርን ክስ መስርተው የነበረ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ግራና ቀኝ በማየት የግለሰቡን ክስ ውድቅ ማድረጉ በመጥቀስ የአቃ/ቃ/ክ/ከ/አስተዳደር ምላሽ ሰጥቶናል:: በመሆኑም የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮም ከላይ የተዘረዘሩትን ምላሾችና ሌሎች የህግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ከሰጣቸው ምላሽ በመነሳትና በራሱ ባለሞያም በመመርመርና በማመሳከር ርስዎ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን እንገልፃለን::
አቶ ጌታቸው ከበደ የተባለ ግለሰብ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 የቤት ቁጥር 395 እስከ 400 ድረስ የተዘረዘሩት ክፍል ቤቶች ከወላጅ አባታቸው በአቶ ከበደ ወንድምጊዜ ሥም በአደራ መንግስት እንዲያስተዳድረው የሰጡ መሆኑን እና በጉለሌ ክፍለከተማ ቤቶች አስተዳደር ጽ/ቤት ወረዳ 07 የቀድሞ ቀበሌ 04 የቤት ቁጥር 077 በማካካሻ የተሰጣቸው መሆኑን በመግለጽ የአደራ ቤቱ እንዲሰጣቸው ባመለከቱት መሠረት
በየደረጃው በሁለቱም ክፍለ ከተሞች እንዲሁም በቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ በኩል በተሰጣቸው ምላሽ ላይ ቅሬታ ያላቸው በመሆኑ ቢሮው ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ምላሽ መስጠት ይችል ዘንድ ከቀረቡ ማስረጃዎች አንጻር አስተያየት እንድንሰጥበት በቀረበልን ጥያቄ መሠረት የህግ ክፍሉ የሚከተለውን አስተያየት አቅርቧል::
ይኸውም ከላይ በተጠቀሱትና አመልካች የአደራ ቤቱ እና የማካካሻ ቤቱ አለ በሚሏቸው ክፍለ ከተማዎች በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ የደብዳቤ ልውውጦች እንዲሁም ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ እልባት ለመስጠት በቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ/ በተቋቋመው ኮሚቴ ከቀረቡ ማስረጃዎች አንጻር በጉለሌ ክ/ከተማ ያለው ቤት የማካካሻ ሳይሆን የከተማ ቦታና ትርፍ ቤትን የመንግስት ንብረት ለማድረግ በወጣው አዋጅ ቁ.47/67 መሠረት የተወረሰ መሆኑን የሚያረጋግጡ ከመሆኑም በላይ በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ የሚገኙ ስድስት (6) ቤቶች ከአዋጁ በፊት በኪራይ የሚተዳደሩ መሆኑን እና ግለሰቡ ያስረከቡበት ቅጽ በእጃቸው የነበረውን ያቀረቡ በመሆኑ በተለይም ለዚሁ ዓላማ የተቋቋመው ኮሚቴ በ23/11/2011 ዓ.ም ባቀረበው የውሳኔ ኃሳብ ላይ ግለሰቡ ያቀረቡትን አቤቱታ መነሻ በማድረግ ከክ/ከተማው የመጣውን ሰነድ በማየት ይገባቸዋል ወይስ አይገባቸውም በሚለው ጉዳይ ላይ የውሳኔ ኃሳብ ለመስጠት ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በቀረበው ሰርኩላር መሠረት አመልካች በማካካሻ የተሰጠው ቤት በአሁኑ ወቅት በእጁ የሚገኝና እየተገለገለበት ያለ መሆኑን ማስረጃ ማቅረብ ይጠበቅበታል የሚል ቢሆንም አመልካች አላቀረቡም::
ውድ አንባቢያን እዚህ ላይ አቤቱታ አቅራቢው ከ1968 ዓ.ም እስከ 2007 ዓ.ም ይኖርበት እንደነበር እና በ2007 ዓ.ም ደግሞ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 የቤቶች አስተዳደር ተገደው መውጣታቸውን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደርም ሆነ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ እንደሚያውቅ መገንዘብ ያስፈልጋል:: ነገር ግን አቤቱታ አቅራቢው በማካካሻነት የተሰጣቸው ቤት እጃቸው ላይ ስላልተገኘ ብሎ በአደራ የሰጡትን ቤት አለመመለስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡትን መመሪያን ካለማክበርም ባለፈ ፍትሃዊነቱ እስከምን ድረስ ነው? የሚለውን ፍርድ ለአንባቢያን ትተናል::
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን መስከረም 26/2014