̋ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” የሚል የሀገራችን የቆየ አባባል አለ። በአንድም በሌላም መልኩ የተለያዩ አይነት ምርጫዎች በተለያዩ ጊዜዎች ተመልክተናል። በአብዛኛው የምርጫው ሰሞን ለህዝብ ቃል የሚገባው ቀርቶ ሌላ ያልታሰበ ሊሆን፤ የማይገባው ተግባር ሲከናወን ተመልክተናል።
የቅርብ ጊዜ ትዝታችን የሆነው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው ውጤት መሰረት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብልጽግና ፓርቲ 410 ወንበር አግኝቷል። ከዚህም በሻገር የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ፣ የጌዲኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲና የግል እጩ ተወዳዳሪዎችም በምርጫው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ አግኝተዋል። ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተለያዩ ምክንያቶች ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም ምርጫ ተካሄዷል።
የተመኘነውን ያህል ዥንጉርጉር ምክር ቤት ለማየት ገና ብንሆንም ጅማሬው ይበል የሚየሳኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ለዛሬ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም ከተመሰረተው አዲሱ መንግስት ኢትዮዽያ ምን ትጠብቃለች የሚል ሀሳብ ላነሳ ወደድኩ።። የሰኔ 14 ምርጫ አለምን ባነጋገረ መልኩ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ እስከ እኩለ ለሊት በሰጠው ድምጽ ከሚመሰረተው መንግስት ሕዝቡ ምን ይፈልጋል?
በምርጫው ወቅት አራስ አልቀረ ሀዘንተኛ፤ አቅመደካማ አልቀረ ወጣት ሁሉም በድምፄን የምሰጠው መሪ ቃሉን ያክብርልኝ ሲል ምን ማለቱ ይሆን? እንደኔ እንደኔ የእለተ ጉረሱን ናፋቂ ማህበረሰባችን ፤ የተሰጠችውን አመስግኖ የሚካፈለው ወገናችን፤ ይችኑ አታሳጣን የሚለው ህዝባችን ቢሆን የተሻለውን ካልሆነ ግን የነበረውን እንዳናሳጣው የሚፈለልግ አይመስላችሁም?
መንግስት የሥራ እድል የሚፈጥርባቸውን መስኮች በማስፋት አዳዲስ ዘርፎችን ማካተት እንደሚገባውና ወጣቱ ሥራ ለመፍጠር የሚያስችለውን የአሰራር ሥርዓቶች መዘርጋት ፤ ከሥራ እድል ፈጠራ ጋር ያሉ የአሰራር ማነቆዎችን በመፍታት ወጣቱ ቀልጣፋ አገልግሎት የሚያገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸት ብሎም ወጣቱ በኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ውስጥ ካለው ድርሻ አኳያ አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ወጣቶችንና ሴቶችን በፖለቲካው መስክ አሳታፊ ማድረግ ይጠበቅበታል ።ወጣቱን ለአንድ ሰሞን የምርጫ ማድመቂያ ሳይሆን የሚረከባት ሀገሩን በምን ልክ ማስተዳደር እንዳለበት በማሳየት ተተኪ የማፍራት ስራ ይጠበቃል።
መንግስት የሕግ የበላይነትን ማስከበር ከቻለ በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋትን ማምጣት ፤ ኢትዮጵያ ያሉባትን የውጭ ጫናዎች ተቋቁማ ሉዓላዊነቷንና አንድነቷን ማስጠበቅ የሚኖርበት ከመሆኑም በላይ ተተኪ በማፍራት በተገቢው መልኩ አገራዊ ኃላፊነት የሚወጣ የተቀመጠበት ወንበር ያልሰፋው ለተገቢው ቦታ የሚመጥን ጠንካራ መንግስት ሊሆን ይገባል።
ከዚህም በላይ የኑሮው ሁኔታ ሰማይና ምድር ሆኖ አንዱ በችጋር እየተቆራመደ ሲሰቃይ ሌላው ደግሞ ገንዘቤን የት ላድርስ የሚልበት ዘመን ቀርቶ ሁሉም ኢትዮዽያዊያን እኩል በሀገራቸው ሀብት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ መንግስት ኢትዮዽያ ትፈልጋለች።
የአለማችን ውድ ሀብት የሰው ጉልበት ያላትን ምድር ታቅፎ ልብሱን መቀየር የማይችል ትውልድ ይዘን በብሔር መፎከር ትርጉም ስለማይኖረው ከኢትዮዽያዊነት በፊት ብሄሩን የማያስቀድም ፤ሁሉም በማንነቱ ተከብሮ ሀገር የሁሉም ሆና ማንም ማንንም ሳይንቅ ማንም ማንንም ሳይጥል ሁሉንም በእኩል እያየ ሀገርን ወደ ብልፅግና የሚያሻግር መሪ ፤ለብልፅግና እሴት የታማነ መሪ ያሻናል።
አገሪቱ አሉኝ የምትላቸው ወጣቶቿን ጉልበታቸውን ለዘመናዊ ባርነት ሸጠው፣ በአገሩ ሰርቶ መልማት እንደማይችል ተስፋ የቆረጠ ትወልድ ይዛ ወደ ውጭ ተሰዶ ዞሮ የሚረግማትን ትውልድ እንዳታፈራ የሚያደርግ ኢትዮጵያ የወጣቶቿን ስነ ልቦና በሱስ ፤ በስደት፤ በጥላቻ፤ በቅዠት የሰለበውን ትውልዷን የሚታደግላት ስርአት ትፈልጋለች።
በቀላሉ የኢትዮጵያን ህዝብ ዋጋ ለማየት አረብ አገር ያሉ እስር ቤቶችን ማየት ብቻ በቂ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ወጣት አለ ወይ ብሎ ለማመን በሚከብድ ልክ ወጣቱ ለስቃይ ለሞት ለሰቆቃ መዳረጉን አቁሞ በሀገሩ የሚያገኝ ሀገሩን ለማሳደገ ጉልበቱን እውቀቱን ሳይሰስት የሚያፈስላት በሀገሩ ላይ የሚያኮርፍ እንዳይኖር የሚያደርግ ለወጣቱ ስራ እፈጥራለሁ ሲል ከአፍ በዘለለ መሬት ላይ የወረደ ነገር የሚያሳይ፤ አደርገዋለሁ ያለውን አድርጎ በጎደለው ሰርታችሁ አሳዩኝ የሚል፤ ሰርቶ የሚያሰራ የሙሴን በትር የጨበጠ ወደ ተስፋይቱ ምድር በቃሉ መሰረት የሚያደርስ መንግስት ሀገሬ ትሻለች።
ከኢኮኖሚያዊ አብዮት ይልቅ የብሔር ፖለቲካ አብዮት በላያችን ላይ አውጆ አለም ወደ ፊት ሲሄድ እኛ ወደ ተውናቸው የ16ኛውና የ14ኛው ክፍለ ዘመን ከመለሰን፤ አንድነትን ትቶ የብሔር አስተሳሰብ ውስጥ ከዘፈቀን፤ የብሔርተኝነት አመለካከት በየመንደሩ የራስን ሀይል ገንብቶ እርስ በርስ ከመተራረድ ውጭ ከችጋር ከውርደት ከስደት እንዳላስጣለን ተረድቶ ይሄን ያስተሳሰብ ነቀርሳ አውጥቶ የሚጥል መንግስት እንፈልጋለን።
ለዓመታት ማነቆ ሆኖበት ወደኋላ ከሚጎትተው አመለካከት አላቆ ይሄን ትውልድ አዲስ ምዕራፍ ላይ ማሸጋገር የቻለ የወደፊቷን የኢትዮዽያ ሀያልነት መገንባት የሚችል ቁርጠኛ የሆነ መሪ ይህ ህዝብ ያስፈልገዋል።
የስልጣን ክፍፍላችን ከእምነት እና ከብሔር፤ ከአወኩሽ አወኩህ ተላቆ ለአገር የሚቆም የስልጣን ክፍፍልን መዘርጋት ያስፈልጋል። ችግሮቻችንን በውይይቱ ለመፍታት እራሳችንን ማዘጋጀት ፤ ከጦርነት ልምምድ ወጥተን በአዲስ የሰላም ልምምድ፤ በጠረዼዛ ዙሪያ ችግሮቹን መፍታት የሚችል፤ ታሪክ በልዩነቱ የሚያስታውሰው በአዲስነቱ እያመሰገነው የሚኖር መሪ ኢትዮዽያ ያስፈልጋታል።
ኢትዮጵያውያንን የሚያጣላ የሚከፋፍል የብሔር አስተሳሰብን ይዘን የኢትዮጵያን ከፍታ ማየት አዳጋች እንደሚሆንብን ተረድቶ ሀገር ማለት ሰው ማለት ደግሞ ሀገር መሆኑን የሚያምን ሀገር ተብላ ስትጠራ በውስጧ ያሉትን 85 ቋንቋና የተለያዩ እምነት ባህል ያላቸውን ሰዎች እንጅ መሬቷን ወይም ካርታዋን ብቻ አለመሆኑን በመገንዘብ በአንድ አስተባብሮ የሚመራ መሪ ሀገራችን ያስፈልጋታል።
የህዝብን ፍቅር ሳንይዝ የመሬትና የካርታ ፍቅር መያዝ አይቻልም፤ አዲሱ መንግስትና የኢትዮጵያ ህዝብ የሚከፍሉትን መስዋእትነት ከፍለው በችጋር ለሚሰቃየው ያለሀጥያቱ የሚሞተውን ወገናችንን የሚታደግ፤ አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ እንዳይሆን ምርቱን ከግርዱ የለየ፤ ሁሉን በአንድ የማይጨፈልቅ፤ ሰው በማንነቱ ሳይሸማቀቅ በነፃነት እንደልቡ ወጥቶ መግባት የሚችልባት ሀገር፤ የቀደሙ መልካም እሴቶቻችንን አስጠብቆ የሚያቆይ ለቃሉ የተመነ መሪ ኢትዮዽያ ያሻታልና ፈጣሪም ይህን አንዲቸራት በመማፀን አበቃሁ።
ብስለት
አዲስ ዘመን መሰከረም 26 ቀን 2014 ዓ.ም