ክብርት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣
ወንድሜ ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ፣
የመንግሥታት መሪዎችና ተወካዮች፣
ክቡራትና ክቡራን ኢትዮጵያውያን፣
ላካሄዳችሁት ምርጫ በኬንያውያን እህትና ወንድሞቻችሁ ስም እንዲሁም በግሌ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡ ኢትዮጵያን ለመገንባት ለምታደርጉት ጥረት ድጋፋችንን ለመግለጽ እዚህ ተገኝቻለሁ፡፡ ኬንያ የሰላምና የብልጽግና ቀጣና ለመገንባት ከኢትዮጵያ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዛ ትሰራለች፡፡ የኛ ድጋፍ ምን ጊዜም አይለያትም፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምና መረጋጋት እንዲያመጡና ኢትዮጵያውያንን በጋራና በአንድነት እንዲያቆሙ ኃላፊነት ሰጥቶዎታል፡፡ እርስዎ ድምፅ የሰጡዎትም ያልሰጡዎትም ዜጎች ጠቅላይ ሚኒስትር ነዎት፤ ሁሉም የእርስዎ ዜጎች ናቸው፡፡ አገሪቱን አንድ ለማድረግ ለሚያደርጉት ጥረት ሁለንተናዊ ድጋፋችን አይለይዎትም፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ እናት ናት፡፡ በቅኝ ገዢዎች ያልተገዛች ብቸኛ አገርም ናት፤ አፍሪካውያን ነፃ እንዲሆኑና መፃዒ እድላቸውን በራሳቸው እንዲወስኑ ከአፍሪካውያን ጋር የቆመች ታላቅ አገር ናት፡፡
ኢትዮጵያ የሁላችንም አፍሪካውያን እናት ናት፤እናት ሰላም ካልሆነች መላው ቤተሰብ ሰላም እንደማይሆን ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ሰላም የአፍሪካ ሰላም ነው፡፡ ስለሆነም ክቡር ወንድሜ፣ ኢትዮጵያን ሰላም የማድረግ ትልቅ የቤት ስራ አለብዎት! ሰላማዊና የበለፀገች ኢትዮጵያንና አፍሪካን እውን ለማድረግ በምታደርጉት ጉዞ አብረናችሁ ነን፡፡
ፈጣሪ ይባርካችሁ!