የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት መሀሙድ ቡሃሪ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣
ለኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ለተከበራችሁ የፓርላማ አባላት፣
ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የሚዲያ አባላት፣
የኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ፤
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በተሾሙበት በዚህ በአለ ሲመት ላይ በመገኘቴ የተሰማኝን ጥልቅ ደስታ እገልጻለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ለዴሞክራሲ ስርአት እሴቶች እና መርሆች ለሰጣችሁት ዋጋና ቁርጠኝነት ያለኝን አክብሮት ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ባለፈው ሰኔ ወር ያካሄዳችሁት ሀገራዊ ምርጫ ውጤት የኢትዮጵያ ህዝብ ያካሄደው የነጻ ተአማኒና ፍትሃዊ ምርጫ ሂደት ነጸብራቅ ስለመሆኑ በጽኑ አምናለሁ፡፡
የምርጫው ውጤት የኢትዮጵያ ህዝብ በመሪያቸው አመራር ቁርጠኝነትና ቆራጥነት ላይ ያላቸውን እምነት ያመለከተም ነው፡፡ ዘመናዊ የዴሞክራሲ ስርአትን በኢትዮጵያ ለመገንባት ለሚደረገው ጥረትም ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው፡፡ በዚህ የምርጫ ሂደት ድል ስለተጎናጸፋችሁ በናይጄሪያ ህዝብ ስም የተሰማኝን ከልብ የመነጨ ደስታ በመግለጽ እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ፡፡
ኢትዮጵያ በርካታ ተግዳሮቶች እንደገጠሟት ሁላችንም እንገነዘባለን፡፡ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመፍታት ሁሉም ወገን ለኢትዮጵያ አንድነት፣ እድገትና ደህንነት በጋራ አንዲሰሩ እናበረታታለን፡፡ ሁኔታውን ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመስራት መልካም አጋጣሚ አድርጎ መውሰድም ይገባል፡፡
ናይጄሪያ እንደ ሌሎች ሀገሮች ሁሉ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አንቅስቃሴ ውስጥ የበኩሏን በማበርከት ሀገሪቱ እምቅ ሀብቶቿን አውጥታ እንድትጠቀም ከአዲሱ አመራር ጋራ እንደምትሰራ አረጋግጥላችኋለሁ፡፡ ሀገሬ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋፋት፣ ግንኙነትን በማጠናከር በውጭም በሀገር ውስጥም መተማመንን በመገንባት ከአዲሱ አመራር ጋር አብራ ትሰራለች፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ መጪው ጊዜ መልካም የስራ ዘመን እንዲሆንልዎ እመኛለሁ፡፡ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ፍሬያማ ግንኙነት እንዲኖርም እንሰራለን፤ ናይጄሪያ የኢትዮጵያ አንድነት እና ሉአላዊነት እንዲጠበቅ ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጥላችኋለሁ፤ ፈጣሪ የፌዴራል ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኢትዮጵያን፣ ናይጄሪያን አፍሪካን ይባርክ። አመሰግናለሁ፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መሰከረም 25 ቀን 2014 ዓ.ም