በክቡር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሚመራው የኢትዮጵያ አዲሱ የመንግስት ምስረታ በዓል ላይ በመሳተፌ የተሰማኝን ክብር ለመግለፅ እፈልጋለሁ፡፡ የተከበሩ ዶክተር ዐቢይ አሕመድና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለኔና ለልዑካን ቡድኔ ላደረጋችሁልኝ ደማቅ አቀባበል ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝቦች በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በመሳተፍና በትክክል ይወከለኛል ያሉትን መንግሥት በመምረጥ ዲሞክራሲን በማጠናከራችሁ እንኳን ደስ አላችሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚም የሱማሊያ ሕዝብና መንግስት ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በምርጫ አሸንፈው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆንዎ እንኳን ደስ አለዎ ለማለት ይወዳል፡፡ እርስዎ የሚመሩት መንግስት ፖሊሲውንና የፖለቲካ አጀንዳውን በሕዝቡ ውስጥ በማጎልበት ረገድ ስኬት እንዲገጥመውም ይመኛል፡፡
አለም የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ጨምሮ የአየር ንብረት ለውጥና ሽብርተኝትን የመሳሰሉና ሌሎች ህልውናን የሚፈታተኑ ቀውሶችና ውጣውረዶችን እያስተናገደች ባለችበት በዚህ ግዜ የእነዚህን ቀውሶችና ውጣውረዶች አፈታት ለመረዳት ባለ ራእይና ጠንካራ አመራር መሆንን ይጠይቃል፡፡ ከዚህ አኳያ መሪዎች ለሕዝባቸውና ለሀገራቸው መሻሻልና ብልፅግና ሊያመጡ የሚችሉ መፍትሄዎችንና ተስፋዎችን ማቅረብ አለባቸው፡፡
በተለይ ደግሞ እኛ የአፍሪካ መሪዎች ለወደፊት የጋራ ተጠቃሚነታቸው ከሕዝቦቻችን ጋር ስንሰራ የሚያቆመን ኃይል የለም የሚል እምነት አለኝ፡፡ በኢትዮጵያ የተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ውጤትም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጋር ወደፊት ለመራመድና ከእርሳቸው ጋር በቅርበት ለመስራት ፍላጎት እንዳለው በግልፅ ያሳያል፡፡
ኢትዮጵያና ሶማሊያ ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት፣ በመከባበር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ወዳጅነትና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ያላቸው አገራት ናቸው፡፡ ሁለቱ አገራት በጋራ ሆነው ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትንም እየተዋጉ ነው፤ የንግድ ግንኙነታቸውን ከማጠናከር ባለፈም በቀጠናዊና አህጉራዊ ተቋማት የጋራ ግንኙነት በማድረግ በአፍሪካ ቀንድ ለሕዝቦቻቸው የተሻለ፣ የተቀናጀና የበለፀገ የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ለመፍጠር እየሰሩም ይገኛሉ፡፡
የሶማሊያ መንግስትና ሕዝብ አላማና ምኞትም ከኢትዮጵያና ከተቀሩት የአፍሪካ ጎረቤት ሀገራት እንዲሁም ከአለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር አብሮ መስራት ነው፡፡ በድጋሚ ለኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ላደረጋችሁት የተሳካ ምርጫ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ አዲስ ለተመረጠው መንግስትም ስኬትን እመኛለሁ፡፡
የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሙሐሙድ አብዱላሂ ፎርማጆ
አስናቀ ፀጋዩ
አዲስ ዘመን መሰከረም 25 ቀን 2014 ዓ.ም