የተከበሩ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ የተከበራችሁ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች፤ እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች፤ ጤና ይስጥልኝ ፤
በመጀመሪያ በዚህ ታሪካዊ ፕሮግራም ላይ ተገኝቼ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሂደት በማየቴና በዚህ መሰሉ የአዲስ መንግስት ምሥረታ በዓለ ሲ መት ላይ በመ ታደሜ በራሴና በጅቡቲ ሕዝብ ስ ም የተሰ ማኝን ከፍተኛ ደስታ እገል ጻለሁ።
በዛሬው እለት በተመለከትኩት ነገር እጅግ ከመደሰቴም በላይ በኢትዮጵያ ላይ ትልቅ ተስፋ እንዲኖረኝ አድርጎኛል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድም ለዚህ ቀን በመብቃትዎ በሕዝቤና በራሴ ስም ታላቅ ደስታዬን በመግለጽ እንኳን ደስ አለዎት ለማለት እፈልጋለሁ።
ዛሬ በሕዝቤና በራሴ ስም በታላቅ አክብሮትና ደስታ ላስተላልፍ የምፈልገው መልዕክት ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከብዙ ጥረት በኋላ ለዚህ ቀን በመድረሳችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ፤ ይህ ጅማሬያችሁም ለጅቡቲ ሕዝብ ትልቅ ትምህርት ነው።
ክቡራንና ክቡራት፤ ኢትዮጵያ ትልቅ የሚያኮራ ታሪክ ያላት አገር ናት፤ ወደኋላ መለስ ብለን ታላቋን አቢሲኒያ ስናያትም ኢትዮጵያ የብዙ አፍሪካ አገራት እናት ከመሆኗም በላይ የብዙ አፍሪካ አገራትን ችግሮች ይዛ የመጀመሪያዋ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት /የሊግ ኦቭ ኔሽን/ አባል የሆነች ስትሆን ከዛም በኋላ ደግሞ አፍሪካ ህብረት እንዲመሰረት በማድረግም የተጫወተችው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም።
አሁን በቅርቡ እንኳን ኢትዮጵያ የሚታይና የሚጨበጥ ኢኮኖሚያዊ እድገት በማስመዝገብ በአህጉሩ ተጠቃሽ ከመሆኗም በላይ በተለይም ለምስራቅ አፍሪካ እንደ ሞዴል የምትታይ ሆናለች። ሁላችሁም እንደምታውቁት ባለብዙ ታሪክ ባለቤቷ ኢትዮጵያ በርካታ ሊገለጹ የሚችሉ ደስታና መከራዎችንም ያሳለፈች አገር ናት፤ ዛሬ ላይ ቆመን ስናያት ግን ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረች ነው።
ኢትዮጵያ ለሁሉም ሕዝቦቿ ምቹ ኑሮን ለመስጠት ብሎም ለአህጉሪቱ በሰላምና ጸጥታ እንዲሁም አብሮ በመልማት በኩል ትልቅ ተስፋ የምትሰጥና በወደፊት ራዕይም ትልቅ ሆና የምትታይ አገር ናት ።
ሁላችሁም እንደምታውቁት የአህጉራችን የሰላም ሁኔታ በቀላሉ የሚደፈርስ ነው፡፡ ነገር ግን በታሪክም እንደምናውቀው ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱ ችግሮችን ስትቆጣጠር እና ቀጠናውን ስታረጋጋ ነው የቆየችው፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ ከዚህም በኋላ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብዬ አስባለሁ።
የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት ባህሏንና እምነቷን ጠብቃ የኖረች መሆኗ ታላቅ ያስብላታል። ይህንንም መጠበቅና መንከባከብ ያስፈልጋል።
ብዙ ታሪክ እንዳላት እና የሃይማኖትና የባህል ብዝሃነት የምታስተናግድ የበለጸገች ሃገር ከመሆኗ አንጻር ይህንን ለእድገትና ለብልጽግናዋ መጠቀም እንዳለባት አበክሬ እናገራለሁ። ኢትዮጵያ ምን ጊዜም ጠንካራ ከመሆኗም በላይ ሊበታትኗት የመጡትንም አሳፍራ የምትመልስ ታሪካዊ አገር ናት፡፡ ከዚህም በላይ ለራሷም ሆነ ለመላው አፍሪካ ተስፋ የሆነች አገር ነች፡፡ እንደ ጅቡቲ መንግሥትና ሕዝብም በቀጣይ ለሚኖረው ስራ ከጎናችሁ ነን።
እንኳን ለአዲሱ አመት አደረሳችሁ!
እንኳን ለኢሬቻ በዓል አደረሳችሁ!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መሰከረም 25 ቀን 2014 ዓ.ም