ፓን አፍሪካኒዝም እንዴት ትንሳኤዋን አገኘች ወደ ሚለው ዋና ሀሳቤ ከመሄዳችን በፊት ስለፓን አፍሪካኒዝም ትርጉም እና አመሰራረት ትንሽ ልበል።
«ፓን » የሚለው ቃል ከግሪክ የተወሰደ ሲሆን «ሁሉም » ከሚለው የአማርኛ ቋንቋ ጋር የሚስተካከል አቻ ትርጉም ያለው ነው። ከዚህ የተነሳም ፓን አፍሪካኒዝም ማለት “ሁሉም አፍሪካ” እንደማለት ነው።
ፓን አፍሪካኒዝም እንደ ፖለቲካ አስተሳሰብ ትልልቅ ሁለት አላማዎችን ይዞ የተመሰረተ ነው። አንደኛው አላማ አፍሪካን አንድ ማድረግ ሲሆን ፤ ሁለተኛው ደግሞ በአለም ላይ የሚኖሩ የዘር ሃረጋቸው ከአፍሪካ የሚቀዳ ጥቁር ህዝቦችን አንድ የማድረግ ከፍ ያለ ራእይ የሰነቀ ነው ።
የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ የተጀመረው ከአፍሪካ ውጭ ባሉ በአሜሪካ እና በካሪቢያን በሚገኙ ጥቁር ህዝቦች ነው ። ለአስተሳሰቡ ለመፍጠር ዋናው ምክንያት ደግሞ በውጭ የሚኖሩ ጥቁር ህዝቦች ከመጡበት አፍሪካ ርቀው ከመኖራቸው ጋር ተያይዞ ራሳቸውን ሀገር አልባ እደሆኑ አድርገው ይቆጥሩ ስለነበር ነው። ከዚህም በተጨማሪ ፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰቡ እንዲነሳ ትልቅ መንፈሳዊ አቅም የሆነው ኢትዮጵያ በአደዋው ጦርነት ጣሊያንን የማሸነፏ እውነታ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያመላከታሉ ።
ስለ ፓን አፍሪካኒዝም ሲነሳ ከመስራችነት ተርታ ሁለት ሰዎችን በስፋት ይነሳሉ ። አንደኛው የፓን አፍሪካኒዝም አባት እየተባለ የሚጠራውን “ዱ ቦይስ” ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የአለም አቀፉ የጥቁር ህዝቦች ማህበር መስራች እና መሪ “ማርከስ ጋርቤይ” ነው። እነዚህ ሰዎች ለፓን አፍሪካኒዝም መፈጠር እና መጠናከር የማይተካ ሚና ተጫውተዋል።
ፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ የተጀመረው በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን የመጀመሪያውን ኮንፈረንስ የተካሄደው በለንደን በ1900 እ.ኤ.አ ነው ። ከፓን አፍሪካኒዝም ኮንፈረንሶች ሁሉ ልዩ የሚባለው በማንቸስተር ከተማ የተካሄደው አምስተኛው ኮንፈረንስ ነው ። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ወደፊት ለሚመሰረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት ቁልፍ ሚና የነበራቸው ኩዋሜ ንኩርሁማ፣ ጆሞ ኬኒያታ እና የመሳሰሉ ትላልቅ መሪዎች የተሳተፉበት ስለነበር ነው ። ሁለተኛነት ደረጃ የማንችስተሩን ኮንፈረንስ ልዩ የሚያደርገው ደግሞ የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ስለ አፍሪካ ነጻነት በጥብቅ የተወያዩበት እና ለአፍሪካ ሀገራት ነጻነት መሰረት የተጣለበት ስለነበር ነው ።
የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ከተጀመረ ብዙ ጊዜ ቢያስቆጥርም በምዕራባዊያን እንደ ትልቅ ስጋት በመታየቱ ምክንያት ምዕራባዊያን በፈጠሯቸው ሴራዎች እና የጥፋት ድሮች እየተመረዘ እንዲቀጭጭ ሆኗል ።
እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ አፍሪካን ካዛብላንካ እና ሞኖሮቢያ ብለው በመከፋፈል የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ለመግታት ሞከሩ። ነገር ግን የነጻነት ምዕራፍ ከፋች ፤ የአፍሪካዊያን ኩራት የሆነችው ኢትዮጵያ በመሪዋ አጼ ኃይለስላሴ አማካኝት ምዕራባዊያን አፍሪካን ለመከፋፈል ያጠሩትን አጥር በማፍረስ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን እንዲመሰረት በማድረግ አዲስ ታሪክ ጽፋለች። በዚህም የፓን አፍሪካኒዝምን አስተሳሰብ አንድ እርምጃ ማራመድ ተችሏል ።
በአጼ ኃይለ ስላሴ እንቅስቃሴ የበገኑት ምዕራባዊያን የአጼ ኃይለ ስላሴን አስተዳደር ለመጣል በዙ አርምጃዎችን እንደተጓዙ (the lion of juda in the new world ) የተሰኘው መጽፍ በስፋት ያትታል።
ይህም ሆኖ ግን የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ የተፈለገውን ያህል ሊጓዝ ይቅርና መኖሩ በእራሱ በማይታወቅበት ደረጃ ሲደርስ በተደጋጋሚ ተመልከተናል። ነገር ግን ለምዕራባዊያን የንዋይ ፍርፋሪ ባልተንበረከኩ እና ክብራቸውን በሚያስቀድሙ ብርቅየ የአፍሪካ መሪዎች እና ምሁራን የሚነሳ አጀንዳ ብቻ ሆኖ ሊጠፋ ከጫፍ ደርሶ የተመለሰባቸው ጊዜያት እንደነበሩ በተደጋጋሚ ተመልክተናል።
የፓን አፍሪካኒዝምን የፖለቲካ አስተሳሰብ ህይወት በመስጠት ለአፍሪካ እና ለአፍሪካውያን ክብር ለመስጠት ህይወታቸውን እስከመገበር የደረሱ ብርቅየ የአፍሪካ መሪዎች መኖራቸው የአደባባይ ሚስጠር ነው። በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት መካከልም አጼ ኃይለስላሴ፣ ኩዋሜ ኑኩርሁማ፣ ፓትሪስ ሉሙምባ፣ ቶማስ ሳንካራ የመሳሰሉት ይገኙበታል። ምዕራባዊን እነኝህን የአፍሪካ መሪዎች በሴራ ልክፍት በመንደፍ ከስልጣናቸው ከማባረር ባሻገር በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲገደሉ አድርገዋል። በዚህም የፓን አፍሪካኒዝምን አስተሳሰብ ለመቅበር ብዙ ሰርተዋል።
የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግሮች በራሳቸው መፍታት የሚያስችል የፖለቲካ አቅም የላቸውም፤ ከዛም በላይ ዕጣ ፈንታቸውን በራሳቸው መቅረጽ አይችሉም ፤ ለዚህ የሚሆን በቂ እውቀትና ክህሎት የላቸውም የሚለው ስር የሰደደውን የቅኝ ገዥዎች የፌዝ ትርክቶችን ከአፍሪካና ከአፍሪካውያን የማስወገድ ከፍ ያለ መነቃቃት የፈጠረ ነበር።
አስተሳሰቡ በተለይም በምእራቡ አለም ባለፉት መቶ አመታት ካጋጠሙት ተግዳሮቶች የተነሳ የታሰበውን ያህል መራመድ ባይችልም የአፍሪካ ህብረትን እና አፍሪካዊ ተቋማትን በመፍጠር ደረጃ የነበረው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ እንደነበር ይታመናል። ይህ አፍሪካዊ አስተሳሰቡ ከአንድ ምእተ አመት በኃላ ዳግም ወደ አለም አቀፍ የፖለቲካ መድረክ እየመጣ ሲሆን በአለም አቀፍ መድረክም ተመሳሳይ ተግዳሮት እያጋጠመው ይገኛል።
ለአስተሳሰቡ ዳግም ትንሳኤም በ2010 ዓ.ም ወደ ስልጣን የመጡት ዶክተር አብይ አህመድ ዋነኛ ተጠቃሽ ናቸው። ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት ግንባርን በምላስ የመላስ ያህል ከባድ ተደርጎ በአለም ህዝብ ይታይ የነበረውን የኢትዮ- ኤርትራ ችግር በሰላም እንዲፈታ በማድረግ አለምን ያስደመመ ታሪክ ሰርተዋል። በዚህም የአለም ኖቤል ተሸላሚ መሆን ችለዋል። ይህ የዶክተር አብይ እርምጃ ፓን አፍሪካኒዝምን ከተቀበረበት በመመለስ አፍሪካን አንድ ለማድረግ የተጀመረ የመጀመሪያው መጀመሪያ እንቅስቃሴ ነው ።
ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ሰላማዊ አየር እንዲነፍስ ከማድረግ ባለፈ ለፓን አፍሪካኒዝምን አስተሳሰብ በተቃኘ ቅኝት በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ የድንበር ውዝግብ ውስጥ የነበሩ ሃገራትን በማወያየት እና በማስታረቅ በትብብር እንዲሰሩ በማድረግ ለቀጠናው ሁለንተናዊ እድገት የሚበጅ ተግባር ፈጽመዋል።
በሱዳን ሀይሎች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ሀገር የሚያፈርስ ችግር በውይይት እንዲፈታ በማድረግ ለሱዳናዊያን ከፍ ያለ ውለታ ውለዋል። ሌላም አለም አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው አቅም በውይይት መፍታት እንደሚችሉ ትልቅ መልእክት ያስተላለፈ ነበር።
በሱዳን ላይ ተጥሎ የነበረውን የብዙ አመታት ማዕቀብ እንዲነሳ በማድረግ በአለም አቀፍ ግንኙነቷ እግር ከወርች የነበረችው ሱዳንን በመታደግ ሀገሪቱ የውጭ ግንኙነቷን በማስተካከል ከአለም ሃገራት ጋር በትብብር መስራት የሚያስችላትን እድል ፈጥረዋል።
“እኔ ህወሓት የከፋፈላትን ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን መላ አፍሪካን አንድ የማድረግ ህልም አለኝ “ ሲሉም የተደመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፤ሞቶ የተቀበረ የሚመስለውን የፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ ህይወት እንዲዘራ በማድረግ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚገኙት ኤርትራ ፣ሶማሊያ እና ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ እና በህዝብ ለህዝብ ግኝኙነት በማስተሳሰር አካባቢውን ሠላም ለማድረግ የሄዱበት መንገድ በሰላም ወዳድ የአለም ህዝቦች ዘንድ ትልቅ ይሁንታ ተችሮታል ። ለአካባቢው ሀገራት ህዝቦች አዲስ ተስፋ ፈንጣቂ ክስተት ሆኖም ታይቷል።
ይህ በሆነ ማግስት ግን ፓን አፍሪካኒዝም ከውልደቱ ጀምሮ እንደስጋት ሲቆጥሩት የኖሩት ምዕራባዊያን ፣አስተሳሰቡን ዳግም ለማፈን በተለያዩ መንገዶች ዘመቻ ከመክፈት አልተቆጠቡም። በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ባልተገባ መልኩ ጣልቃ ከመግባት ጀምሮ አለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀሩ ከተቀመጠላቸው መርህ ወጥተው የዘመቻው አካል እንዲሆኑም እያደረጉ ይገኛሉ።
በሀገር ውስጥ ለሚገኙ አሸባሪ ሀይሎች ጥብቅና ከመቆም ባለፈ፤ አፍሪካዊነቷ መቼም ተሰምቷት የማያውቀውን ግብጽን በሀገር ውስጥ ፖለቲካ መረጋጋት ያጣችውን ሱዳንን ሽፋን በማድረግ በዶክተር አብይ ትንሳኤ እያገኘ ያለውን ፓን አፍሪካኒዝም መልሶ ለመቅበር እየሰሩ ነው።
ዘመቻው ከታሰበው ውጪ የአፍሪካ የነጻነት ቀንዲል የሆኑ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት እንዲቆሙ የተሻለ እድል በመፍጠር ለአስተሳሰቡ ትንሳኤ ተጨማሪ አቅም መሆን ችሏል። በዚህም ለመላው አፍሪካውያን የሚተርፍ የታሪክ ምእራፍ ላይ እንድትገኝ አድርጓታል።
በኢትዮጰያዊያን የተካሄደው የመንግስት ምስረታ ፓን አፍሪካኒዝም አፍሪካዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ የመሆን እድሉን ያሰፋዋል በሚል ከምእራቡ አለም ከፍያለ ተግዳሮት አጋጥሞት እንደነበር የአደባባይ ሚስጥር ነው ።ምርጫው እንደ ምርጫ እንዳይካሄድ ከተካሄደም በኃላ የመንግስት ምስረታው እውን እንዳይሆን ህዝባችንን ብዙ ዋጋ ያስከፈሉ ሴራዎች በሀገር ውስጥ ሆነ በአለም አቀፍ መድረኮች ተግባራዊ ተደርገዋል ።
ኢትዮጵያዊያን የምዕራባዊያን ሴራ ለማክሸፍ የፈጸሟቸውን ገድሎች ሁሉንም ለመዘርዘር ስለማስቻል በ2013 ዓ.ም ብቻ የፈጸሙትን ገድል እናስታውስ። አንደኛው በምዕራባዊያን የሚጋለበው አሸባሪው ህወሓት መከላከያን ከኃላው በወጋበት ሰዓት ለህግ ማስከበሩ ዘመቻ ወቅት በኢትዮጵያዊያን መካከል የተደረገው መተባበር የሚገርም እና የአድዋን ጦርነት የሚያስታውስ ነበር ።
ሌላው በ2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ህዝብ የፈጸመው ገድል ደግሞ ከ2013 ዓ.ም ምርጫ ጋር የተያያዘ ነበር። የኢትዮጰያ ህዝብ የመሪውን ድምጽ በመስማት በፍጹም ጨዋነት ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ አድርጓል። ተፎካካሪ ፓርቲዎችም የምእራቡን አለም ሴራ በመረዳት ከሃገር የሚበልጥ ነገር የለም በሚል በምርጫው ሰዓት በተፈጠሩ ስህተቶች ላይ መነታረክን ትትው ከውስጥም ከውጭም ሃገራቸው የተቃጣባትን እኩይ ተግባር ለመመከት ከመሪያቸው ጋር ቆመዋል።
የኢትዮጰያ መንግስት፣ ህዝብ እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለሀገራቸው ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ትንሳኤ የሚሆነውን የመሪያቸውን የፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ ዳግም በአፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ ህይወት እንዲዘራ እያሳዩት ያለው መነቃቃትና የከፈሉት ዋጋ በአፍሪካውያን የነገ ታሪክ ውስጥ የጎላ ስፍራ እንደሚኖረው ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም ።
ይህንን እውነታ በተሻለ መልኩ በመረዳት ዶክተር አብይ ፓን አፍሪካኒዝምን ትንሳኤ እንዲያገኝ እያደረጉት ያለውጥ ጥረት ፍሬ አፍርቶ ለመላው አፍሪካውያን የሚጨበጥ ተስፋ ይዞ እንዲመጣ ኢትዮጵያዊያን ፣ በዚህ ታሪካዊ ወቅት በመሪነት ስፍራ የሚገኙ የአፍሪካ መሪዎች ከፍ ባለ ቁርጠንነት ከዶክተር አብይ ጋር በመቆም የአፍሪካን ትንሳኤ ማፋጠን ይጠበቅባቸዋል።
አሸብር ኃይሉ
አዲስ ዘመን መሰከረም 25 ቀን 2014 ዓ.ም