“ያሳለፍናቸው ጥቂት የለውጥ ዓመታት የሀገራችንን ዕድገትና ሰላም በማይፈልጉ የውስጥ ተላላኪዎችና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን እጅግ የተፈተንበት፣ ታላላቅ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ሚዲያዎች እንኳን ሳይቀሩ “ኢትዮጵያ ፈርሳለች!” በማለት ትናጋቸው እስከሚሰነጠቅ ድረስ የአለቆቻቸውን ከንቱ ማላዘን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስተጋባት ሌት ተቀን የተጉበት፣ ይህንንም ተከትሎ በሕዝባችን ላይ ሞትና አካል መጉደል፣ ንብረት መውደምና መፈናቀል፣ ስጋትና መጠራጠር በሰፊው የታየበት፣ በአንጻሩ ደግሞ በዚህ ክፉ ጊዜ ያልከዱን መልካም አሳቢዎቻችንና ታሪካዊ ወዳጆቻችን በዓለም የፍርድ አደባባይ ላይ ኢትዮጵያ ስለምትከተለው የብልጽግና መንገድ ጥብቅና ቆመው የተከራከሩበትና አሸናፊ የሆኑበት፣ በውጭም በሀገር ውስጥም ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው ሀገራቸውን ለማሻገር ሌት ተቀን የታተሩበት፣ በ6ተኛው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሀገራዊ ምርጫ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያሳዩት የጨዋነትና የአርቆ አሳቢነት ተግባር ደምቆና ፈክቶ የወጣበት፣ በዚህም ወዳጆቻችን የተደሰቱበት፣ ሀገር ሻጮችና ደላላዎች አንገታቸውን የደፉበትና ቅስማቸው የተሰበረበት ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡—
“በሕዝብ የተመረጠው መንግሥትም በየደረጃው ባካሄደው የመንግሥት መሥረታ ውስጥ ሁሉንም አካታች በሆነ መንገድ አስፈፃሚ አካላትን ለማዋቀር ጥረት ያደረገበትና ሀገራችን አዲስ የዴሞክራሲ ምዕራፍ ለመጀመር ቁርጠኝነቷን በተግባር ለዓለም ማኅበረሰብ ያሳየችበት፣ የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ በአደናቃፊዎችና በክፉ አሳቢዎች በእጅጉ የተፈተነ ቢሆንም አሸናፊነቱን ግን ማስቆም አለመቻሉን ማሳየት የተቻለበት፣ ይልቁንም ፈተናዎቹ ተጨማሪ ትምህርትና ጽናት ሰጥተውት ለሕብረ-ብሔራዊ የዴሞክራሲ ሥርዓታችን ጥንካሬና ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የአንድነት መሠረት ለመጣል የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ማገልገሉን መመልከት ችለናል፡፡—
“በአጠቃላይ በዚህ አስቸጋሪና የፈተና ወቅት የማይሳኩ የሚመስሉ ታላላቅ ድሎች ያስመዘገብንባቸውና እንደ ሀገርም ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት አጋጣሚ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የአሸናፊነቷም አንዱ ማሳያ ዛሬ በዚህ የጉባኤ አዳራሽ ተሰባስበን ሰለሀገራችን መጻኢ እድል መምከር መጀመራችን ነው”
አዲስ ዘመን መሰከረም 25 ቀን 2014 ዓ.ም