የተከበሩ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የተከበሩ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኔ፣ የተከበሩ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ ፣የተከበሩ ፕሬዚዳንት ሳልቫኬር ማዮርዴት ፣ የተከበሩ ፕሬዚዳንት ማኪሳ የተከበሩ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የተከበሩ ፕሬዚዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ፣ የተከበሩ ፕሬዚዳንት ማህመድ አቡድላሂ ፎርማጆ፣ የተከበሩ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መህመድ፣ የተከበሩ የኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዢሚ ሼል ዛማሎ ኩንዴ፣ የተከበሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የኢጋድ ዋና ጸሀፊ፣ የተከበሩ ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት፣ የተከበሩ ራማታን ላማምራ የአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፣የተከበሩ ሀይለማርያም ደሳለኝ የቀድሞ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የተከበሩ ሙላቱ ተሾመ የቀድሞ የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት፣ የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን ክቡራትና ክቡራን በኢትዮጵያ ረጅም የመንግሥት አስተዳደር ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ግልጽና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ በማድረግ ህዝባዊ ቅቡልነት ያገኘ መንግሥት በምንመሰርትበት ታሪካዊ ቀን ከፊታችሁ ቆሜ ንግግር ለማድረግ ያበቃኝን ፈጣሪ አስቀድሜ ላመሰግን እወዳለሁ።
በዚህ ወሳኝና ፈታኝ ወቅት በአገራችንና በህዝቦቿ ላይ የተቃጣውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በዱር በገደሉ በቁር በሀሩሩ ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረጉ ለሚገኙት ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን ፣ለመላው የጸጥታ አካላትና ለህዝባዊ ኃይላችን ያለኝን ታላቅ አክብሮትና ምስጋና ልገልጽ እወዳለሁ።
እናንተ የቁርጥ ቀን ልጆች ጀግና የምታከብረው ኢትዮጵያ ውላታችሁን መቼም ቢሆን አትረሳውም። አገራችን እንደ ቀደሙ ጀግኖቿ ለዚህ ትውልድ ፈርጦችም ትልቅ ክብርና ሞገስ ትሰጣለች። የምትከፍሉት መስዋዕትነት በታሪክ ማህደርና በልባችን ብራና ላይ በደማቅ ታትሞ ይኖራል። እልፍ ጀግኖቻችን እልፍ ጀግኖችን ካፈራው አብራክ በመፈጠሬ ሁሌም እንድኮራ ከሚያደርጉኝ ነገሮች መካከል የህዝባችን ጽናት አይበገሬነትና አትንኩኝ ባይነት ቀዳሚውን ሰፍራ ይይዛል።
ህዝባችን በየትኛውም ዘመን የእናት አገር ጥቃት የሚያንገበግበው ጠላት ሲመጣ የግል ቅሬታውን ወደጎን ብሎ አገርን የሚያስቀድም ፣ በሉአላዊነቱ የማይደራደር መሆኑ እሙን ነው። ከዚህም የተነሳ ህዝባችን መተማመኛችን ጦርና ጋሻችን ተዋጊ ደጀናችን ለሆነው አኩሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ያለኝን ክብርና አድናቆት በታላቅ ትህትና ልገልጽ እወዳለሁ።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ድጋፍ በፈለገች ጊዜ ለደረሳችሁላት አቅም፣ ባነሳት ጊዜ ምርኩዝ ለሆናችኋት በመላው ዓለም ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ በህዝብና በመንግሥት ስም የከበረ ምስጋናዬን ላቀርብ እወዳለሁ።
ውድ ኢትዮጵያውያን ክቡራትና ክቡራን ፤ ኢትዮጵያ በአቃፊነቷና በቀደመገናና ታሪኳ በመርከብ ትመሰላለች። በታላላቆቹ ቅዱሳን መጽሐፍት እንደተነገረው መርከቧ ኢትዮጵያ የፍትህ ፣የእኩልነት ፣ የነጻነትና የላቀ ስብዕና አገር ናት።
ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ መልኩን አይቀይርም፤ የተባለላትና ከቀደምት ክርስቲያኖች መካከል አንዱ የሆነውን ኢትዮጵያዊ ጃንደረባን ያፈራች አገር ነች ።ነብዩ መሃመድ አሊ ወሰላት ወሰላም የተከታዮቻቸው ማረፊያ አድርገው የመረጧት የእውነትና ርትህ አገር ብለው ያወደሷትና የመጀመሪያው ሙአዚን ቢላል መነሻ የሆነች አገር ናት፤ ኢትዮጵያ ።
እኛ ማለት የመካከለኛው ዘመን ፖርቱጋላዊ አሳሽና ፀሐፊ ፔድሮ አልቫሌዝ ኢትዮጵያውያን ፍትህና ዳኝነትን የሚያውቁ፤ ኪነህንፃና ስዕሎቻቸው በጥበብ የደመቁ ሲል የመሰከረልን ድንቅ ህዝቦች ነን። ኢትዮጵያ በኤዞጵ ተረቶችና በሜናንደር ተውኔቶች የተወደሰች፤ ግሪካዊ የታሪክ አባት ሔሮዳተስ የወርቃማ ባህልና ስነምግባር ባለቤት የሆኑ ብልህ ህዝቦች ብሎ የፃፈላት ድንቅ አገር ናት፤ ኢትዮጵያ። የዘመናችን አርኪዮሎጂስቶች ምድረ ቀደምትነቷን ያረጋገጡላት ኢትዮጵያ በፀረ ቅኝ ግዛትና በፀረ አፓርታይድ ትግል ወቅት ከራሷ አልፋ ለአፍሪካ ነፃነት ከውስን ሃብቷ ሳሰስት ቀንሳ የሰጠች በጥቁር ህዝቦች መብት ትግል ውስጥ ትልቅ ቦታ በነበራቸው ማርክስ ጋርቬና ዱቦ ይስ ልቦና ውስጥ ጎልታ የተሳለች አፍሪካዊ ማንነቴን የገለጠችልኝ ተብላ የተወደሰች የእውነትና የአፍሪካዊነት ሞገስና ፈርጥ የሆነች ናት፤ ኢትዮጵያ።አንዳንዶች ዛሬ አትችሉም ሲሉን አንድም ከታሪክ መዝገብ ገልጠን የአባቶቻችንን ገድል በማጣቀስ ሁለትም የእኛ ትውልድ ለኢትዮጵያ ብልፅግና የወጠነውን አይቀሪ ተግባር ጉዞ ወደውጤት በመቀየር መቻላችንንና ኢትዮጵያ መሆናችንን ልናረጋግጥ ይገባል። በቀደሙ ድሎቻችን ከሚሰማን የኩራት ስሜት ጋር ሲነፃፀር የነገ ተስፋ ቢበልጥ እንጂ አያንስም። ዋናው ጥያቄ ተስፋ ተስፋውን አይተን እውን ለማድረግ ምን ያህል ቁርጠኞች ነን ? የሚለውን ጥያቄ ደጋግመነን ራሳችንን መጠየቅ ነው። ኢትዮጵያ የምትበለፅገው እኛ አገራችንን ለመለወጥ በፈለግንበት መጠንና የጋራ ራእይ በሰነቅንበር ልክ ብቻ ነው።
ኢትዮጵያ ካዘመመችበት ቀና የምትልበት ጊዜው አሁን ነው። ይህን ለማሳካት የዛሬ ህያው ኢትዮጵያውያን ታላቅ አደራ ተጥሎብናል። ይህንን አደራ ጠብቀን የዘመናት በጎ ድምር ውጤቶችን አጎልብተን፣ ኢትዮጵያ የተባለችውን መርከብ ሞተሯን አድሰን ማእበል ወጀቡ ፈፅሞ ሳያናውጣት እንድትጓዝ ማድረግ ደግሞ የየትውልዱ የኢትዮጵያ ልጆች አደራ ይሆናል።
ውድ ኢትዮጵያውያን፣ ክቡራትና ክቡራን፤
አገራችን ላለፉት ግማሽ ምእተ ዓመታት ዲሞክራሲን በስርአተ መንግስቷ ለመትከል ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጋለች። ተስፋና ስጋት፤ እድልና ፈተና እየተፈራረቁባት አያሌ ውጣ ውረዶችን ተሻግራ እዚህ ደርሳለች። የማንነት፣ ከከተሜ እስከ ባላገር፣ ከመለዮ ለባሽ እስከ ምሁር። ከወጣት እስከ ጎልማሳ። ከልሂቅ እስከ ደቂቅ፤ መላው ያገራችን ህዝቦች የተሳተፉበትና መስዋእትነት የከፈሉበት የዘመናት የህዝብ ጥያቄ ነበር።
ምንም እንኳን 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ከእንከኖች ሁሉ የፀዳና የምኞታችንን ያህል እጅግ የተሳካ ነበር ባይባልም የዘመናት ጥያቄ የነበረውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የመትከልና የማፅናት ህልም እውን ለማድረግ አዲስ ምእራፍ ከፍቷል። አንድ እርምጃም ወደ ፊት አራምዶናል። ስልጣን ከዘር ሀረግ ወይም ከጠመንጃ አፈሙዝ ፤አልያም በሴራና ተንኮል ሳይሆን በእውነተኛ የህዝብ ድምፅ ከምርጫ ኮሮጆ ብቻ የሚመነጭ በማድረግ ፤ ይህ ህዝብ የእንቅፋት ክምር ሳያስቆመው፣ በጊዜያዊ ፈተና ተስፋ ሳይቆርጥ፣ በልዩ ልዩ ሰው ሰራሽ ግጭቶች ሳይረበሽ፤ እንደ ኮቪድ አይነት ወረርሽኞች ባሉ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሳይበገር፤ በአገራዊ ሉአላዊነታችን ላይ በተጋረጠው አደጋ ሳይረታ፤ ከውጭ ኃይሎች በሚደርስበት ተፅእኖ ሳይንበረከክ፤ በሂደቱ የገጠሙትን እንከኖች ሁሉ ተጋፍጦ የዜግነት ድርሻውን አኩሪ በሆነና ኢትዮጵያዊ በሆነ መልኩ ተወጥቶታል።
ውድ የሀገሬ ልጆች፤
በምርጫው የተመዘገበው ድል የአንድ ፓርቲ ብቻ አይደለም። የመንግሽት ብቻም አይደለም። ድሉ ኢትዮጵያ እንደ አገር ኢትዮጵያውያን እንደ ህዝብ በአንድነት ያሸነፍንበት መሆኑን ተገንዝበን ይህንን አጋጣሚ እንደ ሀገር በጥንቃቄ ጥቅም ላይ ካዋልነው ብዙ ቀዳዳዎችን ለመድፈን የሚያስችል ትልቅ እድል መሆኑን መገንዘብ ያሻል። ለዘመናት እየተከማቹ የመጡትን የፖለቲካና ኢኮኖሚ ችግሮች በአንድ ፓርቲ መሪነትና መፍትሄ አፍላቂነት ጨርሶ ማስወገድ እንደማይቻል ታውቆ፤ ተደራርበው የመጡብንን ችግሮች ተባብረንና ተደምረን ለማሸነፍ መነሳት ይኖርብናል።
በእኛ በኩል በሁሉም፣ ከሁሉም፣ ለሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን የመገንባት ህልም ለስኬት እንዲበቃ አሳታፊና አካታች አካሄድ ለመከተል አጥብቀን እንሰራለን። የፖለቲካ ስርአታችን የአሸናፊዎች ፍላጎት ነፀብራቅ ብቻ ሳይሆን የመግባባታችን ውጤት እንዲሆን አበክረን እንሰራለን። በታሪካችን ውስጥ በጉልህ እንደሚታየው የውስጥ ሽኩቻዎቻችን ለጠላቶቻችን መሳለቂያና መረማመጃ አድርገውን ቆይተዋል።
የኦሮሞ
አባቶች
“ወሊ
ገለን
አላ
ገለን”
ይላሉ።
የተግባባ
ከውጭ
ይገባ፤
የተነጋገረ፣
የመከረ
ለአንገብጋቢ
ችግሮቹ
መፍትሄ
ያገኛል።
ሃሳባችንን
አስታርቀን፣
መከበር
የሚገባው
ልዩነታችንን
አክብረን፣
ህብረ
ብሄራዊነታችንን
አጠንክረን
ወደ
ከፍታ
የምንተምበት
ጊዜ
ይሆናል።
ይህም
እንዲሳካ
የፖለቲካ
ልዩነታችንን
ለማጥበብ
አካታች
ብሄራዊ
የውይይት
መድረክ
እናካሂዳለን።
የምክክር
ሂደቱ ችግሮቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ ይፈታሉ ብለው የሚያምኑትን የሚያካትት በፖለቲካ ልሂቃን መካከል ብቻ የሚደረግ ሂደት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ ያገናዘበ፤ አጠቃላይ ሂደቱም አካታችና አሳታፊ፤ እንዲሁም በኢትዮጵያውያን እየተመራ አገር በቀል መፍትሄዎችን ለማፍላቅ ታልሞ የሚከናወን ይሆናል።
ውድ ኢትዮጵያውያን፣ ክቡራትና ክቡራን፤
በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በክህደትና በእብሪት የጠነሰሰው ግጭት ባሳለፍነው ዓመት እንደ አገር እጅግ ከባድ ዋጋ አስከፍሎናል። ይህ ግጭት ጥቂት ግለሰቦች እኛ የማንቆጣጠራት፣ እንዳሻን የማናሾራት አገር ልትኖር አይገባም ብለው የቀሰቀሱት ጦርነት ነው።
ጠላት በአሽከሮቹና አሳዳሪዎቹ እየታገዘ ብረት አንስቶና አውዳሚ መሳሪያዎችን ታጥቆ እንደብሌናችን የምንሳሳለትን የሰሜን እዝ ሰራዊት የግፍ ግፍ ፈጸመበት።በቅርቡ እንኳን የጥሞና እድል ብንሰጠው ክፉ ደጉን ያለዩ ህጻናት የጦር መሳሪያ አስታጥቆ የህዝብ መገልገያዎችን እየናደ ፣ ትምህርት ቤትና ጤና ኬላዎችን እያፈረሰ ፣ቤተሰብ እየበተነ፣ ንጹሐንን እየረሸነ ፣ አርሶአደሩን ከልጆቹ ለይቶ የማያያቸውን ከብቶች በጥይት እየገደለ፣የሃማኖት ተቋማትን እያረከሰ ኢትዮጵያን ሲወጋት ወደን ሳይሆን ተገደን ህልውናችንን ወደማስጠበቅ ዘመቻ መግባታችን ሊታወቅና፤ሊሰመርበት ይገባል ።ሰልፍ ይዘን ስንዘምትም ሆነ ሰይፍ ይዘን ስንነሳ ዋና ጸባችን አገር ሊያፈርሱ፣ ህዝብ ሊያናክሱ፣ ወንበራቸውን ሊያደላድሉና ኪሳቸውን ሊሞሉ ከተነሱ የሴራ ቁንጮዎችና ኢትዮጵያ ጠል ሀይሎች ጋር ብቻ መሆኑም ሊታወቅ ይገባዋል።አገራችን ከውስጥና ከውጭ የገጠማትን ፈተና ተቋቁማ ለማለፍ እና በቀጣይም ብሔራዊ ክብሯንና ጥቅሟን በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበር እንድትችል ትክክለኛ አቋምና የተሟላ አቅም ያለው የጸጥታና ደህንነት ኃይል ትገነባለች።
ክቡራትና ክቡራን፤
ሉአላዊነታችንንና የግዛት አንድነታችንን የሚገዳደረውን ክፉ መሻት በምንከላከልበት በዚህ ወቅት ከዓለምአቀፍ ሀይሎች እያስተናገድን ያለነው የዲፕሎማሲ አዝማሚያ ወደኋላ መለስ ብለን ታሪካችንን እድንገልጥ አስገድዶናል።በዘመናት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችን ውስጥ ሁለት ተቃራኒ ሀቆች አሳልፈናል።ዛሬም እንደትናንቱ የወዳጅነት ታሪክ የቀጠሉ እንዳሉ ሁሉ የክህደት ታሪክ የደገሙም አሉ።ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ የወዳጆቿን አጋርነት አጥብቃ ትሻለች።ነገር ግን ማንኛውም ወዳጅነት የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት በሚሰዋ መልኩ መሆን የለበትም፤ ሊሆንም አይችልም።በፍቅር መንፈስ ለሚቀርቡን አገራት ልባችንና በራችን ለድጋፋቸው ፣ ለምክራቸውና ለመልካም ምኞታቸው ሁሌም ክፍት ነው።
ውድ አፍሪካዊ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ፤
እኛ ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ በሚል መርህ የተባበረች ሰላማዊና የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት ብሎም በዓለም መድረክ ጥቅሟን የምታስጠብቅ አህጉር እንድትኖረን ከመቼውም ጊዜ በላይ ኃላፊነታችንን ለመወጣት እንጥራለን።
በቀጠናችን ከሚያጋጩን ይልቅ የሚያስታርቁን፣ ከሚለያዩን ይልቅ የሚያስተሳስሩን ነገሮች ብዙ ናቸው።የጋሞ አባቶች ‹‹ከሰው ጋር አንድ ዓመት ያላረሰ ለብቻው ሰባት ዓመት ያርሳል›› እንዲሉ እጣ ፋንታችን የተሳሰረ ስለሆነ በቀጠናችን ያለውን የተበታተነ አቅም ሰብሰብ አድርገን ብንተባበር ያሉብንን ችግሮች በንስር ፊት እንደቆመች ድንቢጥ ይኮሰምናሉ።
ክቡራትና ክቡራን ፤
የህዳሴ ግድብ እንደ አገር ከሚያስገኝልን ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ባሻገር ቀጠናዊ ትስስርና መልካም ጉርብትናን የሚያጠናክር ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።ትርጉሙም ግዙፍ ነው።አባይ ማለት የመነሳታችን ምሳሌ፣ በራሳችን አቅም የመቆማችን ማሳያ፣ የህብረታችን ገመድ ነው።አባይ በማይታይ ምትሀቱ ስላስተሳሰረን በማይዳሰስ ሀይሉ ስላበረታንና በራስ መተማመናችንን ስለጨመረ ከህጻናት እስከ አረጋውያን፣ ከከተማ እስከ ገጠር ከቆላ እስከ ደጋ ከደቡብ እስከ ሰሜን፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከእለት ጉርሱና ከመንፈቅ ልብሱ ቀንሶ ግድቡን ለማጠናቀቅ ቆርጧል፤ግድቡም ይጠናቀቃል።
ጎረቤቶቻችንና የአባይ ልጆች ይህንን ሀቃችንን እስከተረዳችሁልን ድረስ በአባይ ወንዝ የጋራ ተጠቃሚነታችንን በሚያረጋግጥ ቀጠናዊ ትስስርን በሚያጠናክር እና ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርግ መንገድ ለመስራት ሁሌም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ዝግጁ መሆናቸውን በድጋሚ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።
ውድ የአገሬ ልጆች ፤
አገራችን ወደ ብልጽግና ጎዳና የማሸጋገር ውጥናችንን ወደ ውጤት ለመቀየር ኢኮኖሚያችን በብዙ ዘርፎች የተዋቀረ ፣ ብዙ ተዋናይ የሚሳተፉበትና ብዙዎችን ተጠቃሚ እንዲያደርግ አበክረን እንሰራለን።ኢኮኖሚያችን በግል ዘርፍ ቀዳሚነትና ገበያን በሚደግፍ መንግሥት አጋዥነት የሚመራ፣ ተወዳዳሪና ከዓለምአቀፍ ንግድና ኢንቨስትመንት ጋር የተሳሰረ ፈጣንና ፍትሀዊ እድገትን የሚያረጋግጥ ፣ ለዜጎቻችን በቂና አስተማማኝ የሥራ እድል የሚፈጥር ምጣኔ ሀብት እንዲሆን እንሰራለን።
ባለፉት ዓመታት የዋጋ ንረትን ከመቆጣጠርና የኑሮ ውድነትን ከመቀነስ አንጻር የተወሰዱት እርምጃዎች የሚፈለገውን ያህል ውጤት እንዳላመጡና ድሃው የህብረተሰብ ክፍል የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆኑን መንግስት በውል ይገነዘባል።ይህንን የህብረተሰብ ክፍል ከጫና ለመታደግ በሚቀጥሉት ዓመታት መንግሥት የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ ከሚሰራቸው የኢኮኖሚ አስተዳደር ሥራዎች መካከል አንዱ የዋጋ ንረትን መግራት ይሆናል።
ውድ ኢትዮጵያውያን ፤ ክቡራትና ክቡራን ፤
የምናልመውና እንደ ግብ የምናስቀምጣቸው በጎ አላማዎች ትርጉም የሚኖራቸው ባለን የማስፈጸምና የማድረግ አቅም ነው።አዲሱ መንግሥት የሚያስብ የሚያቅድ የሚከውን እንጂ በጎ የሚመኝ ህልመኛ ብቻ የሚሆን ሊሆን አይገባም።እስከዛሬ ታቅደው ከጠረጴዛ ላይ ያልወረዱና ተጀምረው የተሰናከሉ ውጥኖቻችን ባለንበት የምንረግጥና አንዳንዴም ወደኋላ የምንሸራተት አድርገውናል።ዜጎቻችን ላይ የሚደርስ ምሬትና መንገላታትን ለመቅረፍ ጀምሮ የመጨረስን ባህል በመላበስ በቴክኖሎጂ የታገዘ ግልጽና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖርና ፣ጩ የህዝብ አስተዳደር እንዲኖር አበክረን እንሰራለን ።በተለይም ሌብነትን እንደ ቀላል ድክመት ሳይሆን እንደከፍተኛ የደህንነትና የህልውና አደጋ በማየት በቀጣይ ዓመታት ትልቅ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን።
ውድ ኢትዮጵያውያን ፤ ክቡራትና ክቡራን ፤
ባሳለፍነው የለውጥ ጉዞ ሰፋፊ ስኬቶች የነበሩ ቢሆንም በርካታ ፈተናዎች አጋጥመዋል።ፍትህ ከሰፈነ እርቃናቸውን የሚቀሩ ፣ ዴሞክራሲ ከተተከለ እስትንፋስ የማይኖራቸው ፣ እኩልነት ጭቆና የሚመስላቸው ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ግለሰብና ቡድኖች አሁንም በአገራችን ይገኛሉ።ወደፊትም በብልጽግና ጉዟችን ውስጥ ሊደቅኑ የሚችሉት ፈተና ጨርሶ እንደማይጠፋ ልንገነዘብ ይገባል።
ባለፉት ድሎቻችን ላይ አከማችተን ፣ ስህተቶቻችንን አርመን በአዲስ ሀሳብ በአዳዲስ እይታ ትውልዱን በሚመጥን አካሄድ፣ ዘመኑን በሚዋጅ ቅኝት ፣ ለመጪው ትውልድ የተሻለ አገር ለማስረከብ ተደምረን ቀን ከሌት ስንሰራም ሆነ ለለውጥ ስንንቀሳቀስ አላማችን በጎ ቢሆንም አልፎ አልፎ ማጥፋትና መሳታችን አይቀርም።ሁሌም እንከን የለሽ ሥራ እንሰራለን የሚል መታበይ የለንም።ነገር ግን ከእኛ በኋላ የሚመጡትና የሳትነውን እንዲያርሙ ፣ የጀመርነውን እንደሚያጎለብቱ ሙሉ እምነትና ፍሬ የሚያፈሩበት ኢትዮጵያም እንደትናንቱ ከፍ ብላ የምትታይበት ጊዜ ይሆናል።በመጪዎቹ ዓመታት አቅማችንን በሚገባ ተጠቅመን አንድነታችንን የሚፈታተነውን ጥላቻ እንደ ህዳር አህያ ሀብት ያለ ሁሉ የፈለኩትን ካልጫንኳችሁ እያለ እንዲመኝ ያደረገውን ድህነታችንን እና ለጠላት ተጋላጭ የሚያደርገንን የውስጥ እና የውጭ ሁኔታ ተገዳድረን ድል ለማድረግ እንተጋለን።ጥላቻን በመግባባት፣ ጭቆናና በዴሞክራሲ፣ ድህነትን በብልጽግና፣ ለጠላት ተጋላጭነታችንን በጠንካራ ብሄራዊ የፀጥታ ኃይል ለመተካት ሁላችንም በአንድነት በኢትዮጵያዊ መንፈስ ልንረባረብ ይገባል።
የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን፤
በመጨረሻም በመጪዎቹ ዓመታት ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከአይበገሬነት ጋር የተሳሰረ መሆኑን የምናስመሰክርበት እንደሚሆን አልጠራጠርም።ፈተናዎች እንደሚያስፈነጥሩን እንጂ አስረው እንደማያስቀሩን የምናሳይበት ጊዜ ይሆናል።መጪዎቹ ዓመታት ኢትዮጵያ ሰንኮፏን የምትነቅልበት፣ ቁስሏን የምታክምበት፣ ህብረ- ብሄራዊ አንድነቷን በአለት ላይ የምታጸናበት፣ ገናናው ስሟን በሰፊው ዓለም ላይ እንዲናኝ የምታደርግበት ዘመን ይሆናል።በመጪዎቹ ዓመታት የድህነት አከርካሪ፣ የጥላቻ አንገት፣ የመከፋፈል ወገብ፣ የመፈናቀል ወሽመጥ፣ የመገዳደል ክንድ፣ በከንቱ የመወነጃጀል ጉልበት በአገር ልጆች ብርቱ ትብብር ይሰበራል።አባቶቻችን “አከ ዱሪፍ ሃርከ ጡሪቲ ሂናፈኒ” ፤ “የቆሸሸ እጅ እና የትናንት ደካማ ማንነት መጥራቱ አይቀርም” እንደሚሉት ፈተናዎች እንደ ወርቅ አንጥረው ያበሯት አገር የአቧራው ብዛት እና የቆሻሻው ክምር ወርቅነቷን የማይለውጣት ኢትዮጵያ ትናንት ነበረች፣ ዛሬም አለች፤ ነገ አቧራዋን አራግፋና የቆሻሻዋን ክምር ንዳ ስትነሳ ያኔ ከፊቷ የሚቆም ምንም አይነት ምድራዊ ኃይል አይኖርም።
ለዚህ ደግሞ አደራ አለብን።ዝናብና ብርዱ ሳይበግራቸው፣ ቁርና ፀሐይ ሳያማርራቸው፣ በሌሊት እንቅልፍ ሳይሰንፉ፣ ኢትዮጵያን ከመረጡ ዜጎቻችን የተሰጠ አደራ፤ ለኢትዮጵያ መዳን ሲሉ ደማቸውን ካፈሰሱ ህይወታቸውን ከገበሩ ውድ የሀገር ልጆች የተጣለብን አደራ፤ ሌት ተቀን ስለ ኢትዮጵያ ሰላም፣ በእምባ የሚማልዱ እናቶች የሰጡን አደራ፤ እንዲሁም ከወዝና ላባቸው በጨለፉት ትጋት አገር ከሚያገለግሉ እናትና አባቶች የተላለፈልን አደራ፤ እኛን ተስፋ አድርገው በኮልታፋ አንደበታቸው ስለ ኢትዮጵያ ከሚዘምሩ ልጆቻችን የተሰጠን አደራ አለብን።አዎ! ከባድ አደራ አለብን።ስለዚህም በቀጣይ ዓመታት የተጣለብንን አደራ ለመጠበቅ እና በላቀ ብቃት ለማስፈጸም እንደማናንቀላፋ፤ ያለንን ሁሉ ያለ ስስት እንደምንሰጥ፤ ለአፍታም እንደማንዘናጋ በዚህ አጋጣሚ ቃላችንን እንደምናድስ በመንግሥታችን እና በፓርቲያችን ስም በድጋሚ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።አትጠራጠሩ በቀጣይ ዓመታት ተስፋችንን አጎልብተን፣ ስጋቶቻችንን ቀርፈን፣ እድሎቻችንን አሟጠን፣ ፈታኞቻችንን አሸንፈን አገራችንን በብልጽግና ጎዳና የምናስኬድበት ዘመን ይሆናል።በኢትዮጵያ ልክ፣ በህዝቧ ልክ መታመን ሌብነትን መጠየፍ፣ አገርና ህዝብን መውደድ፣ በቅንነት ማገልገል፣ ህዝብን ሳይለዩ ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ እንዳይወሰድብን በጸሎታችሁ እንድታግዙን ፈጣሪም እንዲረዳን በታላቅ ትህትና እማጸናችኋለሁ።ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ እና ተከብራ ለዘላለም ትኑር! ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ! አመሰግናለሁ!
ገለቶማ
አዲስ ዘመን መሰከረም 25 ቀን 2014 ዓ.ም