የተከበሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ
የተከበሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ
የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት፣
ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች
ክቡራትና ክቡራን
በአዲሱ ዓመት የሁለቱ ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን መጀመርን በይፋ ለማብሰር በሚከናወነው በዚህ መድረክ ላይ ተገኝቼ ንግግር ማድረግ በመቻሌ በቅድሚያ የተሠማኝን ልባዊ ደስታ መግለጽ እፈልጋለሁ።
ባለፈው ሰኔ ወር በተካሄደው 6ኛ አገራዊ ምርጫ ተወዳድራችሁ ለዚህ ከፍተኛ ኃላፊነት በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ።እንዲሁም በዛሬው ዕለት የሀገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አፈ-ጉባኤዎችና ምክትል አፈ-ጉባኤዎች ሆናችሁ በመመረጣችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ እያልኩ የተመረጣችሁበት ወቅት ለአገራችን ልዩ በመሆኑ መልካም የስኬት የሥራ ዘመን እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ።
አምስት ዓመት የሚቆየው የእነዚህ አዲስ ም/ ቤቶች መከፈት በየዓመቱ ከሚደረጉት የመክፈቻ ሥነ- ሥርዓቶች በብዙ አንጻር ልዩ ትርጉም የሚሰጠው ነው።የአንድ ምዕራፍ መጠናቀቅና የአዲስ ምዕራፍ መከፈትን ያበስራሉ።
አገራችን ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ችግሮችን ያላስተናገደች ይመስል ባለፉት ዓመታት በእጅጉ ተፈትናለች።ሉዓላዊነቷን፣ አንድነቷን፣ አብሮ መኖራችንን ለማናጋት ተሞክራል።ብዙ ዋጋ ተከፍሏል።የዚህ ሁሉ ትግልና ጽናት ድምር ለዛሬዪቷ ቀን አብቅቷታል።
ስለሆነም ለዚህ አዲስ ምዕራፍ መባቻ ላይ እንድንደርስ ደማቸውን ያፈሰሱትን የአገራችን የመከላከያ ሠራዊት፣ ሴቶች፣ ወንዶች፣ አዛውንቶች፣ ወጣቶች ውድ ኢትዮጵያውያንን ማስታወስ ተገቢ ነው።- አገራችን ኢትዮጵያ የተለያዩ ቅርጽና ይዘት ያላቸው ቢሆንም የሕዝብ ውክልና ሥርዓት የዘጠና ዓመት ልምድ ያላት ናት።ፓርላማ ሥልጣኑንና ሉዓላዊነቱን የሚያገኘው በቀጥታ ከሚወክለው ሕዝብ ነው።ከሥልጣኑም ቀዳሚ የሚሆነው የሕዝብ ውክልና ነው።የሕዝቡ ፍላጐት፣ ዓላማዎች፣ ችግሮች ወዘተ ወዘተ ድምጽ የሚያገኙት በተወካዮቹ አማካኝነት ይሆናል ማለት ነው።ለዚህም የፓርላማ አባል፣ የመረጠውና የሚወክለው ሕዝብ መካከል የጠበቀ ግንኙነት መኖር መሠረታዊ ጉዳይ ነው።መንግሥት ለሕዝቡ ተጠያቂ መሆንን ያጠናክራል።ተጠያቂነት ደግሞ ለዴሞክራሲ ግንባታ የማይታለፍ ጉዳይ ነው።ፓርላማ የሕዝብን የልብ ትርታ ለማወቅ እድል ያለው ነው።በየጊዜው እያደጉ የሚመጡ የሕዝቡ ፍላጎቶችን በጊዜ ለመለየት ይረዳል።ከዚህም በላይ ግጭት ድንገት የሚመጣ ባለመሆኑ ምልክቶችን በጊዜ ለመለየትና አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ነው።ካለፈው ትምህርት መውሰድ ቀዳሚ ጉዳይም ነው።
ምክር ቤቶቹ የሕዝቡ ስሜት የሚንፀባረቅበት፣ የሚስተጋባበት የተለያዩ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት፣ የሚፋጩበት፣ ተከራክሮ የሚያሸንፍበት ቦታ መሆን ይጠበቅባቸዋል።ጠንካራ ፓርላማ ለመልካም አስተዳደር፣ ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ ለዜጎች መብት መከበር ዋና መተማመኛ ነው።
ከተመዘገበው ሕዝብ መካከል በብዛት ወጥተው ወደ ምርጫ ጣቢያ የሄዱት ዜጎች ድምጼ ይቆጠርልኛል፣ በማለት ነውና ተመራጮች ቃል የገቡትን መፈጸማቸውን በቅርብ እንደሚከታተሉ እሙን ነው።- ፓርላማ በአንድነት የያዘን ሰንሰለት እንዳይናጋና እንዳይፈርስ ማድረግ ቀዳሚ ኃላፊነቱ ነው።- ፓርላማ ለአንድ አገር ዲኘሎማቲክ ሥራም የማይናቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ይታወቃል።
ባሳለፍነው የ2013 በጀት ዓመት የነበረው አፈፃፀም በተለያዩ ውጥረቶች ታጅቦ የተካሄደ ቢሆንም፣ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱ ምርጫዎች ሁሉ በበርካታ መለኪያዎች የተሻለ ቅቡልነት ያለው ምርጫ ማካሄድ ተችሏል።ምርጫው በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎችን ለማካሄድ ጠንካራ ተቋማት ተጠናክረው ያየንበት፣ ለወደፊቱም ቢሆን ነፃና ገለልተኛ ምርጫ እንዲካሄድ መሰረት የተጣለበት ነበር ማለት ይቻላል።ባለፉት ሦስት ዓመታት ሲወሰዱ የቆዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች ኢኮኖሚውን ከነበረበት ከቁልቁለት ጉዞ በመታደግ እና በማነቃቃት ከፍተኛ ውጤት አምጥተዋል።በተለይም በኢኮኖሚ ማሻሻያው የትግበራ ጊዜያት ካጋጠሙ ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሰራሽ ተግዳሮቶች አንፃር ሲታይ ሲወሰዱ የቆዩት እርምጃዎች ከሞላ ጎደል ውጤታማ ነበሩ ማለት ይቻላል።ሆኖም ግን የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነት ወሳኝ መፍትሄ የሚፈልጉ የኢኮኖሚው ፈተናዎች ሆነው ቀጥለዋል።ባሳለፍነው ዓመት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሊት በስኬት ያጠናቀቅንበት ዓመትም ነበር።የውሃ ሙሊቱ በታቀደለት ጊዜ እንዳይከናወን ዓለም አቀፍ ጫናዎች ገጥመውን የነበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በግንባታውም፣ በዲኘሎማሲ አውድም፣ በገንዘብ ድጋፍም ከፍተኛ ርብርብ በማካሄድ ለስኬት አብቅተውናል።ያለፈው ዓመት እንደ አገር ታላላቅ ክንውኖች ያስመዘገብንበት የመሆኑን ያህል፣ አሳዛኝ ድርጊቶችም ተፈጽመዋል።ከሁሉም በላይ ህገ መንግሥታዊ ሥነ-ሥርዓቱን በኃይል በመናድ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሹ አሸባሪዎች ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በሰሜን ኢትዮጵያ በቀበሮ ጉድጓድ ላይ እየኖረ፣ የአገሩን ዳር ድንበር ሲጠብቅ በቆየው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ ያልታሰበ፣ አሳዛኝ ክህደትና ጭፍጨፋ ፈፅመውበታል።በሌላ በኩል በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር አፍራሽ ህብረት በመመስረት በንፁሃን ዜጎች ላይ የንብረት ውድመት፣ መፈናቀል እና የህይወት መስዋዕትነት ሲፈፅሙ ተስተውለዋል።ይሁን እንጂ በአገራቸው ክብርና በህልውናቸው የማይደራደሩት ኢትዮጵያውያን የውጭ ጠላትና የውስጥ ባንዳዎች በህብረት የወጠኑት ኢትዮጵያን የማፍረስ ሴራ ቀፎው እንደ ተነካ ንብ “ሆ” ብለው በመነሳት ማክሸፍ ችለዋል።በሁሉም የአገራችን ማዕዘናት የሚኖረው ህዝባችን ክቡር መስዋዕትነት እየከፈለ ዛሬም የአገሩን ህልውና በማስጠበቅ ላይ ይገኛል።በዚህም ምክንያት ከሚኖሩን ቀዳሚ የቤት ሥራዎች መካከል ለተጎዱ ዜጎቻችን እየተደረገ ያለው ሰብአዊ እርዳታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ከቤት ንብረታቸውን ትተው የተፈናቀሉ በርካታ ወገኖቻችንን ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ማድረግ ሕብረተሰባችን በቶሎ እንዲያገግም ማድረግ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
የተከበሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ
የተከበሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ
የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት፣
ክቡራትና ክቡራን
ያለፉ ሶስት የለውጥ ዓመታት በመገምገምና ቀጣይ የረጅም ጊዜ እቅዶችን ታሳቢ በማድረግ የ2014 በጀት ዓመት የመንግሥት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች የቀጣይ ብልጽግና መደላድል የሚጣልበት ይሆናል።በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የአገራችን ማክሮ ኢኮኖሚ በማረጋጋት የተጀመረው ዕድገት ወደ ኋላ ሳይመለስ እንዲቀጥል፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ በማስፋፋት የተንሰራፋው ሥራ አጥነት እንዲቃለል፣ የዋጋ ግሽበቱን በመቀነስ የኑሮ ውድነት እንዲስተካከል፣ እንደዚሁም በተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ተግዳሮቶች ያገጠሙ ጉድለቶችን በፍጥነት በማረም ሁለንተናዊ እድገት እንዲረጋገጥ መንግሥት ትኩረት ሠጥቶ ይሰራል።በአገራችን እየጨመረ ለመጣው የዋጋ ግሽበት ብሎም የኑሮ ውድነት መንስኤ የሆኑ የአቅርቦትና የፍላጎት አለመመጣጠን፣ ዝናብን መሠረት ያደረገ የግብርና ሥርዓት፣ የተዛባ የንግድ ሥርዓት፣ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ለማስተካከል በትኩረት ይሠራል።የኑሮ ውድነቱን በዘላቂነት ለመከላከል የገንዘብ እና የፊሲካል ፖሊሲ ቁጥጥር ሥራ አፅንኦት ይሰጠዋል።የንግድ ሥርዓቱን የማስተካከል ሥራም የዚህ ዓመት የትኩረት አቅጣጫ ይሆናል።የመንግሥት ገቢን በ2014 በጀት ዓመት ስድስት መቶ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ለማድረስ ግብ የተጣለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 83 በመቶ የሚሆነው ገቢ ከታክስ ለመሰብሰብ ግብ ተጥሏል።በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት ጠቅላላ የሸቀጦች የወጪ ንግድ ገቢ 5.25 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ግብ ተጥሏል።በግብርና መስክ 592 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት እቅድ የተያዘ ሲሆን በየዓመቱ በመከናወን ላይ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ተጨባጭ ለውጥ እያስገኘ መሆኑ በርካቶች ይስማማሉ።በመጪው ዓመትም የአረንጓዴ አሻራ ባህላችንን በማጎልበት የአገራችን የደን ሀብት ቁጥር እንዲጨምር ይደረጋል።እንደ አገር በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ 20 ቢሊዮን ዛፎችን ለመትከል የያዝነው ራእይ በማሳካት በአገራችን እየተከሰተ የመጣውን የአፈር መሸርሸር፣ የበረሃማነት መስፋፋትና የብዝሃ ሕይወት መመናመን በመግታት የግብርናውን ዘርፍ ልማት በማፋጠን፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናችንን ማረጋገጥ ይገባል።
በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በኩል የነባር አምራቾችን ምርትና ምርታማነት በማሻሻል እንደዚሁም ጥራት ያላቸው አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ ዘርፉ ለሥራ ዕድል ፈጠራ አስተዋጽዖ እንዲያበረክት በትኩረት ይሰራል።በተጨማሪም ስትራቴጂካዊ የሆኑ የገቢ ምርቶችን የሚተኩ የማኑፋክቸሪንግ ውጤቶች እንዲስፋፉ ይደረጋል።የወጪ ንግድ ምርቶችን በብዛት፣ በጥራትና በዓይነት ማምረትና የሀገር ውስጥ ባለሀብቱ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ንዑስ ዘርፍ በስፋት እንዲሰማራ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት የሚያደርገውን አስተዋጽዖ ማሳደግና የንዑስ ዘርፉ ከሀገሪቱ ዘላቂ ልማት፣ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመ ይሆናል።ማዕድናትን በዓይነት፣ በመጠንና በብዛት ለገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እንዲያድግ በብርቱ ይሠራል።ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልጉ ማዕድናት በአገር ውስጥ እንዲቀርቡም ይደረጋል።
ከፍተኛ የማዕድናት ሐብት ባለባቸው አካባቢዎችና አገራዊ ፋይዳቸው በላቁ የማዕድን ኩባንያዎች አካባቢ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች እንዲቀረፉ በልዩ ትኩረት ይሠራል።በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል ልማት በጥራትና ብዛት እንዲኖር ይደረጋል፣ ለባህላዊ እና አነስተኛ የማዕድን አምራቾችም ልዩ ትኩረት ይሰጣል።የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ሀገራዊ አቅም በመገንባት አብዛኛው የሀገር ውስጥ ፍላጎት በሀገር በቀል ኩባንያዎች እንዲሸፈን ይደረጋል።ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ይሆናል።የኮንስትራክሽን ግንባታዎችን የጥራት፣ የወጪ እና የጊዜ ተወዳዳሪነት ማሻሻል ያስፈልጋል።የመንገድ መሠረተ ልማት የተቀናጀ፣ ፍትሐዊ እና ተደራሽ በማድረግ የከተሞች ልማትና የገጠር ዕድገትን የሚያፋጥን እንቅስቃሴ በከተማና በገጠር ተመጋጋቢ በሆነ መልኩ በመተግበር የከተማ ምጣኔ ያድጋል።ከተሞች በተሟላ ዕቅድና ባልተማከለ የከተማ አስተዳደር እንዲመሩ ይደረጋል፡፡
በከተሞች የመሬትና የመኖሪያ ቤት አቅርቦትና አስተዳደር ሥርዓት ውጤታማነት በማሻሻል ምቹ የመኖሪያ አካባቢ ይፈጠራል።ከዚህ በተጨማሪም በከተሞች የምግብ ዋስትና ሥርዓት የማስፋት፣ መልካም አስተዳደር የማስፈን፣ የከተሞችን የፋይናንስ አቅም የማሳደግ ሥራዎች ይሠራሉ።ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ሃብት ለማሳደግ የቅርስ እንክብካቤና ጥበቃ ሥራ በማጠናከር፣ የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል ነባር መዳረሻዎችን ማጎልበት ይገባል።በተጨማሪም አዳዲስ የቱሪዝም መስህቦች እንዲለሙ ይደረጋል።በገበታ ለአገር ኘሮጀክት የተጀመሩ የጎርጎራ፣ የወንጪና የኮይሻ የቱሪስት መዳረሻ ልማቶች በዕቅዳቸው መሰረት ክንውናቸው እንዲቀጥል ይደረጋል።ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሉንን የተፈጥሮ ሃብቶችና የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ሃብት እንዲያመነጩ ይሰራል።ሁሉም ክልሎች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች በአዲስ አበባ የታየውን የቱሪስት መዳረሻ ፓርኮችን የማልማት መልካም ተሞክሮ በየአካባቢያቸው ሊተገብሩት ይገባል።በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ኘሮጀክቶችን በያዝነው ዓመት በማጠናቀቅ ለህዝብ ጥቅም እንዲውሉ ይደረጋል።የመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽንና ኃይጅን አቅርቦትን በማስፋፋት የአገልግሎቱ ተደራሽ ያልሆነው ሕዝብ ተጠቃሚ የሚደረግ ይሆናል።ንፁህ ኢነርጂና ቴክኖሎጂ ለገጠሩ ሕብረተሰብ እንዲዳረስ፣ ጥራት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት እንዲቀርብ በትኩረት ይሠራል።በተለይም ለዘመናት የእንጉርጉሮና የብሶት ምንጭ የነበረው ታላቁ የአባይ ወንዛችን ከዘመናት ቁጭት፣ ልፋት፣ ፅናትና ተጋድሎ በኋላ በያዝነው ዓመት ብርሃን ሆኖ ኢትዮጵያውያንን ከጨለማ ለማውጣት
የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት፣
ባለፈው ዓመት በሰሜን ኢትዮጵያ ለዓመታት ዳር ድንበሩን ሲጠብቅ በኖረው የሰሜን እዝ ላይ የተፈፀመው አስነዋሪ ጥቃት እንደዚሁም በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በሰላማዊ ዜጎች፣ በህዝብና በመንግሥት ተቋማት ላይ ሲፈፀሙ የተስተዋሉ ጥቃቶችና የሽብር ተግባራት ከህግና መርህ፣ ከሞራል እሴታችንና ከባህላችን ያፈነገጡ ነበሩ።በአመፅና በጠመንጃ ትግል አልያም ንጹሃንን በማሸበር የሚገኝ ሥልጣን ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ምድር የማይፈጠር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።ሥልጣን ሰጪውም ሆነ ነሽው የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ነው።ስለሆነም የአገራችን ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርቲዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ በሚካሄድ ህጋዊ ምርጫ ብቻ በመሳተፍ ህዝባችሁንና አገራችሁን የምታገለግሉበት ሰላማዊ የፉክክር መድረኩን ብቻ እንድትመርጡ ለማሳሰብ እወዳለሁ።በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሁሉም ነገር ከህግ በታች ነው፤ ማናቸውም ጉዳዮችም ህግ በሚፈቅደው ብቻ ሊከናወኑ ግድ ይላል።በመሆኑም መላው የአገራችን ህዝብ የህግ የበላይነትን በማክበርና በማስከበር፣ መብትና ግዴታን በማገናዘብ ሊንቀሳቀስ ይገባል።በአገራችን የህግ የበላይነት በዘላቂነት እንዲሰፍን፣ ዴሞክራሲያዊነት እንዲገነባ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል።የሁላችንም መጠለያ በሆነችው ኢትዮጵያ ፣ ከህግም ሆነ ከአገር በላይ የሆነ ኃይል ፍፁም ሊኖር አይገባም።ምርጫ የዴሞክራሲ ሂደት አንድ ክፍል ቢሆንም ምርጫ ማካሄድ ብቻውን ግን ግብ አይደለም።ስለሆነም መንግሥትም ሆነ መላው ኢትዮጵያውያን ከምርጫው ማግስት በጋራ የምንፈፅማቸው በርካታ የቤት ሥራዎች ከፊታችን የሚጠብቁን መሆኑን ተገንዝበን ሁላችንም “እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ” ሆነን ለስኬት ልንረባረብ ይገባል።በአገራችን ለዓመታት የአገርን ህልውና፣ የህዝቦችን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ እንደዚሁም ለቀውስ ምክንያት ሆነው የኖሩ ስንኮፎችን በብሄራዊ መግባባት ሊፈቱ ይገባል።የምንመኘው ብሄራዊ መግባባት ይፈጠር ዘንድም ሆደ ሰፊነት፣ መተማመን፣ መመካከር ህብረትና አንድነት፣ የውይይትና የክርክር ባህሎችን ማዳበር ይኖርብናል።በሌላ በኩል ደግሞ ፍትህና ተጠያቂነትን ማስፈን፣ የተጎዱትን መካስ፣ ማህበራዊ ፍትህ ማስፈን ይገባል።ብሔራዊ መግባባት ነጠላ ሁኔት ሳይሆን ረጅም ጊዜ የሚሻ የለውጥ ሂደት በመሆኑ፣ በአገራችን ብሔራዊ መግባባት ይመጣ ዘንድ መላው ኢትዮጵያውያን ያላሰለሰ ድጋፍ ልናደርግ ይገባል።ክቡራትና ክቡራን
በትምህርት ዘርፍ በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች በገጠር፣ በከተማ፣ በጾታ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዳራ፣ በአካል ጉዳተኝነት፣ በስጦታና ተሰጥኦ በመሳሰሉት ምንም ልዩነት ሳይፈጠር ለሁሉም ዜጎች ፍትሐዊ የትምህርት ተደራሽነትን ፣ጥራትና ተገቢነትን ማረጋገጥ እንደዚሁም በሁሉም የትምህርት ደረጃ ሁሉም ህጻናትና ወጣቶች ሙሉ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ ይሰራል።ከዚህ በተጨማሪም ሥርዓተ ትምህርቱ፣ ከገበያው ፍላጎት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ይደረጋል።በሽታ መከላከል ላይ የተኮረ የማይበገር የጤና ሥርዓት በመገንባት የህብረተሰቡን ጤና ማሻሻል እና ለኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ ይደረጋል።መከላከል በሚቻሉ ምክንያቶች የሚደርሱ የእናቶችና ህጻናት ሞትን መግታት፤ ተላላፊ እና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ሳቢያ የሚደርሱ ህመምና ሞትን መከላከልና መቀነስ፣ ዜጎችን ከድንገተኛ የጤና አደጋዎች መጠበቅ፣ የወረዳ ትራንስፎርሜሽንን ማምጣት እና ተገልጋይ ተኮር እና ተዓማኒነት ያለው የጤና ሥርዓትን መዘርጋት ያስፈልጋል።የሴቶችን እና ህፃናትን ጥበቃ ሥርዓት በማጠናከር ሁለንተናዊ ደህንነታቸውን ማስጠበቅ እና መብታቸውን ማስከበር፣ ሴቶችንና ወጣቶችን በአመራርና በውሳኔ ሰጪነት ፍትሃዊ ተሳትፎ እና ውክልና እንዲኖራቸው የሚደረግ ይሆናል።የሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የማሕበረሰቡ የአመለካከት ለውጥ አስፈላጊ ነው።በመሆኑም የሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች እንዲካተት በማድረግ ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ይገባል።የተከበሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ
የተከበሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ
የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት፤
ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች
ክቡራትና ክቡራን
አገራችን ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን የአገረ መንግሥት ታሪኳ ሉዓላዊነቷን እና ብሔራዊ ጥቅሟን ለየትኛውም ኃይል አሳልፋ ሰጥታ አታውቅም።ዘላለማዊ ክብርና ምስጋና ለቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን ይሁንና ኢትዮጵያ የነፃነት ምልክት ሆና ኖራለች፤ ታሪክም በደማቅ ቀለም ፅፎ ሲዘክራት ይኖራል፡፡በደም የተፃፈን ታሪክ የብዕር ቀለም ሊለውጠው አይችልም ።ኢትዮጵያውያን አሁንም ሆነ ወደፊት በአገራችን ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም ከማንም ጋር አንደራደርም።በመሆኑም የአገራችን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መርህ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያስከብር፤ ብሔራዊ ጥቅማችንንና ክብራችንን የማያጎድል፤ የግዛት አንድነትና ዳር ድንበራችንን የሚያስጠብቅ ሆኖ ይቀጥላል።ኢትዮጵያ በምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ፣ የቀይ ባህር፣ የባብኤል መንደብ፣ የኤደን ባህረ-ሰላጤ እና የቀጠናው አካባቢ የኃያላኑ አገራት ፍጥጫ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።በእነዚህ አካባቢዎች በሚደረጉ አበይት ክንዋኔዎች ኢትዮጵያ የሩቅ ተመልካች ልትሆን አይገባም።በመሆኑም ከጎረቤት አገራት እንደዚሁም በቀጠናው ካሉ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በቀጠናው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅ ሥራ በትኩረት ይሠራል።ከጎረቤት አገራት ጋር ያለን ግንኙነት በአካባቢያችን ዘላቂ ሠላምን፣ ማህበራዊ መስተጋብርን፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስርንና የጋራ ብልጽግናን ለማምጣት የሚያስችል ስትራቴጂ በመንደፍ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡በአፍሪካ ቀንድ ህዝቦች መካከል ሁሉን አቀፍ ትብብርና ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል የሕዝብ ለሕዝብ ፎረም ይመሠረታል።በዙሪያችን ካሉ ጎረቤት አገራት ጋር በባህል፣ በቋንቋ፣ በማንነት፣ በምጣኔ ሀብትና የጋራ እድገት ፍላጎት ጠንካራ ትስስር እንዳለን እንገነዘባለን።ይህንን ታሳቢ በማድረግም ጎረቤት አገራትን ያስቀደመ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ቀርፀን በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን።ከጎረቤቶቻችን ጋር ያለን ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት፣ በህጋዊ ማእቀፍ እና በወንድማማችነት የተቃኙ እንዲሆኑ ይደረጋል።ድንበር ተሻጋሪ የተፈጥሮ ሃብቶቻችን አጠቃቀም በትብብርና በመግባባት፣ በጋራ ተጠቃሚነት መርሆች መሠረት ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚተገበር ይሆናል።ታላቁ ህዳሴ ግድባችን የታችኛውን ተፋሰስ አገራት በማይጎዳ እንደዚሁም የኢትዮጵያን የመልማት መብት በጠበቀ መልኩ በተያዘለት እቅድ ከዳር ለማድረስ በርትተን እንሰራለን።በሌላ በኩል የናይል ተፋሰስ ትብብር ጅማሮን ለማጠናከርና ለማጎልበት ሁሉንም የተፋሰሱ አገራት ያካተተ የውይይትና የምክክር መድረኮች በዘላቂነት ሊከናወኑ ይገባል።ኢትዮጵያ እየተከተለችው ባለው ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ ያላቸው ተሳትፎ አመርቂ ውጤት እያስገኘ ነው።ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በየትኛውም የዓለም ክፍል መብታቸውና ጥቅማቸው ተከብሮ እንዲኖሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት አግኝቶ እየተሰራ ይገኛል፤ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን መልካም ገፅታ በመገንባት፤ የፋይናንስና ልማት አጋር በመሆን፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም በመሳብና በመሳሰሉት ተግባራት በጉልህ በመሳተፍ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩና የሚጠብቁ ይሆናሉ።ወደድንም ጠላንም ተለዋጭ ሀገር የለንም።
ስለሆነም በዚህች ስመ ጥሩዋና ገናናዋ በኢትዮጵያ ካመንን ያለን አማራጭ ተቻችሎ አብሮ መኖር ብቻ ነው።የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንዲሉ የእናት ኢትዮጵያ ልጆች የተለያየን ነን።እኛ የአንድ ሀገር ልጆች ተቻችለንና ተደማምጠን ጥላቻን ተጠይፈን፣ ቁጭ ብለን ተከራክረን፣አማራጭ ሀሳቦች እንዲስተናገዱ ፈቅደን የማይጥመንንም ቢሆን ለመስማት ዝግጁ ሆነን ዘላቂ ሀገራዊ መግባባት መፍጠርና ማዳበር ተቀዳሚ ተግባራችን እንድናደርገው አደራ እላለሁ። ከመደምደሜ በፊት አስቀድሜ አንድ ፈላስፋ የተናገሩትን መጥቀስ እወዳለሁ።ትርጉሙ እንዲህ ይላል።የውጭ ሀገር ሰው ናቸው።ከማንኛውም ፈተና በኋላ ብርሃን አለ።እጆቻችን በሾህ ተወግተው እየደሙ ከሆነ ጽጌሬዳዋ ሩቅ አይደለችም ማለት ነው።የጥቅሱ መጨረሻ እንዲህ ይላል።እኔም ጽጌሬዳዋ እሩቅ አይደለችም እላለሁ።
በመጨረሻም አዲስ ዓመት የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት መልካም የሥራና የስኬት ዘመን እንዲሆንላችሁ ምኞቴን እየገለፅኩ፤
የ2014 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን በይፋ መከፈቱን አበስራለሁ።አመሠግናለሁ።
አዲስ ዘመን መሰከረም 25 ቀን 2014 ዓ.ም