የኢትዮጵያ የለውጥ እንቅስቃሴ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በትላንትናው እለት በህዝበ ይሁኝታ የተገኘ መንግስት በመመስረት የለውጥ መንግስቱ መሰረት እንዲይዝ ማድረግ ተችሏል።ይህ ቀን እንዳይመጣ ካለፉት ሶስት አመታት ጀምሮ ጉድጓድ ሲቆፍሩና አፈር ሲምሱ የነበሩ ሰዎችን ተስፋ የሚያስቆርጠው ይህ የመንግስት ምስረታ እዚህ ለመድረስ ብዙ ፈተናዎችን ተጋፍጧል።ለመሆኑ ይህ የለውጥ ሂደት ያለፈባቸው ፈተናዎች ምን ነበሩ? ምንስ ስከቶች ተመዘገቡ? ይህንን ሙሉ ለሙሉ ለመዳሰስ ብዙ ጥናትና ምርምር እንዲሁም ሰፊ ጊዜ ይወስዳል።ነገር ግን ለትውስታ ያህል ጥቂቶችን ለመዳሰስ ልሞክር፡፡
የለውጡ መንግስት ፈተናዎች የጀመሩት ገና ለውጡ ከመወለዱ በፊት ጀምሮ ነው።የለውጡን ጥንስስ ለማጨንገፍ የአሸባሪው ህወሓት ጁንታዎች ብዙ ጥረዋል፤ የተግባር ሙከራም አድርገዋል።ይህ ደግሞ ከለውጡ ቀደም ብሎ ሁለት ዓመታትን ወደ ኋላ ያስጉዘናል።
በወቅቱ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በወጣቶች የተነሱ ተቃውሞችን ለማዳፈንና በኢህአዴግ ውስጥ የተነሱትን የለውጥ ሃይሎች እንቅስቃሴ በአጭሩ ለማስቀረት የሄዱበት መንገድ ነበር።በዚህ መሰረት በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የዜጎች መፈናቀል እንዲከሰት ሆን ተብሎ የተሰሩ ሴራዎች እና ይህንንም ተከትሎ አመፁን በሃይል ለማፈን የፈፀሟቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ማሳያዎች ናቸው።
በዚህ ወቅት ታዲያ በሱማሌ ክልል የኦሮሞና የሱማሌ ህዝብን ለማጋጨት ብዙ ጥረት አድርገዋል፤ የህወሓትን የማፍያ ቡድኖች እንቅስቃሴ የተቃወሙ የኦሮሚያ ቄሮዎች፣ የአማራ ፋኖዎች እንዲሁም የሌሎች ክልል ወጣቶችን በግፍ ጨፍጭፈዋል።ይህንን ሁሉ ሲያደርጉ የነበረው ደግሞ ለውጥ የሚያስቡ ሃይሎች በዚህ ጉዳይ እንዲጠመዱና የለውጥን ሂደት እንዲያቆሙ ለማድረግ በማሰብ ነበር፡፡
ነገር ግን ለዓመታት የተከማቸው ችግር አብጦ አብጦ ከልኩ አልፎ ነበርና ለውጡን የሚገታ ምንም አይነት ሃይል አልነበረም።ይልቁንም ህዝቡ ለለውጡ ይበልጡን እንዲነሳሳ በማድረግና የለውጥ አንቀሳቃሾችን በመደገፍ ለለውጥ ሃይሎች የሞራል ስንቅ ሆናቸው፡፡
በዚህ መልኩ መንገራገጭ የጀመረው የማፍያው ቡድን ታዲያ ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ ሄዶ መሰረቱን በማጣቱ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ለውጡ እውን ሊሆን ችሏል።ይህ ወቅት ታዲያ መላ ኢትጵያውን በከፍተኛ ሁኔታ ለለውጥ የተነሳሳቡትና ከለውጥ ሃይሉ ጎን የቆሙበት ወቅት ስለነበር ለውጡ አይቀሬ መሆኑን ለመገንዘብ ብዙ ጥናት የሚፈልግ አልነበረም።በተለይ መጋቢት 23 ቀን 2010 ዓ.ም ምሽት የሃገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሰየም በነበረው ፉክቻ የመላ ኢትዮጵያውን የልብ ትርታ በአንድነት የቆመበት እለት እንደነበር የምናስታውስ ነው።
ከዚህ በኋላ የለውጡ ሃይሎች የበላይነት ይዘው ወደስልጣን ቢመጡም የለውጥ አደናቃፊዎቹ ሴራ ግን በዚህ አልቆመም።ይልቁንም ለውጡን ዳግም ለመቀልበስና የሚፈልጉትን አሻንጉሊት መንግስት ለማስቀመጥ ጥረታቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ሂደት ነበር።
“ጉዞው” በተሰኘው በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ተዘጋጅቶ በቀረበውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የሰጡትን ማብራሪያ በያዘው ልዩ መፅሄት ገጽ 12 ላይ እንደተገለፀው ”በህወሓት እና በግብረአበሮቹ የሚመራው አፈናና ግድያ የለውጥ ፍላጎቱን ሊገታው አልቻለም።ይህ እንደማያዋጣ ሲረዱ የመፈንቅለ መንግስት ሴራ መጠንሰስ ጀመሩ።ከፊል የኢህአዴግ አመራሮች `ይህ የመፈንቅለ መንግስት ሳይሆን የመፈንቅለ ሰው ነው መባል አለበት` በማለት ሞገቱ” ይላል፡፡
ይህ የሚያሳየው በወቅቱ የለውጡ ቀንደኛ አቀንቃኝ የሆኑትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በማስወገድ በምትካቸው አሻንጉሊት ጠቅላይ ሚኒስትር የማስቀመጥ ሴራ እንደነበር ያሳል።ይህንን ደግሞ የህወሓት መሪዎች ወደ መቀሌ እስከፈረጠጡበት ጊዜ ድረስ በተለያዩ መንገዶች ሞክረዋል፤ በኢህአዴግ ስብሰባዎች ጠቅላይ ሚኒስሩን ለመቀየር ከመሞከር እስከ ማስገደል ድረስ የዘለቀ ሙከራ አድርገዋል።በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎችም ግጭቶችን በመቀስቀስና ህዝቡ በአዲሱ የለውጥ ሃይል ላይ እንዲያምፅ ለማድረግ ሙከራ አድርገዋል።ሆኖም እነዚህ ሁሉ ሙከራዎች ከሙከራ በዘለለ አንዳችም ፋይዳ አልነበራቸውም፡፡
“ይልቁንም አዲሱ የለውጥ ሃይል ራሱን እያጠናከረና ከህዝቡ ጋርም ያለውን ቁርኝት እያጠበቀ ሄደ።የለውጡ ፊት መሪዎችም ሰላምን፣ አንድነትን፣ ይቅርታን፣ አንድነትን፣ እኩልነትንና ፍቅርን ለኢትዮጵያውን አበሰሩ። በሂደትም በተግባር አስመሰከሩ።አዲስ መንገድ አመላከቱ፤”ጉዞው፤ ገጽ 17፡፡
በነዚህ ሁሉ ሂደቶች ውስጥ ግን እነዚህ ሃይሎች ወደመስመር እንዲገቡ ያልተደረገ ጥረት አልነበረም። የህወሓት ሃይሎች እነዚህን ሁሉ ሴራዎች እየፈፀሙ መንግስት ወደሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱና ከመንግስት ጋር አንዲሰሩ እድል ሰጥቷቸዋል።ከዚህም አልፎ ሸሽተው መቀሌ በተሸሸጉበት ወቅት እንኳን ሳይቀር ወደቀልባቸው ተመልሰው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ፈቃደኛ ከሆኑ አብሮ ለመስራትና ያለፈውን ጥፋት ይቀር ለማለት ዝግጁ መሆኑን ነግሯቸዋል፤ ከዚህም አልፎ ለምኗል፤ አስለምኗል፡፡
ይሁን እንጂ “ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም” እንደሚባለው እነሱ የተነሱበት መንገድ የጥፋት በመሆኑ ከዚህ መንገዳቸው የሚገታቸው አልነበረም።ይልቁንም አንድ ጥፋት ላይ ሌላ ጥፋት እየደረቡ በመሄድ በመጨረሻ የራሳቸው የተንኮል መንገድ ጠልፎ እስኪጥላቸው ድረስ ጉዞአቸውን ተያያዙት።በዚህም ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ
እየተነጠሉ ሄዱ።በተለይ ወደመጨረሻ አካባቢ ወደቀልባቸው ተመልሰው ጥፋታቸውን ከማረም ይልቅ የጥፋታቸው ልክ እያየለ ሄዶ ማዕከላዊ መንግስትን በሃይል ለማፍረስ የመጨረሻ ሙከራቸውን ወደማድረግ ገቡ፤ የጨረቃ ምርጫ አካሄዱ፣ በመጨረሻም የማይነካውን የሃገር መከላከያ ሰራዊት ተዳፍረው የሰሜን እዝን ወረሩ።ይህ ታዲያ የሞታቸው የመጨረሻው ምዕራፍ ነበር፡፡
ከዚህ በኋላ እነዚህ ሃይሎችን የሚታገስ መንግስትም ሆነ ህዝብ የለምና ጥፋታቸውን የማስቆሙ ዘመቻ “ሀ” ብሎ ተጀመረ።በዚህ ወቅት ግን የሃገሪቱን 80 ከመቶ የጦር መሳርያ በእጃቸው አስገብተው ስለነበር በብዙ ኢትዮጵውያንም ሆነ የኢትዮጵያ ወዳጅ በሆኑ የውጭ ሃይሎች ዘንድ ስጋት መፈጠሩ አልቀረም።ይሁን እንጂ በክፉ ተግባራቸው የቆሰለው የሃገር መከላከያ ሰራዊትም ሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እነዚህን የጥፋት ሃይሎች ለመመከት፣ ብሎም ለመደምሰስ ያገደው አንዳችም ሃይል አልነበረም።ብዙዎችን ባስገረመ ፍጥነት በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ይህንን ሃይል በመደምሰስና መቀሌን በመቆጣጠር ግፍና ግፈኞች መቼም ቢሆን ማሸነፍ እንደማይችሉ አስመሰከረ፡፡
በዚህ ወቅት ታዲያ ይህ ቡድን በዚህ መልኩ ለሽንፈት ይዳረጋል ብለው ያላሰቡት የኢትዮጵያ የምንጊዜም ጠላቶች እና እነሱን እንደ አሻንጉሊት ሲጠቀሙባቸው የነበሩ የውጭ ሃይሎች ከሞት ሊታደጓቸው ጥረት ማድረግ ጀመሩ።ለዚህ የዘየዱት መላ ደግሞ ሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል፤ ሰብአዊ ድጋፍ ያስፈልጋል፤ ወዘተ በሚሉ ሰበባ ሰበቦች በመንግስት ላይ ጫና በማሳደር ነው።ለዚህም ጫካ ድረስ በመሄድ የመገናኛ መሳርያዎችን ጭምር በማቀበልና መኖራቸውን ለማሳየት ጥረት አደረጉ፡፡
ይሁን እንጂ የለውጥ ሃይሉ ወደስልጣን ሲመጣ ጀምሮ የያዘው አላማ ኢትዮጵያን ማሻገር ነበርና ከጀመረው አላማ ሊያደናቅፍ የሚችል አንዳችም ሃይል እንደሌለ በማመን ወደፊት መገስገሱን ቀጠለ።በዚህም መሰረት በአንድ እጅ ከነዚህ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚሯሯጡ የውስጥና የውጭ ሃይሎች ጋር እየታገለ፤ በሌላ እጁ ደግሞ የብልጽግና ጉዞውን ተያያዘው። የልማት ስራውን በያዘው አንድ እጁም በርካታ ስኬቶችን አስመዝግቧል።ከነዚህም ውስጥ አዲስ አበባን ብሎም መላውን ኢትዮጵያ የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የገነባቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች አንድ ማሳያ ነው።ከዚህ አንጻር ከሸገር ፓርክ እስከ እንጦጦ፤ ከገበታ ለሸገር እስከ ገበታ ለሃገር በጀመራቸው ስራዎች ያሳካቸው ስራዎች ማሳያዎች ናቸው፡፡
ከዚህም ባሻገር በታላቁ የህዳሴ ግድብ ከግብጽና ተላላኪዎቿ ጀምሮ እስከ አሜሪካና አውሮፓ ድረስ የነበሩ ተግዳሮቶችን በመቋቋም ሁለት ጊዜ ውሃ ሙሌት በማካሄድ ሃይል ለማመንጨት ከሚችልበት ደረጃ ላይ አድርሶታል።
በሃገሪቷ ታሪክ የመጀመርያ የሆነውና እነ አሜሪካና አውሮፓውያን ከኛ ውጭ ምርጫ ላሳር ሲሉበት የነበረውን የምርጫ አካሄድ በሚያስንቅ ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ ተጀምሮ በሰላማዊ መንገድ የተጠናቀቀው ስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ ሌላው የስኬት ማማ ነው።በትላንትናው እለትም የለውጡ መንግስት መሰረት የያዘበት የመንግስት ምስረታ በማካሄድ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሱ ሃይሎችን አንገት ማስደፋት ተችሏል።ትላንት ከሰዓት በኋላ በተካሄደው በዓለ ሲመት ላይም በርካታ የአፍሪካ መሪዎች ተገኝተው ይህንን የኢትዮጵያ ልዩ የስኬት ጉዞ ታድመዋል።ከመታደምም አልፈው ከኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በርካታ ፈተናዎችን ተጋፍጣ በማለፍ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሳች።ከዚህ በኋላ ቀጣዩ ጊዜ የተጀመረውን የብልጽግና ጎዳና እየተከተሉ መጓዝ ብቻ ነው።ለዚህ ደግሞ በአንድ በኩል ይህንን መንገድ በማፍረስ ከመስመሩ ሊያስወጡን የሚሞክሩ ሀይሎችን በንቃት እየተከታተሉ ከጥፋት መንገዳቸው ላይ ዞር ማድረግ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተጀመረውን የልማት ጉዞ ከወዳጆቻችን ጋር በመሆን አጠናክረን መቀጠል ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል።
ውቤ ከልደታ
አዲስ ዘመን መሰከረም 25 ቀን 2014 ዓ.ም