በኢትዮጵያ ታሪክ እንደ ህወሓት የስልጣን ዘመን ጨካኝ መንግሥት አልታየም፡፡ የህወሓት የስልጣን ዘመን ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የጨለማ ዘመን ነበር፡፡ ዓለም በታሪኳ ሂትለርንና ኒሮን የመሳሰሉ ከነሱም የላቁ እጅግ ጨካኝ መንግሥታትን አይታለች፡፡ አነዚህ ግን ከህወሓት ጋር ሲነጻጸሩ ጻድቅ ናቸው፡፡ የህወሓት የጭካኔ በትር በየትኛውም ሀገር፣ በየትኛውም ዘመን ተሰምቶ የማይታወቅ ነው፡፡
በጣም የሚገርመው ደግሞ አብዛኞቹ መንግሥታት ለሀገራቸውና ለወገናቸው ህልውና ሲሉ ጨካኝ የሆኑ ናቸው፡፡ የህወሓት ጭካኔ ግን ከዚህ የተለየ ነው፤ ለራሱ ሲል በሀገሩና በወገኖቹ ላይ ጨካኝ የሆነ ነው፡፡ ሀገሩን በመጥላት፣ በወገኖቹ ላይ ሞትን በማወጅ በንጹሐን ደም ራሱን ያቆመ ድርጅት ነው፡፡ በዚህም ተግባሩ በዓለምና በታሪክ ፊት ተወዳዳሪ የሌለው አረመኔ ቡድን ነው ማለት ይቻላል፡፡
ህወሓት በሃያ ሰባት ዓመታት የስልጣን ዘመኑ ለአሜሪካና ለአንዳንድ የኢትዮጵያ ጠላቶች ወዳጅ በመሆን የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ ከመስጠት ባለፈ ለኢትዮጵያ የጠቀማት ነገር የለም፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የደበዘዙበት፣ የሴራ ፖለቲካ ስር የሰደደበት፣ ሰውነት ክብር ያጣበት የሰቆቃ ጊዜ ነበር፡፡ ህወሓት በአንድ ቃል በደም የቆመ፣ መነሻውንና መድረሻውን ጭካኔ ያደረገ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ታጥቆ የተነሳ የወሮበሎች ቡድን ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ እንዲሆነን ደግሞ ከትላንት እስከዛሬ የተጓዘባቸውን እኩይ አሻራውን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ለምሳሌ ያክል ብናይ ራሱን እንደ አውራ ፓርቲ በማየት በተሳሳተና ባልተገባ አካሄድ ከህዝብ ይሁንታ ውጪ ስልጣንን የሙጥኝ ብሎ በመቆየት ዴሞክራሲን ድራሽ አባቱን በማጥፋት የአንድ ፓርቲ የበላይነትን ሲያቀነቅን ነበር፡፡ ይሄ አልበቃ ብሎት ለብሄር ብሄረሰብ እኩልነት የቆምኩ ነኝ በማለት በብሄር ስም ብሄር እያጠፋ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ መከፋፈልን በመፍጠር ባመነው ህዝብ ላይ ክህደት ፈጽሟል፡፡ ሀገር ገሎ ራሱን ሊያኖር በውሸት ትርክት በህዝቦች መካከል ፍቅር እንዳይኖር የራሱን የሴራ ፖለቲካ ሲያራምድ ነበር፡፡
ስለ ህወሓት ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ አሸባሪው ሕወሓት ሀያ ሰባት ዓመታትን ሀገር አጥፍቶ ራሱን ያኖረ የምንጊዜም የኢትዮጵያ ጠላት ነው፡፡ በአሸባሪው ህወሓት የደረሱ ጥፋቶች ትላንትን በመጥፎ ከሚያስታውሱን አዳፋ መልኮቻችን ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ትላንትም ዛሬም የህወሓት ዓላማ አንድ ነው፤ ኢትዮጵያን በብሄርና በጎሳ በመከፋፈል የራሱን የግል ጥቅም ማስጠበቅ፡፡ ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ እንደሚባለው ዛሬም ፊታችንን ወደ ምሥራቅ አዙረን፣ እጆቻችንን ለሥራ፣ አዕምሯችችን ለልማት ባዘጋጀንበት ሰሞን ላይ ጫካ ገብቶ የተለመደ የተንኮል ሴራውን እየሠራ ይገኛል፡፡ ግን ይሄን ያክል ኢትዮጵያ ምን ብትበድለው ነው?
በታሪክ እንደምናውቀው ኢትዮጵያን ነክቶ በሰላም የኖረ የውጭም ሆነ የውስጥ ጠላት የለም፡፡ አብዛኞቹ በለኮሱት እሳት ሲቃጠሉ ያየንበት በርካታ ጊዜያቶች ነበሩ፡፡ ዛሬም የምናየው ተመሳሳይ ነገር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን ያነሱ ሁሉ ዳግም ላይነሱ የሚደርቁበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ልክ እንደኔ ብዙዎቻችሁ የምታምኑት እውነት ይመስለኛል፤ ደግሞም ነው፡፡ በብርሃናችን ዋዜማ ላይ ከዕርምጃችን ሊገታን የመጣን ማንኛውም ምድራዊ ኃይል ለመታገስ አቅሙ
የለንም፡፡ ትዕግስቱም ሞራሉም የለንም፡፡ ይህ የሁላችንም የጋራ እውነት እንደሆነ አምናለሁ፡፡ መንግሥት ራሱን በማደስ ለሀገርና በህዝብ ቅድሚያ ሰጥቶ ለጋራ ለውጥ እየተጋ ባለበት በዚህ የመንጋት ዘመን ላይ ወደ ትላንት ሊመልሰን የሚሞክርን ማናቸውንም ነገር የሚታገስበት ሙጣጭ አቅም የለውም፡፡
አሁን ሁላችንም ከህወሓትና ከመሰል ጠላት ቡድኖች ኢትዮጵያን የምናድንበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ መግደል ባህሪው የሆነ፣ የህዝቦች ስቃይና እንግልት ፌሽታው የሆነ፣ ከውጭ ሀገራት ጋር ህብረት ፈጥሮ ሀገራችንን እየጎዳ ያለ የሁላችንጠላት ህወሓት ዳግም እንዳይነሳ አድርገን ማውደም አለብን፡፡ የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ይሄ ትክክለኛው አካሄድ ይመስለኛል፡፡
በአሸባሪው ህወሓት የሃያ ሰባት ዓመታት የግፍ አገዛዝ የባከነ ኢትዮጵያዊነታችንን የምንመልስበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ይህ የትላንት ግፍ መልካችን በምንም ዓይነት መልኩ እንዲደገም አንሻም፡፡ ለጋራ ጥቅም በጋራ በመቆም ህወሓትና መሰል የሀገር ጠላት የሆኑ ባንዳዎችን ታግለን ለመመለስ ጊዜው አሁን ነው፡፡ እኛም ሆንን ሀገራችን ትላንትን ስናስብ የሚቆጨን ብዙ ነገር አለ፡፡ ይሄ ነው የምንለው መልካም ነገር በትላንትናችን ውስጥ አልተጻፈም፡፡ ራሳቸውን እንደ ልክና ፍጹማን በሚያዩ አምባገነን ጨቋኞች አሳራችንን ስንበላ ከኖርነው ትላንት ሌላ በመልካም የሚጠራ አንድም የትንሳኤ ቀን አልነበረንም፡፡ በርካታ ግፍና በደሎች የኢትዮጵያ የትላንትና መልኮች ሆነው ኖረዋል፡፡ የቀደመ ቁስላችን ሳይድን ከሞቱበት አንሠራርተው ሌላ ቁስል ሊጨምሩብን ለሚነሱ ከሀዲያን ምህረት የለንም፡፡
ኢትዮጵያን ለማዳን፣ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ አሁን ጥሩ ጊዜ ነው፡፡ ኢትዮጵያን የምንወድ ሁሉ ለኢትዮጵያ ምርጡን ለማድረግ አሁን ጊዜው ነው፡፡ የእኛ ነገር ይገርማል..በርሀብና በጦርነት ዓለም ያውቀናል፡፡ በድህነትና በኋላ ቀርነት ከዓለም አንደኛ ነን፡፡ ድርቅና እሮሮ ያልነካን ጊዜ የለም፡፡ ይሄን ሁሉ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነ መከራችንን ታቅፈን በእውቀታችን ሀገር ለመለወጥ ከመሥራት ይልቅ ሀገር ለማውደም የምናደርገው ስውር ትግል ይገርመኛል፡፡
ህወሓት ከእንግዲህ ነፍስ የለውም፡፡ አይደለም ህወሓት ቀርቶ ከእንግዲህ አሜሪካና ሌሎች ሀያላን ሀገራት እንኳን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ኃይልም መብትም የላቸውም፡፡ ህወሓት መሬት ልሶ የሚነሳ ከሆነም ለውጥና ንጋት የናፈቃቸው እጆች በአንድነት ተያይዘው እንደሚጠብቁት ስነግራችሁ ከልቤ ነው፡፡
ከትላንት እስከዛሬ ስር በሰደደ የእኔነት ስሜት ሀገር ሲያወድም ቆይቷል፡፡ ያወደማትንም ሀገር በይቅርታ ተጋግዘን እንድንገነባ ሲጠየቅ አሻፈረኝ ብሎ አፈገፈገ፡፡ ጥንት እንደለመደው በድሀ ልጅ ሞትና በወጣቱ ጉስቁልና በኃይልና በጉልበት ስልጣን ለመያዝ ሲሞክር በተባበሩ ክንዶች አፈር ከድሜ በላ፡፡ ይሄው አሁን ከውድቀቱ በኋላ ሀገራችን የተስፋ ብርሃኗን አየች፡፡ ይሄው ነጋልን..፡፡ በዚህ ብርሃን ውስጥ ሳለን ነው እንግዲህ ህወሓት ኢትዮጵያን ካላጠፋሁ፣ ብርሃኑን ካላጨለምኩ እያለ የሚፎክረው፡፡
በብዙዎቻችን ልብ ውስጥ እንዳይመለሱ የምንፈልጋቸው በርካታ ትላንትናዎች አሉ፡፡ የሞትንባቸው፣ የተጎሳቆልንባቸው፣ ብዙ ነገር የሆንባቸው አምናዎች በእያንዳንዳችን ትላንትናዊ ገጽ ውስጥ ጥቁር ለብሰው አሉ፡፡ በእያንዳንዳችን ህይወት ውስጥ በህወሓት የተጻፈ ወያባ መልኮች አሉ፡፡ እኚህ ትላንትናዎች፣ እኚህ ወያባ መልኮች፣ እኚህ ክፉ ቀኖቻችን ብሩህ ባልንው ዛሬ ላይ ዳግም እንዳይመጡ ለራሳችንም ሆነ ለሀገራችን ዘብ መሆን ምርጫ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ እንደ ትላንት ያለ የጨለማ ዘመን ዳግም እንዳይመጣ ከእያንዳንዳችን የሚዋጣ የሃሳብ መዋጮ አለ፡፡
ከምንም በላይ ደግሞ የሰላምን ዋጋ የተረዳንበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ከምንም በላይ ሰላም ወጥቶ ሰላም መግባት ያለውን ትርፍ ያወቅንበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ከምንም በላይ ሰውነት ዋጋ እንዳለው የተማርንበት ሰሞን ላይ ነን፡፡ በዚህ የሃሳብ ለውጥ ውስጥ አሻግረን ያየናት አዲስ ኢትዮጵያ አለች፡፡ በዚህ የሃሳብ መታደስ ውስጥ አሻግረን ያየንው ልማትና ብልጽግና አለ፡፡ ይሄ ሁሉ እውነት የሚሆነው በውስጥም በውጭም የተነሱብንን የጋራ ጠላቶቻችንን በጋራ ታግለን መጣል ስንችል ነው፡፡ የታደሰ ማንነታችንን ወደ ትላንት ለመውሰድ የውሸት ትርክት ፈጥረው ሊያባሉን ቀን ከሌት የሚሠሩ የህወሓት ቅጥረኞች አሉ፡፡ ንጋታችንን ሊያጨልሙ የበግ ለምድ ለብሰው በአውቅልሀለው የመጡ፤ እየመጡም ያሉ በርካታ ጡት ነካሾች አሉ፡፡
እኛ ግን የጀመርንው የለውጥ ጉዞ ሩቅ እንዲሄድ ኃላፊነት አለብን፡፡ ብርሃናችን ሩቅ እንዲያበራ ጨለማ ለበስ ከሆነ ከሀዲያን ራሳችንንም ሆነ ሀገራችንን በንቃት መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ እኛ እያለን በሚል የከሰረ አመለካከት በጀመርናቸው የስኬት ድሎች ዓይናቸው ደም የለበሰ ብዙ ጠላቶች ከዚም ከዚያም አሉ፡፡ ለውጥ ያመጣ ነፃነትና እኩልነታችንን በማጠልሸት ዳግም ወደ እንጦሮጦስ ከተውን በስቃያችን ሊስቁ ጥርሳቸውን የሚፍቁ እንዳሉም ልብ ልንል ይገባል፡፡ በህዝባችን ተሳትፎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ባመጣንው ሀገራዊ ለውጥ ተስፋ ቆርጠው የመጨረሻ ዕድላቸውን በመጠቀም ሊያውኩን የሚሞክሩ አሉና ልንበረታባቸው ይገባል፡፡
በሁሉም መስክ ከሩጫችን ሊያደናቅፉን ወጥመድ የሚዘረጉብን ከእኛው አብራክ የወጡ ከሀዲያን እንዳሉ በማሰብ በንቃት መቆምን ልምድ በማድረግ ጠላቶቻችንን ማሳፈር እንችላለን፡፡ ደግሞም ኢትዮጵያዊነት ማሸነፍ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትን በአንድ ቃል ግለጸው ብትሉኝ እኔና እናተን ወክዬ ማሸነፍ እላችኋለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከጥንት እስከዛሬ በብዙ መከራ ውስጥ ያለፈ፤ ግን ደግሞ አሸናፊ ማንነት ነው፡፡
ሊቀ ነብያት ሙሴ እስራኤላዊያንን ከግብፅ ባርነት መርቶ ያወጣው በኢትዮጵያዊው ካህን በዮቶር ጥበብ ተመርቶ ነበር፡፡ በተለያየ ጊዜ ሊጥሉን መረብ በዘረጉብን ጠላቶቻችን ላይ ተረማምደን አሸንፈን እናውቃለን፡፡ በተለያየ ጊዜ የኢትዮጵያን ኋላ መቅረት ከሚመኙ ከሀዲያን ጋር ተዋግተን ረትተን እናውቃለን፡፡ በተለያየ ጊዜ ሳንነካቸው ነክተውን ተዋርደው የተመለሱ ብዙዎች ናቸው፡፡ የህወሓትም ታሪክ ከዚህ የዘለለ አይደለም፡፡ የማይወዳትን ሀገር ከመምራቱም ባለፈ ታሪካዊ ስህተት ፈጽሞ ነው ከስልጣን የተባረረው፡፡ እኔ ሳውቅ እንኳን አደገኛ የሚባሉ ውሸቶችን ካለፈው ገዢ መንግሥት ነበር የተማርኩት፡፡ እስከአሁን ድረስ ብዙ ውሸቶችን ሰምቻለው፡፡ ፈጽሞ ውሸት የሆኑ በእውኑ ዓለም ስለመኖራቸው የሚያጠራጥሩ በርካታ ማጨበርበሮችን በፊልምም አይቻለሁ፡፡ በታሪክም ሰምቻለሁ፤ ህወሓት እንደሚፈጥራቸው ያሉ ውሸቶችን ግን በየትም አልሰማሁም፡፡
በነገራችን ላይ በህወሓት የስልጣን ዘመን ላይ ያለው የዘጠናዎቹና የሰማኒያዎቹ ትውልድ የህወሓት ዱላ ያረፈበት ነው፡፡ ይሄ ትውልድ በትክክል እንዲያስብና ተምሮና ሰልጥኖ ሀገርና ህዝቡን እንዲያገለግል የስነ ልቦና ግንባታ ያስፈልገዋል፡፡ ያለፉት የኢህአዴግ የስልጣን ዘመናት ለትውልዱ የፈየደለት አንዳች ነገር የለም፡፡ ወጣቱ ውስጡ በተዘራ የጥላቻ ዘር ዛሬ ላይ እንደ እናትና አባቱ ማሰብም ሆነ መኖር አቅቶታል፡፡
ያለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው እጅጉን የበዛ የጨለማ ዘመናት ነበሩ፡፡ ያለፈው ጊዜ ሀገርም ትውልድም እንዳፈረሰ ነው የምቆጥረው፡፡ የታመመ ትውልድ፣ ሊፈርስ ያለ ሀገር ትቶልን ነው ያለፈው፡፡ የዛሬ አዳፋ መልኮቻችን በትላንት ቀለም የተሳሉ የአዳፋ እጆች ውጤት ነበሩ፡፡ ትላንታችን ምን ያክል አዳፋ እንደነበረ ዛሬአችንን ማየቱ በቂ
ነው፡፡ በክፋት እጆች ተወላግደንና ተጨማደን ተስለናል፤ ዛሬ ላይ ብሩካን እጆች ያስፈልጉናል፡፡ ከትላንት እስከዛሬ ኢትዮጵያዊያን በጠላቶቻችን ፊት ሀቅን ይዘው ነው የምንከራከረው፡፡ ጀግንነታችን እንዳለ ሆኖ የማንወድቀው በዚህ ሀቅ ውስጥ ስለቆምን ነው፡፡
ሊጥሉን ተንኮል በሚሸርቡብን ከሀዲያን ፊት እንደ አንበሳ በክብር ቆመን እናውቃለን፡፡ አሁንም ቢሆን መንገድ እየዘጉብን ከጉዟችን ሊያዘገዩን በሚፈልጉ የኢትዮጵያ ጠላቶች ፊት በክብር መቆማችን ይቀጥላል፡፡ በዚህ ሁሉ የጠላት ሴራ ውስጥ በርትተን በመራመድ ጀግንነታችንን እስከመጨረሻው ማሳየት ይኖርብናል፡፡ አንድነታችን ከዛሬ አልፎ ነገም የሚዘልቀው እንደ ህወሓት ያሉ አሸባሪ ቡድኖችን ታግለን ስንጥል ብቻ ነው፡፡
በማይወዱት ሀገርና ህዝብ መካከል ተፈጥረው ሀገር ለማውደም ከሚሠሩ ከነሱ ታሪካችሁን ስትጠብቁ፣ ሀገርና ህዝባችሁን ስትታደጉ ያኔ የእውነት ጀግና ትባላላችሁ፡፡ የነአብዲሳ አጋና የነበላይ ዘለቀ ጀግንነት ከትውልድ ትውልድ የሚዘከረው እኮ በሀገራቸውና በርስታቸው ከመጣው የጠላት ኃይል ጋር በመታገላቸው ነው፡፡ እነዘርዐይ ደረስ፣ እነባልቻ አባ ነፍሶ ዛሬም ድረስ የሚታወሱት እኮ ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ክበር በመቆማቸው ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ከማናቸውም ጋር ለመጋፈጥ ራሳችንን ለትግል እናዘጋጅ እያልኩ
ላብቃ፡፡ ቸር ሰንብቱ፡፡
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መስከረም 24/2014