የኢትዮጵያ መንግሥት በዕርዳታ ሽፋን ህግ ሲጥሱ እና ከተፈቀደላቸው ተግባር ውጪ ሲሠሩ የተገኙ ሰባት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች በ72 ሰዓት ውስጥ ሃገር ለቀው እንዲወጡ ውሳኔ አስተላልፏል። ውሳኔውን ተከትሎ የሚሰማው ያልተገባ ጩኸት ግን የዓለም ፖለቲካ የቱን ያህል መስመር እየሳተ እንደመጣ በተጨባጭ አመላካች እየሆነ ነው።
መላው ህዝባችን የኢትዮጵያን ብልጽግና ከዚህም ባለፈ እንደ ሀገር እንዳትቀጥል የማይፈልጉ ኃይሎች በተቀናጀ እና በተናበበ መልኩ ቀን ከሌት እየሠሩ ስለመሆኑ በሚገባ ተገንዝቧል። ይህንን ሴራ ለመቀልበስም ከመቼም ጊዜ በተሻለ መልኩ በአንድነት ለሀገሩ ዘብ ቆሟል።
እነዚህ ኃይሎች በግልጽም ሆነ በስውር ተልእኳቸውን ለማስፈጸም በእጃቸው ያለውን አማራጭ ሁሉ አሟጠው በመጠቀም ላይ ይገኛሉ። እንደ አማራጭ ከያዟቸው ውስጥ ደግሞ አንደኛው በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ግለሰቦችን የተልእኳቸው ማስፈጸሚያ ማድረግ ነው።
ይህንን እውነታ ቀድሞ የተረዳው የኢትዮጵያ መንግሥት ችግሩን ደጋግሞ ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ በግልጽ አሳውቋል። ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን መሰረት አድርገው ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ አንዳንድ ግለሰቦች የአሸባሪው ህወሓት የጥፋት ተልእኮ አስፈጻሚ እየሆኑ እንደሚገኙ፤ ከዚህ ተግባራቸው እንዲታቀቡ የሚመለከተው አካል የዲሲፕሊን ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ሐምሌ 8 ቀን 2013 ዓ.ም በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ፤ “አንዳአንድ ድርጅቶች አገር ውስጥ ሆነው ዕርዳታ እንዲያስተባብሩ ከመደቧቸው ግለሰቦች ውጪ በርቀት ሆነው ከዕርዳታ ይልቅ ፕሮፖጋንዳ የሚያስተባብሩ፣ ኢትዮጵያን የማዋከብና የማጠልሸት ሥራ የሚሠሩ አሉ፤ ይህንን አስጠንቅቀናል፤ የማይታረሙ ከሆነ የራሳችንን ዕርምጃ እንወስዳለን፤ ያለንን ግንኙነት መለስ ብለን ለማየት እና አንዳንዶችንም ከአገር ለማስወጣት እንገደዳለን“ ሲሉ አሳስበው ነበር።
መንግሥት በጉዳዩ ዙሪያ በችኮላ ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ፣ ባልተገባ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ከስህተታቸው በመታረም ከድርጊታቸው እንደታቀቡ በቂ ጊዜ ሰጥቷል። ከዚህ በላይ መታገስ ግን እንደ መንግሥት ከተጣለበት ሀጋራዊ ኃላፊነት ጋር የሚጋጭ እንደሚሆን ይታመናል። ለህገወጦችም ለህገወጥ ሥራቸው እውቅና መስጠት እንደሚሆን ማንም ጤነኛ አዕምሮ ያለው ይረዳዋል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ የዓለም ፖሊስ እንደሆነች አድርጋ ራሷን ለምትቆጥረው አሜሪካ ሊሰወር የሚችል የከበደ ጉዳይ አይሆንም።
እነዚህ በዓለም አቀፍ ተቋማት ስም ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ግለሰቦች በአንድ በኩል የዕርዳታ አቅርቦቶች በአግባቡ ለተረጅው ህዝብ እንዳይቀርብ በማድረግ ከዚያም ባለፈ ከተሰጣቸው ተልእኮ ውጪ ለአሸባሪው ቡድን ያልተገቡ ድጋፎችን በመስጠት ቡድኑ ነፍስ እንዲዘራ ከማድረግ ባለፈ የሀገርን ገጽታ የሚያጠለሹ ተግባራትን ሲፈጹሙ የሐሰት መረጃዎችን በማቀነባበር የአሻባራ ቡድን የፌስ ቡክ ዘመቻ አካል ሆነው ታይተዋል።
በአንድ ሉአላዊ ሀገር የውስጥ ጉዳይ መግባት በዓለም አቀፍ ህግ የተከለከለ ነው። በዓለም አቀፍ ተልእኮ ስም ተመሳሳይ ያልተገባ ተግባር ማከናወን ደግሞ ወንጀሉን ከፍ እንደሚያደርገው ይታመናል። ይህ እውነታ ገዥ ዓለም አቀፍ መርህ በሆነበት ሁኔታ መንግሥት የወሰደውን ዕርምጃ በማውገዝ ድርጊቱ አስደንግጦኛል — ወዘተ እያሉ መጫህ የወንጀሉ ተባባሪ መሆንን በአደባባይ እንደ መግለጽ ይቆጠራል።
የሀገሪቱን ሉዓላዊነት፣ ደህንነት እና ሰላም በሚያደፈርሱ ግለሰቦች ላይ በተቀመጠ የህግ አግባብ ዕርምጃ መውሰድ በኢትዮጵያ ሲሆን አይሠራም ? ወይስ የኢትዮጵያ መንግሥት የመንግሥትነት ባህሪውና ኃላፊነቱ የተለየ ነው ?
መንግሥት ህዝቡና ዓለም አቀፍ ህግ የሰጠውን ሀገርን ከአደጋ የመታደግ ፣ የህዝብን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ለመወጣት የበግ ለመድን የለበሱ ተኩላዎች ሃገር የማፍረስ ድብቅ ተልእኮ ማክሸፍ ሥራው አይደለምን? ወይስ በዚህ ጉዳይ ላይ የመወሰኑ ስልጣን የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ይሆን ?
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “ኢትዮጵያ የድርጅቱን ከፍተኛ ሰብዓዊ አስተባባሪዎች ጨምሮ ሰባት የድርጅቱን ሠራተኞች ለማባረር መወሰኗን በመስማቴ ደንግጫለሁ” ማለታቸው ምን ማለት ነው ? በዓለም አቀፍ ህግና መርህ ያሰማሯቸው ሠራተኞቻቸው የአሸባሪ ድርጅት ደጋፊ ሆነው መገኘታቸውንስ እንዴት አገኙት? መደንገጥ ካለባቸው ሊያስደነግጣቸው የሚገባው የትኛው ነው? ወይስ ያልተገባው ተግባራቸው የድርጅቱና የከፍተኛ አመራሩ ይሁንታ የታከለበት ነው?
በርግጥ ዋና ፀሐፊው ከመደንገጣቸው በፊት ቆም ብለው የሚያስደነግጣቸው እውነት የቱ እንደሆነ በአግባቡ ማየት ነበረባቸው። የኢትዮጵያ መንግሥት የድርጅቱ ሠራተኞች ባልተገባ ተግባር ላይ ተሰማርተው መገኘታቸውን ፤ ይህም ሊታረም እንደሚገባ ደጋግሞ ሲያሳስብ ለምን ጉዳዩ አላስደነገጣቸውም? ለምን ችግሩን ለማጣራት አልሞከሩም ? ከዚህ አንጻር የአንቶኒዮ ጉተሬዝ ድንጋጤ ከምን የመነጨ እንደሆነ ግር የሚያሰኝ ነው። አንድ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ተቋም ከሚመራ ሰው የሚጠበቅ አይደለም።
የመንግሥትን ውሳኔ ተከትሎ የሚሰማው ጩኸት በሰብዐዊ ዕርዳታ ሽፋን ሀገር ለማፍረስ የሚደረግ ሙከራ ለምን ይቀለበሳል ? የሚል የጅል ጩኸት ይመስላል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ራሱ በተጨባጭ ከ 400 በላይ የዕርዳታ መኪኖች በአሸባሪው ህወሓት ለጦርነት ተግባር እየዋሉ እንደሆነ በተጨባጭ እያወቀ ዝምታ መምረጡ፤ቡድኑ ሕፃናትን ለጦርነት መልምሎ ሲያሰልፍ እንዳላየ እንዳልሰማ መሆኑ ፤ ቡድኑ በንጹሐን ላይ በተደጋጋሚ የጅምላ ጭፍጨፋ ሲያካሂድ ሀይ አለማለቱ ከምን የመነጨ ይሆን ? የትኛው ነው የሚያስጮኸው ? የትኛው ነው የሚያስደነግጠው?
‘’የኢትዮጵያ መንግሥት መከላከያ ጦር የትግሬዎችን ጦር በፍጹም አይችሏቸውም’’ የሚለውን የጉተሬዝ ንግግር ከዛሬው ድንጋጤ ጋር አስተሳስረን ስናየው ብዙ የተሰወሩ የሚመስሉ እውነታዎችን ሊገልጽልን ይችላል።
የአሜሪካ መንግሥትና ባለስልጣናቱም በተመሳሳይ መልኩ የመንግሥት ዕርምጃ እንዳስደነገጣቸው እየተናገሩ ነው። የአሜሪካ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት በሀገር ውስጥ ሲሰልሉ አገኛኋቸው ያላቸውን የሀገራት ዲፕሎማቶችና ዜጎች ከሀገር የማባረሩ ዜና የተለመደ ነው። ይህ እውነት ለአሜሪካ ሲሆን ሕጋዊና ትክክለኛ፣ ለኢትዮጵያ ሲሆን ስህተት ያደረገው ዓለም አቀፍ ህግም ሆነ መርህ ምንድን ነው?
በእርግጥ ከአይኤስ ፣ አልሽባብ እና መሰል በዓለም አቀፍ ደረጃ በሽብርተኛነት ከተፈረጁ ድርጅቶች ጋር እንደ መንግሥት ለመደራደር ፈቃደኛ ካልሆነው ፤ነገር ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ሽብርተኛ ብሎ ከሰየመው አሸባሪው ህወሓት ጋር መንግሥት እንዲደራደር ቀን ከለሊት ከሚወተውተው የባይደን አስተዳደር ከዚህ የተለየ መጠበቅ ተገቢ አይደለም።
በአሜሪካ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል የህውሓትን የሽብር ድርጊቶች ዘርዝረን በሽብርተኝነት ማሰየም አይገባንም። ከዚህ ውጪ ግን በአሜሪካ በኩል ብሄራዊ ጥቅሜን አስጠብቃለሁ በሚል ከአሸባሪ ቡድን ጋር ወግኖ መገኘት በታሪክ ተወቃሽ የሚያደርግ ፤ከዚህም በላይ ለዓለም ከፍ ያሉ ማህበራዊ ፖለቲካዊና መንፈሳዊ አሴቶችን ያበረከቱ የአሜሪካን ቀደምት አባቶች የሚያሳንስ ተግባር ነው።
የአሸባሪ ቡድንን የሽብር ተግባር በመደገፍ የሚገኝ ብሄራዊ ጥቅምም አዲሲቷ አሜሪካ የቱን ያህል ከሰብዓዊ እሴቶች እያፈነገጠች እንደሆነች በተጨባጭ የሚያመላክት ሲሆን፤ በህዝቦች መከራና ስቃይ የሚጠበቅም ብሄራዊ ጥቅም የእርግማን ምንጭ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን መስከረም 24/2014