ከሶስት ሺህ ዓመት በላይ የአገርነትና የመንግስትነት ታሪክና ልምምድ ያላት አገራችን በዘመናት መካከል የስልጣኔ ማማ ላይ ወጥታለች፤ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ኃያልነትን ተጎናጽፋለች፤ ሰፊ ግዛትን ያካለለ አስተዳደርን መስርታለች። ከዓለም ጥቂት ገናና እና ኃያል አገራት መካከልም አንዷ ነበረች። የሃይማኖት የቋንቋ፣ የቀለም፣ የባህል ብዝሀነትን አቅፋ አቆይታለች። ነጻነትና እኩልነትን ለዓለም አስተምራለች።
በአንጻሩ ደግሞ በዘመናት መካከል፤ የእርስ በርስ ጦርነቶችን አስተናግዳለች፣ የተስፋፊዎች ተደጋጋሚ ወረራ ሰለባ ሆናለች፣ የዓለም ስልጣኔና ኢኮኖሚ ጭራም ተብላለች፣ በዜጎቿ መካከል ጭቆና፣ ባርነትና ብዝበዛንም ተሸክማ ኖራለች። ከነ ገናና ታሪኳና አሳዛኝ ድህነቷ ዛሬ ላይ ደርሳለች። በዘመኗ ሁሉ ከውጭ ጠላቶቿና ከከሀዲ ልጆቿ በደልና ጥቃት ደርሶባታል። በጀግኖች ልጆቿ አልበገር ባይነትና ድል አድራጊነትን ደግሞ ሉዓላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን አስጠብቃ እነሆ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ ሩብ ክፍለ ዘመን ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያ አሁንም ውስብስብ ችግሮች አሉባት፤ በኢኮኖሚ ድሃና በስልጣኔም ኋላቀር ሆናለች። አሁንም የውጭ ጠላቶቿና የውስጥ ባንዳዎች አልተኙላትም።
ኢትዮጵያን ከአውሮፓውያን ተደጋጋሚ ወረራ ፈጸሙባት እንጂ አልተቀመጡባትም፤ አላሸነፏትም። ግብጽ ለሺህ ዓመታት በግልጽና በስውር ስትወጋት ኖረች እንጂ አሸንፋት አታውቅም። ጣሊያን ተመኘቻት እንጂ ቅኝ አልገዛቻትም። ፋሽስቱ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የከተማችንን ነዋሪዎች ጨፈጨፈ እንጂ እንደ ተመኘው አዲስ አበባን ማዕከሉ ማድረግ አልቻለም። ደርቡሾችና ዚያድ ባሬ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሉዓላዊ ድንበር ጥሰው ገቡ እንጂ አወጣጣቸው አላማረላቸውም።
በየዘመናቱ የመንግስትነት ሚና የነበራቸው ገዢዎቿም ባንድ በኩል ሉዓላዊ መሠረቷን አጽንተዋል፤ በወቅቱ የግንዛቤ ደረጃቸው አገርን ለማዘመንና የሕዝብን ሕይወት ለመቀየር ጥረዋል። በመቅደላና ጎንደር ላይ ሀገራዊ አይበገሬነትና የአሸናፊነትን ስነ-ልቦናን ለትውልድ ገንብተዋል። ከራስ ሕይወት በላይ የአገር ክብርና ሉዓላዊነትን የማስቀደም ዘመን ተሻጋሪ ጀግንነት አውርሰውናል። በአድዋ ላይ የአገር ክብርና ፍቅርን፣ ነጻነትና ሉዓላዊነትን፣ ለነጻነት ተዋግቶ ማሸነፍን ለዓለም ሕዝብ አስተምረዋል።
የሴቶችን ጥበብ፣ እኩልነትና የመሪነት ብቃትም ለቅኝ ገዢዎች ጭምር አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብና ብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋ፣ ኃይማኖትና ሌላም ሌላም ልዩነት ሳያግዳቸው በአገራቸው ጉዳይ ላይ በአንድነት ጠንካራ ክንዳቸውን ማሳረፍ እንደሚችሉ እንደሚያሸንፉም አስተምረውናል። ወኔና የአገር ፍቅራቸውንም አውርሰውናል። እነ አሉላ አባ ነጋ፣ እነ አብዲሳ አጋ፣ እነ በላይ ዘለቀና ሌሎችም እልፍ አዕላፍ ጀግኖቻችን ኢትዮጵያ በልጀቿ አጥንትና ደም ለዘለዓለም የምትኖር የዓለምአቀፋዊ ጀግኖች መብቀያ ምድር መሆኗን አስመስክረዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በውስጥ ችግሮች ተከፋፍለውና ተናንቀው አገራቸውን አዳክመውና አሳንሰው የመንደር ገዢ መሆንን የፈለጉ ልጆቿ ለተደጋጋሚ ጥቃትና የውጭ ጣልቃ ገብነት ዳርገዋታል፤ አንድነቷን አናግተዋል። ለተራማጅ አስተሳሰቦች በራቸውን ዘግተው፤ ተራማጅ ልጆቿን እየቀጩ የለውጥ እድሎቿን አምክነዋል። ስልጣንን የቤተዘመድ ውርስ አድርገው ብዙሃኑ ዜጎቿ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ እንዳይሳተፉ በማግለል ባዳነት እንዲሰማቸው አድርገዋል። መንግሥታቱ ሲቀያየሩ መልካሙን እያስቀጠሉና ጥፋቱን እያቀኑ ከመጓዝ ይልቅ የቀደመውን መንግስት ሥራዎች ሁሉ እየናዱና እየናቁ ለድህነትና ኋላቀርነት ዳርገዋታል።
በታሪኳ ሁሉ በተፈጸመባት ወረራና ጦርነት ኢትዮጵያ የሚታደጓትን ጀግኖች አጥታ እንደማታውቅ ሁሉ መላው ሕዝቧ ስርዓተ መንግስቷ እንዲዘምን አስተዳደሯ በእኩልነት፣ በፍትሃዊነት፣ በአሳታፊነትና በጋራ ይሁንታቸው ላይ የተመሰረተ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ከመታገል ታቅበዉ አያውቁም ነበር።
በቅርብ ታሪኳ እንኳን አጸ ኃይለስላሴ ወደ መንበረ ሥልጣን ሲመጡ መንግስታቸው ከመነሻው ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲመሰረት ተራማጅ ልጆቿ ያደረጉት ጥረት ከሽፏል። በዘመናዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት አስፈላጊነት ተስፋ ያልቆረጡ ልጆቿ ዴሞክራሲያዊ ህገ-መንግስት ለማርቀቅ ያደረጉት ትግል ዴሞክራሲ ላልሰለጠነ ሕዝብ አያስፈልግም በሚል ሰበብ የወቅቱ ጥረታቸው መክኗል። የሕዝቦቿ ያልተቋረጠ የዴሞክራሲያዊ መንግስት ምስረታ ፍላጎት የነዋይ ወንደማማቾችና የአጋሮቻቸውን መስዋዕትነት ጨምሮ በ1950ዎቹና 60ዎቹ ያልተቋረጠ ትግልና መስዋዕትነትን አስከፍሎ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ለመመስረት የሚያስችላትን እድል ፈጥሮላት የነበረ ቢሆንም በሚያሳዝን የታሪክ አጋጣሚ ይህም እድል መክኖ የለየለት ወታደራዊ አምባገነን እጅ ጥሏታል፤ ለባሰበት ሰቆቃና ድቀትም ዳርጓታል።
ይሁን እንጂ ሀገራቸውን ለማዘመንና ዴሞክራሲያዊ ሕዝባዊ መንግስት እንዲኖራት ተስፋ ቆርጠው የማያውቁ ልጆቿ መራራ ትግላቸውን በመቀጠል ውድ ህይወታቸውን ሳይሰስቱ ከፍለው ለሌላ የመንግስት ምስረታ ታሪክ ምዕራፍ ቢያደርሷትም አዲስ መንግስት የመመስረት እድል ያገኘው ቡድንም በተመሳሳይ የታሪክ አዙሪት ውስጥ እንድትቆይ ከማድረጉ አልፎ በታሪኳ ታይቶ ለማይታወቅ የመበታተን አደጋ እንድታጋረጥ አድርጓል። ሆኖም ግን የዚህ አፍራሽ ቡድን የሌብነት፣ የከፋፋይነት፣ የአስመሳይነት፣ የበደለኝነት ወዘተ ድርጊቶች ያንገሸገሸው ዴሞክራሲያዊ መንግስት ናፋቂው ሕዝቧ ባደረገው ትግል ለሌላ የዴሞክራሲ መንግስት ምስረታ እድል በመፍጠርና በቁርጠኝነት በመምራት ለአዲስ የታሪክ ምዕራፍ በቅቷል።
ምንም እንኳን ይህ እድል እንደ ቀደሙቱ ሁሉ እንዲመክን ያልተቋረጠ ፈተናዎች ቢጋረጡበትም ፈተናዎቹን ሁሉ ተቋቁሞ በማለፍ ታሪካዊ እውነተኛ ምርጫ በማካሄድ ኢትዮጵያን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝቦቿ ይሁንታና ነፃ ፍቃድ ላይ የተመሰረተ አሳታፊ፣ ፍትሃዊና ህብረብሔራዊ ወንድማማችነትን መልህቁ ያደረገ መንግስት እንዲኖራት ለሚያስችል አዲስ ምዕራፍ አብቅቷታል።
ከታሪክ በመማር ቀደምት መንግስታት የገነቧቸውን የጀግንነት፣ አልበገሬነት፣ ከራስ ጥቅም ሀገር ማስቀደምንና የሉዓላዊ ክብር እሴቶቿን ጠብቆና አጠናክሮ ከማስቀጠል ባሻገር አገርን ለማዘመንና የሕዝብን ሕይወት ለመቀየር በየዘመናቱ የነበረውን ውጥን አበልጽጎ ዳር ማድረስ የአዲሱ መንግስት የቤት ሥራ ነው።
አገራችን የሰው ሀቅና ድንበር የማትሻ ይልቁንም የተገፉትን የምታስተናግድ የኃይማኖት ብዝሃነት ምድር መሆኗን ነብዩ መሐመድ መስክረውላታል። ለአዲሱ መንግስት ሰላምና ትብብርን ማጎልበትና ውስጣዊ ብዝሀነትን፤ ፍቅርና አብሮነትን፣ እንግዳ መቀበልን አጠናክሮ በመስራት የነብዩ መሀመድ ምስክርነት በዚህ ትውልድም ያልጠፋ ይልቁንም የጎለበተ እሴታችን መሆኑን የማረጋገጥ ግዴታ አለበት።
ኢትዮጵያውያን የዕውቀት ብርሃን ባገኙና የሠለጠነውን ዓለም በጎበኙ ቁጥር የአገራቸው ድሕነትና ኋላቀርነት ያንገበግባቸዋል። በ1950ዎቹ ዘመናዊ ትምህርትን በአገርውስጥና በውጭው ዓለም የቀሰሙ ጥቂት ምሁራን በአገራችን ያለው ጭቆና፣ ብዝበዛና ኋላቀርነት በእጅጉ ያንገበግባቸው ነበር። ገናና ታሪክ ያላት አገራችን በሁሉም ዘርፍ የዓለም ጭራ መሆኗ ያስቆጣቸው ነበር። የነበረው የአጼ መንግስት ለውጥ ያመጣ ዘንድ ወይም ራሱ ይለወጥ ዘንድ ታግለዋል። ለዚሁ ክቡር ዓላማ ክቡር ሕይወታቸውን የሰጡት እነ ግርማሜ ንዋይ የሰዎች መንግስት ለአገርና ለሕዝብ እስካልሰራ ድረስ በሕዝብ አመጽና ተቃውሞ ሊንበረከክ እንደሚችል ለመላው አፍሪካ ታላቅ መነቃቃትን ፈጥረዋል። አዲሱ መንግስት እነዚህ የለውጥ ሐዋርያት የሞቱለትን ፍትህ እኩልነት፣ ዘመናዊነት፣ ብልጽግናናና እኩል ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ድርብ አደራና ኃላፊነትአለበት።
የሚመሰረተው መንግስት እኩልነትና ነጻነትን በማበልጸግ ጭቆናና ጭሰኝነትን አንሸከምም ብለው የታገሉ የባሌ፣ የጎጃምና የትግራይ ገበሬዎችን ህልም ዕውን በማድረግ ክብሩን መግለጽ አለበት።
በአገራችን ሕዝብ ላይ ለዘመናት ተጭኖ የኖረው የመሬት ከበርቴና የጭሰኝነት የኢኮኖሚ ግንኙነት እንዲበጣጠስና ፍትሐዊነትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ መሬት ላራሹ ብለው የተነሱ የኢትዮጵያ ተማሪዎች፣ የሃይማኖቶችና የብሔሮች እኩልነትና ወንድማማችነት እንዲረጋገጥ የተነሱት የኢትዮጵያ ወጣቶች ራዕይና አደራ ተቀብሎ በከተማችን ብልጽግናን፣ እኩልነትንና እኩል ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ኃላፊነት አለበት።
ሉዓላዊነቷና የግዛት አንድነቷ የተከበረ አገርን የማስቀጠል ካለፉት ጀግኖቻችን የተረከብነው ከባድ አደራ መሆኑን ተገንዝበን በትጋትና በቆራጥነት በመስራት አገራችንንና ከተማችንን ከዘርፈ ብዙ ችግሮቿ ለማላቀቅ መረባረብ አለብን። በነበርንበት ለመንከባለል አሁን ጊዜውም፣ የጀግኖቻችን አደራም አይፈቅድም። ስለሆነም የምንመሰርተው አዲሱ መንግስት ድርብርብ የትውልድ አደራና ኃላፊነቶችን ተረክቦ ድርብርብ ተግባራትን አከናውኖ ድርብርብ ድሎችንና ለውጦችን በማስመዝገብ ከተማችንንና አገራችንን የሚያሻግር ተግባር ማከናወን አለበት።
አዲሱ መንግስት ለዕኩልነትና እኩል ተጠቃሚነት የተዋደቁ የዚህ ትውልድ ወጣቶች፣ በአሁኑ ወቅት የአገርን ህልውና ለማስከበር እየወደቁ ያሉ ጀግኖቻችንን፣ በኢትዮጵያውያን ላብና ደም እየተገነባና በመገባደጃ ምዕራፍ ላይ የሚገኘውና የወደፊት ኃያልነታችን ምልክት የሆነው ግድባችንን ለመልካም ፍጻሜ የማብቃት አደራውን የመወጣት ግዳጅ ያለበት መንግስት ነው።
የኢትዮጵያውያን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማዕከል እንዲሁም የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባችንን በትንሿ ኢትዮጵያ እንመስላታለን። በከተማችን የሚመሰረተው አዲሱ መንግስት ተልዕኮም በዚሁ ደረጃ የሚታይ ነው። የአዲሱ መንግስት ተልዕኮ ለመረጠው ሕዝብ የገባውን ቃል ማከናወን ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያ በረዥም ጊዜ ታሪኳ ሕይወት እየከፈሉ በነጻነት ያቆዩዋት ጀግኖቻችንን አደራ መቀበልና ከዳር ማድረስ ጭምር እንጂ!
አዲሱ የከተማችን መንግስት በከተማችን ጽንፈኝነትን በማክሰም አብሮነትን ወንድማማችነትና ሰላምን የማረጋገጥ፣ እንደ ስሟ ውብና የለማች የማድረግ፤ የቀልጣፋ አገልግሎት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የብቁ አመራርና የመልካም ተመክሮ ተምሳሌት የማድረግና ለአገር ውስጥና ለውጭ ቱሪስቶች እንድትመች ለማድረግ ሊሰራ ይገባል። የከተማችን ነዋሪዎች በዘመናት ውስጥ የወረሷቸውን ድህነት፣ ሥራ አጥነት፣ አለመደማመጥና መገፋፋትን በመቅረፍ ብልጽግናን፣ ፍትሐዊነትንና አብሮነትን የማጎልበት ኃላፊነት አለበት።
በአጠቃላይ መዲናችን የብዝሀነታችን መገለጫ ትንሹዋ ኢትዮጵያ እንደመሆኗ እንደ ኢትዮጵያ አስፍታ እያሰበችና እየሰራች ይህ በዓይነቱ ልዩ በሆነ የምርጫ ሂደትና ውጤት የተመሰረተው መንግስት የመረጠውንና ይሁንታ የሰጠውን የዛሬውን ኢትዮጵያዊ በከፍተና ትጋና ታማኝነት ማገለገል ለነገ ይደር ሊባል የሚችል ሥራ አይደለም። በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ለአገራቸው ነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍትሕና ብልጽግና በመሻት ደፋ ቀና ያሉ፣ የታገሉና መራር መስዋዕትነት በመክፈል ህልማቸውን ላወረሱንና አገርን ያስቀጠሉ ጀግኖቻችንን መሻትና ራዕይ በማሳካት ክብሩን የሚገልጽበትና አደራቸውን የሚወጣበት መልካም አጋጣሚ ነውና ሊጠቀምበት ይገባል። አዲሱ መንግስት የጀግኖቻችንን የዘመናት መሻትና ሕልም ዕውን የምናደርግበት፤ የአዲስ ምዕራፍ አዲስ እድል ነው።
መልካም የለውጥና ሥራ ዘመን!
(አባ ቡሌ ከጉለሌ)
አዲስ ዘመን መስከረም 23/2014